ከ16 ሺህ በላይ የካንሰር ህሙማን የህክምና አገልግሎት አግኝተዋል

አዲስ አበባ፡- በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የካንሰር ማዕከሉ 16 ሺህ 600 ለሚሆኑ ተመላላሽ እና ተኝቶ ታካሚ የካንሰር ህሙማን አገልግሎት መስጠት መቻሉን የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ አስታወቀ።

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የካንሰር ህክምና ማዕከል ኃላፊና የካንሰር ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር መሀመድ ኢብራሂም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ የቅዱስ ጳውሎስ የካንሰር ህክምና ማዕከል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለ16 ሺህ 600 የካንሰር ህሙማን አገልግሎት ሰጥቷል።

ማዕከሉ በበጀት ዓመቱ 15 ሺህ ተመላላሽና አንድ ሺህ 600 ተኝቶ ታካሚ ማስተናገድ መቻሉን የገለጹት ዶክተር መሀመድ፤ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የካንሰር ማዕከል ወደ አገልግሎት ሲገባ እንደ ሀገር በዘርፉ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል።

በሆስፒታሉ በ20 አልጋ እንዲሁም ለተመላላሽ የሚሆኑ ሶስት ክፍሎች በሚገኙ ባለሙያዎች ብቻ ነው አገልግሎቱ እየተሰጠ የሚገኘው ያሉት ዶክተር መሀመድ፤ በማዕከሉ ያሉ ክፍተቶች ለመሙላት በሆስፒታሉ የተጀመረው የካንሰር ህክምና ማዕከል ግንባታ በፍጥነት አጠናቅቆ መፍትሔ ለመስጠት ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።

እንደ ዶክተር መሀመድ ገለጻ፤ ማዕከሉ ባለው ሁኔታ አገልግሎቱ ይሰጥ እንጂ ደረጃውን የጠበቀ ህክምና እየተሰጠ ነው ለማለት የማያስደፍር በመሆኑ ቢያንስ ቀላል ችግር የሚባሉትን ቀድሞ ለመፍታት ከሚመለከተው ባለድርሻ አካል ጋር እየተሰራ ነው።

የቦታ ጥበት፣ ተኝቶ ማከሚያ አልጋ ማነስ እንዲሁም የተለያዩ ማሽኖች አለመኖር በማዕከሉ ከሚስተዋሉ ተግዳሮቶች መካከል ይገኛሉ ሲሉ ገልጸዋል።

ዶክተር መሀመድ፤ በዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት መሠረት አንድ የጨረር ማሽን ለአንድ ሚሊየን ሰዎች በመሆኑ ለኢትዮጵያ 120 የጨረር ማሽን የሚያስፈልግ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የሚጠይቀውን ከፍተኛ ወጪ ለማሟላት የግሉ ዘርፍ ማሳተፍ እንደሚጠይቅ አብራርተዋል።

በሆስፒታሉ አብዛኛው ጊዜ የጡት ካንሰር ህሙማን እንደሚመጡ ዶክተር መሀመድ ገልጸዋል።

በቀጣይም በቴክኖሎጂ የተደገፈና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠትና ከተለያዩ ጤና ተቋማት ጋር በጋራ በመስራት ህሙማን በወቅቱ ወደ ሆስፒታሉ መጥተው እንዲታከሙ ለማድረግ እቅድ መያዙንም ነው ዶክተር መሀመድ ያስረዱት።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You