በሕገወጥ ሥራ በተሰማሩ አካላት ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ባለሥልጣኑ አስታወቀ

አዲስ አበባ:- ሕገወጥ ሥራ በሚሠሩ አካላት ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን አስታወቀ። ባለሥልጣኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመዲናዋ ከ74 ሺህ በሚልቁ ሕገወጥ የጎዳናና በረንዳ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱንም አመልክቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን የበጀት ዓመቱን የዘጠኝ ወር አፈጻጸም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ትናንት ገምግሟል።

የተቋሙ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ ፉፋ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ባለሥልጣኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ሕገወጦች ላይ እርምጃ ከመውሰድ አንፃር አመርቂ ተግባራትን ፈፅሟል። በቀጣይም ሕገወጥ ሥራ ካልሠራሁ መኖር አልችልም በሚሉ አካላት ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ ይቀጥላል።

ከመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ ባለሥልጣኑ አሁን በጥብቅ ክትትል እየሠራ መሆኑን ያመላከቱት ምክትል ሥራ አስኪያጁ፤ ባለሥልጣኑ ከአስር ሚሊዮን ካሬ በላይ መሬት ለመሬት ባንክ በማስተላለፍ ጥበቃ በማድረግ ላይ ስለመሆኑም አመልክተዋል።

እንደምክትል ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ በተቋማቸው እስካሁን የተለዩትን ችግሮች እግር በእግር እየተከታተሉ የማቅናት ሥራዎች ቢሠሩም ሕገወጥ ግንባታ ላይ መሠራት የሚገባቸው ቀጣይ የቤት ሥራዎች አሉ።

በደምብ ማስከበር ሂደቱ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚሠራውን ሥራ በተመለከተም ከሥራ በኋላ ያሉ ውጤቶችንም የመገምገምና ክፍተትን የማሟላት ተግባራት እንደሚከውኑ ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የደምብ ማስከበር ሥራ ሂደቱንና መሠል ጉዳዮች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ስለመሠራታቸውም አቶ ደሳለኝ አንስተዋል።

በመድረኩ ሪፖርት ያቀረቡት የባለሥልጣኑ የለውጥና መልካም አስተዳደር ሥራዎች ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ቀፀላ እንዳሉት ተቋሙ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ሕገወጥነትን ከመከላከል አንፃር ሰፊ ሥራዎች ሠርቷል። በዚህም 74 ሺህ 295 ሕገወጥ የጎዳናና በረንዳ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ወስዷል።

ባለሥልጣኑ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 65 ሺህ ሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ አቅዶ ከ74 ሺህ በሚልቁት ላይ ርምጃ መውሰዱንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ዳግማዊት ግርማ

 አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16/2016 ዓ.ም

Recommended For You