ስምምነቱ ከውጭ ለሚመጡ ቱሪስቶች ቀላል የክፍያ አማራጭን ይፈጥራል

አዲስ አበባ፡- ራይድ የትራንስፖርት ድርጅትና ዓለም አቀፍ የዲጂታል ክፍያ ተቋም ቪዛ የፈጸሙት ስምምነት ከውጭ ለሚመጡ ቱሪስቶች ቀላል የትራንስፖርት የክፍያ አማራጭን የሚፈጥር መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ራይድ የትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት እና ዓለም አቀፍ የዲጂታል ክፍያ ተቋም ቪዛ የትራንስፖርት ክፍያን በራይድ መተግበሪያ አማካኝነት መፈጸም የሚያስችለውን ስምምነት ትናንትና አድርገዋል።

በስምምነቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሦስተኛ የዲፕሎማቲክ መቀመጫ እንደመሆኗ በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎችና ቱሪስቶች ይጎበኟታል ፡፡

ይሁን እንጂ ለቱሪስቶች የሚመጥን የክፍያ ሥርዓት ባለመስፋፋቱ ጎብኚዎች የተሳካ ቆይታ እንዲኖራቸው ለነሱ የሚመች የክፍያ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ላይ ከተቀመጡ ግቦች መካከል የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትን ማዘመን አንዱ መሆኑ የገለጹት ይሽሩን (ዶ/ር)፤ ራይድና ቪዛ የፈጸሙት ስምምነት ለጎብኚዎች፣ በኢትዮጵያ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች እንዲሁም የዲያስፖራው ማኅበረሰብ አባላት ፈጣን የክፍያ አገልግሎትን ለማቅረብ እንደሚረዳ አመላክተዋል። ስምምነቱ የዲጂታል ክፍያን በማሳለጥ በዘርፉ ያለውን ችግር በተወሰነ የሚያቃልል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የራይድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሳምራዊት ፍቅሩ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ራይድ አስተማማኝና ቀልጣፋ የክፍያ አማራጭ ለመስጠት ከቪዛ ጋር ያደረገው ስምምነት መንገደኞች ስለ ጥሬ ገንዘብና ምንዛሪ ሳይጨነቁ የትራንስፖርት ክፍያቸውን መፈጸም ያስችላቸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ቱሪስቶች ለትራንስፖርት የሚከፍሉት በኢትዮጵያ ምንዛሪ የነበረ ሲሆን ይህ ስምምነት ግን የቪዛ አካውንታቸውን ወደ አሽከርካሪው በማስገባት ብቻ የአገልግሎት ክፍያቸውን ከአካውንቱ ላይ ተቀናሽ የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ስምምነቱ አገልግሎቱን ከማዘመን በተጨማሪም ሀገሪቷ የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ አስተዋፅዖ ያደርጋል ሲሉ አስረድተዋል። በኢትዮጵያ የቪዛ ክፍያ ተቋም ዳይሬክተር ያሬድ እንዳለ በበኩላቸው፤ ቪዛ በዓለም ዙሪያ ከ200 በላይ ሀገራት የአገልግሎት ተጠቃሚዎች እንዳሉት ገልጸው፤ ስምምነቱ አስተማማኝ የክፍያ ሥርዓትን በማቅረብ በዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ዘንድ የኢትዮጵያ የጉዞና የቱሪዝም ዘርፍን ይደግፋል ብለዋል፡፡

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2016 ዓ.ም

Recommended For You