ሄዋን-  ለሴቶች ጤና መጠበቅ ተስፋ የሆነ የበጎ አድራጎት ድርጅት

በርካታ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ምሥረት ሲታይ አንድ መነሻ ምክንያት አላቸው። በቤተሰብ አባላት ወይም በልጆች ላይ በሚከሰቱ የጤና ችግሮች ምክንያት ከማህበራዊ ሕይወታቸው የተገለሉና የትኛውንም የሕክምና ድጋፍ ሳያገኙ ተደብቀው እና ከማህበረሰቡ ተገልለው የተቀመጡ ሰዎች ቁጥርም ቀላል አይደለም።

አንዳንዶቹ በልጆቻቸው ወይም ቤተሰብ መካከል ከሚያጋጥሙ የጤና ችግሮች ተነስተው መፍትሔ ሲያፈላልጉ እና በተመሳሳይ ችግር ውስጥ ላሉት የማህበረሰቡ አካላትም ጭምር አገዛ ለማድረግ የሚያስችሉ ተቋማት መመሥረት ችለዋል። እነዚህ በቤተሰብ ወይም በሙያ ሂደት የተከሰቱ የጤና እና የተለያዩ አካላዊ ወይም የሥነ ልቦናዊ ችግሮችን ወደ በጎ አድራጎት ድርጅቶች መመሥረቻ አጋጣሚና ምክንያትነት በመቀየር ለብዙ ሰዎች ችግር መፍትሔ በመሆን ተገቢ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ያደረጉ ናቸው።

እነዚህ ድርጅቶች በሂደትም ትልቅ ሀገራዊ ተቋም ወደ መሆን እየደረሱ ለማህበረሰቡም አገልግሎት ሲሰጡ ማየት ትልቅ እርካታን ይፈጥራል። ለዚህ ምሳሌ ከሚሆኑት አንዱ መቄዶኒያ የአረጋውያን መርጃ ማህበር ሲሆን፣ ድርጅቱ አገልግሎቱን እያሰፋ መጥቶ በበርካታ የኢትዮጵያ ከተሞች ተመሣሣይ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በሙያቸው በሥራ አጋጣሚዎች በተመለከቷቸው የበርካታ ሕፃናት ችግሮች ተነሳስተው እንደ ኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ማህበር ዓይነት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን እስከ መመሥረት የደረሱም ጥቂት አይደሉም።

በተመሳሳይ ከቅርበት በሙያ ሁኔታ ከሚገጠሙ የሰዎች ችግሮች የተነሳ ከውስጥ ከሚመነጭ በጎ መነሳሳት በጎ አድራጎት ድርጅቶችን የመሠረቱ በርካታ ናቸው። በጤና ችግር ምክንያት ተመሣሣይ ችግር ላላባቸው የማህበረሰቡ አካላት ተደራሽ የሆኑ በጎ አድራጎት ድርጅቶችም በዚህ መልኩ ተመሥርተው ብዙ አስታዋሽ ያጡትን እና የተቸገሩትን ደግፈዋል፤ እየደገፉም ይገኛሉ።

በቅርቡም ሄዋን የሴቶች የጤና ድጋፍ በጎ አድራጎት ድርጅት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም የማህጸንና የጽንስ ህክምና ባለሙያዎች አማካይነት ተመስርቷል፡፡ ማህበሩ ‹‹የሴቶችን ጤና መደገፍ ማህበረሰብን መደገፍ ነው›› በሚል መነሻ በጤናው ዘርፍ የበርካታ እናቶችን ችግሮች ለመፍታት በማለም የተቋቋመ ነው።

የዚህ በጎ አድራጎት ድርጅት ምሥረታ መነሻ ያደረገውም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የሚመጡ እናቶች በመድኃኒት መግዣ የገንዘብ ችግር ምክንያት ተመላልሰው መታከም ያልቻሉ፣ የመጠለያ ወጪ እና ሌሎችም የኢኮኖሚ ችግሮች ያለባቸውን እናቶች ወጪ የጤና ባለሙያዎቹ ይሸፍኑ የነበረበት ሁኔታ ነው።

የጤና ባለሙያዎቹ በዚህም መታከሚያ ለሌላቸው ታካሚዎች ወጪ ከመሸፈን አንስቶ የሕክምና ርዳታ መስጠትና መሰል በጎ ተግባሮችን እያከወኑ ይገኛሉ። ወደ ሆስፒታል መጥተው መታከም ለማይችሉ ታማሚዎች ቦታው ድረስ እየሄዱ የሕክምና አገልግሎትም ሲሰጡ ቆይተዋል። ከሚሰሩበት ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በተጨማሪ በምኒልክ እና ራስ ደስታ ሆስፒታል የሚገኙ በማህጸን እና ጽንስ ክፍል የሚገኙ ታካሚዎችንም ለመርዳት እየሠሩ ነው።

ከዚህ ባሻገር ታካሚዎቹ ሲታመሙም ብቻ ሳይሆን ሕመም ከመከሰቱ በፊት ቅድመ ምርመራ ያደርጋሉ። በተለይም እንደ የማህጸን ካንሰር ቅድመ ምርመራ ያሉ ቅድመ ጥንቃቄን የሚፈልጉ ሕመሞች ላይ ይሠራሉ። ለወደፊት እንደ ዕቅድ ያሰቡት በሪፈር የሚመጡ ታካሚዎች በቀጠሮ ወቅት ከሚደርስባቸው ተጨማሪ ወጪ እና እንግልት ለመታደግ የመቆያ ሕንፃ ገንብቶ የሚቆዩበትን ሁኔታ ማመቻቸትን ያካተተ ነው።

ማህበሩ ወደ ሆስፒታል ሄደው ተገቢ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት ላልቻሉ እና ሕክምናቸውን ለመከታተል የአቅም ውስንነት ላለባቸው እናቶችም ተደራሽ የማድረግ አቅም እንደሚፈጥር ተስፋ የተደረገበት ነው። በተለይ እናቶች ከወለዱ በኋላ በሚታረሱበት ሰዓት ላይ ኮሪደር ላይ መሆን የለባቸውም በሚል በሀገር ደረጃ የእናቶች በቂ ማቆያ መኖር እንዳለበት ታሳቢ አድርጓል ድርጅቱ።

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ የማህጸን እና የጽንስ ትምህርት ክፍል የጤና አገልግሎት ምክትል ኃላፊ እና የሄዋን በጎ አድራጎት ድርጀት የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ለሚ በላይ የሄዋን (“He­Wan”) በጎ አድራጎት ድርጅት አመሠራረት ሲያስረዱ እንዳብራሩት፤ ለሚ የሄዋን በጎ አድራጎት ድርጅት ለምስረታው ዋነኛው ምክንያት የሆነው በተለያዩ የጤና ሕክምና ጉዳይ ወደ ሆስፒታሉ ከሚመጡ እናቶች መካከል የሕክምና ወጪያቸውን መሸፈን አቅቷቸው ሕክምናቸውን የሚያቋርጡ መኖራቸው ነው።

በተለይም ለወሊድ፣ ለማህጸን ሕክምናዎች፣ ለካንሰር ሕክምና ጭምር ወደ ሆስፒታሉ ሲመጡ የሕክምና ወጪያቸውን መሸፈን አቅቷቸው ሕክምናቸውን የሚያቋርጡ እናቶች እና እህቶች ነበሩ። ይህንን ያስተዋሉ በሆስፒታሉ የሚገኙ የተወሰኑ ዶክተሮች የሕክምና አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት እነዚህን ታካሚዎች ለመደገፍ መነጋገር ይጀምራሉ።

ዶክተር ለሚ በላይ እንደሚያስታውሱትም የተለያዩ ታካሚዎችን ታክመው ሲወጡም መጠየቅ መርዳት የሚፈልጉ ሰዎች ስላሉም እነሱንም ለማገናኘት ጭምር በማሰብ ከሶስት ዓመት በፊት በተለይ ሰባት ዶክተሮች በመሆን በዋትስአፕ ግሩፕ የታማሚዎች ፈንድ ኮሚቴ ተፈጠረ። ይህም ከዚህ አንፃር ያለውን ክፍተት ለማቀናጀት በሚል እሳቤ የተጀመረ ነው። በዚህ ሁኔታ እየተሠራም ከሁለት ዓመት በፊት የቴሌግራም ግሩፕ በመክፈት በማህበራዊ ተሳትፎ የሚያደርጉ ተማሪዎችን ጭምር ማሳተፍ ተጀመረ።

ለካንሰር ታካሚዎችም የተለያዩ ገቢዎችን የማሰባሰብ ሂደት ነበር። አብዛኛው ታማሚ የኬሞ ሕክምናውን ለማድረግ አቅም የሌለው በመሆኑ፣ ከክፍለ ሀገር መጥቶ፣ አልጋ ይዞ፣ ለማረፊያ የሚያወጣቸው ወጪዎችም ስላሉ እነዚህንም ለመርዳት የፋካልቲውም እንቅስቃሴ ነበረ። በሂደትም ይህን ሥራ አንድ ላይ ለማድረግ ከተማሪዎች ጋር በመወያየት ወደ አንድ በማምጣት አደረጃጀት ተሰጠው።

ሁሉም ሰው በየወሩ ምን ያህል ማዋጣት እንደሚችል ፊርማ /ፒቲሽን/ ተሰበሰበ፤ ሁሉም ሰው ማዋጣት የሚችለውን ያህል በመፈረም ከገለጸ በኋላም ለፋይናንስ የተላለፈ ሲሆን ይህም ብር በቀጥታ ተቆራጭ ሆኖ በጋራ አካውንት በየወሩ ገቢ ይሆናል። በዚህም ዶክተሮቹን ጨምሮ ነርሶችና የህክምና ተማሪዎች ሳይቀሩ ገንዘብ አሰባስበው መደበኛ ባልሆነ መንገድ ድጋፍ ማድረግ ይጀምራሉ።

በሆስፒታሉ ያሉ የጤና ባለሙያዎች እና የማህጸን እና የጽንስ ትምህርት ክፍል የጋራ አካውንት በመክፈትም በየወሩ መዋጮ ማድረግ ይጀምራሉ። በዚህ ሂደት ገንዘብ በመሰብሰብ ድጋፍ የማድረግ ሥራ መጀመሩን ያስታወሳሉ። ከዚህ ላይ በመውሰድም ለትራንስፖርት ለመድኃኒት ክፍያ ለመሳሰሉት ድጋፍ ሲደረግ ቆይቷል።

እዚህ ያለውን ታካሚ ብቻ መርዳቱ በቂ አለመሆኑን በመረዳት በተለይ የካንሰር ታካሚዎች ችግሩ ወደ በሽታ ደረጃ ደርሶ የተወሳሰበ ሕክምና ደረጃ ላይ እንዳይደርስ ማድረግ ይቻላል በሚል መሥራትም ተጀመረ ሲሉ ያብራራሉ።

ከዚህ ሆስፒታል ውጭም ድጋፉን ሰፋ በማድረግ ብዙዎችን መርዳት ይቻላል የሚል ጥያቄ መነሳት ይጀምራል። እናቶች ከወለዱ በኋላም የጨቅላ ሕፃናት ሕክምና አልጋ ከተሰጣቸው በኋላ ልጆቻቸውን ለሚያሳክሙት ያሉት ውስን አልጋዎች ወዲያው የሚሞሉ በመሆኑ ማቆያ ቦታዎች፣ በሆስፒታሉም በማህበረሰቡ ውስጥ በሚቻለው ደረጃ የድጋፍ አድማሱን ለማስፋት ሄዋን የተመሠረተ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህ ሂደት የተጀመረው ይህ እንቅስቃሴ በሕጋዊ ማዕቀፍ ስር ሆኖ በኢትዮጵያ የሲቪልና በጎ አድራጎት አደረጃጀት ሥር በበጎ አድራጎት ድርጅትነት ፍቃድ ተሰጦት በይፋ መመሥረቱንም ገልጸዋል።

የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ለሚ በላይ የሌሎችንም ድጋፍ ለማግኘት እና ገቢ ማሰባሰብም እንዲቻል እና የድጋፍ አድማሱንም ለማስፋት በሚል መነሻ ሄዋን የበጎ አድራጎት ወደ መመስረት የመጣ መሆኑን አመላክተዋል። የድርጅቱ አደረጃጀቱም ሰባት የቦርድ አባላት እንዳሉት ጠቅሰው፣ ከተለያዩ ድርጅቶች እና ከመንግሥት አካላት ጋር በመሆን አድማሱን ለማስፋት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ጠቁመዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ የድርጅቱ ዋነኛ ተልዕኮ ሴቶች በጤና ችግር ምክንያት ሕይወታቸው መገደብ የለበትም። ገንዘብ ስላጡ ደግሞ ሕክምና ማጣት የለባቸውም። በተመሳሳይም የትምህርት ደረጃቸው ወይም ግንዛቤ በማጣታቸው ምክንያት መጎዳት የለባቸውም።

በመሆኑም በሆስፒታል እና ከሆስፒታል ውጭ ሥራዎች ይሰራሉ። በሆስፒታል ውስጥ በሚሠሩ ነገሮች ሁለንተናዊ ጤና፣ በቁሳቁስ መታገዝ አለባቸው። ሌላው አንዱ ማየት የተቻለው ችግርም እናቶች ከወለዱ በኋላ ልጆቻቸው ማሞቂያ ከገቡ በኋላ ማቆያ ቦታ የሌላቸው መሆኑ ነው። ለእዚህም ከጳውሎስ ሆስፒታል አስተዳደር ጋር በመነጋገር የተጀመረ ሂደት መኖሩንም ገልጸዋል። የተለያዩ ድርጅቶችም በዚህ ላይ ድጋፍ እንዲያደርጉ እና በሆስፒታሉ ግቢ ባሉ ሕንፃዎች ላይ ማሻሻያዎች ተደርገው የእነዚህ እናቶች ማቆያ ቦታዎች እንዲዘጋጁ እየተሄደበት ነው ብለዋል።

እነዚህ ሥራዎች በጳውሎስ ሆስፒታል ብቻ በመሥራት ውጤት እንደማይመጣም ጠቅሰው፣ በሀገር ደረጃም በተለያዩ ሆስፒታሎች የእነዚህ የእናቶች ማቆያ መኖር አለበት ይላሉ። እናቶች ከወለዱ በኋላ በሚታረሱበት ሰዓት ላይ ኮሪደር ላይ መሆን የለባቸውም። መንግሥትም እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ብዙ እንቅስቃሴ እያደረገ ቢሆንም፣ በጤና ጥበቃ ብቻ ችግሮቹ የማይፈቱ በመሆኑም የተለያዩ ድርጅቶች ተጋግዘው መሥራት አለባቸው ሲሉም አመልክተዋል።

ድርጅቱ እንደ ራዕይ የያዘው አንዱ በግንዛቤ ማጣት ምክንያት እናቶች በተለያዩ ችግሮች መጎዳት የለባቸውም። ይሄንንም የተለያዩ ትምህርታዊነት ያላቸው ፕሮግራሞች በማዘጋጀት ማህበረሰቡ ግንዛቤ እንዲያገኝ መሠራት አለበት ብለዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ አሁን ላይ ከጡት ካንሰር ቀጥሎ እናቶች እየተቸገሩበት ያለው የማህጸን በር ካንሰር ነው። በየጊዜው ምርመራዎችን በማድረግ ይሄ እንዳይሆን ማድረግ ይቻላል። በኢትዮጵያ ደረጃም ሲታይ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር የቅድም ምርመራ ያደረጉ ሴቶች እና እናቶች በጣም አነስተኛ ቁጥር እንዳላቸው ጠቅሰው፣ በመሆኑም ትምህርታዊ የሆኑ መሰል የጤና ችግሮች ላይ ተገቢ ግንዛቤ መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡ ፡ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋርም የማህጸን በር ጫፍ ቅድመ ካንሰር መከላከል ምርመራዎች በሰፊው እንዲሠሩ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

ዶክተር ለሚ በላይ እንደገለጹት፤ የሴቶችን ጤና ለማበልፀግ በሚረዱ የተለያዩ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ላይም ከተለያዩ ባለሥልጣናት እና ባለድርሻ አካላት ጋር ይሠራል። በበጎ አድራጎት ድርጅቱ ውስጥ ያሉትም በርካታ ጥናትና ምርምሮችን የሚያደርጉ ኤክስፐርቶች ይገኛሉ፡፡ ከጳውሎስ ሆስፒታል ውጭም ካሉት የባለሙያ ስብስቦች ጋር በመሆንም የፖሊሲ አቅጣጫዎች ሲያስፈልጉ ማሻሻያዎችንም በጋራ ለመሥራት ታቅዷል።

ድርጅቱ እነዚህን ሁኔታዎች ተደራሽ ለማድረግ ሰፋ ያለ እቅድ ተይዞ የተመሠረተ መሆኑን አስገንዝበዋል። ድርጅቱ በሊደርሺፕ አካዳሚ፣ የተለያዩ የማገገሚያ ማዕከላትንም ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመሆን ለመሥራት ተነሳሽነቱን ይዞ የተቋቋመ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የቦርድ ሰብሳቢው ዶክተር ለሚ እንደሚሉት፤ ድርጅቱ የሰነቀውን ዓላማ ከግብ ለማድረስም ከመንግሥት በጀት መጠበቅ አያስኬድም፤ በሴቶች ጤና ላይ የሚሠሩ የተለያዩ ድርጅቶችን አጋር በማድረግ ይሠራል። በከተማዋ የሚገኙ በሆቴል ዘርፍ የሚሠሩ፣ በጤናም ዘርፍ የሚሠሩና የተለያዩ በሕክምናው ዘርፍ ላይ ያሉ ባለሀብቶችንም በማሳተፍ ይሠራል።

በተመሳሳይም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ለማሳተፍ የሚያስችለውን እና የጎ ፈንድሚ ለማስከፈትም ጥረት መጀመሩን አመላከተዋል። በረጅም ጊዜ እቅዱም የሴቶችን የጤና ችግሮች ለመቅረፍ በሚያስችል ቁመና ላይ እንዲደርስ የራሱን ገቢ የሚያመነጭ ሀገር በቀል ድርጅት እንዲሆንም አቅዶ እየሠራ ነው ብለዋል።

ድርጀቱ በአጭር ጊዜ አቅዱ በጳውሎስ ሆስፒታል ለሕክምና ለወሊድ የሚመጡ እናቶችን መደገፍ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሲሆን፣ በረጅም ጊዜ እቅዱም ወደ ሌሎች ሆስፒታሎች በማስፋት በስፋት እናቶችን እና ሴቶችን ተደራሽ ያደርጋል። ይህንን ዓላማ እና ራዕይ ለመደገፍ ሃሳቡ ያላቸው በሕክምናው ባሉ ሙያዎች ሳይገደቡ በሌሎችም ሙያዎች ላይ ያሉት በጎ አድራጊ ኢትዮጵያውያንን እገዛ ለመቀበል ድርጅቱ በሩ ክፍት መሆን አመላክተዋል።

ከሴቶች እና ከእናቶች የቅድመ ካንሰር መከላከል ምርመራ ውጭ እንደ መቄዶኒያ ያሉ ማህበረሰቡ ውስጥ የተለያዩ ማቆያ ቦታዎች ላይ በመገኘትም በዓመት አንድ ጊዜ የጤና ምርመራ ማድረግ የድርጅቱ ሌላኛው ዓላማ መሆኑንም ጠቁመዋል። ከዚህም ወጪ አቅሙ እያደገ ሲሄድም የተገደበ የማህበረሰብ ክፍል ሳይኖር ሁሉንም ለመደገፍ ይሠራል ሲሉ ጠቅሰው፣ ይሄንን ራዕይ እና ተልዕኮ በመረዳት የተለያዩ የመርዳት አቅሙ እና ፍላጎቱ ያላቸው አሁን ላይ ጳውሎስ ሆስፒታል በሚገኘው ቢሮው እና በዌብሳይቱ በኩል ድርጅቱን ማግኘት እንደሚችሉም አስታውቀዋል። ሴቶችንና እናቶችን በጋራ እንርዳ፣ እናግዝ ሲሉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You