ስዊድን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች

አዲስ አበባ፡- ስዊድን ከረጅም ዘመናት ወዳጇ ኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዘርፈ ብዙ ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች።

የሀገራቱን የ70 ዓመታት የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚዘክር “የኢትዮጵያና ስዊድን አንድነት በአሁነኛው ዘመን” በሚል መሪ ሃሳብ የፓናል ውይይት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናትና ምርምር ተቋም ውስጥ ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ የተገኙት በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር ሐንስ ሄንሪክ እንደተናገሩት፤ የኢትዮ-ስዊድን ሁለትዮሽ ግንኙነት 70 ዓመታትን ተሻግሯል፡፡ በነዚህ ሰባ ዓመታት ውስጥም ሀገራቱ እርስ በርስ ያላቸውን ግንኙነት እያሳደጉ መጥተዋል።

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤ ስዊድንና ኢትዮጵያ በነበራቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች ትብብር ያደርጋሉ፡፡ ግብርና፣ ጤና፣ ንግድና ኢንቨስትመንትም ዋንኞቹ ናቸው፡፡ ሀገራቱ በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ ያላቸው ትብብር በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

አምባሳደር ሀንስ እንዳመለከቱት፤ ስዊድን ከኢትዮጵያ ጋር በነበራት የረጅም ዘመን ግንኙነት በተለይም ከ1960 ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት ከስድስት ሺህ በላይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለኢትዮጵያ ገንብታለች፡፡

የሀገራቱ የትብብር መንገድ ዘርፈ ብዙ መሆኑን ጠቁመው፤ በዋነኛነት በትምህርት ዘርፉ ሰፊ ግንኙነት እንዳላቸው አመላክተዋል።

ስዊድን ለኢትዮጵያውያን እስከ ሦስተኛ ዲግሪ የሚደርሱ የትምህርት ዕድሎችን በማመቻቸት በርካታ ዜጎች የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉም አምባሳደሩ አንስተዋል። በቀጣይም መንግሥታቸው በስፋት የትምህርት ዕድሎችን በማመቻቸት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች የተሠማሩ ከ30 በላይ የስዊድን ድርጅቶች መኖራቸውን አምባሳደሩ አመላክተው፤ ተቋማቱ የሀገራቱን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶች በማጠናከር ረገድ አወንታዊ አስተዋፅዖ እየተወጡ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በመልካም መሠረት ላይ የተጣለ በመሆኑ የወደፊት ግንኙነታቸውም መልካም እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና ስዊድን ባላቸው የረጅም ዘመን ግንኙነት ውስጥ ብዙ ውጣ ውረዶች ቢኖሩም የገጠሙ መሰናክሎች ወዳጅነታቸውን ሳያግዱ ለዛሬ መብቃት መቻላቸው በሀገራቱ መካከል ላለው ግንኙነት ጥንካሬ ማሳያ መሆኑንም አምባሳደር ሀንስ ገልጸዋል።

ዳግማዊት ግርማ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2016 ዓ.ም

Recommended For You