በቦኮሃራም የታገተችው ናይጄሪያዊት ተማሪ ከ10 ዓመት በኋላ ሦስት ልጆችን ወልዳ ነፃ ወጣች

ከአስር ዓመት በፊት በቦኮሃራም ታጣቂዎች ታግተው ከነበሩ ሴቶች መካከል አንዷ የሦስት ልጆች እናት ሆና በናይጄሪያ መንግሥት ወታደሮች ነፃ ወጣች። በአውሮፓውያኑ ሚያዝያ 2014 ቦርኖ ከምትባለው ከተማ የቦኮሃራም ታጣቂዎች 276 ተማሪ ሴቶችን ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤታቸው አፍነው መውሰዳቸው ይታወሳል።

እነዚህ የቺቦክ ትምህርት ቤት ሴት ልጆች መታገት መላው ዓለምን አስደንግጦ በወቅቱ የአሜሪካ ቀዳማዊ እመቤት የነበሩትን ሚሼል ኦባማን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የማስለቀቅ ዘመቻ እንዲጀመር ምክንያት ሆኖ ነበር። ታፍነው ተወስደው ከነበሩት 280 ከሚጠጉት ልጃገረዶች መካከል አስካሁን ድረስ 100 የሚሆኑት በታጣቂዎቹ ቁጥጥር ስር ናቸው ወይም የደረሱበት አልታወቀም።

ሐሙስ ዕለት ደግሞ የናይጄሪያ ሠራዊት ከአስር ዓመት በፊት ከታፈኑት ተማሪዎች መካከል አንዷን ከሦስት ልጆቿ ጋር ከታጣቂዎቹ ነፃ ማውጣቷን አስታውቋል። ታጋቿ ሦስት ልጆቿ በተጨማሪም የአምስት ወራት ነፍሰ ጡር መሆኗን ሠራዊቱ ገልጿል። በቦኮሃራም ቡድን ታፍነው ከተወሰዱ ሴት ተማሪዎች መካከል እስካሁን ከ180 በላይ የሚሆኑት በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ ውስጥ ከምትገኘው ቦርኖ ግዛት የቡድኑ መደበቂያ ሳምቢሳ ጫካ በፀጥታ ኃይሎች ነፃ ወጥተዋል ወይም ከቡድኑ አምልጠዋል።

እስካሁን ከቡድኑ ነፃ ከወጡ ልጃገረዶች መካከል አንዳንዶቹ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ ማርገዛቸው ወይም ልጅ መውለዳቸው ተዘግቧል። የቦኮሃራም ታጣቂዎች ጠልፈው የሚወስዷቸውን ተማሪዎች በወሲብ ባርነት ስር ያቆዮዋቸዋል የሚሉ ዘገባዎች በተደጋጋሚ ሲወጡ መቆየታቸው ይታወሳል።

ወደ ቤታቸው ከተመለሱት መካከልም የተወሰኑት የናይጄሪያ ባለሥልጣናት የሚያስፈልጋቸውን እንክብካቤ እና ድጋፍ እንዳላደረጉላቸው በመግለጽ መንግሥትን ይተቻሉ። በናይጄሪያ ውስጥ አሁንም የጅምላ አፈና ተማሪዎችን እና ወላጆችን የሚያሳስብ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል። የተለያዩ ወሮበላ ቡድኖች ተማሪዎችን ዒላማ በማድረግ ጠልፈው እየወሰዱ ማስለቀቂያ እንዲከፈላቸው መጠየቃቸው የተለመደ ነው።

በሴቭ ዘ ችልድረን በጎ አድራጎት ድርጅት መረጃ መሠረት ከአውሮፓውያኑ 2014 አስከ 2022 ድረስ በናይጄሪያ ውስጥ ከአንድ ሺህ 680 በላይ ተማሪዎች ታግተዋል። ባለፈው መጋቢት ወር ከናይጄሪያዋ ሰሜን ምዕራብ ግዛት ካዱና ትምህርት ቤት ከ130 በላይ ተማሪዎች በታጣቂዎች ተጠልፈው የተወሰዱ ሲሆን፣ ይህም በቅርብ ዓመታት ውስጥ የተፈጸመ ከፍተኛው ጠለፋ ነው መባሉን የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You