ኮርፖሬሽኑ የአንድ ነጥብ 23 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ስምምነት ተፈራረመ

ሀዋሳ፡የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ኢንቨስት ፎር ኤምፕሊዮመንት ከተሰኘ ጀርመን ድርጅት ጋር አንድ ነጥብ 23 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ስምምነት መፈራረሙን ገለጸ፡፡ የስምምነቱ ዓላማ የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ያለውን የውሃ ችግር ለመቅረፍ ያለመ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የፊርማ ሥነሥርዓቱን ያከናወኑት የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ አክሊሉ ታደሰ እና የጀርመኑ ኢንቨስት ፎር ኤምፕሊዮመንት የአፍሪካ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስተር ኢስተፌን ኪሁል ናቸው፡፡

አቶ አክሊሉ ታደሰ በስምምነቱ ሥነሥርዓት ላይ እንደተናገሩት፤ የስምምነቱ ዋና ዓላማ በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ንጹህ የመጠጥ ውሃ በጥራትና በብዛት በዘላቂነት ለማቅረብ አቅም ለመፍጠር ነው፡፡

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚስተዋለውን የውሃ ችግር ሙሉ ለሙሉ ከመቅረፍ አልፎ ለአካባቢ ማህበረሰብ ጭምር እንደሚበቃ አቶ አክሊሉ ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ አክሊሉ ገለጻ፣ በስምምነቱ የተፈረመው አጠቃላይ የገንዘብ መጠን አንድ ነጥብ 23 ሚሊዮን ዩሮ ሲሆን፣ የፕሮጀክቱን 73 በመቶ የሚሸፍን ይሆናል፡፡ ቀሪው ገንዘብ በኢትዮጵያ መንግሥት ይሸፈናል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ባለፉት ዓመታት ከመንግሥት ሀብት ብቻ እየተመደበ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፤ ባለፉት ጊዜያት ፓርኩ ፕሮጀክት ቀርጾ ከውጭ ሀገራት ድጋፎችን እያፈላለገ ቆይቷል ብለዋል፡፡ ስምምነቱም የዚህ ተግባር ውጤት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከመንግሥት ድጋፍ ተላቀው በራሳቸው ሀብት በማፈላለግ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሠራ እንደሆነም አክለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ 177 ሼዶች መኖራቸውን የገለጹት አቶ አክሊሉ፤ ከዚህ ውስጥ በባለሀብቶች ያልተያዙ ሼዶች 22 ብቻ መሆናቸውን አያይዘው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ ስምንቱ ሼዶች በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፤ ሙሉ ለሙሉ ሼዶቹ እንዲያዙ ኮርፖሬሽኑ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢንቨስት ፎር ኢምፕሎይመንት የአፍሪካ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስተር ኢስቴፈን ኪሁል በበኩላቸው፤ የዚህ ፕሮጀክት ስምምነት የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያለውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ሙሉ በሙሉ እንደሚቀርፍ ተናግረዋል፡፡

የዚህ ፕሮጀክት ሥራው የሚጠናቀቀው አንድ ዓመት ተኩል መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የሀዋሳ ኢንዱስተሪ ፓርክ ሥራ አስኪያጅ አቶ ማቲያስ አሸናፊ ስምምነቱን በማስመልከት፣ በፓርኩ ውስጥ የውሃ እጥረት በመኖሩ ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር እያቀረበልን ሥራዎችን ሥንሠራ ቆይተናል ብለዋል፡፡

የፕሮጀክቱ መፈረም አጠቃላይ በፓርኩ ውስጥ ላለው ከ24 ሺህ በላይ ሠራተኛ የመጠጥ ውሃ ችግርን ሙሉ ለሙሉ ይቀርፋል፤ ለአካባቢ ማህበረሰብም ጭምር ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክት መፈራረም ፓርኩ ውስጥ በቂ ውሃ እንዲኖር ከማስቻሉ በላይ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ጠቀሜታ ያለው እንደሆነ አቶ ማቲያስ አንስተዋል፡፡

አብርሃም ሳሙኤል

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You