እግሬ እስኪንቀጠቀጥ ሰልፍ ይዤ የተሳፈርኩበት ታክሲ ውስጥ ነኝ። እስካሁን ድንጋጤው አለቀቀኝም። ከደቂቃዎች በፊት እስከ አናቱ ድንጋይ የቆለለ አንድ ሲኖትራክ እንደዋዛ እየታከከን ማለፉን እያስታወስኩ ነው። አሽከርካሪው ምን እንደነካው ባላውቅም አሁንም ፍጥነቱን አልቀነሰም። ይሮጣል፣ ይከንፋል…
ቀዥቃዣው ሾፌር ባገኘው ቀዳዳ ሁሉ ሾልኮ ለማለፍ ከመኪኖች ይጋፋል። የእኔን ያህል ባይሆንም አብዛኛው ተሳፋሪ ሊደርስ በነበረው አደጋ ሲጮህና ሲንጫጫ ነበር። አሁን ሁሉም በድንጋጤ ዝም ያለ ይመስላል። ግዜው ገና ጠዋት ቢሆንም መንገዱ መዘጋጋት ጀምሯል። ይህን ስመለከት እንዲያ ሲሮጥ የነበረው ሾፌር ውል አለኝና በመስታወቱ አሻግሬ ፊቱን ለማየት ሞከርኩ። ከወንበሩ እንዳለ ከወዲያ ወዲህ ይቁነጠነጣል። በረጅም ሰልፍ የተዘጋውን መንገድ ደጋግሜ ቃኘሁት። ፈጽሞ ጫፉ አይታይም።
አሁን በጠዋት የተነሳሁበት ጥብቅ ጉዳይ ከንቱ መቅረቱ ነው።ተስፋ ቆረጥኩ። ‹‹ዶሮ ርቃ ላትሄድ ማልዳ ትነሳለች ›› ይሉት አባባል ትዝ አለኝ። በረጅሙ ተነፈስኩና ‹‹እንግዲህ ምንም ማድረግ አይቻልም›› አልኩ። ደግነቱ ይህን ያልኩት በልቤ ነው።
ከፊትና ከኋላ መደርደር የጀመሩት መኪኖች ወዴትም መውጣትና ማምለጥ የእነሱ ምርኮኞች ከሆንን አንድ ሰዓት ሊሞላ ነው። አሁንም ንቅንቅ የሚል ነገር አይታይም።ይህ ቀዥቃዣ ሾፌር በጠዋቱ እያቅለበለበ ያጣደፈን ለዚህ ኖሯል። ምን ዋጋ አለው ወይ ይዞን አላመለጠ ወይ አላሳፍራችሁም ብሎ አልከለከለን ይኸው ጉድ ሠርቶናል።
አብዛኛው የታክሲ ተሳፋሪ በያለበት አሸልቧል። እኔም አልዋሽም ጥቂትም ቢሆን ተኝቻለሁ። ብንን ስል ግን አንዳች ለውጥ አልነበረም። መኪኖቹም ተሳፋሪዎቹም በቦታቸው እንዳሉ ነው። ሁሉም ነገር ስልችት ይላል። ደግነቱ ዓይን አያርፍም፡ ከወዲያ ወዲህ መለሰ ቀለስ እያለ ብዙ ይታዘባል። የእኔም ዓይኖች ከዚህ አላለፉም።አሻግረው ይቃኙና ተመልሰው ቦታቸው ይደርሳሉ።
አሁን ዓይኖቼ ርቀው ተሻግረዋል። አንዳች ነገር ላይ በማተኮሬ እነሱም ዒላማቸውን አልሳቱም።ከመንገዱ ባሻገር ሁለት ሰዎች ይታዩኛል። ሁለቱም በልመና ዓለም ስለመኖራቸው ነጋሪ አያሻም። አንደኛው በዕድሜ የገፉ ሽማግሌ ናቸው። ሌላው ደግሞ ከጎልማሳነት ያልደረሰ ወጠምሻ ይሉት አይነት ጎረምሳ ነው።ሰዎቹ ቁጭ ካሉበት ስፍራ ታላቅ ቁምነገር የያዙ ይመስላል።
ሁኔታቸው እየማረከኝ ነው።አሁን የታክሲውን ጉዳይ፣ የመንገዱን መዘጋጋት ዘንግቼ ትኩረቴን በእነሱ ጥያለሁ። ሽማግሌው የለበሱትን ብርድ ልብስ መሳይ ፎጣ ገለጥ ከማድረጋቸው ወጣቱ በእጁ የታሰረውን ረብጣ አስተካክሎ ከእጃቸው ላይ አኖረው።
ዓይኔን ማመን እያቀተው ቢሆንም ግርምታዬ አልተቋጨም። አሁንም በጥቁር ፌስታል ቢጤ የተጠቀለለ አንዳች ነገር ወደኪሳቸው ሲደርስ አስተዋልኩ። ሽማግሌው ጥቂት ገልመጥ ብለው ቃኙና የተቀበሉትን እስር ከኪሳቸው ከተው ፎጣቸውን ደረቡበት። ወዲያው በቀስታ ርምጃ አስፓልቱን ተሻግረው እኛ ወዳለንበት አቅጣጫ አማተሩ። የፈራሁት አልቀረም። በሚያሳዝን ገጽታ እጃቸውን ለልመና ዘረጉ። በጣም ደነገጥኩ።
ከደቂቃዎች በፊት በዓይኔ ያረጋገጥኩት የታሰረ ገንዘብ ኪሳቸው መቀመጡን ነበር። ሰውዬውን እንደእኔ አስተውሎ ያላያቸው ማንም ሰው አይጨክንባቸውም። ሽምግልናቸው፣ የቆሸሸ ልብሳቸውና አሳዛኙ ገጽታቸው እጅን ለምፅዋት ያዘረጋል። ደግነቱ እኔ ያለሁበትን ታክሲ ዘለው ወደሚቀጥለው መኪና አልፈው ሄዱ። ኧረ! እንኳንም አልመጡብን።በጣም ታዘብኳቸው። በጣም!
አሁንም የመኪናችን ልብ እየመታ ነው። ሾፌሩ መነጫነጩን ትቶ በዝምታ ተኮፍሷል። ገና ጠዋት ቢሆንም የታክሲው ውስጥ ወበቅ ግሎ ያነደን ይዟል። ‹‹ወይ አንዳንድ ቀን በቃ ካሰቡበት አያውልም›› ጮክ ያለ ድምፅ ከውስጤ ሲያልፍ ተሰማኝ። አሁንም ግን ያወራሁት ከራሴ ጋር ነበር ።
ከታክሲው ወጣ ብዬ መለስ ከማለቴ ዓይኖቼ ጎኔ ካለች አንዲት ሴት ጋር ተላተሙ።ለአፍንጫዬ ደመቅ ያለ የለውዝ ሽታ ሲደርስ ቢቆይም እስካሁን እሷ እየበላች መሆኑን ልብ አላልኩም። ሴትየዋ ለውዙን ስታኝክ በእልህ ይመስላል።ሁኔታዋ ሥርዓት የለሽ ቢሆንብኝ ዞር ብዬ አስተዋልኳት።
እሷ እቴ ማንም ቢያይ ቢያፈጥባት ደንታ ያላት አይመስልም። ከእጇ ያለውን ለውዝ እየፈለፈለች ታላምጠዋለች፣ ብቻ ሳይሆን ታመነዥጋለች ማለት ያስደፍራል። ምንአልባት የቁርስ ሰዓት ደርሶባት ሊሆን ይችላል ብዬ ከራሴ ጋር ቀለድኩ። ሁኔታዋን በዋዛ መለፍ አልተቻለኝም። እንደምንም ብዬ ገጽታዋን ለማየት ሞከርኩ።
ባለ ለውዟ ሴት ጥርሶቿ ከከናፍሯ ወጣ ብለው የሚታዩ ናቸው። በተለይ ከፊት ጥርሶቿ የላይኞቹ የታችኛውን ከንፈሯን ረግጠው የያዙ በመሆናቸው ገጽታዋን ቀይረውታል። በዛ ላይ ያለፋታ የምታደቀው ለውዝ ከከናፍሯ ደጃፍ ተዝረክርኮ ይታያል። ይህን አስተውሎ ለሚያይ ማንም ሰው ሁኔታዋ ያናድዳል። የሆነውን ሁሉ ባስተዋልኩ ግዜ እህል ያልሻረው ሆዴ ተገላበጠብኝ ።
ደግነቱ መስኮት ጥግ መሆኔ በጀኝ። በሙቀቱ አሳብቤ አየር ወደውስጥ አስገባሁ። ትርክርኳ ሴት አሁንም ለውዟን ማድቀቁን ቀጥላለች። እስቲ አሁን ምን አግብቶኝ ነው እሷ ላይ ማፍጠጤ? ራሴን እየታዘብኩ ዓይኖቼን አነሳሁና ወደውጭ ማማተር ጀመርኩ።
መኪናችን እምብዛም እየሄደ አለመሆኑ ዙሪያ ገባውን ለመቃኘት አይቸግርም። ከውስጥ ሀሳቤ መለስ ብዬ ወደ ውጭ ቀለስ እያልኩ ነው። የገባሁበት ታክሲ ካሰብንበት ደርሶ እግሬ መቼ መሬት እንደሚነካ አላወቅም። ዓይኖቼ ግን ሥራ አልፈቱም። መለስ ቀለስ እያሉ መታዘባቸውን ቀጥለዋል።
አሁን ከፊት ከኋላ ያሉት መኪኖች እንደምንም ወደፊት እየተሳቡ ነው። እንዲያም ሆኖ አካሄዳቸው የልብ አያደርስም። በእኔ በኩል የዕለቱ ጉዳዬ እንደታሰበው ባይሆንም ለመመለስ አላሰብኩም። የሌሎችን ግን አላውቅም። እንግዲህ ሁኔታዎች እንደሚሆኑ ይሆናሉ። ምርጫ የለም።ይህን እያሰብኩ ዓይኖቼን መልሼ አሻገርኩኝ።
በርቀት ሁለት ፖሊሶች አጥብቀው የያዙት አንድ ወጣት ላይ ትኩረቴ አረፈ። ከሁለቱ ፖሊሶች አንደኛው ጎረምሳውን እንደ ቅሪላ ይነርተዋል። ተደብዳቢው ደግሞ ምት ያረፈበት አይመስልም። ጥቂት እንደመለማመጥ ይልና የሚሰጠውን ዱላ በአክብሮት ይቀበላል። ሁኔታው ያናደደው የሚመስለው ፖሊስ እጁን ማሳረፍ የፈለገ አይመስልም። እየደጋገመ ባለ በሌለ ኃይሉ ይነርተዋል።
እኔ ከልቤ ተናደድኩ። ወጣቱ ግን አሁንም ምንም የተሰማው አይመስልም። መቺውም ተመቺውም በዙሪያው ከከበቧቸው እግረኞች ጋር ቀስ እያሉ ወደ እኛ አቅጣጫ ቀረቡን። የታክሲው ተሳፋሪ ጉዳዩን ለማወቅ ጆሮና ዓይኑን ወደውጭ ጣለ።ድንገት አንዲት ቃል ሽው ብላ ለጆሮዬ ደረሰች፡ ፡‹‹ሌባ ነው፣ሌባ ነው›› የሚል ድምፅ ተደጋግሞ ተሰማኝ።
በርቀት ሸሸግ ብለው የቆሙ ወጣቶችን ዓይኖቼ አነጣጠሯቸው።፡ ‹‹በአዩኝ አላዩኝ›› ስጋት ጥግ ይዘው ሁኔታውን በሞባይላቸው ይቀርፃሉ። ፖሊሶቹና ወጣቱ ተያይዘው ባጠገባችን እያለፉ ነው። ወዲያው በአዕምሮዬ ሁኔታው ሁሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲለቀቅ ታየኝና በድንጋጤ አፌን ያዝኩ።
የመንገዱ መዘጋጋት ብዙ ነገሮችን መለስ ቀለስ ብዬ እንድታዘብ አድርጎኛል። አብዛኞቹ ያየኋቸው አስገራሚም አሳዛኝም ናቸው። በነበረው ግዜ ሁሉን ታዝቤ ዓይኖቼን ወደውስጥ ስመልስ ደግሞ ከታክሲው ጣራ ዝቅ ብሎ ይህን አባባል እንዲህ አነበብኩ ‹‹ዛሬ ቀኔ ብሩህ ነው ›› ይላል።
ጥቅሱን ቃል በቃል እየደጋገምኩ ራሴን ጠየኩት። በማለዳ መነሳቴን፣ አሰብኩና የታክሲውን መንቀዥቀዥ ሊያደርስ የነበረውን አደጋ አስታወስኩ። የሁለቱን ሰዎች የገንዘብ ልውውጥ ትዝ ብሎኝ እጃቸው ለልመና መዘርጋቱን ታዘብኩ። የሴትዬዋ ለውዝ አበላል ውል ብሎኝ ሁኔታውን በጎ ባልሆነ ዕይታ ገመገምኩ። የፖሊሶቹ ዱላና የልጁ ሁኔታ ትዝ ብሎኝ የወጣቶቹ የቪዲዮ ቀረጻ ከሀሳብ እንደጣለኝ አስታወስኩ።
አሁን ደግሞ የመኪናው ላይ ጥቅስ ከዚህ ሁሉ እይታ በኋላ ቀኔ ብሩህ ነው ብዬ ራሴን እንዳሳምን እየነገረኝ ነው።እኔ ከነዚህ ሁሉ አጋጣሚዎች በኋላ ቀኔን ብሩህ ነበር ለማለት አልተቻለኝም። ለምን ካሉ አሁንም ከታክሲው አልወረድኩም። ደቂቃዎች እየቆጠርኩ መለስ ቀለስ እያልኩ ነው። መቼ ደርሼ እንደምወርድ እንጃ ። የሌላውን እንጃ እኔ ግን አሁንም ቀኔ ብሩህ ለመሆኑ እርግጠኛ አልሆንኩም።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 12 ቀን 2016 ዓ.ም