የግብርናውን ዘርፍ መልካም ዕድሎች አሟጠን እንጠቀም!

የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት በማሳደግ በኩል እንደ ሀገር በርካታ ተግባሮች ተከናውነዋል፤ ይህን ተከትሎም በርካታ ለውጦች ታይተዋል፡፡ የልማቱን አማራጮች በማስፋት፣ የአርሶ አደሩንና የግብርናውን ቤተሰብ አመለካከት በመቀየር፣ በግብዓት፣ በፋይናንስ አቅርቦትና በመሳሰሉት ላይ በእርግጥም ለውጦች ታይተዋል፡፡

ከመኸርና ከበልግ እርሻ ተገቢውን ምርት ለማግኘት እየተከናወኑ ባሉ ተግባሮች ምርትና ምርታማነቱን ማሳደግ ተችሏል፡፡ ግብርናውን በሜካናይዜሽን፣ በምርጥ ዘርና በማዳበሪያ በመደገፍ፣ ለአርሶ አደሩ ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ የኩታ ገጠም እርሻን በማስፋፋት የምርምር ሥራዎችን መሬት ላይ በማውረድ በእርግጥም ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ ተችሏል፡፡

አንድም ማሳ ጦም እንዳያድር በሚል በተወሰደ እርምጃ ለኢንቨስትመንት የተያዙ መሬቶች ሳይቀሩ በሰብል እንዲሸፈኑ በማድረግ ተሠርቷል፤ በተቋማት ግቢ የሚገኙ ለልማት ያልዋሉ መሬቶችም በተመሳሳይ ለእርሻ ሥራ እንዲውሉ ተደርጓል፡፡

ሰብሎችን እንደ አንበጣና ተምች ካሉት ተባዮች በመጠበቅ፣ ብክነቶችን በመከላከል ላይ በትኩረት በመሥራትም ምርትና ምርታማነቱ ይበልጥ እንዲያድግ በመሠራቱ ለውጦችን ማምጣት ተችሏል፡፡

እነዚህ ሁሉ ሆነውም ከግብርናው ዘርፍ እየተገኘ ያለው ምርት ከሀገሪቱ ፍላጎትና አቅም አኳያ ሲታይ አሁንም እዚህ ግባ የሚባል ሊሆን አልቻለም። ዘርፉ ካለው እምቅ አቅም አኳያ፣ ሀገር ዘርፉን ይዛ ብዙ ርቀት ለመጓዝ ካላት ጽኑ ፍላጎት አኳያ ሲታይ በእርግጥም ዘርፉ ገና ብዙ እንዳልተሠራበት ይገለጻል። ግብርናው ብዙ ከወጣበት የምግብ ዋስትናን በሚገባ ከማረጋገጥ ባለፈም በውጭ ምንዛሪ ግኝትና በመሳሰሉት ብዙ ሀብት ሊገኝበት እንደሚችል የሚታመንበት እንደመሆኑ ይህን ለማረጋገጥ ገና ብዙ መሠራት ይኖርበታል፡፡

መንግሥትም ባለፉት ዓመታት ይህን ሁኔታ ለመቀየር ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት ሊያወጣ የሚችል፣ ሀገሪቱ ያላትን የውሃና የመሬት ሀብት በሚገባ በመጠቀም በተለይ የሰብል ምርትና ምርታማነቷን ማሳደግ በሚያስችል ሥራ ላይ ተጠምዷል፡፡

ይህም በተለይ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በሚገባ እየታየ ነው፡፡ በዚህ ልማት እየተከናወነ ያለው ተግባር በሀገሪቱ የውሃ ሀብትና ለም መሬት ላይ በሚገባ ከተሠራ የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት አሁን ካለበት ጥሩ ሁኔታም በእጅጉ እንዲመነደግ ማድረግ ይቻላል። ይህንንም በዚህ ልማት ባለፉት ዓመታት ከተከናወኑ ተግባሮች መረዳት ይቻላል፡፡

የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት በ2011 ሲጀመር የተገኘው 100 ሺ ኩንታል ስንዴ ነበር፤ ይህን ምርታማነት በ2016 ዓ.ም 120 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡ ከደረሰው የበጋ መስኖ ስንዴ አዝመራ እስከ አሁንም ከ58 ሚሊዮን ኩንታሉ ስንዴ ተሰብስቦ ወደ ጎተራ ገብቷል፡፡ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ የታየው ለውጥ ምን ያህል እንደሆነ ከዚህ መረጃ መረዳት ይቻላል፡፡

በዚህች ሀገር ከአንድ ማሳ ሁለት ሦስቴ ማምረት እየተቻለ ነው፡፡ የመኸርና የበልግ ወቅትን ብቻ ተጠቅሞ የእርሻ ሥራን ከመሥራት በመውጣት፣ በዓመት እስከ ሁለት ሦስቴ ማምረት መቻል ምን ያህል ምርታማነትን ሊጨምር እንደሚችል፣ ምን ያህል የአርሶ አደሩን ሕይወትም መቀየር አንደሚችል መገንዘብ አያዳግትም፡፡

በከተማ ግብርና እና በሌማት ትሩፋት እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮች ከተሜው ሸማች ብቻ ከመሆን እንዲወጣ እያደረጉ ናቸው፡፡ ግብርናን የከተማም ሥራ ጭምር ማድረግ እየተቻለ ሲሆን፣ በከተሞችና አቅራቢያቸው የሚገኙ ክፍት ቦታዎችን ለግብርና ሥራ በማዋል ዜጎች ከአትክልትና ፍራፍሬ፣ የወተትና ወተት ተዋፅዖ፣ ወዘተ ምርቶችን በስፋት የሚያገኙበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ከየከተሞቹ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም ሥራው ውጤታማ እየሆነ መጥቷል፡፡

የሀገራችን አርሶ አደር በበጋ ወቅት አዝመራው ከሰበሰበ በኋላ በሥራ ፈትነት ነበር የሚታወቀው። ይህ ሁኔታ በጥር ወር አካባቢ መካሄድ በጀመረው የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ መሰበር የጀመረ ሲሆን፣ በመስኖ ልማት በተለይም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ እምርታ ማሳየት ችሏል። አርሶ አደሩን ለዚህ አይነት ሕይወት፣ ግብርናውን ለእዚህ አይነቱ የላቀ ደረጃ የበቃ ይህ የእርሻ ልማት እንዲበራከት ማድረግ ላይ በቀጣይም በትኩረት መሥራት ይኖርበታል፡፡

በቀጣይም የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ሊያሳድጉ የሚችሉ የትኛዎቹም ዕድሎችና ምቹ ሁኔታዎች በሚገባ ሊሠራባቸው ይገባል፡፡ ልንጠቀምባቸው የሚችሉ በርካታ ዕድሎች አሁንም አሉን፡፡

አንዳንዴ ወቅቶች መልካም ዕድሎችን ይዘው ይመጣሉ፡፡ ወቅቶች ሲሰጡ መስጠታቸውን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ለአብነትም የዘንድሮውን የበጋ ወቅት መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንደ ዘንድሮው የበጋ ወቅት ያለ ዝናብ ሲገኝ መሥራት ባለብን ላይ መሠራት ይኖርብናል፡፡

የዘንድሮው በጋ ገርና እርጥብ ነው፤ ዝናብ ሰጥቶናል፡፡ በአዲስ አበባም ከአዲስ አበባ በተለያዩ አቅጣጫዎች ሲወጣም ሜዳው ጋራው ሸንተረሩ አረንጓዴ ሆኖ ነው የሚታየው፡፡ ይህ ወቅት ይዞት የመጣው ዕድል ብዙ ነው፡፡

ዝናቡ እንስሳት በቂ ግጦሽና ውሃ እንዲያገኙ፣ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሮች የተተከሉ የፍራፍሬና የተለያዩ የዛፍ ተክሎች እድገት እንዲፋጠን፣ ምርታማነት እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ የጓሮ አትክልቶች በበጋ ወቅት ጉዳት እንዳይደርሰባቸው ብቻ አይደለም የሚያደርገው፤ ምርታማ አንዲሆኑም ያስችላል፡፡

የመሬት እርጥበት እንዲጨምርና የመኸርና የበልግ እርሻው በሬዎችን ሳይጎዳ በቀላሉ እንዲፈጸም ያስችላል፡፡ በተሰነጠቀው ማሳ የዝናቡ ውሃ እንዲተኛና ወደ መሬት እንዲሰርግ በማድረግ ለመሬት እርጥበት መጨመር ትልቅ አስተዋፅዖ ያበረክታል፡፡

ለመስኖ አገልግሎት የሚውሉ ወንዞች ውሃን ከመሟጠጥ ከመታደግም በላይ አቅማቸው እንዲጨምር ያደርጋል፤ ሰፋ አርጎ ለሚያስብም ዝናቡ የከርሰ ምድር ውሃ አቅም እንዲጎለብት ያስችላል፡፡

ይህ አይነቱ ዝናብ የሚገኝበት የበጋ ወቅት ምንም አንኳ እንደ መኸር፣ በልግና የመስኖ ወቅቶች የራሱ መርሐ ግብር ወጥሎት እንደ ዘር ወቅቱ በሬ ተጠምዶ ሆ ተብሎ የእርሻ ሥራ ባይከናወንበትም፣ ለግብርናው ሥራ በአጠቃላይ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ስለመሆኑ ንግግር አያሻውም፡፡

የበጋ ወቅት ዝናብ ስላለው ፋይዳ ከዓመት በፊት ድርቅ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ጉዳት ባስከተለበት ማግስት በጋ ላይ በጣለው ዝናብ የዝናብ ውሃ እንዲይዙ የተሠሩ ግድቦች ውሃ የያዙበት ሁኔታና ውሃው ለከብቶችና ለሰዎች የሰጠው ጥቅም ሲታሰብ የበጋ ወቅቱን ዝናብ መያዝ አስፈላጊነትን ፋይዳ ያመለክታል፡፡ አንዲትም ጠብታ ውሃ ብትሆን እንዳትባክን ለመሥራት ከወዲሁ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡

በመንግሥት የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም ብዙ ርቀት መጓዝ እንደታቸለ ሁሉ መልካም አጋጣሚዎች ይዘዋቸው የመጡ አቅሞችንም በሚገባ አሟጦ መጠቀም ይገባል፡፡

የብሔራዊ ሜትዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ባለፉት ወራት በተለያዩ አካባቢዎች ዝናብ ጥሏል፡፡ መሬት ላይ የሆነውም ይሄው ነው፡፡ አሁንም ዝናብ ማግኘት የሚቻልባቸው ሁኔታዎች ሰፊ ናቸው፡፡ ይህን ተፈጥሮ የቸረንን የዝናብ ፀጋ ለመጠቀም አርሶ አደሮች እንደሚታትሩ ይጠበቃል፡፡ ይህ ጥረታቸው ግን በባለሙያ በሚገባ ሊታገዝና ውጤታማ በሆነ መልኩ ሊቃኝ ይገባል፡፡

እስመ ለአለም

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You