አዲስ አበባ፡– በሀገሪቱ የተለያዩ አካባ ቢዎች ስለተከሰተው የኮሌራ በሽታ ኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲጨብጥ በማድረግ በሽታውን የመከላከል ሥራ እየተሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
የኢንስቲትዩቱ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች የተግባቦት ባለሞያ አቶ መላኩ አበበ በተለይ ከጋዜጣው ሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት፤ በኢትዮጵያ ለኮሌራ በሽታ አጋላጭ ሁኔታዎችና ባህሪዎች ታይተዋል፡፡
በዋናነት የበሽታው አጋላጭ ባህሪዎች ከእጅ አስተጠጣብ፣ ከመፀዳጃ ቤት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የሚመነጩ መሆናቸውን ባለሙያው ጠቅሰው፣ የውሃና መፀዳጃ ቤት አቅርቦት ችግሮችም የበሽታው አጋላጭ ሁኔታዎች ናቸው ብለዋል፡፡
እንደ ባለሙያው ገለጻ፤ እነዚህ ምክንያቶች በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለኮሌራ በሽታ መከሰት አጋላጭ ሁኔታዎችና ባህሪዎች በመሆን ይጠቀሳሉ፡፡ ከውሃና አካባቢ ንፅህና ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች እንዲቃለሉም የክልል ጤና ቢሮዎች የሚያስተባብሯቸው የኅብረተሰብ ጤና ስጋቶች መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ተዘጋጅተዋል። የውሃ ማከሚያዎችና ሌሎችም በበሽታው ለተያዙ ሰዎች የሚያገለግሉ የሕክምና ግብአቶችን የማሟላት ሥራዎችም እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
በጤናው ሴክተር ላይ የሚሰሩ ሁሉም የልማት ድርጅቶችን በማስተባበር በጋራ ምላሽ የሚሰጡበት መንገድ ተመቻችቶ እየተሰራ መሆኑን አቶ መላኩ ጠቅሰው፣ በኢንስቲትዩቱ በኩል የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማስተባበሪያ ተቋቁሞ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማስተባበር በሽታውን የመከላከል ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ ኅብረተሰቡ መረጃ እንዲኖረው በየሳምንቱ ጋዜጣዊ መገለጫ እንደሚሰጥም ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2011
አስናቀ ፀጋዬ