በአውስትራሊያ ሲድኒ በሚገኝ ‘ቸርች’ ውስጥ በርካቶች በስለት ተወጉ

በአውስትራሊያ ሲድኒ ከተማ በሚገኝ ‘ቸርች’ ውስጥ በርካቶች በስለት ተወጉ። አውስትራሊያ ሲድኒ ከተማ ዳርቻ በሚገኝ ‘ቸርች’ ውስጥ በተፈጸመ በስለት የመወጋት አደጋ በርካቶች መቁሰላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

በማህበራዊ ሚዲያ የተለቀቀው ቪዲዮ ቢለዋ የያዘው ግለሰብ መድረክ ላይ የነበረውን አገልጋይ ጎትቶ ሲወጋው ይታያል። ፖሊስ ይህን ጥቃት አድራሽ መያዙን እና ለምርመራ ተባባሪ መሆኑን የፖሊስ ቃል አቀባይን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል። ይህ ጥቃት ከሴንትራል ቢዝነስ ዲስትሪክት በስተምዕራብ በኩል በምትገኘው ዌክሌይ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የተፈጸመ ነው።

በሲድኒ በሚገኝ የገበያ አዳራሽ ውስጥ ስድስት ሰዎች በቢለዋ ተወግተው ከተገደሉ በኋላ በሦስት ቀናት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የተፈጸመ ጥቃት ነው ተብሏል። ትናንት አደጋ የተከሰተው ዌክሌይ ውስጥ የሚገኘው ‘ክሪስት ዘ ጉድ ሸፐርድ ቸርች’ አገልግሎት እየሰጠ ባለበት ወቅት ሲሆን፤ ፖሊስ በቦታው የተሰበሰበውን ሕዝብ ለመቆጣጠር እስካሁን በቦታው እንደሚገኝ ተዘግቧል።

በሰዎች ላይ የደረሰው ጉዳት ለህይወት አስጊ አለመሆኑን እና ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ፖሊስ ገልጿል። በአደጋው የቸርቹ መሪ እና በርካታ ምዕመናን ጉዳት ደርሶባቸዋል። በማህበራዊ ሚዲያ የተለቀቀው ቪዲዮ ቢለዋ የያዘው ግለሰብ መድረክ ላይ የነበረውን አገልጋይ ጎትቶ ሲወጋው ይታያል ሲል አል ዐይን ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You