ባለሥልጣኑ የደምብ መተላለፎችን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራ ነው

አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ ደምብ ማስከበር ባለሥልጣን የከተማይቱ ደምብ መተላለፎች እንዲቀንሱ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ አስታወቀ፡፡

ባለሥልጣኑ ከአዲስ አበባ ፅዳት አስተዳደር እና አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስከያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ እንደገለጹት፤ ቆሻሻ በየቦታው የሚጥሉ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበው ባለሥልጣኑ ደምቡን በሚጥሱ አካላት ላይ ሕጋዊ ርምጃ እንደሚወስድ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ደምብ ማስከበር ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ አበባ እሸቴ በዚሁ ወቅት ባቀረቡት የመወያያ ሰነድ በአዋጅ ቁጥር 150/2015 ዓ/ም ለደምብ መተላለፎች የወጡ የቅጣት ሰንጠረዦች ላይ በዝርዝር በመወያየት፤ ሚዲያዎች ለኅብረተሰቡ ተገቢውን የግንዛቤ መረጃ እንዲሰጡ ይደረጋል ብለዋል።

ከተጠቀሱት የቅጣት ዓይነቶች መካከል፤ በሕገ ወጥ መንገድ የፍሳሽ እና የደረቅ ቆሻሻ ማስወገድ፣ አዋኪ ድርጊት እና መሰል ተግባራትን መፈፀም፣ ሕገ ወጥ የውጭ ማስታወቂያ ማሰራጨት ተጠቃሽ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በተለይ የሚበሰብሱ እና ደረቅ ቆሻሻዎችን ለይቶ በአግባቡ ማስወገድ ሲገባ ይህን የማያደርግ አካል በደምብ መተላለፍ እንደሚጠየቅ መድረኩ ላይ በቀረበው ሰነድ ተገልጿል፡፡

በመድረኩ ላይ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተገኙ ሲሆን፤ የክፍለ ከተማ የፅዳት አስተዳደር ኃላፊዎች፣ አርቲስቶች፣ የፅዳት አምባሳደሮች በቀረበው የመወያያ ሰነድ ላይ ሰፋ ያለ ሀሳብ ሰጥተውበታል፡፡

ከተነሱት ሀሳቦች መካከል የደምብ ማስከበር ሥራን ተግባራዊ ለማድረግ ኅብረተሰቡ በሚዲያዎች በኩል በቂ ግንዛቤ ሊሰጠው እንደሚገባ እና ይህን ተላልፎ ሆን ብሎ በቸልተኝነት ደምብ ለማያከብር አካል ቅጣት ተገቢ እንደሆነ ተነስቷል፡፡

በመሆኑም እያንዳንዱ ሰው እና ተቋም ደምብ የማስከበር ግዴታ እንዳለበት በመረዳት በተለይ ቆሻሻን በተመለከተ ለረጅም ጊዜ ቢሠራበትም መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ያልተቻለበትን ምክንያት በማወቅ፤ ግንዛቤ ከመስጠት ባለፈ ባለሥልጣኑ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን ተጠያቂነት እንዲኖር ይሰራል ብለዋል፡፡

የውይይት መድረኩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደምብ ማስከበር ባለሥልጣን፣ የአዲስ አበባ ከተማ ፅዳት አስተዳደር እና አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በጋራ አዘጋጅተውታል፡፡

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2016 ዓ.ም

Recommended For You