ድሬዳዋ፡-በ2004 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው አምስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት በኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ታሪክ ሁለተኛ የሆነው የድሬዳዋ ደወሌ የክፍያ መንገድ ተመርቆ ሥራውን ጀመረ። የመንገዱ ወደ ሥራ መግባት በኮሪደሩ ያለውን የትራንስፖርት ፍሰት በማሳለጥና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጎልበት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተጠቁሟል።
የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ መንገዱን መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት የማይተካ ላለው የመንገድ ልማት ሥራ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል። ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በተከናወነው ሥራ ከ26 ሺ ኪሎ ሜትር የማይበልጠው የመንገድ ዘርፍ በአሁን ሰዓት 127 ሺ ኪሎ ሜትር ደርሷል። ለዚህም 336 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል። ክረምት ከበጋ ለመድረስ በአማካይ ይፈጅ የነበረው 21 ኪሎ ሜትር ርቀት በአሁን ሰዓት ወደ 403 ኪሎ ሜትር ዝቅ ብሏል። የመንገድ አውታርም ከ22 በመቶ ወደ 72 በመቶ አድጓል፤ በዚህም በአገር ውስጥም ይሁን ከጎረቤት አገራት ጋር ያለውን የትራንስፖርት ግንኙነት ማሳደግ ተችሏል።
እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ፤ የድሬዳዋ ደወሌ የክፍያ መንገድ የዚሁ ሥራ አንድ አካል ሲሆን የመንገዱ እውን መሆን የአገሪቱን ገቢና ወጪ ንግድ ለማሳለጥ ብሎም ከጅቡቲ ጋር ያላትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማጠናከር ያግዛታል። ከዚህም በላይ አፍሪካ በ2063 የያዘችውን አፍሪካን በመሰረተ ልማት የማገናኘት ግብ እውን ለማድረግ አጋዥ የሚሆን ሲሆን ይህን መሰል ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፌ መሀመድ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የመንገዱ እውን መሆን ለክልሉም ሆነ ለአገሪቱ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አለው። መንገዱ የጠረፍ ከተማ ከሆነችው ደወሌ የሚያገናኝ እንደመሆኑ ለሁለቱ አገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ጠንካራ መሰረት ይጥላል። ሆኖም ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውም ሆነ ማህበራዊ ትስስሩ እውን የሚሆነው ቀጣናው ሰላም ሲሆን መሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል። የአካባቢው ማህበረሰብ ለጋራ ኢኮኖሚያዊ ልማትና እድገታቸው ሲሉ ለሰላም መስፈን ለፍቅርና ለወንድማማችነት አብሮ ለማደግና ተደጋግፎ ለመጓዝ መስራት ይኖርባቸዋል። ከዚህ በተጓዳኝ የሶማሌ ክልል ውስጥ መሰረተ ልማት እምብዛም ባለመሆኑ የፌዴራል መንግሥት ይህን ታሳቢ ያደረገ ሥራ ማከናወን ይገባዋል።
የኢትዮጶያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ እንዳሉት፤ ከአዲስ አበባ አዳማ በመቀጠል በኢትዮጵያ ሁለተኛ የሆነው የድሬዳዋ ደወሌ የክፍያ መንገድ 220 ኪሎ ሜትር አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ኢቨር ሲስ የተባለ የቻይና ኩባንያ የቁጥጥር ሥራ እና የማማከር ሥራውን ደግሞ ሻንዶንግ ግሬት ሱፐርቪዥን እና ኮሰልቲንግ የተባለ ኩባንያ አከናውኗል። የመንገዱን ግንባታ ለማካሄድ አምስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል። ወጪውም 85 በመቶ ከቻይና ኤግዚት ባንክ 15 በመቶ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ሸፍኖታል።
እንደ ኢንጅነር ሀብታሙ ገለፃ፤ የድሬዳዋ ደወሌ መንገድ የቀድሞ በጠጠር መንገድ ደረጃ ሆኖ ነገር ግን ለትራንስፖርት አመቺ ስላልነበረ የተለያዩ የጎርፍና የመሬት መንሸራተት እያጋጠመው የትራፊክ መስተጓጎል ሲፈጥር ቆይቷል። አሽከርካሪዎችም ለተደጋጋሚ ብልሽት በመዳረጋቸው ላላስፈላጊ ወጪ ተዳርገዋል። አሁን በተደረገው የአስፋልት ማሻሻያ ሥራ ቀድሞ ከድሬዳዋ ደወሌ ለመድረስ ይፈጅ የነበረውን የአስር ሰዓት ጉዞ ወደ አራት ሰዓት ያሳጥረዋል። ከዚህ ባለፈም መቶ ኪሎ ሜትሮችን በመቀነስ
ከፍተኛ አገልግሎት እየሰጠ ያለውን አዳማ አዋሽ ጋላፊ መንገድ ኮሪደር ላይ ይደርስ የነበረውን መጨናነቅ ያስቀረዋል። ከጅቡቲ ወደብ ጋርም የሚያገኛኝ በመሆኑም የሁለቱን አገራት ግንኙነት ያሳድጋል።
የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ዳይሬክተር አቶ ሙስጠፋ ከድር በበኩላቸው እንዳሉት፤ ኢንተርፕራይዙ ላለፉት አምስት ዓመታት የአዲስ አዳማ የክፍያ መንገድ ተረክቦ ሲያስተዳድር ቆይቷል። በዚህም ከ30 ሚሊዮን ተሽከርካሪዎችን በማስተናገድ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ሰብስቧል። በዚህ ሂደት ያገኘውን ልምድ ተጠቅሞ የድሬዳዋ ደወሌ የክፍያ መንገድ ለማስተዳደር ሲረከብ በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት 438 መኪናዎችን በማስናገድ 90 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ዕቅድ ይዟል። መንገዱ ለቀጠናዊና ለአካባቢው ትስስር ተጠቃሚነትና ለአገሪቱ እድገት ጉልህ ሚና አለው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2011
ወንድወሰን ሽመልስ