በጉንጉን ስብጥርጥር

እንቆቅልህ! ብትሉኝ፤ እኔም ምናውቅ… ብል፤ የእንቆቅልሻችሁን ምላሽ ግን ባውቅም አልነግራችሁ! ምክንያቱም “ሀገር ስጠኝ” እስክትሉኝ ጠብቄ ሀገር ልሰጣችሁ እፈልጋለሁና።

ታዲያ ግን የምሰጣችሁ ማንን እንደሆነ ከገመታችሁ ዘንድ ልንገራችሁ… ያቺን የጉንጉን መሶብ፤ ማጀቴን ልሰጣችሁ ወስኛለሁ።

ምን አለ ከማጀቴ? ካላችሁኝ፤ በእግዜር እጆች በተፈጥሮ ቀለማት በተነከረው የማጀቴ እንብርት ላይ፤ ከጥበብ ብዕር በቆመ ካስማ፤ በምናብ ከተሰናሰነ ወጋግራ፤ በክዋክብትና በብርሃን ጸዳል የቆመች አንዲት ዓለም ተገኝታለች። እሷም “ጉንጉን” ትባላለች፤ እዚያ…ጉንጉን አበባ፤ ጉንጉን ሕይወት፤ ጉንጉን ማንነት፤ የተጎነጎኑ የምናቡ ዓለም የሕይወት ገጸ በረከቶች አሉና ይዘን እንመለሳለን።

ለጉብኝቱ አንዳችም ሃሳብ እንዳይገባችሁ፤ እኔ አለሁና ከጉንጉን ጥበበ ሠሪ፤ ከምናብ ጌታው መድረሻ ማዳረሻውን እቀበላለሁ። መሄዱን ለመረጣችሁም መንገዱ እሩቅ አይደለም። ከመንደርደሪያችሁ አሊያም ከመደብር ጎራ ብላችሁ “ጉንጉን” የምትለዋን መጽሐፍ ያዙ። እኔም፤ እንዲያ ብዬ አልተዋችሁምና በሸንተረራማው ስብጥርጥር፤ ግማሽ መንገዷን ከ“ጉንጉን” ስብጥሮች ጋር ልሸኛችሁ እመርጣለሁ።

ጉንጉን በ1982ዓ.ም ነበር ተወልዶ ለንባብ የበቃው። የመጽሐፉ መሠረት ሲጣል እንዲያው እንደዋዛ ከትንሽዬ የብዕር ጠብታ ነበር። በወቅቱ የነበሩት ደራሲያን የማህበራዊ ሕይወት የደረጀ ነበርና አንጋፋዎቹ ሰበብ ብለው ሻይና ቡናቸውን ፉት እያሉ ስለመጻሕፍት ዓለም የሚጨዋወቱባት የሚያወጉባት ክበብ ቢጤ ነበረቻችው። ከዚህ ስፍራ ሲገናኙ ሁሉም በተቻላቸው አቅም የጥበብ አቁማዳቸውን ሞልተው፤ ብጣሽ ወረቀትም ብትሆን ከኪሳቸው ሸጎጥ አድርገው ነውና ከዚሁ ተነስታ የተመነደገች ነበረች።

ደራሲው ኃይለመለኮት መዋዕል በጉንጉን ዓለም መስታወት ፊት ቆሞ አሻግሮ እሩቁን ማየት ጀመረ። የተባ ብዕሩን ዐሻራ ይዘው የወጡ መጻሕፍቶቹ ብዙ ቢሆንም “ጉንጉን” የተሰኘችው የዛሬው መጽሐፋችን ግን ከደራሲው ለአንባቢያንና ለጥበብ የተበረከተች ጉንጉን አበባ ናት። መስጠት ብቻም ሳይሆን ጉንጉን ምስጋናና ክብርም የተቀዳጀባትና የተቸረባት ናት። ምናልባትም የኃይለመለኮትን ልክ ይዛ የተከሰተችም ጭምር ናት። የዚህች መጽሐፍ የታሪክ ጥንስስ ከማጀቴ ምድር ላይ ነው።

ወደ ማጀቴ እናዝግም። ከማጀቴ ገበያ ወጥተን እህልኑም…ምናምኑን እንሸማምት፤ ወደ ጃራ ወንዝ ወርደን ውሃ እንቅዳ፤ እየዋኘን በልጅነት ትዝታችን እንሳፈፍ፤ ከምንወዳት የማጀቴ ጉብል ጋር ከወንዙ ዳር ሆነን ፍቅር እንስራ…የፍቅርን ቄጤማ ቆርጠን ከድልድዩ ስር በመጎዝጎዝ በፍቅር እነሆልል!፤ ከጎረቤትም ብቅ ብለን ከነ እልፍ ይከንዱ ቤት ቡናውን ፉት ብለን ከቀኛዝማች በላይነህ ክንዴ ጋርም በጨዋታ እናውጋ።

አንቱ በእርሶ መጀን ያሸማግሉን እንበላቸው፤ ከእርሳቸው ቤት ያለው አሸከራቸው እርም አይቀሬ…ደግሞ ያ ማነው የሚሉት… አፈሳ፤ የፈሪ ዱላ መሳይ የፍቅር ጌታውን ምንዳን ቁምስቅሉን እያሳየ አላስቆም አላስቀምጥ ብሏልና ለእርሱስ መካሪ ከወዴት እናገኝለት ይሆን…ብቻ ግን በማጀቴ አፈር ለሁሉም መላ መላውን አናጣምና ወደዚያው እናምራ። ለስንቁም ቢሆን አንዳችም ሃሳብ አይግባን የማጀቴ ሕዝብ በክብር ተቀብሎና እግር አጥቦ እያንከባከበ ያሰነብተናል።

በማጀቴ ቆይታችን የማንመለከተው ጉድ የለም። አመለኛውን ከነአመሉ፤ ጻዲቁን ከነጽድቁ፤ አሸርጋጁን ከነሽርግድ ማንነቱ፤ ሃይማኖተኛውንም እብሪተኛውንም፤ ሕፃን አዛውንት፤ ቆንጆ ጉብል ኮረዳ፤ ለዓይንና ለልባችን አዲስ የሆነ የፍቅር ቄጤማ፤ በአጠቃላይ ግን በ“ጉንጉን” ዓለም ውስጥ ከምንም በላይ ያማሩና ውብ የሆነ የማህበረሰብ እሴቶቻችንን ከነ ነብሳቸው በአካል የቆሙ ያህል ሆነው እናያቸዋለን።

በኃይለመለኮት ምናብ ውስጥ የተሳሉት ገጸ ባህሪያት በመጽሐፍ ውስጥ ያሉ ምናባዊ ፈጠራዎች ሳይሆኑ ከእኛው መንደር ውስጥ ያሉ መስለው ይታዩናል። አስቀድሜ ወደ ማጀቴ እንሂድ ማለቴ፤ የመጽሐፉን ገጾች ባገላበጥን ቁጥር እራሳችንን እንደ አንድ የማጀቴ ነዋሪ መቁጠራችን አይቀርም በማለት ነው።

ምናልባትም ደግሞ እራሳችንን እንደ አንደኛው ገጸ ሰብ ቆጥረን ወዳጁ ወዳጃችን፤ ጠላቱም ጠላታችን ሆኖ አብረን እላይ ታች እንል ይሆናል። ታዲያ ግን ለማንኛውም፤ እንደ ዶሮ ጫር ጫር እያደረኩ ከነዋሪው መሃከል ጥቂቱን ገጸ ባህሪያት በትንሽ በትንሹ ላስተዋውቃችሁና ሸኚ ቤት አያደርስምና… ዝምድናና ወዳጅነቱን ለማጠንከር ከፈለጋችሁ ቀሪውን እናንተው ተገናኝታችሁ ጨርሱት።

ይገርማችኋል ምንዳና ልክየለሽ እንዴት ያሉ ባልና ሚስት መሰሏችሁ… አቤት ፍቅር!፤ አይ መውደድና መዋደድ አንዱ ለአንዱ ያለው መተዛዘን..ጣዝማውን የፍቅር ማር እየቆረጡ ሲጎራረሱማ፤ አንተን ባደረገኝ ምንዳ፤ አንቺን በሆንኩ ልኬ ያስብላሉ። ይህ ፍቅርማ ከአንዱ ስፍራ በቀር ከወዴትም አይገኝምና መምህራቸው ከወዲያው እንደሆነ ያስጠረጥራል። የጉንጉኖቹ ምንዳና ልኬለሽ የፍቅር እስከ መቃብሮቹ በዛብህና ሰብለ ወንጌል አንዳች ግንኙነት ሳይኖራቸው እንደማይቀር ጠረጠርኩ። ይህን ፍቅር ምንዳ ከበዛብህ፤ ልክየለሽ ከሰብለ ወንጌል እግር ስር ቁጭ ብለው የተማሩት ይመስለኛል። አሊያማ እጅን በአፍ የሚያስጭን የእነርሱን ፍቅር መሳይ የታደለ ሌላ ገጸ ባህርይ ለማግኘት የሚቻል አይመስለኝም።

ታዲያ ምን ያደርጋል፤ የፍቅር አበባ ባለበት የፍቅር መቀስ፤ መለያየት የሚሉት የፍቅር ጥቀርሻ አይጠፋምና …የኔ ነገር… በፍቅራቸው መዓዛ ነሁልዬ ሌሎቹን እንዳልዘነጋቸው…የቀዬው ጌታ፤ ቀኛዝማች በላይነህ ክንዴም የዋዛ ሰው እንዳይመስሏችሁ የሰማንያ ሚስታቸውን የእልፍይከንዱን ፍቅር በጭልፋ፤ የቅምጣቸውን የወይዘሮ ደጅይጥኑን ደግሞ በማንኪያ የሚዝቁ ብቻም አይደሉም።

አንዳንዴ በሹኪያም ይዳዳቸውና ወደ አገልጋያቸው ላቀች ዓይነ ስሜታቸውን ያዞራሉ። በጠበቅናቸውም ባልጠበቅናቸውም ቦታ ድንገት የምናገኛቸው የሁለት ዓለም ሰው ናቸው። ቸርነት እንደ ስሙ ቸር ነው። የምንዳ የልብ ወዳጅ ብቻም ሳይሆን አንዳንዴማ ልቡም ጭምር ነው። ጓደኝነትና የልብ ወዳጅነት ሲሰምር ልክ እንደ ሁለቱ ያለውን እንዲሰጣችሁ ተመኙ። ምንም የማይወጣለት ንፋስም ሆነ ዝንብ የማይገባበት ጸአዳ ወዳጅነት ነው።

አለ ደግሞ እንደ አፈሳ ዓይነቱ ፍጹም ጠላት፤ ቅናት እያንጨረጨረው የተንኮል ጅራፉን በፍቅር ዜማ መሃል ድንገት ያስጮሃል። የተንኮሉን ያህል አብዝቶ የተከናነበው ፈሪነቱ ደግሞ አይጣል አያድርስ የሚያስብል ነው። የፈሪ ዱላ ሁሌም የሚመታ ስለሚመስለው ከአንድ አንድ ሳልቀደም ልቅደም በማለት አድብቶ በአሳቻው ሰዓት ከማጅራት ላይ ይወርዳልና በዚህም ምክንያት እርሱ የጠላው ሁሉ ጠላቱ ይመስለዋል። ደጉንና ምስኪኑን ምንዳዬን ዋነኛው ጠላቱ አድርጎ በዚህም በዚያም ሲያዋክበው አንጀት የሚያሳርር ነው።

ብቻ ግን የደራሲው ምናቦች ግብራቸው በሰማይና በምድር መሃከል እንደ ሰማይና እንደ ምድር፤ እንደ መልዓክና እንደ ሰይጣን ያሉ ናቸው። ወደን እስከ ጥግ የምንወዳቸው፤ ጠልተንም እስከ ጥልቁ የምንጠላቸው ሆነው ይገኛሉ። ታዲያ በእነዚህ መሀከል የሚፈጠረው ዓለም እንዴት ያለ ጣፋጭ መሰላችሁ፤ ስሜት የሚያስቆረጥም ነው።

በ“ጉንጉን” ውስጥ የምንመለከተው የደራሲው ልዩ ችሎታና በገጸ ባህሪያቱ ውስጥ የተሰካኩት የሴራ ውቅሮች፤ እጅግ የምንደነቅበት ሌላው እይታ ነው። ብዙውን ጊዜ፤ ቀኛዝማች በላይነህና ባለቤታቸው እልፍይከንዱ በመሃከላቸው የሚፈጠር ሙግትና የውስጥ ግጭት አለ። ይህን አለመግባባት በቃላት አሳምሮ ማስቀመጥ የሚቻል ቢሆንም፤ ደራሲው ግን ሌላ የተለየ እይታን ለመፍጠር ታትሮበታል።

በዚህ መሃል ከቃላቶቻቸው የተለየውን ውስጣዊ የስሜት ነጸብራቅ፤ በቃላት ልንረዳው ከምንችለው በላይ በስዕላዊ እንቅስቃሴና በውስጣዊ ስሜታቸው ይነግረናል። ቃላትን በመጠቀም ስሜትን ከመግለጽ ይልቅ ስሜትን በመጠቀም ያልተጻፉ ቃላትን እንድናነብ ያደርገናል። እልፍ ይከንዱ በትንሽ ትልቁ አብዝተው የቅዱስ ጊዮርጊስን ታቦት የሚማጸኑና ስለት የሚወዱ ሴት ናቸው። በታቦቱ ካላቸው የገዘፈ እምነት የተነሳ መልካምና ደጉን ቀርቶ ለመንቀል የፈለጉትን ሰው እንዲነቅልላቸው ቢማጸኑት እንኳ እንደሚያደርግላቸው ያምናሉ።

ይህን ብታደርግልኝ፤ ዣንጣልና እጣን ከርቤውን…ስለቱን አስገባልሃለሁ ብለው ተማጽነው፤ ነገር አልሆን ስለቱ አልሰምር ያላቸው ጊዜ አፈንግጠው ጊዮርጊስ አልሰማኝም በማለት ወደ ጠንቋይ መንደር ይዘልቃሉ። ባለቤታቸው ቀኛዝማች ደግሞ የኔ የሚሉትና የቅርባቸው የሆነው መልዓክ ቅዱስ ሚካኤል ነው ይላሉ። ሁለቱም በየራሳቸው መልዓኮች ያላቸው የከረረ እምነት፤ የኔው የኔ ብቻ ነው ወደሚመስል ስሜቶች ሲገቡ እንመለከታለን።

አውጥተው በቃላት ባይተነፍሱትም፤ በውስጣቸው አንዱን መልዓክ ከሌላው ማበላለጥና የኔው ነው የሚበልጠው ብሎ የማሰብን አዝማሚያቸውን ያለምን የቃላት ገለጻ እንዲሁ ውስጣቸውን ለመረዳት ስንችል፤ እንዴት ያለው ግሩም የስሜት መነጽር ነው፤ በማለት ደራሲውን ለማድነቅ አፍታም የምንዘገይ አይመስለኝም። “እርም አይቀሬ” የተባለውን የቀኛዝማች የበላይነህ አሽከር፤ ከስሙ ጀምሮ ያለውን ማንነቱን ለመረዳት ሌላ የተለየ መነጽር የሚሻ ነው።

አንድ ቀን፤ እልፍይከንዱ እንደ ልማዳቸው ታቦቱን ተማጽነው፤ ነገሩ አልሆን ቢላቸው ጊዜ ጊዮርጊስ ቀድሞ አልደረሰልኝም በማለት ወደ ጨፍሮቢቷ ጠንቋይ ዘንድ ሄዱ። “…የጠጡትን ስኒ ቡና አተላ በቀስታ እያንጋለሉ ካጠነፈፉ በኋላ፤ ቀሪው አተላ ረግቶ የራሱን የመፍሰሻ ሸንተረራማ ስብጥርጥር ሥዕል መሥራቱን እንዳዩ…”

መጽሐፍ ውስጥ የምናገኛቸው የገጸ ባህሪያቱ ድርጊቶች፤ አንዳንዴም ደራሲው ምን ሲል አሰበው የሚያስብሉን ናቸው። በተመስጦ ውስጥ ሆነን ገጽ ለገጽ የቃላቱን ፍኖት ተከትለን ስንሄድ፤ ድንገት ንባባችንን ገታ አድርገን ነገሩን በአዕምሯችን ለማሰላሰል እንገደዳለን። አንድ ደራሲ ያን ያህል ተጨንቆና ተጠቦ በዚያ መልኩ ይገልጸዋል ብለን የማንጠብቀውን፤ በእውን እንጂ በምናብ ፈጠራ ውስጥ ልናገኘው የማንችለውን ነገር ያሳየናል።

ጥቃቅንና ከአንድ ጊዜ በላይ ደግመን ልናያቸው የማንችላቸው፤ ነገር ግን እኛ እንደዋዛ ተመልክተን ያለፍነውና አዕምሯችን ግን ከማህደሩ አስፍሮት በሆነ ጊዜ በሆነ አጋጣሚ ትዝ የሚሉን ግላዊ ክስተቶች የበዙበት ነው። መጽሐፉ በአንድ አካባቢ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ሊኖሩ የሚችሉ ጉዳዮችን ልቅም አድርጎ አስቀምጦታል። እንደ ምናብ ቁብ የማንሰጣቸው፤ እንደ እውነት ግን ቅልብጭ ያሉ እውነታዎች ታጭቀውበታል።

አልፎም ደግሞ ሰው እንደመሆናችን በሰዋዊ ተፈጥሯችን በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ተሰንገው ሳሉ፤ ነገር ግን ሁላችንም ውስጥ ውስጡን ስናብሰለስላቸው በግልጽ አውጥተን እንዲህ ነው የማንላቸውን ጉዳዮችንም፤ ባህልና ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። የደራሲው ዓይንና የምናቡ ስፋት የተለየ ስለመሆኑ፤ እኚህ በድንገት የምናገኛቸው አዳዲስ እውነታዎች ይነግሩናል። የታሪክና የቦታ፤ የገጸ ባህሪያቱና የድርጊት ስብጥሮቹ ከቃላቱ ጋር የተሰናሰኑበት ዘዬ ማራኪ የጽጌረዳ ጉንጉን አኑሮበታል።

በልቦለድ የምናብ ዓለም ውስጥ እጅግ ወሳኝና የደራሲው የምናብ ጥልቀት የሚፈተንበት አንደኛው ነገር የቦታና ቁስ አካላትን ስዕል መፍጠር ላይ ነው። ገጸ ባህሪያቱ በራሳቸው ቃላትን በመጠቀም ስሜትና ባህሪያቸውን ሊነግሩን ይችላሉ። ግኡዝ አካላትን በተፈጥሮ ልኬት መልክና አንዳንዴም ሰውኛ ባህሪን እያላበሱ እነርሱን ነጋሪና ተናጋሪ ማድረግ የተለየ ጥበባዊ ክህሎትን የሚጠይቅ ነው።

ከገጸ ባህሪያቱ፤ እንቅስቃሴና የቃላት ምልልስ ይልቅ ያሉበትን አካባቢ፤ መልክዓ ምድራዊ ገጽታውን ምስል ከሳችና መሳጭ ማድረግ ይበልጥ የሚስብና የአንባቢውንም ምናባዊ አብሮነት ሳይቋረጥና ሳይቀዘቅዝ እንዲቀጥል ያደርገዋል። በዚህ ሚዛን ውስጥ “ጉንጉን” አንዳች ማግኔታዊ ስበት ያለው ይሆንና ገጸ ባህሪያቱን ረስተን በቦታው የተገኘነው እኛ እንደሆን ይሰማናል። የማህበረሰባችንን ቀደምት ልምዶችንና ባህላዊ የማንነት እሴቶቻችንን መልክ ይዞና እንደ ጉንጉን አበባው ስጦታ እንካችሁ ሲል ይሰማናል። ኢትዮጵያዊነት አፍ አውጥቶ ሲናገር እንመለከታለን። ወይዘሮ ደጅይጥኑ ከአቦ ፀበል መልስ በሼህ መሐመድ መቃብር በኩል ሲያልፉ፤

“በአንቱ ከራማ፣ በአንቱ መጀን፤

አባቴ የኔ አድባር የዕለት ጉርሴን፤

የዓመት ልብሴን አትንፈጉኝ፤”

በማለት በግጥማዊ የተማጽኖ ዜማ፤ ውስጥን የሚፈነቅል ኢትዮጵያዊ ማንነታችን በልባችን እንደ ቀስተ ደመና ያለ መስመር ሰርቶ ሲያልፍ ይሰማናል። ከቀብሩ ስፍራ ደርሰው መጀን ማለታቸው፤ እንደዋዛ ሲያልፉ ብቻ ሳይሆን ከአቦ ፀበል፤ ከመድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ፀሎት አድርሰው ሲለን፤ ለነገሩ ክብደት ለመስጠት ብቻም ሳይሆን፤ ደራሲው እዚች ጋር ለማስቀመጥ የፈለገው ጉንጉንም መኖሩ ነው።

አይ ክፉ ቀን! ያ የፍቅር መሶብ፤ የመልካምነት አገልግል ምንዳ ከጠላቱ እጅ ወደቀ። በጥይት ተመቶ ወደቀ። ይሄኔ ልክየለሽ ምን ይውጣት ነጠላዋን ከወገቧ ላይ አድርጋ እሪ! እያለች እንባዋን እያዘራችው ነው። ምስኪኖቹ ሕፃናት ልጆች፤ ከደጁ ላይ ኩርምት ብለው፤ ዓይኖቻቸውን ሲያንከራትቱ አንጀትን ይበላሉ።

ጉንጉን ከወዲያ ወዲህ እየጎነጎነ የሚያሳየንና የሚሰጠን በምናባዊ ቀለማት የተቀለመው የማህበረሰባዊ የጋቢ ጥለት ውስጥ የማናገኘው እኛነትና እኔነት የለም። ከድውሩ እስከ ጥለቱ መቋጫ ድረስ ባለው ሂደት፤ እንደ ባለሙያው የምንሠራውም፤ እንደ ጋቢውም የምንሠራው እኛው ሆነን እንገኛለን።

“ጉንጉን” በራሱ ዛቢያ፤ በሚያደርገው በምናባዊ እሽክርክሪቱ እየከሰተ ባሳየን ድንቅ ዓለምና ድንቅ ታሪኩ ብቻም ሳይሆን፤ እንደ መጻሕፍት ዓለም ክዋክብቶቻችንም አብረቅራቂው የኦሪዮን ኮከብ ነው። በጣት ቆጥረን ከምንጠቅሳቸው መጽሐፍቶቻችን መሃከል “ጉንጉን” ስለመኖሩ ማናችንንም የሚያወላዳ አይደለም። እናም ስብጥርጥሩን የማጀቴን መንገድ ተከትላችሁ ሂዱ ይህቺን ማጀቴ፤ ያንንም ጉንጉን ያዙ።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You