ከቱሉ ቦሎ እስከ ኬላ የሚወስደው መንገድ 95 በመቶ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፡- ከቱሉ ቦሎ እስከ ኬላ 80 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የመንገድ ግንባታ 95 በመቶ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ቡታ ጅራ አካባቢ ኮንስትራክሽን ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ገዛኸኝ ወከለ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳሉት፤ ፕሮጀክቱ አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞለት በ2010 ዓ.ም ግንባታው የጀመረ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ጠቅላላ ግንባታው ከሚሸፍነው ሰማንያ ኪሎ ሜትር ውስጥ ሰባ አምስት ኪሎ ሜትር ወይም 95 በመቶ ተጠናቋል ብለዋል።

ይህ ፕሮጀክት መነሻውን ቱሉ ቦሎ ከተማ ላይ በማድረግ ሦስት ወረዳዎችን የሚያቆራርጥ ሲሆን፤ በስፍራው የሚገኙትን አጎራባች ከተሞች ከአዲስ አበባ ቡታጅራ ሆሳዕና፣ ከአዲስ አበባ ወልቂጤ ጅማ መስመር ያሉትን አውራ መንገዶች እንደሚያገናኝ አመልክተዋል።

የመንገድ ሥራው የቻይናው ዓለምአቀፍ ሥራ ተቋራጭ በሁናን ሁንዳ ሮድ ኤንድ ብሪጅ ኮርፖሬሽን እየተከናወነ ሲሆን፤ የግንባታ ጥራት እና ቁጥጥሩ በተባበሩት የምህንድስና አማካሪዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

መንገዱ ሲጠናቀቅ የሚሰጠው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የጎላ እንደሆነ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፤ አካባቢው ላይ በስፋት የሚመረቱ ምርቶች ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ባቄላ እና እንሰት ወደ ማዕከል ገበያ በማቅረብ ገበሬው የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም እንዲኖረው ዕድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

በተጨማሪም ይህ ደረጃውን የጠበቀ መንገድ ማህበራዊ መስተጋብሩን በማሳለጥ የጤና፣ትምህርት እና መሰል ተቋማት ተደራሽነታቸው በእጅጉ እንዲጨምር እንደሚያደርግም አብራርተዋል።

የፕሮጀክቱ ሙሉ ወጪ በፌዴራል መንግሥት የተሸፈነ ሲሆን፤ የመንገድ ግንባታውን በስድስት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

የቀረውን ሥራ በፍጥነት ለመጨረስ እንቅፋት የሆኑትን በሁለቱም ከተሞች (ቱሉቦሎ እና ኬላ) ያልተነሱ የውሃ መስመሮች፣ የኤሌክትሪክ መስመሮች፣እና መኖሪያ ቤቶች እንዲነሱ ለማድረግ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የፕሮጀክቱ ተጠሪ መሐንዲስ የሆኑት አቶ መኮንን ከበደ በበኩላቸው፤የመንገድ ሥራው 95 በመቶ መጠናቀቁን በመግለፅ፤ ከመንገድ ግንባታው ጋር ሦስት ጥራታቸውን የጠበቁ ድልድዮች መገንባታቸውን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ከተያዘለት በጀት የስምንት ሚሊዮን ብር ጭማሪ ማሳየቱን የገለጹ ሲሆን፤የዚህም ምክንያት የነዳጅ ዋጋ መናር እና ጥራት ያላቸው ማቴሪያሎች በየጊዜው በሚያሳዩት የዋጋ ጭማሪ እንደሆነ አስረድተዋል።

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You