የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ፅህፈት ቤት የዕድሮች ምክር ቤት የሰላምና የልማት ንቅናቄ ዓመታዊ የውይይት መድረክ ዛሬ አካሂዷል፡፡
የአዲስ አበባ የዕድሮች ምክር ቤት ዛሬ በግሎባል ሆቴል ባካሄደው ዓመታዊ የውይይት መድረክ ዕድሮች ኃይማኖት፣ ብሔር፣ ዘርና ፆታ የሌላቸው የጋራ የሆኑ ዕሴቶች በመሆናቸው ለሰላምና ለልማት ግንባታ አምባሳደር በመሆን አስተዋፅዋቸው ከፍተኛ ነው፤ ተብሏል፡፡
የምክር ቤቱ ዋና ሰብሳቢ አቶ ታምራት ገ/ማሪያም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፣ እድሮች በደስታም ሆነ በሀዘን ከሚያደርጉት አስተዋፅኦ በተጨማሪ ሰላምና ልማትን በማረጋገጥ በሀገር ግንባታ ላይ ጉልህ ሚና አላቸው፡፡
በአዲስ አበባ ከ7 ሺህ 500 በላይ ዕድሮች የሚገኙ ሲሆን በተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች ማለትም ወላጅ አልባ ህፃትን በማስተማርና በማሳደግ፣ ጧሪ አልባ አዛውንቶችን እንዲጦሩ በማድረግና በሌሎችም አኩሪ የሆነ ተግባራትን እያከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
ምክር ቤቱ ባካሄደው ዓመታዊ የውይይት መድረክ በተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች አርአያነት ያለው ተግባር ያከናወኑ የግል፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አበበች ነጋሽ፣ ዕድሮች ለሀገራችን ሰላም፣ መቻቻል፣ አንድነትና ልማት የሚያበክቱት ሚና ከሁሉም የላቀ መሆኑን አውስተው፣ ከተማ አስተዳደሩ ከምንጊዜውም በበለጠ ለዕድሮች ምክር ቤት ልዩ ትኩረት በመስጠት በተቻለ አቅም ድጋፍ ለማድረግ በቁርጠኝነት ይሠራል ብለዋል፡፡
በቀጣይም ዕድር በሌላው ዓለም ላይ የሌለ ታላቅ አገራዊ ዕሴት በመሆኑ በዮኒስኮ እንዲመዘገብ ይሠራል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ሞገስ ተስፋ