የዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪክ አስጀማሪው ጀግና

በሆቴሎች፣ ካፌዎች፣ በተቋማት እና በሌሎች ቦታዎች የኢትዮጵያ መሪዎች ፎቶ ተሰቅሎ እናያለን። ሁሉም ማለት በሚያስችል ሁኔታ የሚጀመሩት ከአጼ ቴዎድሮስ ነው፡፡ ከአጼ ቴዎድሮስ ጀምሮ እስከ ወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ ድረስ ይታያሉ፡፡ የአጼ ቴዎድሮስ ልክ እንደ መነሻ ይሆናል ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያን መሪዎች በፎቶ የማወቅ ጥያቄ ቢጠየቅ አብዛኛው ሰው የሚያውቀው ከአጼ ቴዎድሮስ በኋላ ያሉትን ነው፡፡

የታሪክ ምሁራን እና ፖለቲከኞች ስለኢትዮጵያ ታሪክ እና የፖለቲካ ሁኔታ ሲያወሩ ብዙ ጊዜ መነሻቸውን የሚያደርጉት ከአጼ ቴዎድሮስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አንድነት፣ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ከአጼ ቴዎድሮስ እንደሚጀምር ተደርጎ ይነገራል፡፡ የዚህ ምክንያቱ የታሪክ ሰው ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ዘርፍ ላይ ያሉ ሰዎች እንደሚያውቁት አጼ ቴዎድሮስ በዘመነ መሳፍንት ተበታትና የነበረችዋን ኢትዮጵያን አንድ በማድረጋቸው ነው፡፡ በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን 156 ዓመታትን ወደኋላ መለስ ብለን በዚህ ሳምንት ልክ በዛሬዋ ቀን ራሳቸውን የሰውትን የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስን እናስታውሳለን፡፡

ነገሩ በአጭሩ እንዲህ ይጀምራል፡፡ የፋሲካ ማግሥት ዕለት መቅደላ አምባ ላይ የአፄ ቴዎድሮስ ሠራዊት እና በሎርድ ኔፒዬር የተመራው የእንግሊዝ ሠራዊት ጦርነት ገጥመው ድሉ የእንግሊዞች ሆነ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ አፄ ቴዎድሮስ በእንግሊዞች እጅ ከመውደቅ እራሳቸውን ማጥፋትን መርጠው ሽጉጣቸውን ጠጥተው ሞቱ፡፡ ቀብራቸውም በመቅደላ መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተፈጸመ፡፡ የዚህን ጀግና ታሪክና ሥራዎች ዘርዘር አድርገን እናስታውሳለን፡፡

ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ የጀግና ምሳሌ ናቸው፡፡ የቆራጥነትና ወኔ ማሳያ ናቸው፡፡ ስለጀግንነትና ቆራጥነት ሲነሳ በአጼ ቴዎድሮስ ይመስላል፡፡

የታሪክ ባለሙያዎችና ምሁራን የሚሉት አንድ ነገር አለ፡፡ አጼ ቴዎድሮስ የጦር ጀግና ብቻ አልነበሩም። ዘመናዊነትንና ሥልጣኔን የሚመኙ ባለራዕይ ነበሩ፡፡ በነገራችን ላይ ለዚህ መታሰቢያ የደበረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ጋፋት ኢንዱስትሪ በሚል የቴክኖሎጂ ንቅናቄ ጀምሮ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በየጊዜው ውይይቶችንም ያዘጋጃል፡፡ ከአራት ዓመታት በፊት ዩኒቨርሲቲው ባዘጋጀው አንድ የውይይት መድረክ ላይ ተሳታፊ ነበርኩ፡፡ ብዙ ምሁራን ሲያነሱ የነበረው አጼ ቴዎድሮስ የቴክኖሎጂ ራዕይ የነበራቸው መሆኑን ነው፡፡ ንባብና ሥልጣኔን ያስተዋውቁ ነበር፡፡ አብዛኛው ታሪካቸው ግን የሚታወቀው ከጦር ጀግንነት ጋር የተያያዘው ነው። የዚያን ዘመን ባህሪ ስለነበር ነው፡፡ አጼ ቴዎድሮስ ግን ከዘመን ቀድመው ቴክኖሎጂን የተመኙ ነበሩ፡፡

ስለ አጼ ቴዎድሮስ የታሪክ ጸሐፊዎችና ተመራማሪዎች በተለያየ ጊዜ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ እነዚህ የታሪክ ጸሐፊዎች የአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆኑ የውጭ አገራት ጸሐፊዎች ጭምር ናቸው። ጥቂቶችን መጠቃቀስ እንችላለን፡፡

ፕሮፌሰር ዶናልድ ክራሚ

‹‹ቴዎድሮስ የዘመናዊ ሥልጣኔ ሐሳብ የገባው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ንጉሥ ነበር።»

ቫልድማየር፡

‹‹ቴዎድሮስ፣ ኃይልና ታላቅነት ሳያንሰው፣ የምቾትና የቅምጥል ኑሮ የማያታልለው እንዲህ ያለ ንጉሥ ከቶ የት ይገኛል? የሁላችንም እምነት እግዚአብሔር ኃይሉን የለገሠው የሕዝቡንም ቁሣዊና መንፈሣዊ ደኅንነት ለማረጋገጥ የታጨ መሣሪያ መሆኑ ነው።»

በባህሩ ዘውዴ የታሪክ መጽሐፍ ላይ እንደተገኘው መረጃ፤ ቴዎድሮስ ለአገራቸው ዕውቀት መስፋፋት የነበራቸውን ጉጉት ለንግሥት ቪክቶሪያ በጻፉት ደብዳቤ እንዲህ በማለት ነበር የገለጹት።

(1) ጥር 1858፣«የኢትዮጵያ ሰዎች ድንቁርነታችን ዕውርነታችን ሳይሰሙት አይቀርም።»

(2) መጋቢት 1858፣ « አሁንም እኔ የምፈልገው ዕውር ነኝና ዓይኔ እንዲበራ ጥበብ ነው።»

(3) ሚያዝያ 1858፣ « የኢትዮጵያ ሰዎች ዕውር ነኝ፤ ዓይናችንን ያበሩልን፤ እግዚአብሔር በሰማይ ያብራልዎ!»

(4) ሚያዝያ 1859፣ «ከብት አለመፈለጌ ክብር ሆኜ አይደለም፤ ዕውር አህያ ነኝና ለጥበብ ዓይኔን ትከፍቱልኝ ብየ ነው እንጂ፣ በእግዚአብሔር ኃይል፤»

ከእነዚህ ደብዳቤዎች አንድ ነገር እንረዳለን፡፡ ይኸውም አጼ ቴዎድሮስ ለእውቀት ሽግግር የነበራቸውን ከፍተኛ ፍላጎት፡፡ ለአገሪቱ ዘመናዊነት ያደረጉት ጥረት እዚህ ላይ ግልጽ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለእርሳቸው የተጻፉ አንዳንድ መጻሕፍት እንደሚሉትም አጼ ቴዎድሮስ ከራሳቸው በላይ ለሌላው ያስባሉ፡፡ የግል ሕይወታቸው አያሳስባቸውም፡፡ ከአገር ውስጥ የታሪክ ጸሐፊዎችም ተክለጻድቅ መኩሪያ እንዲህ ብለው ነበር። ‹‹ ቴዎድሮስ፣ ሞትን የናቁ፣ ድሎትን የራቁ» ናቸው ሲሉ ይገልጿቸዋል።

በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ታስረው ከነበሩት እንግሊዛውያን ውስጥ አንዱ የነበረው ዶክተር ሔንሪ ብላንክ ስለአፄ ቴዎድሮስ እንዲህ ብሎ ነበር፡፡

‹‹ለመጀመሪያ ግዜ በ1852 ዓ.ም አፄ ቴዎድሮስን ሳገኛቸው ዕድሜያቸው 48 ይሆን ነበር! በሰላም ግዜ ለስላሳ ሆነው ደስ የሚያሰኙ በተቆጡ ግዜ ደግሞ በርበሬ መስለው የሚያስደነግጡና የሚያሸብሩ እሳተ ገሞራ የሚወረውሩ ነበሩ! በድንገት ሲቆጡ መላ አካላቸው የሰውን ልጅ ከፍ ካለ ድንጋጤ ላይ ይጥላል! ጠይሙ ገላቸው ሲኮሰኩስ … ስሱ ከንፈራቸው ሲንቀሳቀስና ፀጉራቸው ሲዘናፈል በጠቅላላ ሰውነታቸው የአንበሳነት ፀባይ የያዘ አስደንጋጭ ይሆናል!››

አፄ ቴዎድሮስ የንግሥና ስያሜያቸው ቴዎድሮስ እንዲሆን የመረጡት ‹‹ቴዎድሮስ የሚባል ንጉሥ ሲነግስ ኢትዮጵያን እስከ ባሕር ያሰፋታል፤ ፍርድና አስተዳደርንም ያስተካክላል›› የሚባል ትንቢት ስለነበር ሕዝቡ ‹‹ይህ ትንቢት የእርስዎ ነው›› እያሉ አሞካሿቸው። ‹‹ስሜን ቴዎድሮስ በሉ›› ብለው እንዳወጁ ታሪካቸውን ጽፎ በ1985 ያሳተመው ደራሲ ጳውሎስ ኞኞ ይነግረናል።

ጳውሎስ ‹‹ቴዎድሮስ እንዴት ያሉ ሰው ነበሩ?›› የሚለውን ጥያቄ በመፅሐፍ አንስቶ ‹‹ሁሉንም ጠባይ አሟልተው የያዙ ሰው ነበሩ። ይህም ማለት ደግ ናቸው፣ ክፉም ናቸው፣ ሩህሩህ ናቸው፣ ጨካኝም ናቸው፣ ፍርድ አዋቂ ናቸው፣ ፍርድ ገምድልም ናቸው›› ሲል ማስረጃ እያጣቀሰ ይገልፃቸዋል።

እስኪ የአፄ ቴዎድሮስን ፍርዶች እንመለከትና በዘመኑ የነበረውን የፍትህ ስርዓት በመጠኑ እንቃኝ። አጼ ቴዎድሮስ በሰጧቸው ፍርዶች መነሻነትም በትንቢት ተነግሮላቸዋል። እንደተባለው ፍርድና አስተዳደርን በማስተካከል ረገድ ምን ያህል ተሳክቶላቸው ነበር የሚለውን የራሳችንን ግንዛቤ እንይዛለን። ፍርዶቹ አንዳንዶቹ አስገራሚ፣ አንዳንዶቹ አሳዛኝና አስደንጋጭ አንዳንዶቹም አስተማሪ ናቸው።

የጋይንቱ ችሎት

አፄ ቴዎድሮስ ጎንደር ጋይንት ላይ ሰፍረው ስለ ወታደሮቻቸው በአርሶ አደሩ ላይ ተሰሪ አገቡአቸው። ተሰሪ ማግባት ማለት አርሶ አደሩ ወታደሮቹን እንዲቀልብ በየቤቱ መመደብ ማለት ነው። በወቅቱ የተደራጀ ጦር ሰራዊትና ለጦር ሰራዊቱ የሚመደብ የመንግሥት ባጀት ስላልነበር የነገስታቱ ጦር በየደረሰበት ያለው ሕዝብ እንዲቀልበው ይታዘዝ ነበር። ከእነኚህ የጋይንት እና የአካባቢው አርሶ አደር እንዲቀልባቸው ከታዘዘላቸው የቴዎድሮስ ወታደሮች መካከል አንዱ ወታደር አንዱን አርሶ አደር ገደለው። የሟች ዘመዶች ለአፄ ቴዎድሮስ አመለከቱ። አፄውም ወታደሮቻቸውን አፈርሳታ አስቀምጠው ገዳዩን እንዲጠቁሙ አዘዙ። ሆኖም ወታደሮቹ በሙሉ በአንድ ላይ አድመው ገዳዩን አናውቅም ብለው በቄስ እየተገዘቱ ስለወጡ ገዳዩ ሊታወቅ አልቻለም።

ቴዎድሮስ ገዳዩን ወታደር ለማወቅ የተደረገው ሙከራ ባለመሳካቱ ተናደው ‹‹ወታደር ብላ! ባላገር አብላ! ያልኩ እኔ ነኝ። ደመኛህም እኔ ነኝና እኔን ግደል›› ብለው ተነስተው ለከሳሽ ነገሩት። ከሳሽም ምኑ ሞኝ ‹‹እኔ ንጉስ መግደል አይቻለኝም›› አለ። ቴዎድሮስ እንግዲያውስ ደም በከንቱ ፈሶ አይቀርም ብለው ለሟች ወገኖች የደም ካሳ ገንዘብ ከፍለው አሰናበቷቸው።

የንጉሱ ትዕዛዝ

ቴዎድሮስ ለአንድ ታማኝ ወታደራቸው ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላልፈው ‹‹በፈርቃ በር በኩል እርጉዝ ሴት እንኳን ብትሆን እንዳታልፍ ጠንክረህ ጠብቅ›› አሉት።

ከጥቂት ቀናት በኋላ ደግሞ ሌላውን ወታደራቸውን ጠርተው ‹‹ፈረስ እያለዋወጥክ ይህን ወረቀት የጁ አድርሰህ በስድስት ቀን ውስጥ በአስቸኳይ ተመለስ›› ብለው አዘዙ። መልዕክተኛው ወታደር መልዕክቱን ለማድረስ ፈርቃ በር በሚባለው ቦታ ማለፍ ግድ ሆነበት። ፈረሱን እየጋለበ ፈርቃ በር ደረሰ። አስቀድሞ ማንንም እንዳያሳልፍ የታዘዘው የፈርቃ በር ዘበኛም የንጉሱን መልዕክት እንዳያልፍ ከለከለው።

መልዕክተኛው ‹‹ከንጉሡ በስድስት ቀን የጁ ደርሼ እንድመለስ በአስቸኳይ ተልኬ ነው ልለፍ›› አለው።

የፈረቃ በር ጠባቂም ‹‹ከንጉሥ ከተላከ አትከልክሉት ይለፍ የሚል በማህተም የተደገፈ የይለፍ ደብዳቤ ካለህ አሳየኝ እና አሳልፍሃለሁ ካልሆነ ግን እኔም የንጉሥ ትዕዛዝ ስላለብኝ አታልፍም›› ሲል መለሰለት።

መልዕክተኛው ወታደርም የንጉሥ ትዕዛዝ ሆኖበት በግድ አልፋለሁ ብሎ መንገድ ሲጀምር ጠባቂው ወታደር በጥይት ተኩሶ ገደለው።

የሟቹ መልዕክተኛ ወገኖችም ጉዳዩን ከሰሱና ለፍርድ አፄ ቴዎድሮስ ዘንድ ቀረቡ። በችሎት የተቀመጡት ፈራጆች ሁሉ ገዳይ ላይ ፈረዱ ‹‹እምቢ አልፋለሁ ቢልህ ለንጉሥ ማመልከት ሲኖርብህ እንዴት የንጉሥ መልዕክተኛ ትገላለህ! ለጥፋትህ ሞት ይገባሃል›› ሲሉ ፈረዱበት።

አንድ አስተዋይ ፈራጅ ከተቀመጡበት ተነስተው ‹‹መታየት የሚገባው ከንጉሡ የተሰጠው ትዕዛዝ ነው። ንጉሡ የፈርቃ በር ጠባቂን ጠርተው ያለኔ ፈቃድ እርጉዝ ሴት እንኳን እንዳታልፍ ብለው አዘዙ። መልዕክተኛውን ደግሞ በአስቸኳይ የጁ ደርሶ እንዲመጣ በማዘዛቸው በዚያ በፈርቃ በር በኩል ማለፍ ነበረበት። ስለዚህ ጥፋቱ የሚመለከተው ንጉሥ ነገስቱን ነው። ነገር ግን ብርሃን ናቸውና ምን ይደረግ›› ብለው ተቀመጡ።

እዚህ ጋር እንግዲህ በዚያ ዘመን የነበረውን ንጉሥ የሚያስተች ዲሞክራሲ ሳናደንቅ አናልፍም። የአስተዋዩ ፈራጅ ንግግር ብቻ ሳይሆን የንጉሡም ምላሽ የሚደንቅ ነው።

አፄው ምን አሉ መሰላችሁ! ከመቀመጫቸው ብድግ ብለው ‹‹እንዲህ ነው መሸምገል፣ ሁለት ጠጉር ማብቀል›› ብለው የአስተዋዩን ፈራጅ ፍርድ ካደነቁ በኋላ ‹‹በደለኛው እኔ ነኝ ፍረዱብኝ›› ብለው በተከሳሹ ወታደር ቦታ ወርደው ቆሙ። ከዛም ፈራጆች በሰጡት ፍርድ መሰረት ለሟች ወገኖች 500 ብር የደም ካሳ እንዲከፍሉ አፄ ቴዎደሮስ ላይ ፈረዱና ጉዳዩ በዚህ ተቋጨ።

የአጼ ቴዎድሮስ ታሪክ ለታሪክ ቅርብ በመሆኑ ሰዎች ብቻ የሚታወቅ አይደለም፡፡ የሕዝብ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ፤ ስለአጼ ቴዎድሮስ የተገጠሙ የለቅሶ እና የውደሳ ግጥሞች የሕዝብ ስነ ቃል እስከሚመስሉ ድረስ በብዙዎች ዘንድ ይታወቃሉ። በእርግጥ የሕዝብ ናቸው፤ ምክንያቱም በሕይወት ዘመናቸው ያወደሳቸውም፣ የሰደባቸውም ሕዝብ ነው። ሲሞቱ ያለቀሰላቸውም ሕዝብ ነው፡፡

እዚህ ላይ አስገራሚው ነገር ያ አስፈሪ ጀግና አጼ ቴዎድሮስ ይሰደቡ ነበር፡፡ አንዱን ብቻ እንጥቀስ።፡ አባቷን እና ወንድሟን በአጼ ቴዎድሮስ የተገደለባት አልቃሽ እንዲህ ብላለች፡፡

አንድ እግር በርበሬ መንቀል አቅቷችሁ

አንድዶ ለብልቦ አቃጥሎ ይፍጃችሁ

ይህንን ሲሰማ ያጓራል ለአመሉ

ማናትም ካላችሁ «ምንትዋብ ናት!»በሉ!

እንዲህ ያለችዋ ሴትዮ እንዳልተገደለችና ይልቁንም በእኔ ሞታ ዝናን ለማግኘት ነው ብለው አጼ ቴዎድሮስ እንደተናገሩ ተክለጻድቅ መኩሪያ ጽፈዋል፡፡ በሌላ በኩል ግን ከደጃች ጎሹ ጋር በነበራቸው የጉራምባ ጦርነት ላይ አንድ አዝማሪ አቋሙን ቀይሮ አጼ ቴዎድሮስን ለማወደስ የሚሞክር ግጥም ገጥሞ ‹‹እንዲህ አይነት አስመሳይና ወላዋይ አይጠቅምም›› ብለው አስገድለውታል፡፡ አዝማሪው መጀመሪያ ከደጃች ጎሹ ጎን ሆኖ እንዲህ አለ።

ያንዣብባል እንጂ መች ይዋጋል ካሳ

ወርደህ ጥመድበት ከሽንብራው ማሳ

ወዲያውኑ ድል ለአጼ ቴዎድሮስ ሆነች፡፡ የደጃች ጎሹ ጦር ተሸነፈ፡፡ ይህ አዝማሪ ጉዱ ፈላ፡፡ ያሸነፈውን እያወደሰ መኖር ፈለገ፡፡ ወዲያውም እንዲህ አለ፡፡

አወይ የአምላክ ቁጣ

አወይ የእግዜር ቁጣ

ሰው ወዳጁን ያማል የሚሰራው ሲያጣ

ዱላ ይገባዋል የአዝማሪ ቀልማጣ

በማለት አጼ ቴዎድሮስ ወዳጄ ናቸው አለ፡፡ ንጉሡ ግን እንዲህ አይነት ከሃዲ ወዳጅ የለኝም ብለው ‹‹ዱላ ይገባኛል›› ሲል ግዴለም ጥይት ይሁንልህ ተባለ፡፡

የአጼ ቴዎድሮስ ነገር ጳውሎስ ኞኞ እንዳለው ነው፡፡ ደግ ናቸው፣ ክፉም ናቸው፣ ሩህሩህ ናቸው፣ ጨካኝም ናቸው፡፡ ከወኔ እና ጀግንነታቸው በተጨማሪ ለሥልጣኔና ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ጥረት ያላቸው ባለራዕይ ነበሩ፡፡ ካሳ ኃይሉ (በንግሥና ስማቸው ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ) እነሆ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ አስጀማሪ ሆነው በታሪክ ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You