«ግብርናችን በጥሩ የእድገት ጉዞ ላይ ነው»-አቶ ኡስማን ሱሩር

አቶ ኡስማን ሱሩር በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ  የግብርንና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ

ኢትዮጵያ የተቀናጀ ግብርና ልማት መተግበር በመጀመሯ በዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣች መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ በዋናነት የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የምግብ ሥርዓትን ከማሻሻል አኳያ እምርታ እያሳየች ትገኛለች፡፡ እያንዳንዱ አርሶ አደር ከራሱ አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ ምርት እንዲያመርት በማድረግ የሌማት ቱሩፋት መርሃ ግብርና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሥራም አወንታዊ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡ እነዚህን መርሃ ግብሮች በመተግበር ከፍተኛ ውጤት እያመጡ ካሉ ክልሎች መካከል የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አንዱ ነው፡፡

ክልሉ እንደ አዲስ ከተመሠረተ ወዲህ ከሌማት ቱሩፋት ጎን ለጎን 30-40-30 ብሎ በነደፈው ኢኒሼቲቭ አማካኝነት እያንዳንዱ አርሶ አደር በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ100 በላይ የፍራፍሬ ችግኝ እንዲኖረው በማድረግ የራሱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና ብሎም የገቢ አቅሙን ለማሳደግ እያስቻለው መሆኑን ይገለፃል። በክልሉ እየተከናወነ ያለውን የግብርና ሥራ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የጋዜጠኞች ቡድን በቅርቡ የመስክ ጉብኝት ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ይህንን በሚመለከት አዲስ ዘመን ጋዜጣ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የክልሉ የግብርንና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ጋር ቆይታ አድርጐ እንደሚከተለው አቅርቦላችኋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ እንደ አዲስ ከተደራጀ በኋላ የሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻልና ልማትን ለማም ጣት ምን እየተሠራ ነው?

አቶ ኡስማን፡- እንደሚታወቀው ክልላችን ከተመሠረተ ገና ስድስተኛ ወሩ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ነሐሴ 15 በአዲስ መልክ ሲደራጅ ብዙ ውስብስብ ችግሮች የነበሩበት ቢሆንም፤ ነገር ግን አመራሩ በነበረው አብሮነት፤ የጋራ ራዕይና የተቀናጀ እንዲሁም የተናበበ እይታ ስለነበረ ክልሉ በተመሠረተበት እለት ቁጭ ብሎ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጓል፡፡

በሶስተኛው ቀን የአመራር ምደባ ተደርጓል። አመራሩ በእለቱ ያስቀመጣችው መሠረታዊ ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ከጉዳዮቹ መካከል ሕዝቡ ሰፊ የልማት ጥያቄ አለው፡፡ በአብዛኛው በሚባል ደረጃ በንግድ እንቅስቃሴ ያለ በመሆኑ ለቴክኖሎጂ እና ለመረጃ ቅርብ ነው፡፡ ለምሳሌ የከንባታን ሕዝብ ብናነሳ በየትኛው የሀገሪቱ ክፍል በተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ የሚገኝ ታታሪ ሕዝብ ነው፡፡ ሃድያም በተመሳሳይ ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ በንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ ነው። ጉራጌና ስልጤም እንደ ሀገር ሥራ ፈጣሪ የሚባሉ ማህበረሰቦች ናቸው፡፡ ይሄ በጥቅሉ ክልሉን ለማሳደግ ትልቅ እድል ነው፡፡

ክልሉ ሲመሠረት አመራሩ የተነሳው በአንድ እጁ ሽግግሩን በሌላኛው እጁ ልማቱን ይዞ ነው፡፡ ልማቱን ለማምጣትም ለአፍታም ቢሆን ማሸለብ አይፈቀድም። ከተቻለ ከ14 እስከ 16 ሰዓት መሥራት ያስፈልጋል። ለዚህም መሰጠት፤ ቁርጠኝነትና ፅናት ይጠይቃል፡፡ ክልሉ ራሱን ችሎ ሲደራጅ የመጀመሪያው ጉዳይ የ30 እና የ40 ዓመት ጥያቄዎችን ወዲያውኑ መልሷል፡፡ ከእነዚህም መካከል የዞንና ልዩ ወረዳ እንሁን ጥያቄዎች ወዲያውኑ ምላሽ እንዲያገኙ አድርጓል። እነዚህን ጥያቄዎች እየመለሱ በሌላ እጅ ደግሞ ልማትን በተሳካ ሁኔታ መምራት ስለሚያስፈልግ አስተባባሪው እንደ አንድ አካል ሆኖ እየሠራ ነው።

በዚህም መሠረት አምስት ዋና ዋና ጉዳዮችን የለየን ሲሆን፤ የመጀመሪያው በክልሉ አስተማማኝ ሰላም ማስፈን ነው፡፡ ሁለተኛው ቁልፍ ጉዳይ የግብርና ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ሲሆን በመቀጠልም የክልሉ የገቢ አቅም ከፍ ማድረግና ሥራ እድል ፈጠራን ማስፋት የሚሉ ጉዳዮችን በቅደም ተከተል አስቀምጠን ወደ ሥራ ገብተናል። ወደ ተግባር ሲገባም የ100 ቀን እቅድ ያቀድን ሲሆን፤ ለእዚህም ስኬት በእጃችን ያሉ እድሎችንና ምቹ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። በሁሉም ዘርፍ ያሉ አንኳር ሥራዎች ለአፍታም ሳይዛነፉ እንዲተገበሩ ጥረት ስናደርግ ቆይተናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በተለይም የግብርናውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እያከናወ ናችሁ ባላችሁት ሥራ ምን ያህል ውጤታማ እየሆናችሁ ነው?

አቶ ኡስማን፡- አስቀድሜ እንዳነሳሁት ክልሉ ሲመሠረት ቁልፍ ጉዳይ አድርጎ ከያዛቸው የልማት መርሃ ግብሮች መካከል የግብርናውን ምርትና ምርታማነትን በላቀ ደረጃ ማሳደግ ነው፡፡ ለእዚህም መሳካት የተቀናጀ ግብርና ልማትን ለመተግበር ሰፊ ንቅናቄ አድርገናል። በዚህም ንቅናቄ ሰባት መሠረታዊ ጉዳዮች የተያዙ ሲሆን፤ በወቅቱ በነበረው ተጨባጭ ሁኔታ የመኸር ምርትን ሳይዛነፍ መተግበር ዋናው ሥራችን አድርገን ስንረባረብ ነበር፡፡ በተለይም የገባነው ከብክነት በፀዳ መልኩ በቴክኖሎጂ ታግዞ ምርት የመሰብሰብ ሥራ መሠራት አለብን የሚል መሠረታዊ አቅጣጫ ይዘን ነው።ሁለተኛው የበጋ መስኖ ልማት ሲሆን፤ እርጥበትን በመጠቀም ያሉንን ማሳዎች በመስኖ ለማልማት ትኩረት አድርገን ተንቀሳቅሰናል፡፡ በዚህም መሠረት 147 ሺ ሄክታር መሬት በማልማት 33 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ያቀድን ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ ደግሞ 11 ሺ 230 ሄክታር የበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት 434 ሺ ኩንታል ምርት ለማግኘት ጥረት ስናደርግ ቆይተናል፡፡

ሌላው ጉዳይ የሌማት ቱሩፋት መርሃ-ግብር ሲሆን፤ ይህም ለአፍታም ቢሆን ምንም ዓይነት መቀዛቀዝና መፋዘዝ ሳይኖር ለማስቀጠለ ጥረት አድርገናል፡፡ በተለይ ሽግግር ላይ ብዙ ውስብሰብ ነገሮች የሚያጋጥሙ በመሆናቸው ንቅናቄያችን የነበረውን ግለት ጠብቆ እንዲሄድ አቅጣጫ አስቀምጠናል፡፡ በተጨማሪም የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት መርሃ-ግብርንም በስፋት የማስቀጠል ትልም ይዘን የተንቀሳቀስን ሲሆን፤ በዋናነት 393 ሚሊዮን ችግኝ ለማባዛት ግብ አስቀምጠን እየሠራን እንገኛለን፡፡ እንዲሁም የተከልናቸውን መንከባከብና የማፅደቅ ሥራ ጎን ለጎን እየተከናወነ ነው፡፡

ከዚህ ባሻገርም ቡና እና ቅመማ ቅመም ልማት ላይ አተኩሮ መሥራት አለብን ብለን አስቀምጠናል፡፡ ሰባተኛው የህብረት ሥራ ልማትና የግብይትና የፋይናንስ ሥራ ነው፡፡ በተለይ ህብረት ሥራ በግብዓት አቅርቦቱ፤ በምርት ግብይት አምራቹን አርሶአደር ካላስፈላጊ የገበያ ሰንሰለትና ደላላ በመከላከል አምራቹ ከሸማቹ ጋር በቀጥታ እንዲገናኝ መሥራት እንዳለብን ተማምነናል፡፡ የገባነው በከተሞች አካባቢ የሚታየውን ተገቢ ያልሆነ የገበያ ውድነትንም ለመከላከል የህብረት ሥራ ማህበራት በዚህ የግብይት ሥርዓት ውስጥ ተዋናይ የሚሆኑበትን ሁኔታ መፍጠር አለብን ብለን ነው ፡፡

እነዚህን ሰባት ጉዳዮች ይዘን ገብተን፤ ባለፈው ዓመት የመኸር ምርት አሰባሰብ በሰብል ከተሸፈነ 532 ሺህ ሄክታር መሬት የጠበቅነው 47 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ነበር ፡፡ ይህንን ምርት ከብክነት በፀዳ ፣ ጥራቱን ጠብቆ በገበያ ተወዳዳሪ በሚሆን መንገድ ምርቱ መሰብሰብ እንዳለበት መግባባት ላይ ደርሰናል። አንዳንድ ጊዜ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊያጋጥም ስለሚችል በክልል ደረጃ ያለው ንቅናቄ እስከታች እንዲወርድና ሁሉንም ባለቤት ባደረገ መልኩ እንዲተገበር ተደርጓል፡፡ በተለይ ምርት አሰባሰብ ላይ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ አርቲስቶች በዚህ ጉዳይ ላይ ባለቤት እንዲሆኑ ህብረተሰቡን የማንቃት ሥራ ተሰርቷል፡፡

በተለይም ቆላማው የክልላችን አካባቢ ምርት ቀድሞ የሚደርስ በመሆኑና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የሚመጣ በመሆኑ ምርት የሰበሰብነው በቶሎ ነው፡፡ ያም በመሆኑ እንደ አጋጣሚ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝንብ ቢከሰትም በአጠቃላይ በነበረው ንቅናቄ ከፍተኛ መናሳሳት ተፈጥሮ ምርት ለመሰብሰብ ተችሏል፡፡ ከኦሮሚያ ክልል ከ650 በላይ ኮምባይነሮች በኪራይ በማምጣት ምርቱን በመሰብሰባችንና አጠቃላይ ሥራችንን በሜካናይዜሽን የተመራ በማድረጋችን ብክነት ማስቀረት ችለናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በበጋ መስኖ ልማትና በሌማት ትሩፋቱ የተገኘው ስኬት እንዴት ይገለፃል?

አቶ ኡስማን፡- በክልላችን በበጋ መስኖ ልማት ሥራ ውጤታማ ሰፋፊ ሥራዎችን አከናውነናል፡፡ በተለይም ክልላችን ከሌሎች ክልሎች አንፃር በቆዳ ስፋትም ከእርሻ መሬት አኳያ አነስተኛ እንደመሆኑ ይህንን ውስን መሬት በአግባቡ ተጠቅሞ ፈጣን ልማት ከማምጣት አኳያ የተሠሩት ሥራዎች የሚያበረታቱ ናቸው። ክልሉ ምንም እንኳን ሰፋፊ የውሃ አካላት ባይኖሩትም ያሉትን የውሃ አማራጮችን ሁሉ ተጠቅሞ ዓመቱን ሙሉ ማምረት የሚያስችሉ የመስኖ ልማቶችን አከናውኗል፡፡ እስካሁን ባለው ተሞክሮ ግን አብዛኛው የክልሉ መሬት እየለማ የነበረው ዝናብን በመጠበቅና በአርሶ አደሩ ብቻ ነበር፡፡ በመሆኑም ይህንን ጠንካራና ሥራ ወዳድ ሕዝብ ተጠቅመን ወደ ከፍተኛ እሴት ወይም ገበያ መር የሆኑ ሰብሎችን ለማምረት ተንቀሳቅሰናል። በተለይም ለኑሮ ውድነት መቃለል እና የሥራ እድል ለመፍጠር ትልቅ አስተዋፅኦ ያላቸውን ሰብሎች ላይ አተኩረን ስንሠራ ቆይተናል፡፡

በዚህም መሠረት አትክልትና ፍራፍሬ ምርት ላይ ትኩረት አድርገን ሰርተናል፡፡ ከዚህ ቀደም በክልላችን አርሶ አደሮች ሲመረቱ ከቆዩ የሰብል ዓይነቶች በተጨማሪ ያልተለመዱትንም እንደ ኩከበር፣ ዝኩኒ፣ አበባ ጎመንና መሰል አትክልቶችን ለማልማት አቅደን ከ110 ሺ ሄክታር መሬት በአትክልትና ስራስራ ምርቶች መሸፈን ችለናል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ ከ80 ሺ ሄክታር በላይ ምርት ተሰብስቧል፡፡ በዚህም ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ተፈጥሯል፡፡ በተለይ ሥራ አጥ የነበሩና ተመርቀው የተቀመጡ ወጣቶች የዚህ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ የግል ባለሀብቱም መነሳሳት ተፈጥሮለታል፡፡

በሌላ በኩል ምርታማነትን ማጎልበት በመቻሉ በክልላችን ይታይ የነበረውን የግብርና ምርቶች ዋጋ ንረት በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማረጋጋት ተችሏል፡፡ ለአብነት ከቅርብ ጊዜ በፊት ሽንኩርት በኪሎ እስከ 180 ብር ይሸጥ ነበር፤ ቲማቲም 100 ብር ደርሶ ነበር፡፡ አሁን ግን ቲማቲም እስከ 15 ብር ሽንኩርት እስከ 60 ብር ድረስ እየተሸጠ ነው። ይህም ከአካባቢው አልፎ ለሀገር ውስጥ ገበያ መረጋጋት የበኩሉን ሚና ለመጫወት አስችሏል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሥራውን ስንሠራ ደግሞ በተቀናጀ፣ በተናበበ መልኩ በመሆኑ፤ እስከ ታች ያለው አካል የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት በማበጀታችን የሚታይ ውጤት መጥቷል፡፡

በሌማት ቱሩፋት መርሃ ግብሩ ተጨባጭ ውጤት በመምጣቱ፣ ህብረተሰቡም ጥቅሙን ማጣጣም በመቻሉ ሌሎችም ወደ ግብርና ሥራ እንዲገቡ ከፍተኛ መነቃቃት ተፈጥሯል፡፡ በተለይ ደግሞ በዶሮ፣ በንብ፣ በወተት ልማት ሥራ ላይ በርካታ የክልላችን ነዋሪዎች የመሰማራት ፍላጎት እያደረባቸው ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ያለፈውን ሰባት ወር ተሞክሮ ብናይ፤ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች የዶሮ ልማት ሥራ ለመግባት ጥያቄ አቅርበው ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የአንድ ቀን ጫጩትና የ45 ቀን ቄብ ተሠራጭቷል። ይሄ ከዚህ ቀደም ታይቶ አይታወቅም፤ አሁን ላይ  ፍላጎቱም ሆነ አቅርቦቱ ጨምሯል፡፡ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ወጣቶች በኢንተርፕራይዝ ደረጃ ተደራጅተው የዶሮ ጫጩት የማስፈልፈልና የማቅረብ ሥራ እየሠሩ ነው፡፡ ይህም ከዚህ ቀደም በክልሉ የነበረውን የዶሮና የእንቁላል እጥረት በመፍታት ረገድ አወንታዊ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡

ኢንሼቲፎቻችን የየራሳቸው ስያሜ አላቸው፡፡ ለምሳሌ ዶሮ ልማትን 5-10-25 የሚባል ኢኒሼቲፍ አለ፡፡ በዚያ መሠረት ለአንድ ቤተሰብ ቢያንስ አምስት ዶሮ እንዲኖር በማድረግ በሶስት ዓመት ውስጥ ከ25 ያላነሱ ዶሮዎች ባለቤት እንዲሆን ታልሞ ተሰርቷል፡፡ ይህም ልማቱ አካታች እንዲሆን ምክንያት ሆኗል፡፡ እያንዳንዱ አርሶ አደር ከሚያረባው ዶሮ የሚያገኘውን እንቁላል በመሸጥ ፍየል ወይም በግ ይገዛል፤ በመቀጠልም ጊደር በመግዛት ኢኮኖሚውን በከፍተኛ ፍጥነት እያሳደገ ነው፡፡ በመሆኑም እኛ የዶሮ እርባታን የምናየው እንደ ኢኮኖሚ ሽግግር ማምጫ መሳሪያ ነው፡፡

በሌማት ቱሩፋት መርሃ ግብር እያከናወናቸው ካሉ ሥራዎች ውስጥ ሌላው የንብ ማነብ ሥራ ሲሆን፤ በዚህም በተደረገው ሰፊ ንቅናቄ አሁን ላይ በክልላችን በርካታ የንብ መንደሮች አሉን፡፡ በዋናነትም አንድ ቤተሰብ ቢያንስ ሶስት ዘመናዊ፤ ሰባት ባህላዊ ቀፎ እንዲኖረው ሲሰራ ቆይቷል። በዚህም የተቀናጀ ግብርና ሥራ አርሶ አደሩ ማር እያመረተ በመሸጥ ሌሎች ተጨማሪ ቀፎች የሚጨምርበትን ሽግግር እያደረገ ይገኛል። ይህም ሲባል የንብ መንደሮችን የምንፈጥረው ዝም ብሎ በምናብ ወይም እንዲሁ ለማለት ያህል አይደለም፤ ይልቁኑ በተጨባጭ መሬት ላይ እየተተገበረ ያለ የልማት ሥራ ነው፡፡ ለዚህም አካታች የሆነ የልማት አቅጣጫ በመከተላችን የሚታይ ውጤት ማምጣት ችለናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ ’30-40-30′ በማለት እየተገበረ ባለው ኢኒሼቲፍ ምን ያህል የአርሶ አደሩን ሕይወት መለወጥ ተችሏል?

አቶ ኡስማን፡- እንደተነሳው የአረንጓዴ ዐሻራ አካል የሆነውና 30-40-30 ኢኒሼቲፋችን በዋናነት የተቀረፀው የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ነው። ይህም ማለት አንድ ቤተሰብ በሶስት ዓመት 100 የፍራፍሬ ዛፍ ይኖረዋል፡፡ ለክልላችን አግሮኢኮሎጂ የሚስማሙ የፍራፍሬ ዓይነቶችን ለይተናል፡፡ በዚህም መሠረት አፕል፣ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ሙዝና ፓፓያን ለይተናል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ማንጎ እንደ ሀገር በሽታ ስለተስፋፋ ለጊዜው አቁመነዋል፡፡ ደጋው ላይ አፕልና አቮካዶ፤ በወይና ደጋውና በቆላው አካባቢ ሙዝ በስፋት እያመረትን ነው፡፡ በመሆኑም አንድ ቤተሰብ በሶስት ዓመት ውስጥ 100 የፍራፍሬ ችግኝ እንዲኖረው እየተደረገ ነው፡፡

ተቋማት ደግሞ ከ100 እስከ 10 ሺ የፍራፍሬ ዛፍ በሶስት ዓመት እንዲኖራቸው ይጠበቃል፡፡ ተቋም ሲባልም የማህበረሰብም ሆነ የመንግሥትንም ያካትታል። አብዛኞቹ የማህበረሰብ ተቋማት የምንላቸው የእምነት ተቋማት ሰፊ ጊቢ ይዘው የሚደጎሙት በሕዝብ ነው። ከዘላቂ ማረፊያዎች ውጭ ያሉ የእምነት ተቋማት ቦታዎች ላይ እያንዳንዳቸው 10 ሺ የፍራፍሬ ችግኝ ቢተክሉ የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አቮካዶ ከ25 እስከ 30 ሺ ብር ያወጣል። 10 ሺ የፍራፍሬ ዛፍ ብንተክል ከአስር ዓመት በኋላ አንዷ ዛፍ በትንሹ 25 ሺ ብር ታወጣለች፡፡ ይህም ማለት እያንዳንዱ ተቋም ከፍራፍሬ ልማት ብቻ 250 ሚሊዮን ያገኛል፡፡ በመሆኑም ሁሉም ቤተእምነት ባሉት ቦታዎች እስከ 10 የሚደርሱ ፍራፍሬዎችን ቢተክል ምዕመናን የሚደግፍ እንጂ ከምዕመናን የሚለምን ሊሆን አይችልም፡፡ ተቋማቱ ከተረጂነት ወደረጂነት ይለወጣሉ፤ ይህ ብቻ ሳይሆን የምግብና ሥርዓተ ችግርን ይፈታሉ፤ የሥራ እድል ይፈጥራሉ፤ ምግብ ያቀርባሉ፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት ያቀርባሉ፤ ለውጭ ንግድ ያቀርባሉ፡፡

ይህ መርሃ-ግብር ከመጀመሩ በፊት አንዳንዶች ‘አይሳካም’ የሚል ጥርጣሬ ነበራቸው፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ እኛ ባለፈው ዓመት ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ላይ 10 ሺ አቮካዶ በአንድ ቀን ተክለናል፡፡ በኋላ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አምስት ሺ ጨምሮ በአንድ ካምፓስ 15 ሺ አቮካዶ ተተክሏል፤ አሁን ላይ ሁሉም ፀድቋል፡፡ ስለዚህ ሁሉም የትምህርት ተቋሞቻችን በትንሹ ሶስት ሺ ችግኝ ቢተክሉ የመንግሥት ድጎማ አይጠብቁም፡፡ ራሳቸው መንግሥትንም ሆነ ሀገርን የሚደጉሙ ይሆናሉ። ይሄ ዝም ብሎ ያልተገባ ምኞት ወይም ቀቢፀ ተስፋ ሳይሆን ምህራኑን አማክረን በጋራ ባጠናነው ጥናት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

የንብ ቀፎቹም የሚኖሩት ዛፎቹ ላይ ነው፤ ዶሮና ከብቱም በአንድ በተወሰነ ቦታ ላይ የሚሰራ በመሆኑ በትንሽ መሬት ላይ ከፍተኛ ሀብት መፍጠር ይቻላል። ይህንንም ከንባታ ላይም ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ተግብረነው በተጨባጭ ውጤት ያመጣንበት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በማምረት ሳይሆን በመረዳት የሚታወቁ፤ የአደጋ ስጋት የነበሩ አካባቢዎች ዛሬ ወደ ሀብት ፈጣሪነት ተቀይረዋል፡፡ ብልፅግና ‘ከእዳ ወደ ምንዳ’ እንደሚለው ትናንት እዳ የነበሩ ዛሬ ላይ ወደ ምንዳ ተቀይረዋል፡፡

ከተስፋ መቁረጥ ወደሚጨበጥ ተስፋ ተቀይረዋል። ለአብነት ሲምቢጣን ማንሳት እንችላለን፡፡ የሃላባም ሆነ የስልጤ ሲምቢጣ የተባሉ ሁለት ቀበሌዎች በታሪክ የሚታወቁት በጎርፍ ነው፡፡ በሁለቱም ቀበሌዎች ዝናብ ከመጣ ክልልም ሆነ ፌዴራል ያለ አካል ርዳታ ለማቅረብ፤ ድንኳን ለማድረስ ፤ ለተፈናቀሉ ሰዎች ምግብ ለማቅረብ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ አሁን ላይ ያ የጎርፍ አደጋ ታሪክ ሆኖ ቀርቷል። በዚህ መርሃ-ግብር አማካኝነት በተፈጠረው መነቃቃት ህብረተሰቡ ባዶ መሬቶችን በማልማትና ሙዝ በመትከል አሁን የፍራፍሬና የአትክልት ቀጠና እስከመሆን ደርሷል፡፡ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ድህነት ጨርቁን ጥሎ ከአካባቢው እየጠፋ ነው፡፡ በመሆኑም የ30-40-30 ኢኒሼቲቭ ብዙ ያላየናቸው እድሎችን እንድናይ ፤ ግብርናችን ወደ ውጤት እንዲሄድ አድርጎልናል፡፡

ሌላ ምሳሌ ልጥቀስ፤ በዚህ መርሃ ግብር አማካኝነት ወደ ልማት ከገቡት ደግሞ የቀድሞ ታሪካቸው ድህነትና ችግር ከሆነባቸው አካባቢዎች መካከል ሻሸጎ ዶኦሻ ጎላ ቀበሌ ስትሆን ፤ ይህች ቀበሌ ቀድማ ድህነትን በማሸነፍ ለሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ተምሳሌት ሆናለች። የሚገርመው በአካባቢው የመስኖ አውታር ከተገነባ 15 ዓመት ቢሆነውም፤ ሕዝቡ ግን ግንዛቤ ስላልተፈጠረለትና መስኖውን ተጥቅሞ ስለማያለማ በችግር ውስጥ ለዓመታት ኖሮዋል፡፡ የፍራፍሬ ልማት መርሃ ግብሩ ከተጀመረ ወዲህ ወደ ሀብት ፈጠራ ተሸጋግረዋል። አሁን ላይ ከሰፋፊ የሙዝ መንደሮች ባሻገር በቆሎና መሰል አዝዕርቶች በስፋት እየተመረቱ ነው፡፡ እንግዲህ አስቀድሜ እንደገለፅኩት መሬቱም፤ ውሃውም፤ ሰውም ነበር፤ ሆኖም ሃሳብ ስላልነበርና አቅጣጫ የሚያሳይና ምቹ መደላደል የሚፈጥርለት ባለመኖሩ በድህነት ውስጥ ነበር፡፡ አሁን ሃሳቡ ወደ ተግባር ተቀይሮ ዜጎች ከድህነት መውጣት እና የሥራ እድል መፍጠር ጀምረዋል፡፡ እንደ አጠቃላይ በእኛ ግምገማ ግብርናችን በጥሩ የእድገት ጉዞ ላይ ነው፡፡

ሌላው ከአረንጓዴ ዐሻራ ጋር ተያይዞ ሀገራችን ያላትን ብዙ ፀጋዎች ትርጉም ሳትሰጥ በስህተት መንገድ ላይ ቆይታለች፡፡ እኛ ደግሞ ከክልላችን አንፃር የተለየ ባህሪ ያለው እንሰት እየጠፋ አደጋ ላይ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም እንሰትን ከመጥፋት ወደ ማስፋፋት መሄድ አለብን የሚል ንቅናቄ አካሂደን እንሰት የቀጣዩ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ የሥነ-ምግብ ተስፋ እንዲሆን አቅደን ተንቀሳቅሰናል፡፡ በዚህም የሚታይ ለውጥ አምጥተናል፡፡ በዋናነትም ልማቱን የማስፋፋት ፣ ድህረ ምርት የማቀነባበር ሥራ በመሥራት የሚያስወጣውን ጉልበት የመቀነስና ቴክኖሎጂን መጠቀም እንዲሁም በሽታን ለመቀነስ የጀመርነው ሥራ አለ፡፡

ስለዚህ እንሰት ለሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለኤክስፖርት በሚሆን መንገድ ወደ ዱቄት ቀይረን የምንልክበትን ሁኔታ መፍጠር አለብን ብለን እየሠራን ነው፡፡ በዚህ ዓመት ወደ 84 ሚሊዮን የእንሰት ችግኝ እናቀርባለን ብለን 87 ሚሊዮን ተክለናል፡፡ ዋና ትኩረት አድርገን እየሠራን ያለነው በቆላማ አካባቢ ነው፡፡ መታወቅ ያለበት፤ ከእንሰት ምርት የሚጣል አንድም ነገር የለም፡፡ እንሰት ለሰው ምግብ ነው፤ ለእንስሳት መኖ ነው፤ ለአፈር ማዳበሪያ ይሆናል፡፡ ከምግብነት አንፃር ጤፍ፣ ሩዝ፣ ገብስም ሆነ ሌላ ሰብል በተጋገረ በሶስተኛው ቀን ይሻግታል፤ ከእንሰት የሚዘጋጀው ቆጮ ተጋግሮ ከአንድ ወር በላይ ይቆያል፡፡ ይሄ ወደፊት ምርምርም የሚደረግበት ነው፡፡ በሚቀጥለው ዓመት 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ለመትከል አቅደን እየሠራን ነው፡፡

ዘንድሮ ለየት የሚያደርገው እንሰት ብዙ በማይታወቅባቸው እንደ ሃላባ ባሉ አካባቢዎች እየለማ መሆኑ ነው፡፡ ንቅናቄያችን በጥቅሉ እንደዚህ ዓይነት የተለዩ ነገሮችን ማምጣት አስችሏል፡፡ አሁን የተገኙት ውጤቶች በሙሉ የአዲሱ እሳቤ ቱሩፋቶች ናቸው፡፡ አዲሱ እሳቤ ፀጋን መለየት፣ የለየነውን ፀጋ ማልማት፣ በመጨረሻም ከፀጋችን በመጠቀም ከድህነት ማምለጥ ነው፡፡ ክልላችን እንደ ተቋቋመ ከድህነት የተሻገረ ህብረተሰብ እንፈጥራለን ብለን ነው የተነሳነው፤ መሻገር ዝም ብሎ በህልም አይሆንም፤ በእያንዳንዱ ቦታ አካባቢውን የሚመስሉ እቅዶች ተዘጋጅተው ወደ ተግባር ገብተናል፡፡ ስለዚህ እስከ አሁን የመጣንባቸው መንገዶች በበጋ መስኖም፣ በሌማት ቱሩፋቱም ሆነ በአረንጓዴ ዐሻራም የሚታዩ ተጨባጭ ለውጦች ተገኝተዋል። በተለይም በሌማት ቱሩፋት ማዕድን ከማትረፍረፍ ባለፈ በአካባቢው ልማት ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል ተፈጥሯል፤ በዚህ ልማት የተሳተፉ አርሶ አደሮች በተለይም ሴቶች ገቢያቸውን ማሳደግ ችለዋል፡፡ የግል ባለሀብቱም በዚህ ሥራ ላይ ለመሰማራት መነሳሳት ተፈጥሮለታል፤ የቴክኖሎጂ ሽግግር እየመጣ ነው፡፡ አጠቃላይ ዘርፉ ለዜጎች የገቢና የኑሮ ለውጥ ትልቅ እድል መሆኑን በተግባር ማየት ተጀምሯል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ በቅመማ ቅመም ዘርፍም ለሀገር ከፍተኛ ገቢ እያስገኘ ስለመሆኑ ይጠቀሳል፤ ስለዚህ ሁኔታ ቢያብራሩልኝ ?

አቶ ኡስማን፡– ልክ ነው፤ እንደተባለውም ቀደም ሲል ቡና እና ቅመማ ቅመም በዚህ ክልል እብዛም አይታወቅም ነበር፡፡ ነገር ግን ባለፉት ሁለት ዓመታት የቡና መሬትን ሽፋን የማስፋፋት እና ምርታማነቱን የማሳደግ ሥራ እየተሠራ ነው። በዚህ ዓመት ወደ 52 ሚሊዮን ችግኝ እያባዛን ነው፤ ከዚህ ውስጥ 44 ሚሊዮኑ በዚህ ዓመት የሚተከል ነው፡፡ 10 ሚሊዮኑ ከሚያዝያ ጀምሮ እየተተከለ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን በማድረግ አሁን ወደ 146 ሺ ሄክታር ደርሰናል፤ ይህንን ወደ 165 ሺ ሄክታር ለማድረስ እየሠራን ነው፡፡

ሌላው ቅመማ ቅመም ነው፤ ምቹ የአየር ንብረት በመጠቀም ዝንጅብል፣ ኮሰረት፣ ድንብላልና ሮዝመሪ ወደ ማምረት ገብተናል፡፡ በተለይ ሮዝመሪ ላይ ከፍ ባለመንገድ እየሄድን ነው፤ ሮዝመሪን ለውጭ ገበያ በስፋት ለማቅረብ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ በዚህ መነሻ ዘንድሮ  ከስልጤ ዞን ብቻ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 22 ሺ 760 ኩንታል ሮዝመሪ ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት ልከን 4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ማስገባት ችለናል፡፡ አሁን ይህንን ሮዝመሪ ወደ ጉራጌ ፣ ሃድያ፣ ከንባታ ፤ ወደ ሃላባም የማስፋፋት ሥራ እየሠራን ነው፡፡

ሮዝመሪ ድርቅን እና አሲዳማ አፈርን ይቋቋማል፤ እንዲሁም ደረቃማ በሆነ መሬት ላይ ምርት ይሰጣል።በእነዚህ መነሻዎች ካለፈው ዓመት ጀምረን ሮዝመሪን በተለየ መንገድ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው፡፡ በርበሬ ደግሞ እሴት ጨምረን የመላክ ሥራ ጀምረናል፤ 13 ሺ 780 ኩንታል በመላክ 6 ነጥብ 1ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ችለናል፡፡ ሮዝመሪን በ2014 ዓ.ም ወደ ገበያ ያስገባነው ቢሆንም፤ ባለፈው ዓመት 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ችለናል፡፡ ይሁንና በአካባቢው ሮዝመሪ ከዚህ በፊት የሚታወቀው ለመጥበሻነት እንጂ ዶላር ማምጫነት አይደለም፤ አሁን ሮዝመሪ ከመጥበሻ ወጥታ ወደ ዶላር ማምጫና ሥራ እድል መፍጠሪያ የሀገር ሀብት ምንጭ ሆናለች።

የእኛ ሮዝመሪ አሁን ላይ አውሮፓ ገበያ ገብቶ ግሎባል ካፕ ሰርተፍኬት አግኝቷል፡፡ ሶስት ሺ አርሶ አደሮች ግሎባል ካፕ ሰርተፍኬት እንዲያገኙ አድርጓል። ይህንን ሰርተፍኬት ማግኘታቸው ፕሪሚየም ፕራይዝ እንዲያገኙና አስተማማኝ ገበያ እንዲኖር ያስችላል። ስለዚህ የእኛ ሥራ ጥራቱን ጠብቆ በተቀመጠው መስፈርት መሠረት ማምረትና ማስፋፋት ነው። መጀመሪያ የነበረው አንድ ቀበሌ ላይ ነው። አሁን በሰልጤ ወረዳዎች ሁሉ የማስፋፋት ሥራ ተሠርቷል። በትምህርት ቤቶች፣ በጤና እና በእምነት ተቋማት የመትከል ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ጉራጌ ላይ ወደ 2 ሺ ሄክታር አካባቢ ደርሷል፡፡ ወደ ሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች የማድረስ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ በመሆኑም ሮዝመሪ ለክልላችን በአዲስ እይታ የመጣ አዲስ ምርት ነው፡፡ በቀጣይ ሌሎችንም ቅመማ ቅመሞችንን ለማዕዛማ ዘይት የሚውሉና በትንሽ መሬት ሀብት የሚመነጭባቸውን እየለየን ነው፡፡

ቡናው ላይ የጀመርነው ሥራ በተለይ ባለፉት ወራት አራቱም ዞኖች የየአካባቢያቸውን ስያሜ እንዲያገኙ አድርገናል፡፡ በቀጣይም የማስተዋወቅ ሥራ እንሠራለን፡፡ የአካባቢው ቡና በጣዕም የተለየ ስለሆነ ወደ ውጭ ገበያ እንዲገቡ ከዞኑ ጋር በመተባበር እየተሠራ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በክልሉ የህብረት ሥራ ተቋማት የዋጋ ንረትን ከመከላከል አኳያ ምን ያህል ተጨባጭ ሥራ እየሠሩ ነው?

አቶ ኡስማን፡- ከህብረት ሥራ አንፃር በዚህ ዓመት እንደ ሀገርም እንደ ክልልም ሰፊ የኑሮ ውድነት አጋጥሞ ነበር፡፡ ይሁንና የኑሮ ውድነቱ ሰው ሠራሽ ነው፤ ምርት እያለ የገበያ ሰንሰለቱ በመራዘሙ ምክንያት የማይገባቸው አካላት በገበያ ውስጥ ገብተው በሚጫወቱት ሕገወጥ ሚና የምርት ዋጋ እየናረ ነበር፡፡ በመሆኑም ህብረት ሥራ ማህበራት በክልል ባሉ ትላልቅ ከተሞች የሰንበት ገበያ፣ የሐሙስ፣ የማክሰኞ ገበያ ወዘተ እያልን በማቋቋም በሳምንት ሁለትና ሶስት ቀን ማህበራቱ ምርቶቻቸውን እያቀረቡ ለአካባቢው ዋጋ መረጋጋት ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ነው፡፡ ስለዚህ የህብረት ሥራ ማህበራቱ የግብርና ምርቶችን ዋጋ ለማረጋጋት ሸማቹ ህብረተሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርት በማቅረብ ረገድ ሰፊ ሥራዎች ተሰርተዋል።የእኛ ግምገማ እንደሚያሳየው በዚህ ተጨባጭ ውጤቶች መጥተዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በክልሉ ከ30 ዓመታት በፊት ተተክለው የነበሩ ባህር ዛፎችን በሙዝ የመተካቱ ሥራ ምን ያህል ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ይኖረዋል ?

አቶ ኡስማን፡- እንደተነሳው በክልላችን ባህር ዛፍን በፍራፍሬ የመተካት ሥራ በስፋት እየተሠራ ነው፡፡ ይህ ባህር ዛፍ ለኢኮኖሚው እዚህ ግባ የማይባል አበርክቶ ስላለው ብቻ ሳይሆን፤ በሥነ-ምህዳሩ ላይ እያደረሰ የነበረው አሉታዊ ተፅዕኖ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። ያደረሰውን ለአብነት መጥቀስ ካስፈለገ ስልጤ ዞን ላይ የሚገኘው ስልጢ ሃይቅ ተጠቃሽ ነው። ስልጢ ሃይቅ ከሶስት ዓመት በፊት ዙሪያው በባህር ዛፍ የተሸፈነ ነበር፡፡ ሃይቁ በባህር ዛፉ ምክንያት ውሃው እየቀነሰ፤ በዙሪያወም የነበረ የተፈጥሮ ሀብት እየጠፋ ነበር። ሆኖም ባለፉት ሁለት ዓመታት በተሠራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራና ሰፊ ንቅንቄ 25 ሄክታር ተነቅሎ፤ ሙዝ እንዲተከል ተደርጓል፡፡ እዚህ ላይ ሙዙ ዝም ብሎ የተተከለ አይደለም፡፡ ያመጣው ኢኒሼቲፉ ነው፤ በዙሪያው የሚኖሩ አርሶ አደሮችን የማሳመን ሥራ ተሠርቷል፤ አርባ ምንጭ ሙዝ አምራች አርሶ አደሮች ጋር ተሞክሮ ወስደዋል፡፡

ከኢኮኖሚ ፋይዳ አኳያ በአንድ ስኩዌር ሜትር መሬት ከሁለት ባህር ዛፍ በላይ አይተከልም፤ ከዚህም ቢሆን ገቢ ለማግኘት እስከ ሰባት ዓመት ይወስዳል፡፡ ሲሸጥም አራት መቶ ብር በላይ አይሆንም፡፡ ግን በአንድ ስኩዌር መሬት ላይ አንድ ሙዝ ቢተክል በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ከእናት ሙዙ ውጭ ከ10 እስከ 15 የሙዝ ችግኝ (ሰከር) ማውጣት ይቻላል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ስምንቱን ብቻ ነቅሎ ቢሸጥ 240 ብር ይገኛል፡፡ በድምሩ በችግኝ ብቻ አምስት መቶ ብር ማግኘት ይቻላል፡፡ በመሆኑም መጀመሪያ የሠራነው ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ነው፤ በኋላ ተሞክሮ ወስዶ ወዲያው ወደ ተግባር እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ አሁን ላይ ከሰልጤ ባሻገር ከንባታና አላባ እንዲሁም በሌሎቹ የክልሉ አካባቢዎች ባህር ዛፍ እየተነቀለ ሙዝ የመትከል ሥራ በስፋት እየተሠራ ነው፡፡

ባህር ዛፍ ተዘርዝሮ የማልቁ የሥነ ምህዳር ጉዳቶችን ያደርሳል፤ አንደኛው ውሃ የሚባል አይኖርም፡፡ ወንዝ፣ ሃይቅና ጅረትንም ጭምር የማድረቅ አቅም አለው፡፡ በሌላ በኩል ባህር ዛፍ ባለበት አካባቢ ማንኛውም ሌላ አዝርዕትም ሆነ ተክል አይበቅልም፡፡ ደግሞም ባህር ዛፍ በበቀለባቸው መሬቶች የአፈር ተፈጥሯዊ አወቃቀር ሳይቀር ይቀየራል፡፡ ከሁሉ የባሳው ደግሞ በባህር ዛፍ የተጎዳ አፈርን ወደ ተፈጥሯዊ ይዘቱ ለመቀየር ጊዜ ይፈልጋል። በጥቅሉ ባህር ዛፍ ትጋት የሚፈጥር ሳይሆን ትጋት አምካኝ ነው፡፡ ከገቢ አንፃርም አንዴ ተተክሎ የሚደርስ ከሰባት ዓመት በኋላ ነው፤ በመሆኑ ሕዝቡ ቁጭ እንዲል እንጂ እንዲሠራ አያበረታታም፡፡ አካባቢም ያመክናል፡፡ የአፈር ለምነት የሚባል ነገር አይታሰብም፡፡

የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራችን፤ የጠቅላይ ሚኒስትራችን ኢኒሼቲቮች ደግሞ ዘላቂ የሕዝቦችን ጥቅም የሚያረጋግጡ ናቸው። የበለፀገች ሀገር ለመገንባት፣ የዛሬውን ትውልድ እየጠቀመ፣ ለነገው ትውልድ ቅርስ ማኖር ነው፡፡ ያ ከሆነ ሐይቆቻችንም መጠበቅ አለባቸው፤ ወንዞቻችን መልማት አለባቸው፣ ምንጮቻችንም ይበልጥ መጎልበት አለባቸው። ባህር ዛፍ ግን ይህንን እያመከነ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ለማስተካከል እየሠራን ነው። በአጠቃላይ በክልላችን የተቀናጀ ግብርና ልማት ሥራችን በውጤታማ ጉዞ ላይ እንደሆነ ገምግመናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በክልሉ እንደ በቆሎ ያሉ ሰብሎች ምርጥ ዘር ፤ እንዲሁም እንደትራክተርና የውሃ መሳቢያ ፓምፖች ያሉ መሳሪያዎች እጥረት እንዳለ በመስክ ምልከታችን ተመልክተናል፡፡ የክልሉ መንግሥት ይህንን ችግር ከመፍታት አንፃር ምን እያከናወነ ነው?

አቶ ኡስማን፡- ሁልጊዜም ቢሆን ልማት ሲመጣ አዳዲስ ፍላጎቶችን ይፈጥራሉ፤ ተፈጥሯዊ ነው፤ ወደ ሃላባ ስትሄዱ ሲምቢጣ የሚባለው አካባቢ ሙሉ ለሙሉ የሚታወቀው በጎርፍ ነው፡፡ መኪና መንገድ ቢፈለግ እንኳን ድንኳን ለማስጋባት ወይም የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማውጣት ካልሆነ በስተቀር ሌላ አጀንዳ አልነበረም፡፡ አሁን ላይ ያ አካባቢ በመልማቱ ምርት ለማውጣት የመንገድ ጥያቄ አለ፡፡ እዛ ብቻ አይደለም ሌሎች ቦታዎች ላይ ልማቱ ሲመጣ ልማቱ የወለደው ጥያቄ አለ፤ እሱን መመለስ የግድ ይላል፡፡ እኛ አልምተን፤ መናሳሳት ከፈጠርን በኋላ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ መስጠት የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡

ልማት የወለዳቸው ጥያቄዎች ችግር የማይሆንበት ምክንያት ለምሳሌ ሃላባም ሆነ ሌሎች አካባቢዎች ላይ ፓምፕ እያቀረበ ያለው መንግሥት ነው፡፡ ቀድመው የቀረቡት በነዳጅ የሚሰሩ ነበሩ፤ አሁን ላይ ደግሞ ለአገልግሎት እየዋሉ ያሉት በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ ናቸው። በዋጋ እነዚህኞቹ ቀነስ ስለሚሉ፤ ቤኒዚኑንም ሆነ ናፍጣውን ማግኘት እንዲሁም ማጓጓዝም ፈታኝ በመሆኑ አሁን ላይ የሚነሳው ጥያቄ በፀሐይ የሚሰሩ በርከት ብለው ይግቡ የሚል ነው፡፡

በመሠረቱ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ ሲባል መንግሥት በተወሰነ ደረጃ ገዝቶ ሊሰጥ ይችላል፤ ሆኖም ገዝቶ የመጠቀም ኃላፊነት የአርሶ አደሩ ነው፡፡ በፀሐይ የሚሰሩትን ፓምፖች ያስገባንባቸው እንደ ሲምቢጣ፣ ላንፎሮ፣ ሳንኩራ ፣ ማረቆና መስቃን አካባቢዎች ላይ ተጨማሪ የይምጣልን ጥያቄ ይነሳል፡፡ የሚመጣው ከውጭ ነው፤ ዝም ብሎ በአጭር ጊዜ የሚሆን አይደለም፤ ግን ደግሞ እየሠራን ነው። በተለይ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት በግብርና ሚኒስቴርም ጥያቄውን አቅርበናል። እዚህ ላይ ሶላር ፕንፑን ማስመጣት ከጀመርን ገና ሁለት ዓመት አልሞላውም፤ ነገር ግን ፍላጎቱ በአንድ ጊዜ ጨመረ፡፡ ይህ በእኛ እይታ ጥሩ ነው፡፡ በተለይ ከበቆሎ ምርጥ ዘር አኳያ የተነሳው ጥያቄ አጠቃላይ የበቆሎ ዘር እጥረት ኖሮ ሳይሆን ከተለመደው ዝርያ ለመውጣት ካለመሻት የመነጨ ነው፡፡

ፓዮነር የተባለ የበቆሎ ዝርያ እጥረት አለ። የሚባዛው ወለጋና ጎጃም እንዲሁም ጉራጌ ዞን አበሽጌ ላይ ነው፡፡ የሚሰራጨውም ለመላው ሀገሪቱ ነው፡፡ ፍላጎቱ ከፍ ስላለ ለሁሉም ማድረስ አይቻልም፡፡ ግን ፓዮነር የተባለው ዝርያ የሚሰጠውን ያህል ምርት የሚሰጡ ምርጥ ዝርያዎች አሉ፡፡ በመሆኑም ታች ያለው የእኛ መዋቅር ቢሆን አንዴ የገባውን ምርት ዘር ከማየት ይልቅ ሌሎች አማራጮችን ያለ ማየት ችግር አለ። ደግሞም በቆሎ ብቻ መዝራትም ላያስፈልግ ይችላል፤ ሌሎች ሰብሎችን እንደ አማራጭ መጠቀም ይገባል። ድንችም፤ ሽንኩርትም መትከል ይቻላል፡፡ እንደየአካባቢው ሥነ ምህዳር፤ አየር ንብረትና ወቅት እያዩ አዋጭ የሆነውን ምርት ማምረት ይቻላል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ሌላ ምሳሌ ላንሳ ዘንድሮ የበጋ ስንዴ አምና ካመረትነው አንፃር በጣም ቀንሰናል፡፡ በዚያ ምትክ የተቀረውን መሬት በአትክልት በመሸፈን አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን አድርገናል፡፡ በበልግም በቆሎ ማሽላና ዘንጋዳ በተለምዶ ይመረትባቸው የነበሩ አካባቢዎች አትክልት እያለማን ነው። በዚህም ብዙዎች ላይ መነሳሳት ተፈጥሯል። አንዳንዶች ጋር የጎመን ክላስተር፣ የቲማቲም ክላስተር ተፈጥሮ እየለማ ነው፡፡ ምክንያቱም ደግሞ አዋጭ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሄክታር በቆሎ ዘርተን የቱንም ያህል ብንከባከበው ከ80 ኩንታል በላይ በሄክታር ማግኘት አይቻልም፡፡ ድንች ተክለን ከ350 እስከ 450 ኩንታል ማግኘት እንችላለን፡፡ ይህም ከበቆሎው ጋር ፈፅሞ ሊነፃፀር የሚችል አይደለም፡፡ በምርት መጠንም ሆነ በዋጋ የሚገኝ አይደለም፡፡

አዲስ ዘመን:- በመስክ ጉብኝታችን የወተት ምርት በብዛት እየተመረተ ቢሆንም የገበያ ትስስር ባለመፈጠሩ አምራቾች ይበላሽብናል የሚል ስጋት አለባቸው፤ ከመሠረተ ልማት ማሟላት ጋርም አትክልት፣ ፍራፍሬና ሰብሎች የሚፈለግበት ቦታ ሳይደርስ እንደሚበላሽ ተመልክተናል ከዚህ አኳያ ክልሉ ምን እየሠራ ነው?

አቶ ኡስማን:- ገበያ ትስስሩ ላይ የተሠራው ምርቱን ማትረፍረፍ ነው፡፡ በዛው ላይ የገበያ ትስስሩን በተለያየ መንገድ ማጠናከር ላይ ትኩረት ተደርጓል፡፡ በመጀመሪያ የፈጠርነው የወተት መንደሮች ነው፡፡ አምራቾቹ ወደ ህብረት ሥራ ማህበራት እንዲቀየሩ በመቀጠል ተደራጅተው በአነስተኛ ደረጃ እያመረቱ ያሉትን ከሀገር ውስጥ ገበያ ጋር የማስተሳሰር፤ በመቀጠልም አነስተኛ የማቀነባበሪያ ኢንደስትሪዎች ውስጥ እንዲገቡ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ለምሳሌ ከምባታ በቅርቡ ይጀመራል፡፡ በመቀጠል ቡታጅራ፣ ወልቂጤ፣ ወራቤ፣ ሀላባ እያልን እንቀጥላለን። እንደ እኔ እምነት የማስቀመጥና የማጓጓዝ ጉዳይ ችግር አይሆንም፡፡ እርጎውም፣ ቅቤውም፣ ክሬሙም አንዱ ጋር ሲከማች ሌላ ቦታ ሄዶ ይሸጣል፡፡ መጀመሪያ ግን የተሠራው የወተት መንደሮችን የመፍጠር ሥራ ነው፡፡ ጎን ለጎን ገበያውን የማመቻቸት ሥራ እየተሠራ ነው፡፡

የመንገድ ጉዳይ የብላቴ እና ሌሎችም ልማቱ እስካለ ድረስ መንገዱ በተለያየ መንገድ ይሠራል፡፡ በሕዝብ ተሳትፎ የሚሠራ፣ በወረዳ አቅም፣ በዞንና በክልል ደረጃ በዩራፕ ፕሮግራም የሚሠራ እና በክልል አቅም ከዞኖች ጋር በመቀናጀት ይሠራል። ይህም ቅደም ተከተል ወጥቶለት ይሠራል፡፡ ከክልል አቅም በታች የሆነ ጥያቄ ዋናው ልማቱ እስካለ ድረስ የክልል መንግሥት ኃላፊነቱን ወስዶ ይሠራበታል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በስልጤ ዞን ሲምቢጣ በተባለው አካባቢ ለዓመታት ጥቅም ሲሰጥ የቆየ የመስኖ ግድብ በመሰበሩ ምክንያት ሙዝ አምራች ገበሬዎች በከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸውን አይተናል፡፡ የክልሉ መንግሥት ይህንን ችግር ያውቀዋል? ካወቀ ችግሩን ለመፍታት ምን እየሠራ ነው?

አቶ ኡስማን፡- በነገራችን ላይ ይህ የብላቴን ወንዝ በመጥለፍ ለልማት የተሠራው ግድብ ከተገነባ 15 ዓመት አልፎታል፡፡ ሆኖም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ጥቅሙን ተገንዝቦ ልማት ላይ ያዋለው አልነበረም፡፡ ሆኖም ከሁለት ዓመት ወዲህ በተደረገው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ወንዙ በሚያዋስናቸው ስልጤ ፤ ሃላባና ሃድያ እንዲሁም ጉራጌ ዞኖች ላይ መስኖው በተለይም ለሙዝ አምራቾች ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጓል። እንዳልኩት ይህ ወንዝ ለዓመታት እንዲሁ ሲፈስ ኖሮ የበጋ መስኖ ማምረት ከተጀመረ በኋላ የላይኛው አምራቾች በተለይ ጉመር ላይ ሲያመርቱ ውሃው እያነሰ መጣ፡፡ በዚሁ ውሃ ምክንያት ሃላባ አንዳንድ ቀበሌዎች አምና እንዳላመረቱ መረጃ አለኝ፡፡

የክልሉ መንግሥት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እየተካሄደ ይገኛል። የውሃ ተጠቃሚዎች ማህበር ተደራጅቶ በትብብር እየተሠራ ነው፡፡ ችግሩ ተለይቷል ለመፍትሔው እየተሠራ ነው፡፡ ግድቡ ላይ የደረሰውን ጉዳት በሚመለከት በጎርፍ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ሥራውን ለማከናወን ሀብት እየተፈለገ ይገኛል፤ የክልሉ ውሃ አስተዳደር ኤጀንሲ ይሠራዋል። በሽግግር ላይ ያለ ክልል እንደመሆኑ ጊዜ የሚፈልጉ ሥራዎች አሉ፡፡

አዲስ ዘመን:- በክልሉ ከአነስተኛና ጥቃቅን ተነስተው ወደ መካከለኛ ኢንተር ፕራይዝነት መሸጋገር ለሚፈልጉ ወጣቶች እየቀረበ ያለው የብድር አቅርቦት አነስተኛ መሆኑን ሰምተናል ችግሩን ለመፍታት ምን እየሠራችሁ ነው ? ለጀማሪዎች በፋይናስ ተቋማት የተቀመጠው መስፈርትስ ተገቢ ነው ብለው ያምናሉ?

አቶ ኡስማን:- የብድር አቅርቦቱን በሚመ ለከት የቸሃ ወጣቶች ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ጥሩ ሞዴል የሚሆኑ ናቸው፡፡ ከ28 ሺ ብር ተነስተው አሁን በርካታ ሚሊዮን ብር ላይ ደርሰዋል፡፡ ከአንድ ሄክታር ተነስተው ዛሬ 30 ሄክታር አካባቢ አልምተዋል፡፡ ይሄ ደግሞ ብዙ ሀብት እየፈጠረ ነው፡፡ ለእርሱ ሀብት መፍጠር ብቻ ሳይሆን አምስት ሆነው በርካታ የሥራ እድል ፈጥረዋል፡፡ ይሄ ሽግግር ነው፡፡ መጀመሪያ ትናንሽ ኢንተርፕራይዝ ነበሩ፣ ወደ መለስተኛ ከሄዱ በኋላ ወደ ኢንቨስተር ሲሸጋገሩ ከልማት ባንክ ጋር ይተሳሰራሉ፡፡ ችግሩ በዚህ ይፈታል፡፡ እንደተነሳው ከክልሉ ኢንደስትሪና የኢንቨስትመንት ቢሮ ጋር ባደረግናው የመስክ ምልከታ ችግሩን አይተናል፤ ብዙም ባረዘመ ጊዜ ችግሩ መልስ ይሰጠዋል፡፡

መስፈርትን በሚመለከት የሚሠራው የክልሉ ሥራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ነው። ሀገራዊ መስፈርት ተደራጅቷል። በእነርሱም በኩል እርሾ ያስፈልጋል፤ እርሾና መንግስት የሚያቀርበው መመጣጠን አለበት። ማየት ያለብን ያደጉ ሀገራትን አይደለም፡፡ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሀብት በየቦታው ባክኖል፡፡ ትክክለኛ አልሚው የትኛው እንደሆነ የሚለየው እድል ተሰጥቶ ነው እንጂ እንዲሁ መፈረጅ አይቻልም፡፡ የብድሩ መጠን ይደግ መባሉ ጤናማ ነው፡፡ ነገር ግን የሥራ አጥ ቁጥር ብዙ ነው፡፡ ያለው ሀብት ደግሞ ትንሽ ነው፡፡ በመሆኑም ማጣጣም ያስፈልጋል፡፡ የተሳሳተ አስተሳሰብ በመያዝ ገንዘብ ተበድረው ያልተቀየሩ ብዙዎች አሉ፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ተበድረው ሰርተው የተለወጡ፤ ለሌሎችም የሥራ ዕድል የፈጠሩም አሉ፡፡ በመሆኑም ሁሉንም በሚዛኑ ማየት ተገቢ ነው ባይ ነኝ፡፡

አዲስ ዘመን:- ምስራቅ ጉራጌ ዞን መስቃን አካባቢ የግሪሳ ወፍ ወረርሽን መከሰቱን አይተናል። ይህንን በመከላከል ረገድ ምን እየተሠራ ነው?

አቶ ኡስማን:- እንደተባለው በመስቃን የተወሰነ አካባቢ ላይ በጣም ጥቂት በሚባል ደረጃ የግሪሳ ወፍ ሥርጭት ታይቷል፡፡ ሆኖም በወረርሽኝ ደረጃ የሚነሳ አይደለም፡፡ ግን ደግሞ ጥቂት ቢሆን ምላሽ መሰጠት ስላለበት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር እየተነጋገርን እንገኛለን። በሄሊኮፍተር ኬሚካል ርጭት መፍትሔ ለማምጣት እየተሠራ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን ሄሊኮፍተሮቹ የሚመጡት ከአጎራባች ክልሎች እየተነሱ በመሆኑና ርቀት ያለው በመሆኑ የሚፈለገው ያህል ውጤት በፍጥነት ማምጣት ከባድ ነው፡፡ በመሆኑም በቅርብ ርቀት ማረፊያ ሥፍራ ለማዘጋጀት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

አቶ ኡስማን፡- እኔም ስለክልሉ የልማት ሥራ እንዳብራራ እድሉን ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You