ዩናይትድ ስቴትስ እና የአውሮፓ ኅብረት፤ እስራኤል ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ኢራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ለመጣል እየተሰናዱ ነው።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ጃኔት የለን “በሚቀጥሉት ቀናት” ርምጃ እንወስዳለን ሲሉ የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊስ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል ደግሞ ኅብረቱ ማዕቅብ ለመጣል እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
እስራኤል አጋሮቿ የኢራን የሚሳዔል ፕሮግራም ላይ ማዕቀብ እንዲጥሉ ጠይቃለች።
የተባበሩት መንግሥታት የኢራን የሚሳዔል ፕሮግራም ላይ የጣለው ማዕቀብ ባለፈው ጥቅምት ጊዜው አብቅቷል።
እነዚህ ማዕቀቦች የሚጣሉት የኢራንን የኒውክሌር ፕሮግራም ለመግታት ነው የሚሉ ሃሳቦች ከፖለቲካ ተንታኞች ዘንድ ይሰማሉ።
አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ኢራን ላይ የተለያዩ ማዕቀቦች ከዚህ ቀደም መጣላቸው አይዘነጋም።
የእስራኤል ጦር ሠራዊት ኤታማዦር ሹም ሌተናንት ጄኔራል ሄርዚ ሀሌቪ ባለፈው ሰኞ በሰጡት አስተያየት ኢራን ያደረሰችው ጥቃት ምላሽ ሳያገኝ አያልፍም የሚል አስተያየት ሰጥተው ነበር።
ኢራን ባለፈው ቅዳሜ ለመጀመሪያ ጊዜ እስራኤል ላይ ቀጥተኛ ጥቃት ባደረሰችበት ወቅት 300 ሚሳዔሎችና ድሮኖች ከራሷ ክልል፣ ከኢራቅ፣ ሶሪያ እና የመን አስወንጭፋለች። አብዛኛዎቹ ሚሳዔሎች እና ድሮኖች በእስራኤል እና አጋሮቿ ዒላማቸውን ሳይመቱ እንዲከሽፉ ተደርገዋል።
ቴህራን እንዳለችው ጥቃቱን የሰነዘረችው እስራኤል፤ ሶሪያ በሚገኘው ቆንስላዋ ላይ ጥቃት አድርሳ 13 ሰዎችን ለገደለችበት ጥቃት አፀፋውን ለመመለስ ነው።
እስራኤል ለደረሰባት ጥቃት እስካሁን ቀጥተኛ ምላሽ አልሰጠችም። በምትኩ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ኢራንን ለማሽመድመድ እየሠራች ትገኛለች። እስራኤል 30 የሚሆኑ አጋር ሀገሮች የኢራን የሚሳዔል ፕሮግራም ላይ ማዕቀብ እንዲጥሉ ጠይቃለች።
አልፎም እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ (ኢስላሚክ ሪቮሎሺናሪ ጋርድ ኮር) የተባለው የኢራን ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ኃይል ሽብርተኛ ተብሎ እንዲፈረጅ ጠይቃለች። አሜሪካ ከዚህ ቀደም ቡድኑን ሽብርተኛ ብትልም ዩኬ ይህን ከማድረግ ተቆጥባለች።
ማክሰኞ ዕለት ንግግር ያደረጉት የአሜሪካ ግምጃ ቤት ሚኒስትር የለን “በሚቀጥሉት ቀናት ኢራን ላይ ማዕቀብ እንደምንጥል ይጠበቃል” ብለዋል።
ሚኒስትሯ አክለው ኢራን ወደ ውጭ የምትልከው ነዳጅ “ምናልባት የምናየው ይሆናል” ካሉ በኋላ “ኢራንም አሁንም በግልፅ ነዳጅ እየሸጠች ነው፤ ስለዚህ ጉዳይ የምናደርገው ነገር ይኖራል” ሲሉ ማዕቀቡ ምን ላይ እንደሚያተኩር ጠቁመዋል።
የለን፤ ኢራን ከሀገር ውጭ ያሉ ቡድኖችን በገንዘብ እንዳትደጉም እንዲሁም ሩሲያ ዩክሬን ላይ ያወጀችውን ጦርነት እንዳትደግፍ ለማድረግ የገንዘብ ዕቀባ መደረጉን አውስተዋል።
500 ሰዎች እና ኩባንያዎች በአሜሪካ ማዕቀብ እንደተጣለባቸው ይታወቃል። አሜሪካ ኢራን ላይ በጣለችው ማዕቀብ መሠረት ሁለቱ ሀገራት ምንም ዓይነት ንግድ አያከናውኑም።
የአሜሪካው ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን ሀገራቸው ልትጥል ያሰበችው አዲስ ማዕቀብ የኢራንን “የሚሳዔል እና ድሮን ፕሮግራም” እንዲሁም አብዮታዊውን ዘብ እና መከላከያ ሚኒስትሩን የሚመለከት ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊስ ኃላፊው ቦሬል ደግሞ አንዳንድ የሕብረቱ ሀገራት ኢራን ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ጠይቀዋል ብለዋል።
ቦሬል አክለው የሀገራቱ ጥያቄ ወደ ሕብረቱ ዲፕሎማሲ አገልግሎት ተልኮ “አስፈላጊው ሥራ” ተጀምሯል ብለዋል። የዓለም ሀገራት በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው አለመረጋጋት የበለጠ እንዳይስፋፋ ኢራን ላይ ማዕቀብ መጣል አስፈላጊ ነው ይላሉ።
ለእስራኤል ያላቸው ድጋፍ “ከብረት የጠነከረ” እንደሆነ የተናገሩት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እስራኤል ድል አውጃ “ማሸነፏን እንድትቀበል” አሳስበዋል።
የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ደግሞ ከእስራኤሉ አቻቸው ኔታኒያሁ ጋር ማክሰኞ ምሽት ባደረጉት የስልክ ልውውጥ እስራኤል ምላሽ ለመስጠት በሚል በቀጣናው የበለጠ አለመረጋጋት እንዳትፈጥር አስጠንቅቀዋል። ኢራን፤ እስራኤል ምላሽ እስካልሰጠች ድረስ ሁኔታው “ተቋጭቷል” ብላለች።
የኢራኑ ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራይሲ “ማንኛውም የኢራንን ፍላጎት ሊነካ የሚችል ነገር ላይ የሚደርስ ጥቃት አፀፋው በጣም የከፋና ስቃይ የበዛበት ሊሆን ይችላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የኢራን አጋር የሆነችው ሩሲያም በቀጣናው መረጋጋት እንዲመጣ የጠየቀች ሲሆን፤ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከፕሬዚዳንት ራይሲ ጋር ባደረጉት የስልክ ልውውጥ ሁኔታው ቀዝቀዝ እንዲል መጠየቃቸውን ክሬምሊን አስታውቋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም