ምጉምቱው ብዕረኛ!

ብዕረኛውን ብዕር ያነሳዋል:: የሀገራችን የጥበብ ቤት ጭር ብሎና ሰው አልባ፤ ኦና ሆኖ አያውቅም:: በየዘመናቱ ሁሌም ቢሆን ብዕራቸውን እያነሱ በከተቡ ቁጥር “አቤት እንዴት ያለው ብዕረኛ ነው!” እያልን የምንደመምባቸው ዛሬም አሉ:: ይህኛው ዘመንም፤ በስነ ጽሁፉ የድርሻውን ይዞ ቆሟል:: በዛሬው የዝነኞች ገጻችን ከዚህኛው ዘመን የኪነ-ጥበብ ፈርጥ ከሆኑት መካከል ስለ አንድ ሰው የህይወት ታሪክ፣ ዘመን አይሽሬ ከሆኑ ስራዎቹ ጋር በማጣመር ልናቀርብላችሁ ወደናል። ይህ ሰው በሠራቸው የስነ-ጽሁፍ ስራዎቹ ከአንባቢያንና ሀያሲያን ዘንድ ትልቅ አድናቆትንና ዝናን የተቸረ፣ ድንቅ በሆኑ የፈጠራና በራሱ የአጻጻፍ ስልት ልዩ ልዩ ሽልማቶችን ማግኘት የቻለ ባለ ብዙ ተሰጥኦና ድንቅ አዕምሮ ባለቤት፤ ደራሲና ገጣሚ አዳም ረታ ነው። ከማንነቱ ጫፍ እስከ ብዕሩ መድረሻ፤ ከትናንቱ ተነስተን ዛሬን በዚህ ውስጥ እንፈልገዋለን::

ሀምሌ 8 ቀን 1950 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የተወለደው አዳም ረታ ገና በልጅነቱ በውስጡ የተጸነሰው የስነ-ጹሁፍ ዝንባሌ ዛሬ ላበረከታቸው ተወዳጅ ስራዎቹ መሰረት ጥሎለታል። ስለ ሥራዎቹ በተነሳ ቁጥር ሁሌም የሚለው አለው:: በልጅነቱ ያሳለፈው ኪነ ጥበባዊ ጊዜ ለደረሰበት ትልቅ መሰላል ሊሆነው ስለመቻሉ ነው:: በአንድ ወቅትም በ“አዲስ ነገር” ጋዜጣ ላይ በሰጠው ቃለ መጠይቅም እንዲህ የሚል ነበር፤ 5ኛ ክፍል እያለሁ አርብ አርብ ከሰአት በኋላ ሪፖርት እናቀርባለን:: ደንቡ ከጋዜጣ ያነበብነውን ወይም ከሬዲዮ የሰማነውን ነገር በራሳችን አማርኛ አሳጥረን ጽፈን ክፍል ውስጥ ማቅረብ ነው:: ሁልጊዜ ርእስ የሚሆኑት የጃንሆይ ጉብኝት ፤ የአዲስ አበባ አንደኛ ዲቪዚዮን እግር ኳስ ውድድር ውጤት እና የመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት ነው:: ነገር ግን ይህን መጻፍ ሰለቸኝ:: አንድ ቀን በመንገድ ላይ ስሄድ የዶሮ ነጋዴዎች ሀይለኛ አውሎ ነፋስ መጥቶ ሲያተራምሳቸው እና ዶሮዎቹ ከቅርጫት እየበረሩ ሲያመልጡ ነጋዴዎቹም እነሱን ለመያዝ የሚያደርጉትን መውደቅና መነሳት አየሁ እና ገረመኝ:: ያን ለመጻፍ ወሰንኩ:: ጽፌም ክፍል ውስጥ አቀረብኩና ተማሪዎቹን ትንሽ አስደሰትኳቸው:: ከዚያ መምህሩ ከየት አመጣኸው ሲሉኝ ከጋዜጣ አንብቤ ነው አልኩ:: ጋዜጣ ላይ እንዲህ አይነት ነገር አይጻፍም ብለው ጢሜን አበረሩኝ::ከዚያ ግን ለተማሪዎች አዳሙ ደራሲ ነው የሚሆነው ብለው ተናገሩ:: ደራሲ መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ያኔ አልገባኝም::” በማለት መነሻውን በትውስታ ያጋራል::

አዳም በአብዛኛው የሚጽፈውና ጉምቱነቱን የተቀዳጀው በልቦለዶች ቢሆንም ግጥሞችንም የመጻፍ ልዩ ችሎታ አለው። በእርግጥ ግጥሞቹን ሰብስቦ በመድብል ደረጃ ባያወጣቸውም፤ ነገር ግን በተለያዩ ጊዜያት በመፅሔቶች ላይ መታተም ችለዋል:: ከእርሱ ዘንድ ብቻ ተሸሽገው ያሉ በርካታ ያልታተሙ ግጥሞችና የስነ-ጽሁፍ ስራዎቹም እንዳሉት ይናገራል። “ታዲያ ምን ትጠብቃለህ አዳም?” ያስብላል፤ እንዲህ እንደ እርሱ ያሉ የብዕር ጠብታዎች ሲባክኑ መልካም አይደለምና:: በስነ-ጽሁፉ ብቻ ሳይሆን በቀለም ትምህርቱም የተሻለ ደረጃ ላይ መድረስ የቻለው አዳም ረታ በጂኦግራፊ የመጀመሪያ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተቀበለ ሲሆን፤ ሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ በውጭ ሀገር አግኝቷል።

አዳም ረታ ለመጀመሪያ ጊዜ ልዩ ተሰጥኦው እንደ ሻማ ያበራበትና የብርሃን ችቦውን የለኮሰበት ጊዜ ነበር:: በ1977ዓ.ም፤ በኢትዮጵያ የስነ-ጽሁፍ ተከታዮች እና አንባቢያን ልብ ውስጥ የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጠበትን የበኩር ስራውን ይዞ በአንዲት መጽሐፍ ብቅ አለ። ይሄውም “አባ ደፋር እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች” የተሰኘው መጽሐፍ ነው። በዚህ የአጫጭር ታሪኮች ስብስብ ውስጥ የተለያዩ ጸሐፊዎች የተሳተፉበት ሲሆን፤ ደራሲ አዳም ረታ ድብድብ፣ ዕብዱ ሺበሺ፣ ሲሮኮ እና ሲፊንክስ በድምሩ አራት ስራዎችን በመጽሐፉ ውስጥ ለማካተት ችሏል። በ1990 ዓ.ም “ጭጋግና ጠል” የአጭር ታሪኮች ስብስብ ውስጥ “ዘላን” የተሰኘ ልቦለዱ ታትሟል። እነዚህ ሁለቱ ከሌሎች ደራሲዎች ጋር፤ በጥምረት የታተሙለት በመሆኑ እንደ ወጥ ሳይቆጠሩ ቀርተዋል።

ደራሲው የመጀመሪያ ወጥ የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ የሆነውን “ማህሌትን” ለመጀመሪያ ጊዜ በ1981ዓ.ም ለማሳተም በቅቷል። ሌላው በሻማ ቡክስ በ1997 ዓ.ም የታተመው “ግራጫ ቃጭሎች” የሚለው መጽሐፉ ለአዳም ረታ ትልቅ የመሸጋገሪያ ድልድይና ልዩ ችሎታው የታየበት ወጥ ረጅም ልቦለድ ነው።

ጉዟቸውን የቀጠሉት የአዳም ረታ የማይነጥፉ የብዕር ጠብታዎቹ በ2001ዓ.ም አለንጋና ምስር እንዲሁም እቴሜቴ ሎሚሽታ በ2002 ዓ.ም ከሰማይ የወረደ ፍርፍር፣ በ2003 ዓ.ም ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ እና በ2004 ዓ.ም ሕማማት እና በገና በተከታታይ በየአመቱ ታትመው ለንባብ በቅተዋል። ከዚህ በኋላ ደግሞ መረቅ በ2007 ዓ.ም፣ የስንብት ቀለማት በ2008 ዓ.ም ሌላው በ2010 ዓ.ም አፍ የተሰኙ በርካታ ድንቅ ስራዎችን በተለየ አቀራረብ በመስራት ለአንባቢያን እነሆ ማለት ችሏል።

በአንድ ወቅት በ“አዲስ ነገር” ጋዜጣ ላይ በከተበው ጽሁፍ ስለራሱ ሲናገር በድግግሞሽና በአንድ አይነት መንገድ መሄድ በጣም እንደሚያሰለቸው ገልጾ ነበር። ለዚህ ደግሞ ስራዎቹን መመልከት ከቻልን ወጣ ያለና የራሱን የአቀራረብ ስልት ይዞ መምጣቱ ምስክር ነው።

ቀደም ሲል “በአባ ደፋርና ሌሎች ስብስቦች” ውስጥ ስራዎቹን የማቅረብ እድል በማግኘት የጀመረው አዳም ረታ የጥበብ ጉዞ ከስኬቶቹ ኋላ ቆየት ብሎም ሌሎች ወጣት ጸሐፊያን ፈለጉን ይከተሉ ዘንድ “አማሌሌ” በተሰኘው መጽሐፍ ላይ አብሯቸው በጥምረት ሰርቷል። ስራዎቹ በብዛት በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊና መሰል መስተጋብሮቻችን ውስጥ በሚገኙ ቀላል በሚመስሉ እምቅ ሃሳቦች ላይ የሚያጠነጥኑ ሲሆኑ፤ ኪናዊ ለዛን በተላበሰ መልኩ በጨዋታ እያዋዛ ልባችንን እንዲኮረኩሩን አድርጎ አቅርቧቸዋል። ቆም ብለን ደግሞ በጥልቀት እንድናስብና እራሳችንን እንድንመረምር ያደርገናል። የምናቡ ርቀትና ገለጻው፣ የሚያነሳቸው ሃሳቦችና የቋንቋ ሀብቱ ሁሌም አፍ ያስከፍታሉ::

አዳም ነዋሪነቱ በካናዳዋ ኦታዋ ይሁን እንጂ ሀገሩን በተመለከተ የምናብ ችግር የለበትም::እንዲያውም ከሌሎች ደራሲያን በተለየ የኢትዮጵያውያንን ሁለንተናዊ ገጽታ በድርሰቱ ውስጥ እስከ ጥቃቅኗ ቅንጣት ድረስ ወርዶ በዝርዝር ይተነትናል::በአንድ ወቅት ሀልዮ ከተባለ መጽሔት ጋር በነበረው ቆይታ ይህን ሲያስረዳ “ከሀገርህ ስትወጣ ራስህን ባዶ አድርገህ አይደለም የምትወጣው ሁሉን ነገር ትውስታህ ውስጥ ትይዛለህ” ብሏል::አክሎም “የትረካ ቅርጹን ነው እኔ የምፈጥረው እንጂ በውስጡ ሊነሱ የሚችሉ ግብረገባዊ እና ሌሎች ነገሮችን እኔ የምፈጥራቸው አይደሉም፤ አለም የሚሰጠኝ ነው::እኔ ህብረተሰቡ ውስጥ የምገኝ ቢሆንም በምጽፍ ጊዜ ግን ራሴን ነጥዬ ገለል ብዬ ለመመልከት እሞክራለሁ::”በማለት የአጻጻፍ መንገዱን ተናግሯል::

የብዕር ስራዎቹና ሃሳቦቹ እንደ ዓባይ ጅረት የማይነጥፉና ተቀድተው የማያልቁ ግዙፍ ባህር ናቸውና እስቲ ከሰራቸው ስራዎች መሀከል ከመጽሐፉ መጽሐፍ፣ ከገጽ ወደ ገጽ እየዘለልን በጥቂቱ እንቃኛቸው።

“ባዕዳን ከፋፍሎ ሊገዛህ ሲያሴር ካልገባህ እና እንደሰራህ ከተሰራህለት በአእምሮው ስፋት በለጠህ ማለት አይደለም? ለመሆኑ እግዚአብሔር ተፈጥሮንና ሰውን እንዴት ፈጠረው? በቃሉ ትዕዛዝ ነው። ሰው ሁን አለ ሰውም ሆነ። ዛፍ ሁን አለ፤ ዛፍም ሆነ ወዘተ…… ባዕዳን ተጣሉ ሲሉን መጣላት፣ ሩጡ ሲሉን መሮጥ፣ ራቁታችሁን ሁኑ ሲሉን መሆን፣ ሁሉ ነገራችን ከዚያም ዝቅ ያለ ነው። በተለይ በፖለቲካ ሳይንሱ። (የስንብት ቀለማት)

ይህ 960 ገጾችን የያዘው የስንብት ቀለማት መጽሐፍ ራሳችንን በደንብ እንድንመለከት ይጋብዘናል:: ከተወሰኑ ገጾች መሐከልም፦

****

“የእኛ ሰፈር አዋቂ ይገርመኛል፤ ላባ አይቶ ‘አሞራ አየሁ’ የሚል፣ ጅና አይቶ ‘አንበሳ አየሁ’ የሚል፣ ጠብታ ውሃ አይቶ ‘ዶፍ በዚህ አልፎ ነበር’ የሚል፣ ቆዳ ቦት የሚያዘወትር ሰውዬ ቢያይ ‘ወታደር አየሁ’ የሚል ነው። (እነዚህን አይነቶች ፖለቲከኛ አያድርግብዎ!)

***

“የሚያስፈራኝ ደሃነትና የመንገድ መፍረስ አይደለም:: የሥጋና የአጥንቴ መድከም አይደለም:: የዕቃ መወደድ አይደለም:: እግዜር የከፈተውን አፍ ሳይዘጋው ካደረማ፤ እግዜሩም እግዜር እኔም ሰው አይደለሁም።

(የስንብት ቀለማት)

***

“ፍትህ ትወዳለህ፤ ፍትህ እንደጎደለ እያወቅህ ግን ዝም ትላለህ። አየህ ይሄ አንድ ሰው ሲከፋፈል ነው።”

***

“መኖር የሚከብደው ከሰው ጋር ብቻ አይደለም፤ ከዶሮም ጋር ነው። አሁን ከጎረቤቶቼ መጣላት ብፈልግ በ’ዶሮአችሁን ሰብስቡ’ ሰበብ አምባጓሮ መቀስቀስ እችላለሁ። ዋናው እውነት መሆኑ አይደለም። ደፍሮ የመዘባረቅ ነው።”

(መረቅ)

“ዛሬ በትንንሽ ምሬት ይሞላና ጊዜ ይለወጣል።

ምንም የረባ ሳይደረግ ሰዎች ወዲያና ወዲህ ይራራቃሉ፣

የተያያዙ ይፈታታሉ፣

ፍቅር የገመዳቸው ይበታተናሉ።

ሁሌም ሚስጥር ነው።

ለምን እንደወደድንም ለምን እንዳልወደድንም ምስጢር ነው።”

(እቴሜቴ_ሎሚ_ሽታ)

****

“ጠዋት እዚህ ፀሐይ ስሞቅ የቆረጥኩት የአውራ ጣቴ ጥፍር ለስንት ጉንዳን እራት ይሆናል? ባላርስም አበላሁ ማለት ነው… ሂሂሂ”

***

“አብዮተኛ ውስጥ ቡርዧ አለ፣

ቡርዧ ውስጥ ፊውዳል አለ፣

ፊውዳሉ ውስጥ ገበሬ አለ፣

ገበሬው ውስጥ እረኛ አለ፣

እረኛ ውስጥ ላም አለ፣

ላሟ ውስጥ ሳር አለ፣

ሳሩ ውስጥ አፈር አለ::

ለሊታችን ተቆፍሮ ቢታይ ሁላችንም የምናልመው በእርግጥ አፈር ነው:: ታላቅ የመሰለው፣ የረቀቀ የመሰለው ፅንሰ ሃሳብ ሁሉ በምላስ ሙጫ የቆመ የአፈር እንክብል ነው።” (መረቅ)

****

“ይሄ ኀብረተሰብ እኔን ጎድቶኛል።

ቁስሌን መፍጠራቸውን ረስተውታል።

እኔ አልረሳሁትም።

አንድ ጥፊ ሲሰጡት ሌላ የሚጠብቅ

ወይ ጠንካራ ጉንጭ ያለው ነው፣

ወይ ጅል ቅዱስ ነው”

(ማህሌት)

*****

“አዕምሮአቸው ብሩህ ባህላቸው ግን የባርያ የሆኑ ስንት አሉ በእግዜር። ባላምንበትም ልማልበት።አይ አም ኢንተለጀንት ብሎ የሚናገር ግን ዘር ማንዘሩ በቁንጫ የሚበላበት፣ በጎጥ ብራንድ የነደደ ሰው አያበሽቅህም? በ’ነኝ’ ሰው የሚበላለጥ ቢሆን የአለም ጌታዋ ብዙ ነበር። ‘ውበት ሃሰት ነው ደም ግባትም ከንቱ ነው’ እንደሚባለው አዕምሮም ሃሰት ነው ብልጥነትም ከንቱ ነው። ሁሉ ረጋፊ ነው።” (አፍ)

አዳም ረታ በተለየ የአጻጻፍ ስልቱ እና በስራዎቹ ጥልቀት ከአንባቢያንና የጥበብ አፍቃሪያን አድናቆትን ከማትረፉ ባሻገር ከሀገራችን ጉንቱ ሃያስያን ዘንድ አዎንታዊ ሂስ እና ምስክርነትን ማግኘት ችሏል።

ለምሳሌ ያህል ዳኛቸው ወርቁ ስለ አዳም ረታ ይህንን ብሎለታል፤ በ“አደፍርስ” የኢፒሶዲክ ሕግጋትን አጋምሶ ለማስተዋወቅ ከሞከረ ወዲህ በአማርኛ ሥነ-ጽሑፍ በኢፒሶዲክ ተሟልቶ የተገኘ ድርሰት “ግራጫ ቃጭሎች” ነው። … “ግራጫ ቃጭሎች” ከገፀ-ባህሪው አካልና ሥነ-ልቡና አሳሳል አልፈን ድንቅ ዓላማውን፣ ቋንቋውንና የሕይወት አተረጓጎሙን ስንመለከት የአዳም ረታ እውቀትና ልምድ ጠንከር – ጠጠር ብሎ በመዝገቡ በኩል ሲያስተጋባ ነው የምንመለከተው።…

ደራሲና ገጣሚ አዳም ረታ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ሽልማቶችን ማግኘት የቻለ ሲሆን በዋናነት በ2009ዓ.ም

ኢስትዌስት ኢንተርቴይመንትና ኤቨንት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለመጀመሪያ ጊዜ ባዘጋጁት “ሆሄ” የሥነ ፅሑፍ ሽልማት ላይ በምርጥ የአመቱ ረዥም ልቦለድ ዘርፍ “የስንብት ቀለማት” በተሰኘው መጽሐፉ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል። የጉምቱውን ብዕረኛን ግሩም ቀለማትን በመቀየጥ በጥቂቱም ቢሆን ይችል ታህል ስንል፤ ነገም በማይነጥፉና በተሻሉ ህብረ ጥበባት ውስጥ እንደምናገኘው ተስፋ በማድረግ ነው::

ሙሉጌታ ብርሃኑ

Recommended For You