ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት ከሰነዘረች በኋላ የዓለም ነዳጅ እና ወርቅ ዋጋ ቀነሰ

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ኢራን እስራኤል ላይ የጥቃት እርምጃ ከወሰደች በኋላ ከሰኞ ጀምሮ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ላይ ቅናሽ ታይቷል። የዓለም የነዳጅ ዋጋ ማነጻጸሪያ የሆነው የድፍድፍ ነደጅ ዋጋ እያሽቆለቆለ ሲሆን በበርሜል ወደ 90 ዶላር እየተጠጋ ይገኛል።

ተንታኞች ኢራን እስራኤል ላይ ያደረሰችው ጥቃት ዓለም አቀፍ የገበያ ሰንሰለት ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ ወደፊት የሚታይ ይሆናል ብለዋል። የዓለም የነዳጅ ዋጋ መለዋወጥ በርካታ ሀገራት ለምርት የሚመረኮዟቸውን የቤንዚል እና ናፍጣ ዋጋን ተቀያያሪ በማድረግ የዓለም ገበያ እንዳይረጋጋ ያደርጋል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በዓለም ዙሪያ ለታየው የምርቶች ዋጋ ማሻቀብ ዋነኛው ምክንያት የነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2022 የሩስያ ዩክሬንን ጦርነት ተከትሎ የአንድ በርሜል ነዳጅ ዋጋ ወደ 120 ዶላር ጨምሯል። የዚህም ምክንያት ሩስያ ላይ ምዕራባውያን የጣሉት ማዕቀብ ነው።ይህ እርምጃ የነዳጅ ዋጋ ብቻ ሳይሆን በዓለም የምርቶች ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ እንዲታይ ሰበብ ሆኗል።

ታዲያ እስራኤል አሁን የምትሰጠው አጸፋ የዓለም የነዳጅ ዋጋን ለመወሰን ወሳኙ እንደሆነ ታምኗል። የእስራኤሉ መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት ከኢራን ጋር የገባነው ፍጥጫ አላበቃለትም ብለዋል።ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ኢራን ባለፈው ቅዳሜ እስራኤል ላይ ለፈጸመችው ጥቃት ምላሽ ለመስጠት እየተዘጋጁ ነው።

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል 92 ነጥብ 18 ዶላር የነበረ ሲሆን፤ ይህም ከጥቅምት ወር ወዲህ የተመዘገበው ከፍተኛው ዋጋ ነበር። ሆኖም ትናንት ሰኞ ወደ 89 ነጥብ 50 ዶላር ወርዷል። ሌላው በዓለም ገበያ አስተማማኙ ኢንቨስትመንት እንደሆነ የሚቆጠረው የወርቅ ዋጋም ቀንሷል።

የወርቅ ገበያ ባለፈው ዓርብ በወቄት 2 ሺህ 431 የነበረ ሲሆን፤ ይህም ከፍተኛው የወርቅ ዋጋ ሆኖ ተመዝግቧል። አሁን ዋጋው በወቄት ወደ 2 ሺህ 332 ነጥብ 9 ዶላር ቀንሷል። ኢራን የዓለም ሰባተኛዋ ከፍተኛ ነዳጅ አምራች ሀገራት ስትሆን፤ ሦስተኛዋ ትልቁ የነዳጅ ላኪዎች ኅብረት ወይም ኦፔክ ሀገራት አምራች ነች።

ታዲያ ተንኞች የዓለም የነዳጅ ዋጋን የሚወስነው በግጭቱ ሆርሙዝ ሰርጥ ምን ያህል ተጽዕኖ ውስጥ ይወድቃል የሚለው እንደሆነ ይናገራሉ። ሆርሙዝ ሰርጥ ነዳጅ የሚመላስበት መስመር ነው። በኦማን እና ኢራን መካከል ያለው ይህ ሰርጥ የዓለም እስከ 20 በመቶ የሚደርሰው ነዳጅ የሚጓጓዝበት ነው። የኦፔክ አባላት የሆኑት ሳዑዲ አረቢያ፣ ኢራን፣ ዩኤኢ ኩዌት እና ኢራቅ ይህንን መስመር ተጠቅመው ነዳጅ ይልካሉ።

ባለፈው ቅዳሜ ኢራን በዚህ ሰርጥ ሲተላለፍ የነበረ እና ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያለውን መርከብ ይዛለች። በሰርጡ ይህንን አይነት ውዝግብ ከቀጠለ እና ጉዞዎች የሚስተጓጎሉ ከሆነ የዓለም የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ሊያናጋው እንደሚችል ተሰግቷል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You