ለውጪ ገበያ ከቀረቡ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች 23 ነጥብ አራት ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኘ

-የገበያ መቀዛቀዝ ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ቅናሽ አሳይቷል

አዲስ አበባ፡በ2016 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረቡ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች 23 ነጥብ አራት ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል አስታወቀ። የምርት መዳረሻ ሀገራት ገበያ በመቀዛቀዙ ከቆዳ ዘርፉ ለማግኘት የታቀደውን ገቢ ማሳካት አለመቻሉም ተመላክቷል።

የማዕከሉ ተወካይ ሥራ አስኪያጅ አቶ መሐመድ ሁሴን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከቆዳና ቆዳ ውጤቶች የውጪ ንግድ 41 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 23 ነጥብ አራት ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል።

በዘጠኝ ወሩ የተገኘው 23 ነጥብ አራት ሚሊዮን ዶላር ገቢ ጫማ፣ ቦርሳ፣ የቆዳ ጓንት፣ ያለቀለትና በከፊል የተጠናቀቀ ቆዳን ለውጭ ሀገራት ገበያ በማቅረብ መሆኑን ገልጸው፤ ከቆዳ ፋብሪካ 15 ሚሊዮን ዶላር፣ ከጫማ ፋብሪካ አንድ ሚሊዮን ዶላር፣ ከጓንት ሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ዶላር፣ ከቦርሳ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን ጠቅሰዋል።

ቻይና፣ ኢንዶኔዢያ፣ ሕንድና ቬትናም ዋነኛ የኢትዮጵያ ቆዳ ውጤቶች መዳረሻ ሀገራት ሲሆኑ፤ ወደ አውሮፓና አሜሪካ የሚላከው የቆዳና ቆዳ ውጤት ምርት በተለያዩ ምክንያቶች ቀንሷል ብለዋል።

እንደ አቶ መሐመድ ገለጻ፣ በዘጠኝ ወሩ 41 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት የታቀደ ቢሆንም ማግኘት የተቻለው 23 ነጥብ አራት ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው። የፋብሪካዎች በሙሉ አቅም አለማምረት፣

የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የገበያ መቀዝቀዝ፣ ጫማ ፋብሪካዎች በሀገር ውስጥ ገበያ ትኩረት ማድረጋቸው እና የአጎዋ ማዕቀብ አፈጻጸሙ ደካማ እንዲሆን ምክንያት መሆናቸውን አስረድተዋል።

በዘርፉ ያሉትን ማነቆዎች ለመፍታት የ10 ዓመት የቆዳ ልማት ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ተግባር የተገባ መሆኑን ገልጸው፤ የጥሬ ቆዳ ጥራትና አቅርቦትን የማሻሻል፣ የገበያ አማራጮችን የማስፋፋት፣ የግብዓት፣ የቴክኖሎጂ እና የፋይናንስ አቅርቦትን የማሻሻል ሥራ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ እቅድ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሠራ ተናግረዋል።

አምራች ፋብሪካዎች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን በሀገር ውስጥ ገበያ ራሳቸውን ማብቃት ተገቢ ነው ያሉት አቶ መሐመድ፤ በቴክኖሎጂ፣ በዲዛይን፣ በፋሽን እና በምርት ልማት ድጋፍ በማድረግ በጥራትና በብዛት እንዲያመርቱ፣ በሀገር ውስጥ ገበያው እንዲጠቀሙ እና በዓለም አቀፍ ገበያው ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ ይሠራል ብለዋል።

በሙሉ አቅማቸው የማያመርቱ ፋብሪካዎች የሀገር ውስጥ ገበያን ተጠቅመው እንዲንቀሳቀሱ የማድረግ ሥራ መሠራቱን የገለጹት አቶ መሐመድ፤ በቀጣይም በተጠናከረ ሁኔታ አምርተው ወደ ውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።

አምራች ፋብሪካዎች እርስ በእርሳቸው በገበያ የማስተሳሰር፣ ገበያ የማፈላለግ፣ በቆዳ ኢንዱስትሪው የሚሳተፉ የተለያዩ ባለሀብቶች፣ ባለሙያዎች እንዲሁም ሸማቾችን በማገናኘት ዘርፉ እንዲነቃቃ ጥረት ይደረጋል ሲሉ አስታውቀዋል።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You