ጋናዊው ግለሰብ ከአንድ ሺህ 100 በላይ ዛፎችን በማቀፍ አዲስ ክብረወሰን አስመዘገበ

የተፈጥሮ ጉዳዮች ማህበራዊ አንቂ እና የስነ ደን ተማሪ የሆነው ጋናዊው አቡበከር ታሂሩ በአንድ ሰዓት ውስጥ በርካታ ዛፎችን በማቀፍ አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን አስመዝግቧል።

አቡበከር ታሂሩ የተባለው የ29 ዓመቱ ጋናዊ በአንድ ሰዓት ውስጥ በአጠቃላይ አንድ ሺህ 123 ዛፎችን ያቀፈ ሲሆን፤ በአንድ ደቂቃ ውስጥም በአማካይ 19 ዛፎችን ማቀፍ መቻሉ ነው የተነገረው።

በጋና ገጠራማ አካባቢ በሆነችው ቴፓ ያደገው አቡበከር፤ በአርሶ አደር ቤተሰቦች መካከል ማደጉ ለተፈጥሮ ልዩ ፍቅር እንዲኖረው እንዳደረገው ይናገራል።

አቡበከር በስነ ደን የመጀመሪያ ዲግሪውን በጋና ታዋቂ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ካጠናቀቀ በኋላ በዚሁ የስነ ደን ትምህርት ሁለተኛ ዲግሪውን ለመማር ወደ አሜሪካ ማቅናቱም ነው የተነገረው።

አዲስ ክብረወሰን የማስመዝገብ ሙከራውን ያካሄደው አሁን በሚገኝባት ሀገረ አሜሪካ ሲሆን፤ ክብረወሰኑን ያስመዘገበውም በአላባማ ውስጥ በሚገኘው ቱስኪጊ ብሔራዊ ደን ውስጥ ነው።

በዚህም አቡበከር ዛፎቹን በሁለት እጆቹ ጥብቅ እያደረገ ሲያቅፍ የነበረ ሲሆን፤ በሙከራው ወቅትም አንድን ዛፍ ደግሞ ማቀፍ እንደማይቻል እና በሚያቅፍበት ጊዜ በዛፎቹ ላይ ጉዳት ካደረሰም ሙከራውን እንደሚሰርዘው ቅድመ ሁኔታ ተቀምጦለት ነበር።

አቡበከር ስለ ዛፍ ማቀፍ ክብረ ወሰኑ ሲናገር፤ “በጣም ከባዱ ነገር በዛፎቹ መካከል የሚደረገው ምልልስ እንዲሁም እያንዳንዱ ዛፍ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት መታቀፉን ማረጋገጥ ነበር” ብሏል።

ክብረወሰን የመስበር ሙከራውን የበለጠ ከባድ አድርጎበት የነበረው ሌላኛው ነገር ደግሞ የረመዳን ወቅት መሆኑ እና በመሀል ውሃ መጠጣት አለመቻሉ እንደሆነም አቡበከር ተናግሯል።

ያም ሆኖ አቡበከር ክብረወሰን የመስበር ሙከራውን ያሳካ ሲሆን፤ በየሦስት ሰከንድ ልዩነት አንድ ዛፍ በማቀፍ በአጠቃላይ 700 ዛፎችን በአንድ ሰዓት ውስጥ ማቀፉ አቡበከርን የክብወሰን ባለቤት ለመሆን በቂው ነበር።

ሆኖም ግን ጋናዊው አቡበከር በአንድ ደቂቃ በአማካኝ 19 ዛፎችን በማቀፍ በአጠቃላይ በአንድ ሰዓት ውስጥ አንድ ሺህ 123 ዛፎችን በማቀፍ ክብረወሰኑን የግሉ አድርጓል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You