የኮሪደር ልማት የብርታትና ቅንጅታዊ አሠራር ማሳያ ነው

በአንድ ወቅት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኝ የግል ትምህርት ቤት አብረን ስናስተምር የነበረ ወዳጄን ሰሞኑን አራት ኪሎ ቱሪስት ሆቴል አገኘሁት። በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት፣ በትኩረት እየተከታተለ መሆኑን በመግለጽ ‹‹ስማርት ሲቲ›› ለማድረግ የሚደረገውን ጥረትና አፈጻጸሙ እንዳስደሰተው ነገረኝ፡፡

የመንገድ ሥራውን ደግሞ በልዩ ሁኔታ በማየት የተመለከተውን የአሠራር አካሄድና ቅንጅታዊ አተገባበር በማድነቅ ዘርዘር አድርጎ አስረዳኝ። አያይዞም፣ እየተሠራ ያለበትን ፍጥነትና በየቀኑ የሚታየውን ለውጥ በመጥቀስ ኢትዮጵያውያን ካበረቱን መሥራት እንደምንችል አወጋኝ፡፡

በተለይ ትኩረቱን የሳበው፣ አራት ኪሎ ትምህርት ሚኒስቴር አጠገብ ሥራው እየተፋጠነ የሚገኘው ዋናው አስፋልት ወደታች ተቆፍሮ እየተሠራ ያለው የዋሻ የእግረኛ መንገድ (በአስፋልት ስር የሚያልፍ የእግረኛ መንገድ) መሆኑን ጠቅሶ፤ የከተማዋ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ‹‹ቡና እና ሻይ የሚጠጣበት ሱቅ ይኖረዋል›› ብለው ስለተናገሩት ሥፍራ ተጠናቆ በተግባር ለማየት ከፍተኛ ጉጉት እንዳደረበት ነገረኝ፡፡

አያይዞም ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን ስንፍና ካሳዩን ለሥራ እንለግማለን፤ ብርታት ካሳዩን ለሥራ እንተጋለን›› በማለት በመንግሥት ትምህርት ቤት በሳምንት ከ6 እስከ 10 ክፍለ ጊዜ ሲያስተምር የነበረበትን እንዲሁም በግል ትምህርት ቤት ከ24 እስከ 30 ክፍለ ጊዜ ያስተማረበትን ወቅት በመግለጽ የስንፍናውንና የብርታቱን ጊዜያት ጠቀሰልኝ፡፡

እኔም በኮሪደር ልማቱ የመንገድ ሥራ ላይ ያስተዋልኩትን የሥራ ባህል መቀየር በተመለከተ ለመጻፍ መነሻ ምክንያት ሆነኝ፡፡

ወዳጄና ሌሎች የከተማው ነዋሪዎች እንደነገሩኝና እኔም ተዘዋውሬ እንደተመለከትኩት፣ በኮሪደር ልማቱ የመንገድ ሥራው አሠራርና ሁኔታው በቀጣይ ለሚሠሩ ሥራዎች ምርጥ ተሞክሮ ሊሆን በሚችል መልኩ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ቀደም ሲል የቻይና የኮንስትራክሽን ድርጅቶች መንገድ ሲሠሩ ፍጥነታቸውን እናደንቅ ነበር፡፡ አሁን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገዶች ባለስልጣን ከእነርሱ በላቀ ደረጃ አፈጻጸሙን በማሳደግ እያስደሰተን ይገኛል፡፡

እኔ ዕለት በዕለት በምመለከተው ከአራት ኪሎ ወደ ፒያሳ በሚወስደው መንገድ የአስፋልት ማስፋትና የእግረኛ መንገድ ማስዋብ ሥራ በአዲስ መልክ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአስፋልት ማንጠፍ ሥራው በአብዛኛው ቦታ እየተገባደደ ሲሆን፤ ውስጥ ለውስጥ የሚቀበሩት የመብራት፣ የውሃና ፍሳሽ እንዲሁም የቴሌ መሰረተ ልማቶች በተቀናጀ ሁኔታ በመሠራት ላይ ናቸው፡፡ የእግረኛ መንገድ ጠጠሩ ተስተካክሎ አልቆ የቴራዞ ንጣፍ ለመሥራት ቴራዞው እየቀረበ ነው፡፡

እዚህ ላይ ማንሳት ያለብኝ ጉዳይ መሰረተ ልማት አቅራቢ ድርጅቶች እስካሁን በዚህ ልክ ተቀናጅተው ሲሠሩ አለመታየታቸውን ሲሆን፤ ከዚህ በኋላም ወደኋላ ለመመለስ ቢሞክሩ የተገኘው ተሞክሮ ከፍተኛ ስለሆነ ቀላል እንደማይሆንላቸው እገምታለሁ፡፡ ስለሆነም በርቱ፣ በዚሁ ቀጥሉ ሊባሉና ሊመሰገኑ ይገባል፤ መልካም ሲሠሩ ማመስገን ተገቢ ነውና፡፡

ወደ መንገድ ሥራው ልመለስና ቀደም ሲል በጠቀስኩት ኮሪደር የአስፋልት ማስፋትና የእግረኛ መንገድ በአዲስ መልክ ሲሠራ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች ለማስገባት ጠዋት መሬቱ ከተቆፈረ ከሰዓት ቱቦው ተቀብሮ ይጠናቀቃል፡፡ ወይም ሌሊቱን መሬቱ ተቆፍሮ ቱቦው ተቀብሮ ተደልድሎ ያልቃል፡፡ ጠዋት ለተሽከርካሪ ክፍት ይሆናል፡፡

ይህም በአካባቢው ለሚኖሩና ለሚሠሩ ሰዎች የመንገድ ሥራው ሳያውካቸው እየተሠራ ስለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከስድስት ኪሎ ወደ ፈረንሳይ በሚወስደው እንዲሁም ኮተቤ አካባቢ ይታይ የነበረው የመንገድ ግንባታ ተጀምሮ ይህ ነው የሚባል ሥራ ሳይሠራ በቁፋሮው ምክንያት የአካባቢው ነዋሪና ሠራተኛ እንግልት ውስጥ መግባት ይታይ ነበር፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ውስጥ ግን ይህ እንግልት የለም፡፡

እንዲያውም የመንገድ ሥራው ተገቢው የመንገድ ሥራ ማሽኖችና የሰው ኃይል ተመድቦለት ከመፋጠኑ የተነሳ አስፋልቱ በከፊል ለተሽከርካሪዎች ክፍት ሆኗል። ከእሪ በከንቱ በቱሪስት ሆቴል እንዲሁም በአራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት አድርጎ ወደ ቅድስት ማርያም የሚወስደው መንገድ ተሽከርካሪዎች እንደልባቸው እየተመላለሱበት ነው፡፡

ተሽከርካሪዎች እንደልባቸው ከመመላለሳቸው በፊት ግን ሥራው ሲሠራ አስፋልቱ በማሽነሪዎች ጨቅይቶ ስለነበር ተጠርጓል፤ ከዚያም አቧራ እንዳይሆን ውሃ ተደርጎበታል፡፡ ግነት እንዳይሆንብኝ ብዬ እንጂ ማለት የነበረብኝ አቧራ እንዳይሆን ውሃ ተደርጓል ሳይሆን በውሃ ታጥቧል ነበር፡፡ ምክንያቱም ከፍተኛ መጠን በሚረጭ ውሃ ነበር አስፋልቱ ይታጠብ የነበረው፡፡

ከሜክሲኮ ወደ ሳር ቤት የሚሄደው መንገድ አስፋልቱ ተስተካክሎ አስፋልት ለብሶ የእግረኛ መንገድ ላይ የሚደረገው የቴራዞ ሥራ አንዳንድ ቦታ በመገባደድ ላይ ይገኛል፡፡ ሕንፃዎች ውስጥ የእግረኛ መንገድ ሲገባ የሕንፃዎቹ ባለቤቶች በአፋጣኝ የገባውን ቦታ በማፍረስ እንዲሁም በረንዳውን አፍርሶ በማስተካከል ለሥራው መሳለጥ የሚያደርጉት ምላሽ የሚደነቅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ስለሆነም ኅብረተሰቡ ለልማቱ እየሰጠ ያለውንም በጎ ምላሽም ማመስገን የሚገባ ይመስለኛል፡፡

ከአራት ኪሎ ወደ መገናኛ የሚወስደው መንገድ አራት ኪሎ ላይ የተዘጋ ይሁን እንጂ ከአራት ኪሎ በመጀመር ወደ መገናኛ የሚሄዱ ተሽከርካሪዎች ሥራው እየተሠራም ቢሆን እየተመላለሱ ይገኛሉ። ሥራው ለተሽከርካሪዎች ዝግ ሳይሆን ተግባራዊ እንዲሆን ያደረገው መንገድ የሚያዘጉ ሥራዎች በምሽቱ ተሠርተው ስለሚጠናቀቁ ይመስለኛል፡፡

ይህን ያልኩበት ምክንያት ማታ በሥራ መውጫ ላይ ያልተጀመረ መንገድ ሊያዘጋ የሚችል ሥራ፣ ለምሳሌ ዋናውን መንገድ የሚያቋርጡ የቱቦ ቁፋሮና ቀበራ ሥራዎች በምሽቱ ተጀምረው ተጠናቀው ጠዋት አስፋልቱ ለተሽከርካሪ ክፍት ሆኖ በማየቴ ነው፡፡ በአንድ ምሽት የማይጠናቀቁት ደግሞ እስከ ምሳ ሰዓት ተሠርተው ይጠናቀቃሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት አካሄድ በመንገድ ልማቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም የመሰረተ ልማት አውታሮችም የሚታይ ነው፡፡

ይህን ዓይነት የተቀናጀ አሠራር በሁሉም የኮሪደር ልማት እየተከናወነ ሲታይ ደግሞ ‹‹የመሠረተ ልማት ሥራዎች ቅንጅታዊ አብዮት›› ማለት ይቻላል፡፡ በእኔ እይታ አሠራሩ በቅንጅትና በፍጥነት እየተተገበረ ስለሆነ የመንገድ ሥራው ክረምቱ ሳይገባ በሁሉም ኮሪደሮች ያሉት ሥራዎች ይጠናቀቃሉ፡፡

ይህን መተማመን የፈጠረው ደግሞ የከተማዋ አስተዳደር ኃላፊዎች ቀን እና ሌሊት የሥራውን ሁኔታ እየተመለከቱ የሚሰጡት አመራርና የብርቱ ሠራተኞች ትጋት ውጤት ነው፡፡ ኃላፊዎቹ ቀንም ሆነ ምሽት ሥራው በትጋት እንዲሠራ ብቻ ሳይሆን የሚከታተሉት በመንገድ ሥራው ስፍራ ምሽቱን ተገኝተው ‹‹በርቱ፣ ጎናችሁን ጠግኑ!›› በማለት የሚጎረስ እህል በማቅረብ የምገባ መርሐ ግብር እያዘጋጁ መመገባቸውም ለስኬቱ የራሱን አስተዋፅኦ ያደርጋል እላለሁ፡፡

ሥራው በፍጥነት ይሠራል፤ ክትትል ይደረግበታል፤ አፈጻጸሙ ተገምግሞ የሥራ አቅጣጫ ይሰጥበታል። ለመበርታት እንጂ ለመለገም ጊዜ የለም፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ብርታት ካሳዩን ለሥራ እንተጋለን!

ስሜነህ ደስታ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You