አለባበሳቸውን አሳምረው ባማረና በትልቅ መኪና ከሱቃችሁ ደጅ ላይ ወርደው ‹‹እስቲ ሲጋራውን ስጠን ብለው››፤ ከዚያ ወዲያ ግን የሰጣችኋቸውን የ15 ብር ሲጋራ ቀምተው በመኪናቸው ይሸሻሉ ብላችሁ እንዲያው ለአፍታስ ታስቡ ይሆን? በአዲስ ዘመን ትውስታ ውስጥ ግን ይሄ አለ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 12 ዓመታትን የሠሩት፤ ኢጣሊያዊ ነጋዴ ሀብት ንብረታቸውን ጥለው ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ኮብልለው ሸሽተዋል፤ ባለሀብቱ ነጋዴ የገጠማቸው ምን ኖሯል…ከጳውሎስ ኞኞ አጫጭር ደብዳቤዎች ጋር በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ለትውስታ ቀርበዋል፡፡
ሲጋራ ከሱቅ ወስደው ሳይከፍሉ በመኪና አመለጡ
አፍንጮ በር ከሚገኘው ሙሐመድ ሼክስሩርና ከድር ኑር ከሚያካሂዱበት የጋራ ሱቅ ውስጥ ስማቸውና መልካቸው ገና ያልታወቀ ሁለት ሰዎች ግምቱ 15 ብር የሆነ 10 ፓኮ ዊንስተን ሲጃራ፤ ባለፈው ሰኞ ምሽት ቀምተው መሄዳቸውን ባለቤቶቹ ገለጡ፡፡ ቅሚያውን የፈጸሙት ሰዎች አንድ ትልቅ ሽንጣም በመኪና ይዘው እንደነበሩ ገልጠዋል፡፡
ቅሚያው በተፈጸመበት ጊዜ፤ በሱቁ ውስጥ ተረኛ ሁኖ ሸቀጥ ይሸጥ የነበረው ከድር ኑር ሲሆን፤ ሁለቱ ሰዎች ከመኪና ውስጥ ሁነው በጣም አንገላተውት እንደነበር አስረድቷል፡፡ በዚህም ወቅት ከድር ከሦስት ቦታ ላይ የመቁሰል አደጋ የደረሰበት መሆኑን ለመመልከት ተችሏል፡፡
ከድር ኑር ከትናንት በስቲያ አደጋው እንዴት እንደደረሰበት እያለቀሰ ሲያስረዳ፤ “ሁለት ሰዓት ላይ አንድ ትልቅ ሰማያዊ መኪና ከሱቅ አጠገብ እየበረረ መጥቶ ቆመና ጥሩንባ ነፋ፡፡ ከሁለቱ ሰዎች አንዱ በሩን እየከፈተና እየዘጋ ያንገራግር ነበር፡፡ እንደገና ጠራኝና አስር ፓኮ ሲጃራ አምጣ ካለኝ በኋላ ወስጄ ሰጠሁት” ሲል አስረድቷል፡፡
ከዚያም “መጀመሪያ ከሾፌሩ አጠገብ የነበረው ሰውዬ ሲጃራውን ተቀበለኝና መኪናውን ለሚነዳው ከሰጠው በኋላ ሾፌሩ ኪሱን መዳበስ ጀመረ፡፡ ትንሽ ቆይቶም፤ ስማ ለሕይወትህ ያሰጋሃል ብሎ ሲናገር ሸሚዙን ስይዘው እየጎተቱ መኪናውን እየነዱ ሔዱ” ብሏል፡፡
በዚህን ወቅት አንገቱ ከመኪናው ውስጥ በመሆኑም ሲጮህ ስላልተሰማ ለጊዜው የጎረቤት እርዳታ በፍጥነት ሊያገኝ አለመቻሉን ከድር ገልጧል፡፡ ከዚህ በኋላ ቅሚያውን የፈጸሙት ሰዎች በግምት አምስት መቶ ሜትር ያህል እየጎተቱ ወስደው የጣሉት መሆኑን፤ ከዚያም ተማሪዎች የመኪናውን የሠሌዳ ቁጥር መያዛቸውን ከድር አስረድቷል፡፡
ወንጀሉ እንደተፈጸመ ከድር ከሥራ ባልደረባው ጋር ሁኖ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ ድረስ ሔዶ ያመለከተ መሆኑን ገልጧል፡፡ ወንጀሉ ሲፈጸም ያዩትን ሰዎች በምስክርነት መዝግቦ ለፖሊስ ያቀረበ መሆኑን ጠቅሷል፡፡
(አዲስ ዘመን ጥቅምት 10 ቀን 1963ዓ.ም)
ኢጣሊያዊው ነጋዴ ንብረታቸውንው ኮበለሉ ጥለ
በልደታ ወረዳ የአሸዋና የድንጋዮች ኢንዱስትሪ ባለቤት የሆኑት ኢጣሊያዊ ሲኞር ሜሪኒ ቪኒስቶ ንብረታቸውን እንዳለ ጥለው ቤተሰባቸውን ይዘው ግንቦት 22 ቀን የጠፉ መሆናቸውን ከመሥሪያ ቤታቸው የተገኘው ዜና ያስረዳል፡፡
ባለንብረቱ ቤተሰባቸውን ይዘው ግንቦት 22 ቀን እሑድ ጧት በ12 ሰዓት ከቤት የወጡት ላንጋኖ እሔዳለሁ ብለው ለሠራተኞቻቸው ነግረው መሆኑን ታውቋል፡፡
ሠራተኞቹም ሰኞ ዕለት እንደተለመደው የተመደቡበትን ሥራ በማከናወን ላይ እንዳሉ፤ በአምስት ሰዓት ላይ ባለንብረቱ ወደ ኬኒያ የሔዱ መሆናቸውን ሠራተኞቹ ከፀጥታ ተረዱ፡፡
ከዚያም ዕለት ጀምሮ በድርጅቱ ውስጥ የሚሠሩ 29 ሠራተኞች የሚያሠራቸው ከማጣታቸውም በላይ፤ ለማን እንደሚያስረክቡ ግራ ገብቷቸው የግቢውን ንብረት በየተራ በመጠበቅ ላይ መሆናቸውን ገልጠውልናል፡፡
በግቢውም ውስጥ ስድስት ከባድ መኪናዎች፤ የአሸዋ ክምሮችና እንዲሁም በውስጡ ምን እንዳለ ያልታወቁ ዘጠኝ ክፍል ቤቶች ተቆልፈው ይገኛሉ፡፡
በድርጅቱ ውስጥ የሚሠሩትም ሠራተኞች አሠሪው የ2 ወር ደሞዛቸውን ሳይከፍሏቸው የጠፉ መሆኑንና ለንብረቱ ያገባኛል የሚል እንዲቀርብ፤ ባይቀርብ ደግሞ ብዙ ዘመን ያገለገልን መሆናችንን አስመስክረን የአገልግሎት ካሣ እንዲሰጠን ሲሉ ለፍርድ ቤት ያመለከቱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ እንዲሁም ይህንኑ ለጣሊያን ቆንሲል አመልክተው አያገባንም የሚል መልስ ያገኙ መሆኑም ታውቋል፡፡
ከሠራተኞቹ ለማወቅ እንደተቻለው ሲኞር ቪኒስቶ፤ በዚሁ ሥራቸው ላይ 12 ዓመት እንዳላቸውና ከጀመሩም አንሥቶ አብረዋቸው 12 ዓመት የሠሩ ሠራተኞች ከ20 በላይ እንዳሉ ታውቋል፡፡
…
ባለንብረቱም ከአገር መውጣታቸውን የሰሙት በቤቱ ውስጥ ያለውን ንብረትና የቆሙትን መኪናዎች እንወስዳለን እያሉ 10 የሚሆኑ ሰዎች መምጣታቸውን አስረድተዋል፡፡
(አዲስ ዘመን ሰኔ 13 ቀን 1963ዓ.ም)
አንድ ጥያቄ አለኝ
-አዘጋጅ ጳውሎስ ኞኞ
*ከጓደኞቼ ጋር ተቀምጠን ስንጫወት የጂማ ታርጋ ያላቸው 2 መኪናዎች ከፊት ለፊታችን ቆመው አየን። የስሙ አጻጻፍ አንዱ ጂማ ሲል ሌላው ደግሞ ጅማ ይላል። ትክክለኛው የስሙ አጻጻፍ እንዴት ነው?
ይስሐቅ ቀኖ፤ መልኬ ለማ (ከአጋሮ)
(አዲስ ዘመን ነሐሴ 13 ቀን 1963 ዓ.ም)
-ሁለት ዓይነት ስም የሚጽፈው የጅማ ማዘጋጃ ቤት መልሱን ይስጠን እንጂ፤ እኔ ለራሴ የትኛው ትክክል እንደሆነ አላውቅም፡፡
*ዓለም ክብ ናት ይሏታል፡፡ ክብ ባትሆን ኖሮ ግን እንወድቅ ነበር እያሉ ሰዎች ሲናገሩ እሰማለሁ፡፡ ክብ ባትሆን ከምን ላይ እንወድቅ ነበር?
ዓለም ፀሐይ ገሠሠው(ዓድዋ)
-ክብ ባትሆን ኖሮ እኛ ብልጦች እንሆንና እንዳንወድቅ ወደ ዳሯ አንሔድም ነበር፡፡ ምናልባትም አንዳንዱ ቀበጥ ቢወድቅ፤ እንደ ቅዱስ ገብርኤል ሰይፍ በአየር ውስጥ ሲንሳፈፍ ይኖር ነበር፡፡
* በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አራት ኪሎ ስድስት ኪሎ እየተባሉ የሚጠሩት ሥፍራዎች በምን ምክንያት በእንዲህ አይነት ስም ሊጠሩ ቻሉ?
ዘሪሁን ተሰማ
-አራት ኪሎ አራት ማዕዘን መንገድ ስላለውና፤ ስድስት ኪሎም ስድስት ማዕዘን መንገዶች ስላሉት ይመስለኛል፡፡
(አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 10 ቀን 1963ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2016 ዓ.ም