አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ በተጀመሩ ምሁራንን ያሳተፈ ውይይት ላይ የተገኙ ሀሳቦች በቀጣይ በሚወጡ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ መካተት እንዳለባቸው ተገለፀ።
የፖለቲካና የኢኮኖሚ ምሁር የሆኑት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ እንደሚናገሩት፤ በአገሪቱ የሚደረጉ የተለያዩ የውይይት መድረኮች ለህብረተሰብ ግንባታ በጣም ጠቃሚ በመሆናቸው በቀጣይ በአግባቡ ለአገር ግንባታ ሥራ መዋል አለባቸው።
የህዝብ ክርክሮች ወይም ህዝቡ የሚሳተፍበት ውይይት በአገሪቱ አለመኖሩ ብዙ የሚወጡ ፖሊሲዎች፣ መመሪያዎች የህዝብ ስሜት የሌላቸው እየሆኑ ነበር የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በቅርቡ በተጀመሩ ምሁራንንና ህዝቡን ያሳተፉ ውይይቶች ላይ የሚገኙ ሀሳቦች በሚወጡ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ ከተካተቱ ለአገር ግንባታ ትልቅ ፋይዳ እንደሚያመጡ ጠቁመዋል።
በአገሪቱ ያለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አገሪቱን ህዝብ ወክለው የሚንቀሳቀሱ ናቸው የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ ነገር ግን ቀደም ብሎ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤትም ሆኑ የፌዴሬሽን ምክርቤት አባላት በየአካባቢያቸው እየሄዱ ህዝብን እያወያዩ የሚወጡ ፖሊሲዎች ለህዝቡ ጥሩ ናቸው ወይስ አይደሉም የሚለውን መስራት ላይ ችግሮች እንደነበሩ አስረድተዋል።
እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ አባባል፤ በአብዛኛው በበለፀጉ አገሮች ፖሊሲና ስትራጂዎች ከመተግበራቸው በፊት ለህዝብ ውይይት ይቀርባሉ። እንደዚህ አይነት ውይይቶች ደግሞ ፖሊሲና ስትራቴጂ ሲወጣ ለውሳኔ አሰጣጥ እንዲመች ነው። በኢትዮጵያ ምሁራን የሚሰጡት ሀሳቦችና ምክሮች መተግበር ግን በጣም አነስተኛ ነበር። በሌላ የህዝብ ውይይቶች በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይም መስፋፋት አለባቸው። በአገር ጉዳይ ላይ መወያየት እንደባህል ማደግ አለበት። በአሁን ወቅት እንደ ቲንክ ታንክ አይነት ቡድኖች እንዲቋቋሙ በማድረግ ፖሊሲና ስትራቴጂ ሲወጣ ምሁራን እንዲሳተፉ መደረግ አለበት።
ምሁራንና ህዝቡን በሰፊው ያሳተፈ መድረክ በየከተማው ሊደረጉ እንደሚገባ የጠቀሱት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ አብዛኛው ጊዜ ፖሊሲዎች ሲወጡ ህዝብን ያሳተፉ ባመሆናቸው ፖሊሲዎችና ህጎች በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብቻ ተወስነው የሚተገበሩ በመሆናቸው አዋጁን አልቀበልም ያለ አካል ጫና ይደርስበት እንደነበር አስታውሰዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2011
መርድ ክፍሉ