የጤናውን ዘርፍ አገልግሎት ከሚያሳልጡና ከሚያዘምኑ ሥራዎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የመረጃ ሥርዓቱን ማሻሻልና ማዘመን ነው። በተለይ ደግሞ የመረጃ ሥርዓቱ ቴክኖሎጂ መር ሲሆን በጤናው ዘርፍ የሚታየውን የውሳኔ አሰጣጥ ክፍተት በመሙላት ረገድ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ይሆናል። የአገልግሎት ጥራቱንም ይጨምራል፤ የተገልጋይ ርካታንም ከፍ ያደርጋል።
ለዚህም ከዛሬ ስምንት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ደረጃ የጤና መረጃ ሥርዓት አዘጋጅታ ወደሥራ ያስገባችው። ይህ ሀገር አቀፍ የጤና መረጃ ሥርዓት ታዲያ ላለፉት ስምንት ዓመታት የጤና ዳታዎች ሲሰበሰብበት ቆይቷል። የጤናውን ዘርፍ በማሻሻል ረገድም ጥሩ ውጤት እንደተገኘበት ተመስክሯል። በዚህ መነሻነት ይህንኑ የጤና መረጃ ሥርዓት ይበልጥ ለማሻሻል ምክክር ተደርጎበታል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ በፕላንና ፕሮግራም ዳይሬክቶሬት ውስጥ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ አቶ ትዛዙ ቢጋር እንደሚሉት፣ ሀገር አቀፍ የጤና ሥርዓቱ /ዲ ኤች አይ ኤስ/ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በክልሉም በሁለት መንገድ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል። አንደኛው በኦን ላይን ወይም የኢንተርኔት አገልግሎት በሚያገኙ ተቋማት ላይ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ኦፍ ላይን ወይም የኢንተርኔት አገልግሎት በማያገኙ ተቋማት ላይ ነው። ከመንግሥት ተቋማት በተጨማሪ በግል ተቋማት ላይም እየተሠራበት ይገኛል።
ይህ የጤና መረጃ ሥርዓት ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ በኋላ ከወረቀት አሠራር ወደ ዲጂታል በመግባት ውሳኔ ሰጪ አካላት ወይም ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ የተለያዩ አካላት መረጃውን በቀላሉ አግኝተው ለውሳኔ አሰጣጥ ምቹና ቀልጣፋ እንዲሆን አድርጓል። ሁሉም ተቋማት ወይም አገልግሎት ሰጪዎች ክፍተታቸውን በመለየት መገልገልና መጠቀም እንዲችሉ ያደረገ ሥርዓት ነው። በዚህ ረገድም ለውጦች እየታዩ መጥተዋል። በፊት ከነበረው አሠራር አንፃርም በብዙ መልኩ ወጪ ቆጣቢ ሆኖ ተገኝቷል።
ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማቱ መድኃኒቶችን ወይም የሕክምና አገልግሎቶችን በሪፖርት ደረጃ የሚመለከተው አካል በቀላሉ ተደራሽ በማድረግ በዛ መረጃ መሠረት ግብዓት ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ የሚያስፈልጉ የሕክምና ግብዓቶችን በቀላሉ ተደራሽ በማድረግ የማሳለጥ ሥራውን ሥርዓቱ ይከውናል። በዚሁ መሠረት መረጃውን በቀላሉ በማግኘት ለእነዛ መረጃዎች በቶሎ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የጤና መረጃ ሥርዓት አገልግሎት ማሳለጫ ሥርዓት ነው።
ይህ ሀገር አቀፍ የጤና መረጃ ሥርዓት ሲያድግ ደግሞ የጤና መረጃ መሰብሰቢያዎች ውስጥ ከዚህ በፊት ያልነበሩ እንደ አዲስ የተካተቱ አብረው በዚህ በሚሻሻለው የጤና መረጃ ሥርዓት ውስጥ ይካተታሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ በፊት ተጠቃሚዎች ሲገለገሉ ሪፖርቱን ለማውጣትና ለመጠቀም እንደ ችግር ሲያነሷቸው የነበሩ ችግሮች ይቀረፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በተጨማሪም የጤናውን ሥርዓት ለሚደግፉ አጋር አካላትና ድርጅቶች መረጃዎችን በማሳለጥ አስፈላጊውን ሪፖርት በሰዓቱ ማድረስ መድረስ የሚያስችልበትን አሠራር በማካተት ከዚህ በፊት የተነሱ ችግሮችን ያሻሽላል ተብሎ ይታሰባል።
አቶ አዳነ ለታ የሀብቴክ ሶሊዩሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። በተጨማሪም ድርጅቱ ከጤና ሚንስቴርና ቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ጋር በሚሰሩት ፕሮጀክት ላይ የፕሮጀክቱ ዳይሬክተር ሆነው ያገለግላሉ። ሃብቴክ በኢትዮጵያ በአምስት ባለሙያዎች የተመሠረተ ሲሆን አምስቱም ዘርፎች የተለያዩ ልምዶች አሏቸው። በተለይ ሶፍትዌር ማልማት፣ የዳታ ሳይንስ፣ ዳታ አናሊቲክስና ህብረተሰብ ጤና ምርምር ጋር የተገናኘ ልምድ ያላቸው አምስት ባለሙያዎች ድርጅቱን አቋቁመዋል። ድርጅቱ ከተቋቋመም ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል። ነገር ግን ደግሞ በሁለት ዓመታት ጊዜው ውስጥ በርካታ ሥራዎችን ሰርቷል።
በተለይ የሀገር አቀፍ የጤና መረጃ ሥርዓትን ከጤና ሚንስቴር ጋር በመሆን አዘጋጅቷል። ከዚህ በተጨማሪም ዳታን መተንተን፣ የተተነተነውን ዳታ ደግሞ ለውሳኔ ጥቅም እንዲሰጥ የሚያስችሉ ስልጠናዎችን ለጤና ሚንስቴርና ለክልል ጤና ቢሮዎች እየሰጠ ይገኛል። ድርጅቱ ሲቋቋም አላማው የጤና ሥርዓቱ ላይ ታማኝ የሆነና የተሰጠውን ሥራ በአግባቡ የሚያደርስ ድርጅት የለም ብሎ አስቦ ነው ድርጅቱ የተቋቋመው። ወደፊት ታማኝና ኃላፊነት የሚጣልበት በተለይ ጤና ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሴክተሮች ዲጂታል ኢትዮጵያን በ2025 እውን ለማድረግና ከዚህ በኋላ የሚመጡትን እንደ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ዓይነት ጋር የተገናኙ ሥራዎችን ይሠራል ተብሎ ይታሰባል።
ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚ ከፍ እንድትል ይፈለጋል። ለዚህም ደግሞ ድርጅቱ የራሱን አስተዋፅኦ ያደርጋል። በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ያሉ ወጣት የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችን በመጠቀም የሀገርን ችግር የሚፈቱ የተለያዩ መፍትሔዎችን ከአብዛኛዎቹ የድርጅቱ አጋሮችና ከሚንስቴር መሥሪያ ቤቶች ጋር በመሆንና በመነጋገር ሥራዎችን ለመሥራት ታስቧል።
ሥራ አስኪያጁ እንደሚናገሩት የሀገር አቀፍ የጤና መረጃ ሥርዓት ፎረም እንደ አንድ የመማማሪያ መድረክ እንዲሆን ይፈለጋል። ፎረሙ ባለፈው ዓመት ይጀመር እንጂ ድርጅቱ ድጋፍ እያደረገ አይቀጥልም። ምክንያቱም ይህ ሀገራዊ ንቅናቄ እንዲሆን ነው ድርጅቱ የሚፈልገው። ጤና ሚንስቴር ከሌሎች አጋር አካላት ጋር መሆን እንዲያስቀጥለው ያስፈልጋል።
ሃሳቡ በጤና ሚኒስቴር ደረጃ እንደ የጤና መረጃ ሥርዓት በሀገር ውስጥ የተተገበረ ሥርዓት የለም። ስለዚህ ድርጅቱ ይህ ሥርዓት እንዲቀጥል ይፈልጋል። ለሌሎችም መማሪያ እንዲሆን ይፈልጋል። ይህን ለማድረግ ደግሞ የመማሪያ ፎረም ያስፈልጋል።
ድርጅቱ የመማማሪያ ፎረም ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ስልጠናዎችንም ለጤና ሚንስቴርና ለክልል ጤና ቢሮዎች ባለሙያዎች ይሰጣል። አስራ አራት የሚሆኑ የበቁ ባለሙያዎች በየክልሎች በተለይ የዲ ኤች አይ ኤስ 2 ትግበራን የሚደግፉ ተቀጥረው እየሠሩ ይገኛሉ። አዳዲስ ተመራቂ ልጆችን በማብቃት ሀገራዊ ችግሮችን እንዲፈቱ ማድረግ ነው ድርጅቱ የሚፈልገው። ይህንኑ መድረክ አመቻችቶም ነው እየሠራ የሚገኘው።
ከጤናው ዘርፍ ውጭ ሃብቴክ በሌሎች ሴክተሮችም ውስጥ በቀጣይ ገብቶ የሚሠራ ይሆናል። ሀገር አቀፍ የመረጃ ሥርዓቱ ለጤናው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን ለግብርናና ለሌሎችም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችም ሊሰራና ሊያገለግል የሚችል ነው። አሁን ላይ ከሌሎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጋር ውይይቶች አሉ። በተለይ የኢትዮጵያ ግብርና እድገት እንዲፋጠንና ችግርም እንዳይኖርበት ከተፈለገ እንዲህ ዓይነቱን መረጃ ሥርዓት በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል። ስለዚህ ዲ ኤች አይ ኤስ ለጤናው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ሴክተሮች ሊሆን ይችላል። ድርጅቱም ያሉትን ባለሙያዎች ተጠቅሞ ዲ ኤች አይ ኤስ 2 ወደ ሌሎች ሴክተሮች ለመውሰድ ጥረት እያደረገ ነው። ስለዚህ ድርጅቱ አሁን በጤናው ዘርፍ ያከናወነው ሥራ ውጤት ወደፊት የሚታይ ይሆናል።
በጤና ሚኒስቴር የዲጂታል ጤና ክፍል አስተባባሪ አቶ ገመቺስ መልካሙ እንደሚናገሩት በጤና ሴክተር ውስጥ ከጤና ኬላ ጀምሮ እስከ ጤና ሚኒስቴር ድረስ የሚሰበሰቡ ዳታዎች አሉ። እነዚህ ዳታዎች ከዚህ በፊት በወረቀት ነበር የሚሰበሰቡት። ነገር ግን ከስምንት ዓመት ወዲህ ከኦስሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ዲ ኤች አይ ኤስ 2 /District Health Information System 2/ የተባለ ሶፍትዌር በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ እንዲዘጋጅ ተደርጓል። ሶፍትዌሩ ከወረዳ ጀምሮ ያሉ ዳታዎችን እንዲሰበስብ ተደርጎ የተሠራ ቢሆንም ከጤና ተቋማት ጀምሮ ይበልጥ እንዲሻሻል ተደርጎ ጥቅም እየሰጠ ይገኛል።
ይህ ሀገር አቀፍ የጤና መረጃ ሥርዓት ሥራ ላይ መዋል ከጀመረ ስምንት ዓመት ሆኖታል። እስካሁንም ዳታዎችን እየሰበሰበ ይገኛል። ምን ዓይነት ዳታዎች መሰብሰብ አለባቸው፣ የተሰበሰቡ ዳታዎች ምን ይመስላሉ የሚለውን ለማወቅ ወደ ማዕከል በማምጣት በሶፍትዌሩ ላይ በየዓመቱ ውይይት ይደረግበታል። በሶፍትዌሩ ብቃት፣ በሚይዛቸው ዳታዎች፣ ለውሳኔ አሰጣጥ አመቺነት ላይ ውይይት ይካሄዳል። በስምንት ዓመታት ውስጥ 1 ቢሊዮን የሚሆን ዳታ ተመዝግቧል። ይህን ዳታ እንዴት መጠቀም እንደሚቻልም ከተለያዩ የጤናው ዘርፍ ከተውጣጡ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል።
እንደ ሀገር በሁሉም የመንግሥት ተቋማት በተለይ የመብራትና የኢንተርኔት አገልግሎት ያላቸው በቀጥታ ከተቋማቸው ዳታውን ሰብስበው ማስገባት ይችላሉ። የተወሰኑ የግል ተቋማት፣ ትላልቅ ሆስፒታሎችም የጤና መረጃ ሥርዓት ሶፍትዌሩን ተግብረዋል። በጤና ጣቢያ ደረጃ 3 ሺ 600 አካባቢ የሚሆኑ ጤና ጣቢያዎች ሶፍትዌሩን ተግበረዋል። 400 የመንግሥት ሆስፒታሎችም እንዲሁ ሶፍትዌሩን ተግብረዋል። የግል ሆስፒታሎች እንዳዛው ተግባራዊ አድርገዋል።
ከዚህ ውጭ በወረዳ የሚገኙ ጤና ቢሮዎች በሶፍትዌሩ አማካኝነት ዳታዎችን ሪፖርት ያደርጋሉ። የዞንና የክልል ቢሮዎችም በተመሳሳይ ዳታዎችን በዚህ ሲስተም አማካኝነት ይልካሉ። ሁሉም የጤና ተቋማት በዚህ ሥርዓት ውስጥ ገብተዋል። የጤና መረጃ ሥርዓቱ በትንሹ 35 የሚሆን ተጠቃሚ አለው።
እንደ አስተባባሪው ገለፃ እስካሁን ባለው ሂደት ዳታው በመረጃ ሥርዓቱ አማካኝነት ሪፖርት የሚደረገው ከወረቀት ላይ ተሰብስቦ ነው። ነገር ግን በቀጣይ ከየክፍሉ ዳታውን በመሰብሰብ ጥራት ያለው ዳታ ወደ ጤና መረጃ ሥርዓቱ የሚገቡበት አሠራሮች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ከአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር በማገናኘት የሚሰራበት ሁኔታ ላይም ጥናቶች እየተካሄዱ ነው። ስለዚህ በዚህ መሠረት ምን ያህል ታካሚዎች ወደ ሆስፒታል መጥተዋል፣ ምን ያህሎቹ ቲቢና ወባ አለባቸው፣ ምን ዓይነት መድኃኒት ታዞላቸዋል የሚለውን የስምንት ዓመት 1 ቢሊዮን ዳታ ተሰብስቧል።
ይህን ዳታ በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ተጠቅሞ የሕክምናና የመድኃኒት አገልግሎት በትክክል አግኝተዋል፣ የትኞቹ በሽታዎች ናቸው እንደሀገር ላለፉት ስምንት ዓመታት የነበሩት የሚለውን ማየት የሚያስችል ሥራ መሥራት ይቻላል። ስለዚህ የዳታ አጠቃቀሙን ለማህበረሰቡና ለአጥኚዎች ጥቅም በሚሰጥ መልኩ እየተሠራ ነው።
ከዚህ በፊት በጤናው ዘርፍ ውሳኔዎች የሚሰጡት ከወረቀት በሚሰበሰቡ መረጃዎች ነበር። አሁን ግን በጤናው ዘርፍ በሁሉም ደረጃዎች ላይ የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች በቀላሉ ዳታ ማግኘትና ውሳኔዎችን፣ ማሳለፍ ይችላሉ። በዚህም ይህ ሀገር አቀፍ የጤና መረጃ ሥርዓት የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቱን አሻሽሏል። ተቋማትም የመታየት እድላቸው ጨምሯል። ያ ማለት አንድ ጤና ጣቢያ ምን እንደሚሠራ በሀገር አቀፍ ደረጃ መታየት ጀምሯል። የውድድር መንፈስ ይፈጥራል፤ የተሻለ ሥራ እንዲሠራ ያደርጋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 12 ቀን 2016 ዓ.ም