ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው። ያለ ሰላም ወጥቶ መግባት፣ ዘርቶ መቃምም ሆነ ወልዶ መሳም፣ ማሳደግ፣ ወዘተ አይቻልም። ልማት ብቻ አይደለም ሰላምን የሚፈልገው። እዬዬም ሲዳላ ነው እንዲሉ ለመከራ ወቅትም ቢሆን ሰላም ወሳኝ ነው።
ሰላም ሕይወት ላለው አካል ብቻ ሳይሆን ለግዑዙም ጭምር ወሳኝ ነው። ስትንፋስ ያለው ሁሉ ሰላምን በእጅጉ እንደሚፈልገው ሁሉ፣ የማይተነፍስ፣ የማይንቀሳቀሰው ግዑዙም እንዳማረበት ለመቆየት ሰላም የግድ ያስፈልገዋል።
ከምንም በላይ ወሳኝ ለሆነው ሰላም ዘላቂነት ሰርክ፣ ሌት ተቀን ሊሠራ ይገባል። ሰላም አንድ ጊዜ ተሠርቶ የሚያበቃ ሳይሆን የእድሜ ልክ ሥራ መሆኑን መገንዘብ ያሻል። ከዚህም ባሻገር ሰላም የሚመጣው በመንግሥት ወይም በፀጥታ ኃይሎች ብቻ እንዳልሆነ መረዳትም ብልህነት ነው።
ሰው እንደገባው መጠን ለመኖር ከፈለገ እና ካመነበት ሰላምን ሁሉጊዜም ሊንከባከባት ይገባዋል። እሱም ሰላምን ከሚያደፈርሱ ተግባራት መታቀብ ይኖርበታል።
ይሁንና ሰላም ያላትን ይህን ሁሉ ዋጋ ያህል ትኩረት የሰጠናት አይመስልም። ሰላም የመጠበቁን ሥራ ለሌላ አካል ሰጥተን እጃችንን አጣጥፈን የተቀመጥን ጥቂት አይደለንም። ይህ ግዴለሽነት ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል።
ለሰላም መደፍረስ ምክንያቱ ብዙ ነው፤ ጦርነትና ግጭት ዋናዎቹ ጉዳዮች ቢሆኑም ለፀጥታ ችግር መነሻ የሚሆኑ ሌሎች ምክንያቶችም ሊጠቀሱ ይችላሉ። ጦርነትና ግጭት ተንቀሳቅሶ ለመሥራት እንቅፋት ይሆናሉ። እነዚህንና የመሳሰሉትን ምክንያቶች ተገን ያደረጉ አካላትም ሌሎች የሰላም ጸሮች ናቸው። ይህ ሁሉ ሲደራረብ የሰላም መታጣቱ መባባሱና ወደ ከፍተኛ ቀውስ ሊያመራ ስለመቻሉ የተለየ ጥናት ማድረግ አይጠይቅም።
በሰላም እጦት ሳቢያ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ይፈናቀላሉ፤ ይሰደዳሉ፤ አለፍ ሲልም ሕይወታቸውን በአሰቃቂ ሁኔታ ጭምር ሊያጡ ይችላሉ። ብቻ የሰላም እጦት መዘዙ ብዙ ነው።
ባለፉት ዓመታት በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ከታየው የሰላም እጦት ይህን እውነታ ተመልክተናል። በሰላም እጦት ሳቢያ አያሌ ዜጎች ከሞቀ ቤታቸው ተፈናቅለው፣ ለምግብ እጦትና ለአካል ጉዳት ተዳርገው፣ የልማት ተቋማትና መሠረተ ልማቶች ወድመው፣ ወዘተ አይተናል።
በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው እገታ፣ በታጋቾች ላይ እየተፈጸመ ያለው ግድያ፣ ቤተሰቦቻቸውን ዘመድ ወዳጆቻቸውን ጭምር ለማይገባ ወጪ እየዳረገ ያለው ይህ ሕገወጥ ተግባር የሰላም እጦቱ አንድ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
በሀገራችን ስለእገታም ሆነ አፈና ይሰማ የነበረው በርቀት ነበር። በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን አማካይነት “እከሌ የሚባለው ባለሀብት ወይም ዝነኛ ታገተ” በሚል የሚነገረውን የሌላውን ሀገር ዜና ከመስማት ባለፈ በእኛ ሀገር ተከስቶ አስተውለን አናውቅም ነበር።
የእገታ አይነት ከሀገር ሀገር ፣ ከአጋች አጋች ማንነት ይለያያል። አንዳንዶች ለገንዘብ ፍለጋ ይፈጸሙታል፤ አንዳንዶች ደግሞ ለፖለቲካ አላማ ይፈጽሙታል፤ አንዳንዶች ስማቸውን ከፍ አድርገው ለማሰማት ሲሉም ይፈጽሙታል። ለበቀል ሲባልም ይፈጸማል፤ አስገድዶ ለመድፈር ወይም ለግድያ ጭምር ሊሆን ይችላል።
የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያስረዱት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ እገታ/አፈና ከሚካሔድባቸው ሀገራት መካከል ግንባር ቀደሟ ቱርክ ናት፤ ከአህጉራችን ደግሞ ደቡብ አፍሪካ ስድስተኛውን ደረጃ ይዛለች።
የሀገራችንንም ሰላም ዘላቂ ማድረግ ላይ እስካልሠራን ድረስ ትናንት በሩቅ የሰማናቸው የእገታ ዜናዎች ዛሬ የእኛ መገለጫዎች መሆናቸው አይቀርም። አሁን በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ይህን ችግር እየተመለከትን ነው። አበው ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ ችግሩ ከእስከ አሁኑም በበለጠ ስር ሳይሰድ ከወዲሁ በጋራም በግልም እልባት ልንፈልግለት ይገባል።
በኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ በተለያዩ ምክንያቶች እገታዎች ሊፈጸሙ ቢችሉም፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተፈጸመ ላለው እገታ ምክንያቱ የሰላም እጦቱ ነው የሚል እምነት አለኝ። እገታውን ፀረ ሰላሞች ለፖለቲካ አላማ ሲሉ የሚፈጽሙት ሊሆን ይችላል። ለዘረፋ ሲሉ የሚያግቱም ይኖራሉ።
ሰዎችን በማገት በመቶ ሺዎች ገንዘብ መጠየቅና ተቀብሎ ታጋቾችን መልቀቅ በተደጋጋሚ እየታየ ነውና። በሌላ በኩል ደግሞ ግር ግር ለሌባ ይመቻል እንዲሉ ነፍጥ ያነገበ ሁሉ እየተነሳ አጋች የሆነበት ሁኔታም እንዳለ ይሰማኛል። በሕዝብ ስም እየማለ፤ ሕዝቤን ነጻ አወጣለሁ የሚሉ አንዳንድ አካላት ዛሬ እገታን የጥፋት ተግባሩ መሳሪያ አድርገውታል።
አሁን አሁን ከአጋቾቹ ዘንድ በስፋት እየተሰማ ያለው “ይህን ያህል ብር አምጡ” የሚል ነው። ዘመድ አዝማድ ገንዘብ አሰባስቦ ታጋቹን እያስለቀቀ መሆኑም ይሰማል። ለራሱ የሚላስ የሚቀመስ የሌለው ከሆነና የተባለውን ብር የማያገኝ ከሆነ ደግሞ “ታጋቹን ለማስለቀቅ ቸልተኝነት ታይቶበታል” በሚል የታጋቹን ሕይወት የሚቀሙም እንዳሉ ይገለጻል።
ታጋችን ለማስለቀቅ ቆላ ደጋ የሚለው አካልም ምናልባትም ለታጋቹ ማስለቀቂያ የተጠየቀውን ገንዘብ በሕይወት ዘመኑ ቆጥሮት አይደለም ሰምቶት የማያውቀውን መጠን ስለሚሆን በሀዘን ከመቆራመድ ያለፈ እጣ አይኖረውም።
ሰዎች ላለመታገት በሚል ካሉበት አካባቢ ብዙ ርቀት ከመሄድ የተቆጠቡበት ሁኔታ ይታያል። ስጋቶች አሉ። መንግሥትም ችግሩን ከስሩ ለማድረቅ የፀጥታ ኃይሉን በማሰማራት እየሠራ ይገኛል። የፀጥታ ማስከበር ሥራዎቹ ተጠናክረው መቀጠላቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎችም እየወጡ ናቸው። በዚህ ጉዳይ ከሚጠረጠሩት መካከል በርካታ ታጣቂዎች እጃቸውን እየሰጡ ስለመሆናቸው እየተገለጸ ነው።
የፀጥታ ኃይሉ እገታ ተፈጸመ በተባለበት ስፍራ ደርሶ የአጋቾችን ማንነት በመከታተል ወደፍርድ ያመጣቸው እንዳሉ ይታወቃል፤ ሰላምን ለማምጣት እያካሄዳቸው የሚገኙ ሥራዎችና እየተገኙ ያሉ ውጤቶች ችግሩ ችግር ሆኖ ብዙም እንደማይቀጥል ያመላክታል።
ይህ ሁኔታ የአጋቾቹ ምሽግ እየተደረመሰ መሆኑን ይጠቁማል። የፀጥታ ኃይሉን ውጤታማ ተግባር ያመለክታል። ችግሩ በየቤታችን ገብቶ ሲያሳስበን የቆየን በሙሉ ይህ የፀጥታ ኃይሉ እርምጃ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን የድርሻችንን መወጣት ይኖርብናል።
በአጋቾቹ ሲፈጸም የቆየው እንዲህ አይነቱ ሰቆቃ ሰላም የማያሳጣው የኅብረተሰብ ክፍል የለም፤ አንድ ምንም የማያውቅ ሕፃን ወይም ባለሀብት ወይም ደግሞ ገንዘብ ያስገኛል የተባለ ግለሰብም ሆነ አንድ ፖለቲከኛ ታገተ ሲባል ታጋቹን የሚጠብቀው አደጋ እንደተጠበቀ ሆኖ የታጋቹ ወገኖች ሁሉ የሚያጋጥማቸውን ፈተና ቤታቸው ይቁጠረው ብሎ መተው ይሻላል።
ይህ ድርጊት የሀገራችንን ገጽታ በእጅጉ የሚያበላሽ አስጸያፊ ተግባር ነው። ከኢትዮጵያውያን ማንነት፤ ሥነ ምግባርና እሴት በተቃራኒ አጋች ነን ባዮች እየፈጸሙት ያለው ተግባር ሁላችንንም ሊያስቆጣን ይገባል፤ ይህ ብቻ አይደለም፤ የድርጊቱ ፈጻሚዎች፣ ደጋፊዎች ሁሉ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድባቸው ለማድረግ የበኩላችንን ማድረግ አለብን።
የመንግሥት እርምጃ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ የሕዝቡ ትብብር ወሳኝ ሚና ይኖረዋል። መንግሥት አጋቾቹን አንድ በአንድ እየለቀመ ወደፍርድ ሊያመጣቸው የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል ተብሎ አይገመትም፤ አጋቾቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሕዝቡ ትብብር ያስፈልጋል። ሕዝብ ያላጋለጠውን የፀጥታ አካል ብቻውን በቁጥጥር ስር ሊያውለው ይቸገራል።
ጉዳዩ እየከፋ እንደመሄዱ ኃላፊነቱን ለመንግሥት ወይም ለፀጥታ አስከባሪ ብቻ ሰጥቶ መቀመጥ አይገባም። መንግሥት ብዙዎቹን ወደፍርድ እንዳመጣው ሁሉ አሁንም የሕዝብን ሰላም ለማስጠበቅ ሲል ለአጋቾች ምቹ ሁኔታ ለፈጠረው የዘላቂ ሰላም እጦት መፍትሄ ለማምጣት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራቱን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
ሀገሪቱ በልማት ጎዳና እየተጓዘች ትገኛለች፤ ዜጎች ምርታማነት እንዲያድግ ምጣኔ ሀብት እንዲጎለብት፣ ወዘተ. እየሠሩ ናቸው። በአንጻሩ ፀረ ሰላሞች ደግሞ የዚህ ልማት አረም ሆነው የጥፋት አላማቸውን ማራመዳቸውን ቀጥለዋል። እነዚህ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የታየውን የሰላም መደፍረስ ተገን አድርገው የሚንቀሳቀሱ አረሞች ነቅሎ ማስወገድ የሚቻለው የኅብረተሰቡ የነቃ ትብብር እና ተሳትፎ ሲታከልበት ነው። በየስርቻው የተደበቁ አጋቾችን ማጽዳት የሚቻለው ኅብረተሰቡ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በእነዚህ አረሞች ላይ ሲያረጋግጥ ጭምር ነው።
ወጋሶ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 11 ቀን 2016 ዓ.ም