ባለስልጣኑ የተሰጠውን የኦዲት ግኝት ማስተካከያ እንዲተገብር ተጠየቀ

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን በፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የተሰጠውን የኦዲት ግኝት ማስተካከያ እንዲተገብር ተጠየቀ።

በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የማሪታይም ባለሥልጣን የ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት ሂሳብ ኦዲት ሪፖርት ውይይት በተካሄደበት ወቅት የፌዴራል ምክትል ዋና ኦዲተር አቶ አበራ ታደሰ እንደተናገሩት፤ ተቋሙ ዋና ኦዲተር ማስተካከያ እንዲያደርግ ባሳወቀው መሠረት የተወሰዱ እርምጃዎች ቢኖሩም አሁንም ያልተስተካከሉ ግኝቶች አሉ።

ከእነዚህም መካከል በተለያዩ ጊዜያት ዓመታዊ የእቅድ አፈጻጸምና ግምገማዎች ሲካሄዱ ሠራተኞች ስለመገኘታቸው የሰዓት መቆጣጠሪያ ፊርማ አለመፈረማቸው እንዲሁም ከመ/ቤቱ ውጪ የመጡ መገጣጠሚያ ደብዳቤ ሳያቀርቡ 261 ሺ 429 ብር አላግባብ አበል ተከፍሏል። አስራ ስድስት ለሚሆኑ የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች ለሥራ ጉዳይ በሄዱባቸው የተለያዩ ቦታዎች መከፈል ከሚገባው የአበል ተመን በላይ 5 ሺ 235 ብር መመሪያው ከሚፈቅደው ውጪ ክፍያ ተፈጽሟል፡፡

በተመሳሳይ ከመደበኛ የሥራ ሰዓት ውጪ የሚከናወኑ ሥራዎችን ለኮሚሽኑ በማሳወቅ ክፍያ መፈጸም ሲገባቸው ፈቃድ ሳያገኝ ከመመሪያ ውጪ 11 ሺ 291ብር ከ50 ሳንቲም የትርፍ ሰዓት ክፍያ ተፈጽሟል። ሠራተኞች አዲስ አበባ ለሰለጠኑባቸው ቀናት በሚል በቀን አንድ መቶ ብር በማሰብ 81 ሺ 400 ብር ክፍያ ተፈፅሟል። በተጨማሪ ከግዢ፤ ከተሰብሳቢና ከተከፋይ ሂሳብ እንዲሁም ከበጀት አፈጻጸምና የንብረት አያያዝ ጋር ክፍተቶች ተገኝተዋል። በመሆኑም እነዚህን ክፍተቶች በአጭር ጊዜ ተቋሙ ሊያስተካክል እንደሚገባ አሳስበዋል።

በገንዘብ ሚኒስቴር ኢንስፔክሽን መምሪያ አቶ መኮንን ጌታሁን በበኩላቸው የ2014 ዓ.ም የዋና ኦዲተር ምላሽ ከተሰጠ በኋላ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ክትትልና ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል። የእርምት እርምጃ የተወሰዳባቸው፤ ተመላሽ የተደረጉ ገንዘቦችንና ለመመለስ በቀጠሮ ያሉትን የጊዜ ገደቡን እንዲያስቀምጡም አድርጓል።

በቀጣይ እርምጃ የሚወሰድባቸውም ላይ እንዴትና ምን አይነት እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚቻል በጋራ ውይይት ተደርጓል። ግዢን በተመለከተም ተጠያቂነትን ለማስፈን የሄዱበትን ርቀትና በኦዲት የተገኙ ስህተቶች አለመደገማቸውን የማረጋገጥ ሥራ ተከናውኖ ለተቋሙና ለሚመለከታቸው አካላት ግብረ መልስ ተሰጥቷል ብለዋል።

በዚህም መሠረት እስከ ሚያዝያ ሰላሳ ድረስ እርምጃ ባልተወሰደባቸው ላይ እርምጃ ወስደው እንዲያቀርቡ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል። ይህ ሳይሆን ከቀረ ግን ከሚያዝያ ሰላሳ በኋላ ገንዘብ ሚኒስቴር በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሠረት ወደ እርምጃ የሚገባ ይሆናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልበር ሸምሱ የኦዲት ክፍቱን በመቀበል በሰጡት ምላሽ በናሙና ኦዲት የተገኙ ግኝቶች የምናስተካክላቸውና አስተማሪ ናቸው ብለዋል።
ግኝቶቹ በገንዘብ ደረጃ ዝቅተኛ ቢሆኑም የክትትልና የቁጥጥር መርሀ ግብር በማዘጋጀት አሠራራችን ሕግና ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ እንዲሆን የምናደርግ ይሆናል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ እስካሁንም የዋና ኦዲተር ግብረ መልስ ከተሰጠን ጀምሮ በርካታ ማስተካከያዎችን ስናደርግ ቆይተናል ብለዋል።

አንዳንዶቹ ነገሮች በሕግ አግባብ የማይፈቀዱ ቢሆንም ስህተት ሆነው ሳይሆን በሁኔታዎች አስገዳጅነት የተከናወኑ መሆናቸውንም ለቋሚ ኮሚቴውና ለዋና ኦዲተር አስረድተናል። ይህም ሆኖ በሚቀጥሉት ሃያ ቀናት የሚጠበቅብንን በማስተካከል ውጤቱን ለሚመለከታቸው አካላት የምናሳውቅ ይሆናል ብለዋል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You