ክልሉ ከሮዝመሪና በርበሬ ምርቶች ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አግኝቷል

አዲስ አበባ፡ባለፉት ዘጠኝ ወራት እሴት የተጨመረበትን 13 ሺ 786 ኩንታል በርበሬ እንዲሁም 22 ሺ 760 ኩንታል ሮዝመሪ ወደ ተለያዩ ዓለም ሃገራት በመላክ 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስታወቀ፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዑስማን ሱሩር ለኢፕድ አንዳስታወቁት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ወደ ተለያዩ የዓለም ሃገራት ከላካቸው የግብርና ምርቶች መካከል እሴት ከተጨመረበት 13 ሺ 786 ኩንታል በርበሬ 6 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ከ22 ሺ 760 ኩንታል ሮዝመሪ 4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር በድምሩ 10 ነጥብ 2 ዶላር ማስገባት ችሏል፡፡

እንደአቶ ዑስማን ገለፃ፤ የክልል መንግሥት ‘በአዲስ አስተሳሰብ፤ አዲስ ምዕራፍ፤ አዲስ ተስፋ ለአዲስ ክልል’ በሚል የልማት ንቅናቄ ከዚህ ቀደም ያልተለመዱ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ በስፋት በማምረትና ወደ ተለያዩ ሃገራት በመላክ ለሃገር የውጭ ምንዛሪ ግኝት የበኩሉን ሚና ለመጫወት እየተረባረበ ይገኛል። ከእነዚህም የግብርና ምርቶች መካከል በርበሬና ሮዝመሪ ዋነኞቹ ሲሆኑ በተለይም በርበሬ ላይ እሴት በመጨመርና በማቀነባበር በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው።

‹‹ቀደም ሲል ቡና እና ቅመማ ቅመም በዚህ ክልል እምብዛም አይታወቅም ነበር›› ያሉት አቶ ዑስማን፤ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ግን የቅመማ ቅመምንም ሆነ የቡና መሬትን ሽፋን የማስፋፋት እንዲሁም ምርታማነቱን የማሳደግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል። በዚህ ዓመት ወደ 52 ሚሊዮን የቡና ችግኝ ለመትከል ርብርብ እየተደረገ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 10 ሚሊዮኑ ከሚያዚያ ጀምሮ እየተተከለ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቅመማ ቅመም ልማት ረገድም በክልሉ ያለውን ምቹ የአየር ንብረት በመጠቀም ዝንጅብል፣ ኮሰረት፣ ድንብላልና ሮዝመሪ ወደ ማምረት መገባቱንም ተናግረዋል። ‹‹በተለይ ሮዝመሪ ላይ ከፍ ባለመንገድ በማምረት ለውጭ ገበያ በስፋት ለማቅረብ ጥረት እያደረግን ነው›› ያሉት አቶ ዑስማን፣ በዚህ መነሻ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከስልጤ ዞን ብቻ 22 ሺ 760 ኩንታል ሮዝመሪ ወደ ተለያዩ የዓለም ሃገራት ልከን 4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ማስገባት ችለናል ሲሉ ጠቁመዋል።

‹‹በአካባቢው ሮዝመሪ ከዚህ በፊት የሚታወቀው ለመጥበሻነት እንጂ ዶላር ማምጫነት አይደለም፤ አሁን ሮዝመሪ ከመጥበሻ ወጥታ ወደ ዶላር ማምጫና ሥራ ዕድል መፍጠሪያ የሃገር ሃብት ምንጭ ሆናለች›› ብለዋል።

አክለውም ‹‹የእኛ ሮዝመሪ አሁን ላይ አውሮፓ ገበያ ገብቶ ግሎባል ካፕ ሰርተፊኬት አግኝቷል። ሦስት ሺ አርሶአደሮች ግሎባል ካፕ ሰርተፍኬት እንዲያገኙ አድርጓል›› ያሉት አቶ ዑስማን፣ አርሶአደሮቹ ይህንን ሰርተፍኬት ማግኘታቸው ፕሪሚየም ፕራይዝ እንዲያገኙና አስተማማኝ ገበያ እንዲኖራቸው የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል።

በመሆኑም የክልሉ መንግሥት ጥራቱን ጠብቆ በተቀመጠው መስፈርት መሠረት የማምረትና ማስፋፋት ኃላፊነት ያለበት መሆኑን አመልክተዋል። ‹‹ሲጀመር አንድ ቀበሌ ላይ ነው የነበረው፤ አሁን መላው ስልጤ ወረዳዎች ላይ የማስፋፋት ሥራ ተሠርቷል። በትምህርት ቤቶች፣ በጤና እና በእምነት ተቋማት የመትከል ሥራ እየተሠራ ነው። ጉራጌ ላይ ወደ 2 ሺ ሄክታር አካባቢ ደርሷል›› ብለዋል።

ሥራው ወደ ሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች የማድረስ ሥራ እየተሠራ መሆኑንና በቀጣይ ሌሎችንም ቅመማ ቅመሞችንን ለመዓዛማ ዘይት የሚውሉና በትንሽ መሬት ሃብት የሚመነጭባቸውን በመለየትና በስፋት በማምረት ለሃገር የውጭ ምንዛሪ ግኝት ሁነኛ ምንጭ ለመሆን ጥረት የሚደረግ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የክልሉ መረጃ እንደሚያመላክተው፤ ሮዝመሪ ድርቅንና አሲዳማ አፈርን የመቋቋም አቅሙ ከፍተኛ ነው። ደረቃማ በሆነ መሬት ላይ ምርት በመስጠትም ይታወቃል። ወደ ሕንድ፣ ዱባይ፣ መካከለኛው ምሥራቅና አውሮፓ ገበያ ከተላከው በርበሬ 90 በመቶ የሚሆነው ከስልጤ ዞን ቀሪው ከሃላባ ዞን ነው የተገኘው፤ ሮዝመሪው ግን ሙሉ ለሙሉ የተመረተው በስልጤ ዞን ነው።

ማሕሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You