ከሥራ ጠባቂነት ወደሥራ ፈጣሪነት

ዜና ሐተታ

እጅ ካልቦዘነ ሥራ አይጠፋም እንደሚባለው በኦሮሚያ ክልል በሸገር ከተማ አስተዳደር፣ በገላን ጉዳ ክፍለ ከተማ በተለያየ ሴክተር ተደራጅተው ወደሥራ የገቡ ማኅበራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሥራ ጠባቂነት ወደሥራ ፈጣሪነት እየተሸጋገሩ መሆናቸውን ይገልጻሉ።

ቀደም ሲል ቋሚ ሥራ ያልነበራቸውና ገሚሱም በቤት እመቤትነት ኑሯቸውን ይገፉ እንደነበር የሚናገሩት በማኅበር የተደራጁ ዜጎች፤ በአሁኑ ወቅት ግን በገላን ጉዳ ማዘጋጃ ቤት አማካይነት በተገነባላቸው ሼዶች ውስጥ በማኅበር ተደራጅተው ሥራ ከጀመሩ ከአንድ ወር በላይ እንደሆናቸው ያስረዳሉ። በአጭር  ጊዜ ውስጥ ለውጦችን እያስተዋሉ መሆናቸውንና በቀጣይ ሥራቸውን አሳድገው ከራሳቸው አልፈው አገርን ለመጥቀም እንደሚተጉ ነው ያመላከቱት።

ሮበሌ፣ መለሰ እና ጓደኞቻቸው የወተት ከብትና እርባታ ኅብረት ሽርክና ማኅበር አባል የሆኑት አቶ መለሰ ጋረደው እንደሚናገሩት፤ ማኅበሩ በአምስት አባላት ሲመሠረት 16 የወተት ከብትና እርባታ እንስሳቶችን ይዘው ነው። ሥራውን የጀመሩት መንግሥት ባመቻቸው ሼድ ሲሆን፣ ቀደም ሲል ግን ተባራሪ ሥራ በመሥራት ጉልበትና ገንዘባቸውን ከመጨረስ ውጭ ያተረፉት ነገር አልነበረም። በአሁኑ ወቅት አቅም በማጎልበት ላይ በመሆናቸው ለሦስት ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደቻሉ ይናገራሉ።

የቀድሞዎቹ ሥራ አጦች፤ ከሥራ ጠባቂነት ወደሥራ ፈጣሪነት እየተሸጋገሩ በመሆናቸው ለሌሎች ሥራ ማግኘት ምክንያት መሆን መቻላቸውን ያስረዳሉ።

በገላን ጉዳ ክፍለ ከተማ ዳለቲ ወረዳ ማሕሙድ፣ ሀዋ እና ጓደኞቻቸው ኅብረት ሽርክና ማኅበር አባል የሆኑ አቶ ሐጂ ከድር በበኩላቸው፤ ማኅበራቸው፤ መንግሥት በሰጠው ሼድ ሁለት ሺ 500 የእንቁላል ዶሮዎችን በማርባት ላይ እንደሚገኝ ይገልጻሉ።

ቀደም ሲል ሥራ ያልነበራቸው መሆኑንም ጠቅሰው፤ አሁን በገላን ጉዳ ክፍለ ከተማ በተደረገላቸው ድጋፍና ያልተቋረጠ ክትትል ውጤታማ ሥራ በማከናወን ከራሳቸው አልፈውም ለሁለት ሰው የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ይናገራሉ።

ማኅበራቱ በተደረገላቸው ድጋፍ ወደሥራ መግባታቸውን ጠቅሰው፤ የውሃ እና የመብራት ችግርም እንደሌለባቸው ነው ያመላከቱት። ይሁንና ሼዱ አጥር የሌለው መሆኑ እንዲሁም፣ የከብት እና የዶሮ መኖ እጥረት በመኖሩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

የሸገር ክፍለ ከተማ የገላን ጉዳ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዱጉማ ሙለታ በበኩላቸው እንደሚያስረዱት፤ ከሦስት ወር በፊት ሼዶችን ለመሥራት ብዙ ጥረት ተደርጓል። ጥረቱ ተሳክቶም 106 ሼዶች የተሠሩ ሲሆን፣ በእነዚህም ሼዶች ውስጥ ዘጠኝ ክላስተር ይገኛል። ከእነዚህም ውስጥ የወተት ላም እርባታ፣ የሥጋ እና የእንቁላል ዶሮ እርባታ፣ የከብት ማደለቢያና ሌሎችም ይካተቱበታል። አንድ ሼድ እስከ 40 ላሞች ወይም በሬዎችን የሚይዝ ነው።

እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ሼዶቹ የተሠሩት ለወጣቶችና ለሥራ አጦች ሲሆን፣ በልማድ ከብቶችን ያረቡ ለነበሩ አርሶ አደሮችም ጭምር ነው። በአሁኑ ወቅት በሼዶቹ ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሥራ መጀመር ችለዋል። ሼዶቹ መብራትም ውሃም እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን፣ የሚቀረው የአጥር ሥራም በመሠራት ላይ ይገኛል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል የሥራ ዕድል ፈጠራ ቢሮ በጋራ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ያተኮረ የመስክ ምልከታን ለጋዜጠኞች ባስጎበኙበት ወቅት የሥራ ዕድሉ የተፈጠረላቸው ማኅበራት፣ መንግሥት ባመቻቸላቸው ሼዶች በመጠቀም ውጤታማ ሥራ መጀመራቸውን አሳውቀዋል።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You