ኢትዮጵያን የአፍሪካ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተምሳሌት ለማድረግ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡- በ2022 ኢትዮጵያን በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በተሻሻለው አምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ዙሪያ ከፌዴራል ተቋማት ሥራ ኃላፊዎች፣ ከአምራች ኢንዱስትሪ የዘርፍ ማኅበራት አመራሮችና ከባለድርሻ አካላት ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት መድረክ ትናንት ተካሂዷል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ በ2022 ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት የሚያደርጉ እቅዶች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው፡፡

በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የማድረግ እቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው ያሉት አቶ መላኩ፤ በ2022 በተለይ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት የሚያደርጉ እቅዶች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው ብለዋል፡፡

ሀገራዊ እቅዶችን ለማሳካት ፖሊሲዎችን፣ አሠራሮችን፣ መሠረተ ልማቶችን፣ የሰው ኃይሉን ማሻሻል እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፤ የአምራች ዘርፉን ሊመራ የሚችል ወጥና ሁሉን አቀፍ ፖሊሲ በማውጣት ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የፖሊሲው ይዘት ገበያ መር፣ በግሉ ዘርፍ የሚመራና የመንግሥትን ሚና በግልፅ ያመላከተ መሆኑን በመግለጽ፤ የኢንዱስትሪ ክላስተር፣ ለወጪና ተኪ ምርት የተመጣጠነ ትኩረት የሰጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የፖሊሲው ዓላማ የምርት ልማትና ተወዳዳሪነት ማረጋገጥ፣ የሰው ኃብት ልማትና አስተዳደር ማሳደግ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ፣ ፋይናንስ አቅርቦትና ተደራሽነትን ጨምሮ፣ ማክሮ ኢኮኖሚና የቢዝነስ ሥነ- ምሕዳር ማሳደግ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በዘርፉ በኢንዱስትሪ ባሕልና በሥራ አመራር ክህሎት የዳበረ የሰው ኃይል ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ በፋይናንስ አቅርቦትና ተደራሽነት የብድር አቅርቦት፣ የውጪ ምንዛሪ፣ የመድን ሽፋንና ሌሎች የፋይናንስ ምንጮችን ለመጠቀም ትኩረት መደረጉን አመላክተዋል።

ፖሊሲው የኢንዱስትሪ ክላስተር አሠራርን በመከተል የግብዓት ምርት ልማት ትስስርን የሚደገፍ መሆኑን ገልጸው፤ ለወጪ ንግድና ለተኪ ምርት ልማት እንዲሁም ለምርት ጥራት ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡

ማክሮ ኢኮኖሚና የቢዝነስ ሥነ-ምሕዳርን መነሻ በማድረግ የተረጋጋና ተገማች የማክሮ ኢኮኖሚ ሥርዓት መፍጠር እንደሚገባ በመግለጽ፤ ፖሊሲው አስቻይ የቢዝነስ ሥነ- ምሕዳር መፍጠር የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የአምራች ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የአሠራር ማሻሻያዎችን ማየት ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ የዘርፉን ልማት ለማረጋገጥ የሁሉንም ተቋማት ርብርብና ድጋፍ ይጠይቃል ብለዋል።

በሀገሪቱ በአሁኑ ጊዜ በሁሉም ዘርፎች ተስፋ ሰጪ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ የዘርፉን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል አሠራርና አደረጃጀት መፈጠሩን ገልጸዋል።

በመድረኩ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሐመድን ጨምሮ የአምራች ኢንዱስትሪው ማኅበራት አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2016 ዓ.ም

Recommended For You