ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዞን አምስት (ቀጣና-5) ከ18 ዓመትና ከ20 ዓመት በታች ታዳጊዎችና ወጣት ወንዶች የእጅ ኳስ ውድድርን እንደምታስተናግድ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። በውድድሩ የሚያሸንፉ ሀገራት በቀጥታ ለአፍሪካ እጅ ኳስ ሻምፒዮና እንደሚያልፉ ተገልጿል።
ውድድሩን የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ከአፍሪካ እጅ ኳስ ኮንፌዴሬሽንና ዓለም አቀፉ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በትብብር እንደሚያዘጋጁት ተነግሯል። ውድድሩ ከግንቦት 4-9/2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳል። ዓለም አቀፉ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን ሻምፒዮናውን በበላይነት በመምራት በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ፣ በአራት ኪሎ ትምህርትና ሥልጠና እና በአዲስ አበባ ትንሿ ስቴድየም ይከናወናል። ውድድሩ ቀጣናዊ እንደመሆኑ ኢትዮጵያ በማዘጋጀቷ ከስፖርታዊ ውድድር ባሻገር ቀጣናዊ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊው ፋይዳው የላቀ አንደሆነ ተመላክቷል።
የውድድሩ መክፈቻና መዝጊያ ሥነ ሥርዓት በዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ለማካሄድ ከተማ አስተዳደሩን ለማስፈቀድ ጥረት እየተደረገ ነው። አዘጋጇን ሀገር ኢትዮጵያን ጨምሮ አስር የቀጣናው ሀገራት በውድድሩ ይሳተፋሉ። ውድድሩ ባማረና በደመቀ መልኩ ከተከናወነ ለሀገርና ለፌዴሬሽኑ የጎላ አስተዋፅዖ ስለሚያበረክት ሰፊ ቅድመ ዝግጀት እንደሚደረግ ተገልጿል።
የውድድሩ ዓርማ የተዋወቀ ሲሆን ”የምሥራቅ አፍሪካን የሕዝብ ለሕዝብ ወዳጅነት እናጠናክራለን” በሚል መሪ ሃሳብ በተቀመጠው መርሐ ግብር ይካሄዳል። የውድድሩ ስያሜ የዓለም አቀፍ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ዋንጫ 2024 (IHF THROPHY 2024 AFRICA ZONE-5) በመባል ይጠራል።
ከውድድሩ ጎን ለጎን የIHF THROPHY የአሠልጣኞች ሥልጠና እና IHF THROPHY የዳኞች ሥልጠና ከዓለም አቀፉ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን በሚመጡ ባለሙያዎች ይሰጣል። ከ 20 ቡድኖች የተወጣጡ 40 አሠልጣኞች የሚሠለጥኑ ሲሆን ኢትዮጵያ አዘጋጅ ሀገር በመሆኗ ተጨማሪ አሠልጣኞችንና ዳኞችን እንድታሰለጥን በር እንደሚከፍት ተገልጿል።
ከሁሉም ተወዳዳሪ ሀገሮች በሁለቱ የእድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶችና ታዳጊዎች ውድድራቸውን ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ። በዚህም መሠረት አንድ ሀገር ሁለት ቡድን ሲኖረው አንድ ቡድን 17 ልዑካኖችን ያቅፋል። በአጠቃላይ ለውድድሩ የሚመጡት 400 የሚደርሱ ልዑካኖች መሆናቸው ተነግሯል። የውድድሩ የበላይ ጠባቂ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንደሆኑም ተጠቁሟል።
በሁለቱም የእድሜ እርከን የሚያሸንፉ ብሔራዊ ቡድኖች ለአፍሪካ ሻምፒዮና በቀጥታ የማለፍ እድል የሚፈጥር ውድድር በመሆኑ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሁለቱም የእድሜ እርከን ተጫዋቾች መርጦ በመጨረሱ ከሚያዝያ አራት ጀምሮ ሆቴል በመግባት ዝግጅት ይጀምራሉ። የ18 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በዋና አሠልጣኝ ዋና ኢንስፔክተር ተስፋዬ ሙለታና በምክትል አሠልጣኝ ጃቢር ሸምሱ ይሠለጥናል። የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰጠኝ አዲስ በቡድን መሪነት ተሰይመዋል።
በዚህም መሠረት ተጠባባቂን ጨምሮ 16 ተጫዋቾች ምርጫ ተደርጓል። የቡድኑ አሠልጣኝ ተስፋዬ ሙለታ ብሔራዊ ቡድኑ ከዚህ በፊት ያለ በቂ ዝግጅት ተሳትፎዎችን በማድረግ ሜዳሊያ ውስጥ መግባቱን ተናግረው፣ አሁን ውድድሩ በኢትዮጵያ በመሆኑ በደንብ ዝግጅት ከተደረገ ለአፍሪካ ዋንጫ የማይታለፍበት ምክንያት እንደማይኖር ተናግሯል።
ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአሠልጣኝ ሙሉጌታ ግርማ እና በምክትል አሠልጣኝ አማኑኤል ሥዩም የ16 ተጫዋቾች ምርጫ ተደርጓል። የ18 ዓመት በታች ቡድኑ አብዛኛው ተጫዋቾች የፓስፖርት ሂደት የተጠናቀቀ ሲሆን የ20 ዓመት በታች ሙሉ ለሙሉ ተጠናቋል። የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊው አቶ ሞላ ተፈራ የዚህ ቡድን መሪ ሆነዋል።
አሠልጣኝ ሙሉጌታ ግርማ ሥራው ከተሰጣቸው ግዜ ጀምሮ ቅደመ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረው፣ በእጅ ኳስ አስር ክለቦች በመኖራቸው ሰፊ የመምረጥ ዕድልን ተጠቅመው ከሁሉም ክለብ ተጫዋቾች ተመርጠዋል። ኢትዮጵያ በ2006 ውድድሩን አዘጋጅታ አሸንፋ የነበር ሲሆን አሁንም ጥሩ ዝግጅት በማድረግ ታሪክ መሥራት እንደሚፈልግ ጠቁሟል። በዚም መሠረት ፌዴሬሽኑ በጊዜ ወደ ሆቴል አስገብቶ ጥሩ ዝግጅት ከተደረገ፣ ሚዲያው የሚያበረታታ ከሆነ፣ የተጫዋቾቹ መነሳሳት እና የተፎካካሪ ሀገራት አቋም ከታወቀ ድል የማይመጣበት ሁኔታ እንደማይኖር ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍትሕ ወልደሰንበት ኢትዮጵያ የዞኑን ፌዴሬሽን በኃላፊነት መምራቷ ውድድሩ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ዕድል ሊፈጥር ችሏል። ከውድድሩ ጎን ለጎን የአሠልጣኞችና የዳኞች ሥልጠና ይሰጣል። ይህም ለኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ዕድሉን ተጠቅሞ እራሳቸውን ለማሻሻል ይጠቅማል። ለውድድሩ ልዑካን ጥሩ የሆነ አቀባበልንና ዝግጅት በማድረግ ኢትዮጵያ ሌሎች ውድድሮችን እንድታዘጋጅ ለማመቻቸት ይሠራል።
የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ውድድሩ የተሳካ እንዲሆን አስፈላጊውን የማዘወተርያ ስፍራዎች ዝግጅት እና የበጀት ድጋፎች እንደሚያደርግ አስታውቋል። ለዚህም መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ቅድመ ዝግጅት አድርጓል። ለብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ሲሆን በቂ ዝግጅት አድርጎ ለውጤት እንዲበቃ ይሠራልም ተብሏል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም