የምሥራቁ ክፍል የማይዳሰስ ቅርስ- የቱሪዝም ዘርፉ ተስፋ

ኢትዮጵያ የበርካታ ባህሎችና ሃይማኖቶች መገኛ ነች። በዓለማችን ላይ በህብረ ብሄራዊነትና በብዝሀ ሃይማኖት ከሚታወቁ ሀገራት ቀዳሚውን ስፍራም ትይዛለች።

ሀገሪቱ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በርከት ያሉ ሃይማኖታዊና ባህላዊ /የማይዳሰሱ/ ቅርሶችን ማስመዝገብም ችላለች። ከእነዚህ ውስጥ መስከረም 17 የሚከበረው መስቀል፣ በዚሁ ወር የሚከበረው የኢሬቻ በዓል እንዲሁም ከጥር 10 እስከ 12 የሚከበረው ጥምቀት እንዲሁም የፍቼ ጨምበላላ በዓላት ይገኙበታል።

ከዚህ በተጨማሪ በምሥራቁ ክፍል በምትገኘው የሀረሪ ክልል ብሄረሰብ በልዩ ድምቀት የሚከናወን ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሥርዓትን አጣምሮ የያዘውን የሸዋልኢድ በዓል ስነ ሥርዓት ለዓለም ሕዝብ አበርክታለች። ዩኔስኮም ይህንን ደማቅ ሥነ ሥርዓት በቅርቡ በዓለም ቅርስነት በይፋ መዝግቦታል።

ሸዋልኢድ በድምቀት የሚከበረው በአንጋፋዋና ጥንታዊቷ የሀረር ከተማ ነው። በዓሉ በሀረሪ ሕዝብ ባህላዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር በአዋጅ የተደነገገው ጥቅምት 8 ቀን 1999 ዓ.ም ሲሆን፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮና በኋላም ባህላዊ እሴቱ እየጎላና እየበረታ ሄዶ፣ ከሀረር አልፎ የኢትዮጵያ፣ ከኢትዮጵያ ተሻግሮም የዓለም ቅርስ ለመሆን በቅቷል።

የበዓል አከባበሩን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ በ2012 የተጀመረው ሥራና ጥረት ውጤት አምጥቶ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የበዓሉን አከባበር ከዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል መዝግቦታል።

የአንድ ማህበረሰብ ባህልና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ለባለቤቱ ከሚሰጡት ጥልቅ ትርጉም ባሻገር ሰፊ አንድምታ የያዙ መሆናቸው ይገለፃል። በተለይ የማህበረሰብ ባህላዊ ልምምዶች የእርስ በእርስ መስተጋብርንና እሴቶችን ያጎለብታሉ፤ በተጨማሪም የቱሪዝም ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው ጉልህ መሆኑን በዘርፉ ሰፊ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ይናገራሉ። በተለይ የአንድን ሀገር ቱሪዝም ለማሳደግ ከማይዳሰስ ቅርስ ውስጥ የሚመዘገቡ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሥርዓቶች ግዙፍ ድርሻ አላቸው።

ሸዋልኢድም ይህን መሰል እምቅ አቅም ካላቸው የዓለማችን የማይዳሰሱ ቅርሶች ተርታ የተመደበ ነው። በየዓመቱ በጥንታዊቷ ሀረር ከተማ የሚከበረው ይህ ተወዳጅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓል ኢትዮጵያ በዓለም መድረከ ላይ ይበልጥ ጎልታ እንድትታይ ከማድረግ ባሻገር ሰፊ የቱሪስት ፍሰት እንዲኖር የማስቻል አቅም እንዳለው ይገለፃል። የዘንድሮው ዓመታዊ በዓልም ባሳለፍነው ሳምንት በከተማዋ ሲከበር ይህንን የማይተካ ሚናውን ለማጉላት እንደሚሰራ ተገልጿል።

‹‹ኢትዮጵያ የአስደናቂ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ፀጋዎች ምድር ናት›› ያሏት በሸዋልኢድ፤ ክብረ በዓል ላይ የታደሙት የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናንሲሴ ጫሊ፤ ታይተው የማይጠገቡ፣ ከእኛ አልፈው ዓለምን የሚያስደምሙና ቀልብን የሚገዙ ውብ የቱሪዝም ሀብቶች አሏት ሲሉ አመልክተዋል፡፡ ከእነዚህ ሀብቶች መካከል ዘመናትን የተሻገሩ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ፣ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ ባህላዊ ሀብቶች በብዛት መገኘታቸው ኢትዮጵያ የብዝሃነት ተምሳሌት እና የውብ ባህሎች ባለቤት መሆኗን የሚያስረግጥ እውነት ነው ብለዋል፡፡

ሚኒስትሯ እድሜ ጠገቧ የሀረር ከተማ ለዚህ አይነተኛ ማሳያ እንደሆነች ጠቅሰው፤ በውስጧ ታሪካዊ አሻራዎችን፣ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶችን አምቃ የያዘች ሙዝየም እንደሆነች አስረድተዋል፡፡

ከተማዋ የቀደምት ስልጣኔ ባለቤትና የሃይማኖት ማዕከል እንደመሆኗ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲወራረዱ የመጡ ትውፊታዊ መገለጫዎችና ቱባ ባህሎች ዛሬም ቢሆን የሚንፀባረቁባት እንደሆነች ይገልፃሉ፡፡ በተጠናቀቀው ሳምንት የተከበረው የሹዋልኢድ ፌስቲቫልም ከዚህ የባህልና ሃይማኖት ምንጭ የሚቀዱ እሴቶች መካከል አንዱ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

‹‹ሹዋልኢድ የታላቁን የረመዳን ወር መጠናቀቅን ተንተርሶ የሚከናወን እና በሀረር ህዝብ የሚከበር ደማቅ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ነው›› የሚሉት አምባሳደር ናንሲሴ ጫሊ፤ ወቅቱ የረመዳን ወር መጠናቀቅን ተከትሎ የሀረር ከተማ ሞገስና ልዩ መለያ የሆነው የጀጎል ግንብ በሸዋልዒድ ክብረ-በዓል የሚያሸበርቅበት፣ ስሜትን የሚቆጣጠሩ ትዕይንቶች የሚከወኑበት፣ ሀረር ከወትሮው በተለየ መልኩ የምትፈካበት፣ የፍቅርና የእንግዳ ተቀባይነት ምልክት የሆነው የሀረር ህዝብ በቱባ ባህሉ የሚደምቅበት መሆኑን ይገልፃሉ፡፡

እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ፤ በመንፈሳዊ መዝሙሮችና ውዝዋዜዎች ተጀምሮ በቅዱሳን መፅሐፍት ንባብ ተዋጅቶ በምርቃትና መልካም ምኞቶች የሚቋጨው ሹዋልዒድ በውስጡ ከኢትዮጵያ አልፎ ለዓለም ህዝቦች ፋይዳ ያላቸው እሴቶችን መያዙንም ጠቁመዋል፡፡ ይህ መሆኑም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት በዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ እንዲካተት እና የዓለም ህዝቦች ሁሉ ሀብት እንዲሆን አስችሎታል ብለዋል፡፡

ይህን ሃይማኖታዊ ሁነት በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገብ ያስቻሉ አንኳር ጉዳዮችን የሚያነሱት አምባሳደር ናንሲሴ ጫሊ፤ የመጀመሪያው ሸዋልዒድ ፆታ ሳይለይ በሁሉም የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ የማህበረሰብ አባላትን በአንድነት የሚያስተሳስር እና የእድሜ ባለፀጋዎች ለቀጣዩ ትውልድ እውቀትና ልምድ የሚያጋሩበት ሥርዓት መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ወጣቶች የራሳቸውን ባህልና ወግ እንዲያውቁ፤ በቤተሰብም ሆነ በማህበረሰብ ደረጃ ለቀጣዩ ትውልድ አስተምህሮቶች የሚሰርፁበት እንዲሁም ስነ-ስርዓቱ የሚካሄዱባቸው ስፍራዎች ጭምር በቅርስነት የሚጠበቅበትን ሁኔታ የሚያወርስ ሃይማኖታዊ እሴት በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

ሚኒስትሯ እንዳስታወቁት፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደርየለሽ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የቱሪዝም ሀብቶች ባለቤት እንደመሆኗ ለቱሪዝም ልማትእምቅ አቅም አላት፡፡ እነዚህን ፈርጀ ብዙና መጠነ ሰፊ የቱሪዝም ሀብቶች አልምቶ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም በማስተዋወቅ የጎብኝዎችን ፍሰት ማሳደግ ይገባል፡፡ ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥም ያስፈልጋል፡፡

ለዚህም መንግሥት የቱሪዝም ዘርፍን ከኢትዮጵያ የእድገትና የብልፅግና መሰረቶች መካከል አንዱ በማድረግ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ሚኒስትሯ አስታውቀዋል፡፡ ሚኒስትሯ ኢትዮጵያዊያን በተለይም ይህን ሃይማኖታዊ ሀብት ጠብቆና ተንከባክቦ በትውልድ ቅብብሎሽ ለዚህ ክብር ላበቃው የሀረሪ ህዝብ ምስጋና እንደሚገባውም ገልጸዋል።

የሸዋልኢድ በዩኔስኮ በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡ ቀደም ብሎ በሚዳሰስ ቅርስነት ከተመዘገበው የጀጎል ግንብ ጋር ተዳምሮ ለሀረር ልዩ ገፅታን እንደሚያጎናፅፋትና የቱሪስት መዳረሻነቷንም በይበልጥ እንደሚያሰፋው ይናገራሉ፡፡ እንደ ሀረር ያሉ የቱሪዝም ፀጋዎች ማዕከላት በቱሪዝም መሰረተ ልማትና በቱሪስት ፋሲሊቲዎች እንዲጠናከሩ በማድረግ እና ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ ተመራጭና ተወዳዳሪ የቱሪስት መዳረሻዎች ማድረግ ቀዳሚ ትኩረት እንደሚያስፈልግም ያስገነዝባሉ፡፡ እንደ ሸዋልኢድ ያሉ በሀረሪ ክልል የሚገኙ የቱሪዝም ሀብቶችን በማልማትና በማስተዋወቅ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር ቱሪዝም ሚኒስቴር ከክልሉ መንግሥት ጋር በትብብር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ የሀረሪዎች የጥበብና የእውቀት ውጤቶች ድንበር ተሻግረው የዓለም ህዝቦች የቅርስ ሀብት መሆናቸውን ይገልፃሉ። ሀረሪዎች ከደማቅ ታሪኮቻቸው ጎን ለጎንም የሰላምና የፍቅር ተምሳሌት መሆናቸውን ይናገራሉ።

‹‹በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው የሸዋልኢድ በዓል የፍቅር በዓል ነው›› የሚሉት ሚኒስትሩ፤ አኩሪ ባህሎቻችንና ቅርሶቻችንን በመንከባከብ፣ በመጠበቅና ለትውልድ ለማስተላለፍ በሚከናወኑ ስራዎች ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ያስገነዝባሉ።

የሸዋል ኢድ በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የትምህርት ተቋም (ዩኔስኮ) በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት ህዳር ወር 2016 ዓ.ም ነበር የተመዘገበው። በዓሉ በዩኔስኮ ከተመዘገበ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀናት ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል።

በተለያዩ ስርዓቶች በሀረር ከተማ በድምቀት የተከበረው የሸዋል ኢድ በዓልን ለማስተዋወቅ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤሊያስ ሽኩር በሰጡት ማብራሪያ፤ በዓሉ ባህላዊ ይዘቶቹን ጠብቆ እንዲጎለብትና ለአካባቢው ተጨማሪ የቱሪስት መስህብ እንዲሆን ወደ ሥራ መገባቱን ይናገራሉ። ለዚህም ከሀረሪ ክልል አስተዳደርና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሀረሪ ማህበረሰቦች ለቅርስ የሚሰጡት ትኩረትና ትርጉምም ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ያስረዳሉ።

እንደ ኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን መረጃ የሸዋል ኢድ በዓልን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጎብኝዎች በይበልጥ ለማስተዋወቅም በሀረር ከተማ አራት ሙዚየሞች ተመርጠው የተለያዩ ዝግጅቶችና የቅርስ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

ጥንታዊቷ የሀረር ከተማ የበርካታ ቅርሶች መገኛ በመሆኗ በርካታ ቱሪስቶች ለጉብኝት ወደ ስፍራው እንደሚያቀኑ በተለያዩ ጊዜዎች የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። በመሆኑም የሸዋልኢድና ሌሎች ቅርሶች በአግባቡ ተጠብቀው እንዲጎለብቱና ለቱሪዝም ዘርፉ ያላቸው አበርክቶ እንዲያድግ ትኩረት መሰጠቱን የቱሪዝም ሚኒስቴር እንዲሁም የሀረሪ ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት የባህልና ቱሪዝም ቢሮ እየገለፁ ይገኛሉ።

ሸዋልኢድ የሚከበርባት ሀረር የጥንታዊት ኢትዮጵያ የሥልጣኔ ማሳያ ተብላ የምትጠቀስ ሲሆን፣ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በወቅቱ ሀረርን ያስተዳድሯት የነበሩት አሚር ኑር ከተማዋን ከጥቃት ለመከላከል የገነቡት የጁገል ግንብ በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል። ይህ ቅርስ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም እ.ኤ.አ በ2006 የተመዘገበ ሲሆን፣ አምስት በሮች እንዳሉት ይታወቃል። በ7ኛው ክፍለ ዘመን እንደተቆረቆረች የሚነገርላት ጥንታዊቷ ሀረር በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡትን የጀጎል ግንብ እና የሸዋል ኢድ በዓልን ጨምሮ የበርካታ የመስህብ ስፍራዎች መገኛም ነች።

ኢትዮጵያ የባህል፣ የታሪክ፣ የተፈጥሮና የቅርስ ሀብቶች በስፋት ከሚገኝባቸው ቀዳሚ ሀገራት ተርታ ትመደባለች። ይሁን እንጂ እነዚህን ሀብቶች በሚፈለገው መጠን የማስተዋወቅ፣ የማልማትና ከሀብቱ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ አቅም ግን አሁንም ድረስ እንዳልጎለበተ ይታመናል። ይህን እክል ለመቅረፍ መንግሥት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ነድፎ እየሠራ መሆኑን በተለያዩ መድረኮችና መንገዶችም ሲገልፅ ይሰማል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን  ሚያዝያ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You