አዲስ አበባ:- በፍትህ ስርዓቱ ላይ የሚካሄደው ማሻሻያ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት የፍትህ ስርዓቱ ተዓማኒ እንዲሆን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተገለፀ። “የፍትህ ስርዓት አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ“ ለሁለተኛ ጊዜ ውይይት ተካሂዶበታል።
ትላንት በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶች፣ ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ ዳኞች፣ ዓቃቢያነ ህግ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህግ ምሁራን፣ የህግ ባለሙያዎችና ጠበቆች፣ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ እና የህገ-መንግስት አጣሪ ጉባኤ አባላት፣ የቀድሞው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የበላይ አመራርና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በተገኙበት ውይይት የተካሄደበት ይህ ረቂቅ አዋጅ እስከዛሬ በዘርፉ የነበሩትን ተግዳሮቶች ሙሉ ለሙሉ በማስወገድ የአገሪቱን የህግ ስርዓት በመሰረታዊነት ይለውጠዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል።
በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቢ ህግ የዳኝነት ስርዓት አማካሪ ጉባኤ አባልና የረቂቅ ህጉ ዝግጅት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ማንደፍሮት በላይ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት ይህን ረቂቅ አዋጅ ማዘጋጀት ያስፈለገበት አቢይ ምክንያት በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ የማንንም ወገን ጣልቃ ገብነት ለማስቀረት፣ የፍትህ ስርዓቱን ተቋማዊ ለማድረግ፤ የደኞችን ነፃነት፣ ገለልተኝነት እና ተጠያቂነት በህግ ለመደንገግ፤ የፍርድ ቤቶችን አደረጃጀትና አሠራር ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ከሙስና የፀዳ ለማድረግ፤ በፍትህ ስርዓቱ ላይ ተፅእኖ የሚፈጥሩ ህጎችን፣ ደንቦችና መመሪያዎችን ለማስወገድ፤ የሲቪል ማህበራትና ተቋማትን አቅም ለማጎልበት፣ በህገ-መንግሥቱ የተደነገገውን የዜጎችን ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ሙሉ ለሙሉ እንዲከበር ለማድረግ በማሰብ ነው።
የፍትህ ስርዓቱን እና የዳኝነት አሠራርን የአገልግሎት ጥራትን ከማሻሻል፣ ከዘመድ አዝማድና ጓደኝነት ላይ ከተመሰረተ አሰራር እና ከመሳሰሉት ተግዳሮቶች ከማላቀቅ አኳያ ረቂቅ አዋጁ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው የሚሉት አቶ ማንደፍሮት በላይ በረቂቁ ዝግጅቱ ወቅት የበርካታ አገሮች ልምድ መፈተሹን፣ እነሱን ያጋጠማቸው ችግር እኛንም እንዳይገጥመን በማሰብ ትምህርት መወሰዱን፣ በአገሪቱ አሉ በተባሉ ባለሙያዎች ያለምንምና ማንም ጣልቃ ገብነት ፍፁም ሙያዊ በሆነ ሁኔታ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
“ከውይይት መድረኩ ከፍተኛ ግብዓት አግኝተናል። እነዚህን ግብአቶችም ወደ ቢሯችን እንደተመለስን እንጠቀምባቸዋለን። ከዛም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርቦ ይሁንታን ሲያገኝ ለተወካዮች ምክር ቤት ይቀርብና ከፀደቀ በኋላ ወደ ሥራ ይገባል” በማለት ያስረዱት የረቂቅ አዋጁ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አዋጁ በሚገባ ታስቦበትና የሁሉንም አካላት አመኔታና ተአማኒነት እንዲያገኝ ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑንም ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2011
ግርማ መንግስቴ