ቡልቂ፣ ተወልደው ፊደል የቆጠሩባት ትንሽዬ ከተማ ናት። ትምህርታቸውን የጀመሩት ቄስ ትምህርት ቤት ነው፣ እዛ እንዲገቡ የተደረገበት ዋናው ዓላማ ደግሞ ወደ ድቁናው እና ቅስናው እንዲመጡ ታስቦ ነው። ይሁንና ቄስ ትምህርት ቤት ጥቂት እንደቆዩ ወደመንግስት ትምህርት ቤት እንዲገቡ ተደረገ – የዛሬው የዘመን እንግዳችን ፕሮፌሰር ዘሪሁን ወልዱ (ዶ/ር)። እኚህ እንግዳችን፣ የትውልድ ስፍራቸው በቀድሞው አጠራሩ ጋሞ ጎፋ ጠቅላይ ግዛት፣ ጎፋ አውራጃ፣ ልዩ ስሟ ቡልቂ ተብላ በምትጠራ ከተማ ውስጥ ነው።
ትምህርታቸውን መማር የጀመሩት ገና በለጋ እድሜያቸው ነው። በቡልቂ ከተማ ውስጥ በወቅቱ የቄስ ትምህርት ቤትም ሆነ የመንግስት ትምህርት ቤት አገልግሎት የሚሰጡት በእኩልነት ነው። ሁለቱም ዘንድ የሚማሩ የተማሪዎች ቁጥር የሚተናነስ አይደለምና አስቀድመው በገቡበት የቄስ ትምህርት ቤት ፊደልን አሳምረው ከማወቃቸውም በላይ ማንበቡንም መጻፉን ተክነው መውጣት ቻሉ።
ጥቂት ጊዜ ከቆዩበት ከቄስ ትምህርት ቤት ወጥተው ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን በቡልቂ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሩ። ቀደም ብለው በቄስ ትምህርት ቤት ፊደል ቆጥረው ማንበብና መጻፉን በአግባቡ ተምረው ወደመንግስት ትምህርት በመግባታቸው ሁኔታዎች በጣም ቀለዋቸው እንደነበር እንግዳችን ይናገራሉ። ከዚህም የተነሳ ስድስት ዓመት ይፈጅ የነበረውን ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት በአራት ዓመት ውስጥ ነው። ሰባተኛ እና ስምንተኛን ሳውላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሩ።
በተለይ የስምንተኛ ክፍል ውጤታቸው አመርቂ የሚባል ነበረ። በመሆኑም በወቅቱ ከስምንት ወደዘጠኝ ያለፉ ተማሪዎች ጥሩ ውጤት ያላቸው ከሆነ ተወዳድረው በዊንጌት ትምህርት ቤት መቀጠል የሚያስችላቸው እድል ነበርና እርሳቸውም ተወዳደሩ። በወቅቱ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው በፈረንጆች አማካይነት ነበር። ይሁንና የእንግሊዝኛውን ቋንቋ ከፈረንጅ አፍ መስማቱ ለእርሳቸው እንግዳ ነገር ስለነበር በቅጡ ሊረዷቸው አልቻሉም። በዚሁ ምክንያት ሊሳካላቸው ባለመቻሉ ወደመጡበት ተመለሱ።
በወቅቱ በአንድ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ የሚኖረው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት /ሃይስኩል/ አንድ አሊያም ሁለት ቢሆን ነው። ስለዚህም የበጋሞ ጎፋ ጠቅላይ ግዛት የነበረው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንድ ሲሆን፣ እርሱም የሚገኘው አርባ ምንጭ ስለነበር፤ ከዘጠነኛ ጀምሮ ያለውን ትምህርታቸውን ለመማር ወዲዚያው አቀኑ። የመጡትም ከሌላ ከተማ በመሆኑ በአርባምንጭ ከተማ ቤት መከራየት ግድ ሆነባቸው።
ቤት የተከራዩት በእድሜ ከእርሳቸው ከሚበልጡ ተማሪዎች ጋር በመሆኑ ተጽዕኖ የሚያደርሱባቸው ከመሆኑም በተጨማሪ ከእድሜያቸው ትንሽነት የተነሳ የራሳቸውንም ምግብ በቅጡ አብስለው መመገብ ያቅታቸው ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ሙቀቱና ወባው ተደራርቦ የአርባ ምንጭ ቆይታቸውን በእጅጉ ፈታኝ እንዳደረገባቸው ይናገራሉ። የዚያን ጊዜ ቆይታቸው በሕይወታቸው ካጋጠማቸው ዋነኛው ፈታኝ ጊዜ እንደሆነም ያስታውሳሉ።
12ኛ ክፍል ሲደርሱ ሌላ እድል አጋጠማቸው። በወቅቱ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር የሚገኘው የበዕደማሪያም ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ከ11ኛ ክፍል ይወስድና አንድ ዓመት አሰልጥኖ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ሳይፈትን በቀጥታ ወደዩኒቨርሲቲው እንዲቀላቀሉ የሚደረግበት ስርዓት ነበር። እንግዳችን ፕሮፌሰር ዘሪሁን፣ በወቅቱ ወደበዕደማርያም ሊያስገባ የሚችለውን ፈተና በአስደናቂ ሁኔታ አልፈው ትምህርት ቤቱን ተቀላቀሉ።
12ኛ ክፍልን በጥሩ ሁኔታ የተማሩት እንግዳችን፣ ምንም እንኳ የ12ኛን ክፍል መልቀቂያ ፈተና ሳይፈተኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን መቀላቀል ቢቻልም እርሳቸው ግን ብቃታቸውን መፈተሽ ስለፈለጉ መልቀቂያ ፈተናውን ለመፈተን ቆረጡ። በወቅቱ ይፈተኑ የነበረው አምስት የትምህርት አይነት ሲሆን፣ ለዚህም ክፍያ ነበረውና ለእያንዳንዱ የትምህርት አይነት አምስት አምስት ብር በድምሩ 25 ብር ከፍለው ተፈተኑ፤ ባገኙትም ውጤት ለዩኒቨርሲቲም ብቁ መሆናቸውን አረጋገጡ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአራት ኪሎውን የሳይንስ ፋኩልቲ ከተቀላቀሉ በኋላ ያጠኑት ምርጫቸው የሆነውን ባዮሎጂ ነው። በዩኒቨርሲቲው ሶስት ዓመት ከተማሩ በኋላ ለአንድ ዓመት ከዩኒቨርሲቲ ውጪ ኅብረተሰቡን ማስተማርና ማገልገል የሚያስገድድ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ አገልግሎት (EUS) የሚባል መርሃግብር ስለነበር ለዚያ ተዘጋጁ።
ግዳጁም፣ ሕብረተሰብን ማገልገል ነበርና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ለመሆን ወደ ወለጋ ጠቅላይ ግዛት ጊምቢ ከተማ አቀኑ። ግዴታ የሆነውን ይህን አገልግሎት እንዳጠናቀቁም ወደዩኒቨርሲቲው ተመልሰው መማር እንደጀመሩ አብዮቱ ፈነዳ።
በወቅቱ እድገት በኅብረት የሚባለውን ዘመቻ በመቀላቀላቸው ምክንያት ዲግሪያቸውን ተምረው ያጠናቀቁት ከእነዚህ አገልግሎቶች በኋላ ነበር። እንዳጠናቀቁ ግን ጎበዝ ተማሪ ስለነበሩ እዛው ዩኒቨርሲቲ እንዲቀሩ ተደረገና መምህር መሆን ቻሉ።
ፕሮፌሰር ዘሪሁን፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የተማሩት በሚያስተምሩበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፣ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ያገገኙት ደግሞ በሲውድን ኡፕሳላ ዩኒቨርሲቲ በእጽዋት ስነ ምህዳር ላይ ሰርተው ነው።
አዲስ ዘመንም ከእኚህ ከ90 በላይ የምርምር ጽሑፎችን ብቻቸውንና ከሌሎች ጋር በመሆን በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ካሳተሙ አንጋፋ ምሁር ጋር ቆይታ አድርጓል። የዛሬው የዘመን እንግዳችን ፕሮፌሰር ዘሪሁን ወልዱ (ዶ/ር) ከ40 ዓመት በላይ የካበተ ልምድና ተሞክሮ ያላቸው፣ ተመራማሪና መምህርም ናቸው። ከእርሳቸው ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አጠናቅረን አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- በዕደማሪያም ተምሮ ዩኒቨርሲቲን ያጠናቀቀ ተማሪ ለተወሰነ ጊዜ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስተማር ግዴታ እንዳለበት ይታወቃልና እርስዎ ዩኒቨርሲቲ ሲቀሩ ያንን ባለማድረግዎ ያጋጠመዎ ነገር የለም?
ፕሮፌሰር ዘሪሁን (ዶ/ር)፡- እርግጥ ነው፤ በዕደማርያም የተማሩ ሁሉ ከዩኒቨርሲቲ ወጥተው የተማሩበትን ለማካካስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስተማር ግዴታ አለባቸው። እኔ ደግሞ ለማስተማር የቀረሁት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነው። ቆይታዬን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ካደረግሁ የተማርኩበትን ወጪ 550 ብር መክፈል ግዴታዬ ነበር። በመሆኑም ከዚህ ማምለጥ ስለማልችል ብሩን ከተለያየ ቦታ አሰባስቤ በመክፈሌ ከዕዳ ነጻ መሆን ቻልኩ።
ይህ ጊዜ 1969 ዓ.ም ነው፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ የቢሮ ለውጥ ሳላደርግ በአራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ አሁን ባየሻት ቢሮ ውስጥ እገኛለሁ። ምናልባት ከቢሮዋ የተለየሁበት ዘመን ቢኖር ለሶስተኛ ዲግሪ ወደስዊድን በሔድኩበት ጊዜ እና ለማጠናከሪያ ኮርሶች ወደጣሊያን ባቀናሁባቸው ጊዜ ብቻ ነው ማለት ይቻላል።
ሶስተኛ ዲግሪዬን የተማርኩበት የስዊድኑ ኡፕሳላ ዩኒቨርሲቲ፣ በእጽዋት ስነ ምህዳርና በአጠቃላይ ስለእጽዋት ትምህርት በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀ በመሆኑ ታላላቅ ሰዎች የተመራመሩበትና የሰሩበት ነው። ልክ ሌሎች ተማሪዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ በዚያው መቅረትን አማራጭ አላደረግኩም። ወደ አገሬ ተመልሼ ማስተማሬን ቀጠልኩ። ይሁንና በወቅቱ አገራችን የነበረችበትን ወከባ ሳጤነው በእርግጥ በመመለሴ “ስህተት ሰራሁ አንዴ?!” የሚል ሐሳብ ሰቅዞ ይዞኝ እንደነበር አልዘነጋም።
ይሁንና አገሬን ማገልገል እንዳለብኝ ስላመንኩ ማስተማሬን በችግር ውስጥም ቢሆን ቀጠልኩ። ሶስተኛ ዲግሪ አንድ ሰው ከሰራ በኋላ አንድ ዓመት ደግሞ ማጠናከሪያ በሚል መማር ስለሚቻል ለዚሁ ማጠናከሪያ ወደጣሊያን አቀናሁ። ይህን እድል ያገኘሁት ደግሞ ስዊድን ኡፕሳላ ዩኒቨርሲቲ በመማር ላይ ሳለሁ አብሮኝ በነበረ ጣሊያናዊ አማካኝነት ነው።
በጣሊያን የሚገኘው ትሬይስቴ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምረው ይህ ሰው፣ ባመቻቸልኝ እድል ማቲማቲካል ኢኮሎጂን ለመሰልጠን በቃሁ፤ ኡፕሳላ እንደሚታወቀው የስበት ማዕከል ነው። ተማራማሪዎች እየመጡ የሚያስተምሩበት ዩኒቨርሲቲ ነው፡። የጣሊያኑን አስተማሪ ያገኘሁትም በዚህ ምክንያት ነው።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ በእጽዋዕትም ሆነ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ ዙሪያ ብዙ አጥንተዋል፤ ተመራምረዋልም። ምን የተገኘ ውጤት አለ?
ፕሮፌሰር ዘሪሁን (ዶ/ር)፡– የኢትዮጵያ ስነ ምህዳር መራቆት የጀመረው ከብዙ ሺ ዓመት በፊት ነው። አንድ ምሁር ዋናውና ትልቁ ተግባሩ የምርምር ውጤቶችን ማውጣት ነው። የሚተገብረው ደግሞ ሌላ አካል ነው። በእኔ በኩል ያለብኝን ግዴታ የተወጣሁ ይመስለኛል። ምክንያቱም የምርምር ጽሑፎችን ማውጣትና የሰው ኃይል መፍጠር ነው። እኔ ባጠናሁት ዘርፍ በኢትዮጵያ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ዙሪያ የእኔ አሻራ አለ። በዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ተቋማትም ጭምር ይህ አሻራ አለ። በትግበራ ውስጥም የእኔ ኃላፊነት መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- እንደ አገር በርከት ያሉ የምርምር ማዕከላት መኖራቸው ይታወቃል። ከአገሪቱ ፍላጎት አኳያ ሲታይ ግን ውጤታማ ናቸው ማለት አያስደፍርም። ምክንያቱ ምንድን ነው ይላሉ?
ፕሮፌሰር ዘሪሁን (ዶ/ር)፡- በተወሰነ ሁኔታ ውጤታማነት አለ፤ ውጤታማነት ሙሉ ለሙሉ የለም ብሎ መደምደም አይቻልም። የተፈለገውን ያህል ውጤት ተገኝቷል ከተባለ ግን አነጋጋሪ ነው። ለምን የተፈለገው ውጤት መምጣት አቃተው? ከተባለ ኢትዮጵያን በተለያየ ዘመን ያስተዳደሩ መሪዎች የተለያየ ፍልስፍና ያላቸው ከመሆናቸው በተጨማሪ የፖለቲካ ዓላማቸውም የተለያየ በመሆኑ ነው። ከዚህ የተነሳ በአገራችን የተረጋጋ ዘመን ነበር ለማለት ይቸግራል።
የመንግስት ትኩረትና አስተሳሰብ እንዲሁም የሰው ኃይል ይቀያየራል። እስካሁን የመንግስት መስሪያ ቤት አንድ ወጥ ሆኖ ሊዘልቅ አልቻለም፤ ይለዋወጣል። አንድ የሆነ የትኩረት አቅጣጫ እና የተረጋጋ ነገር ኖሮ ቢሆን የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ይቻል ነበር። የሰከነ ፖሊሲ የወጣበት ዘመንም አለ ብዬ አላምንም። ስለዚህ ውጤቱ ሊቀንስ የቻለው በጥቅሉ የተረጋጋ ጊዜ ባለመኖሩ ነው ባይ ነኝ።
እንደሚታቀው የኢትዮጵያ ስነ ምህዳር የተጎሳቆለ ነው፤ ቢሆንም አቅሙ ግን ከፍተኛ ነው። ዛሬም ቢሆን ምግብ ለማምረት የሚያስችል አቅም አለው። ስነ ምህዳሩ እንዲያገግም በተቀናጀ መልኩ ቢሰራ ወደተፈለገው ውጤት እና ደረጃ መድረስ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ በተለይ ከቅርብ ዓመታት በኋላ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ተቋቁመዋል፤ ግብርና ላይ ማዕከል ያደረገ ግን ጥቂት ብቻ ነው፤ የጀርባ አጥንቱ ግብርና ለሆነ አገር ይህን ማድረጉ ተጽዕኖ አይኖረውም? በዚህ ላይ ትኩረት ተደርጎ ያልተሰራበት ምክንያት ምንድን ነው ብለው ያስባሉ?
ፕሮፌሰር ዘሪሁን (ዶ/ር)፡- ከዚህ በፊት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋና ሆኖ በየጠቅላይ ግዛቱ ለምሳሌ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በጤና ኮሌጅ፣ በዓለማያ ግብርና ኮሌጅ፣ በሐዋሳ ሳተላይት ኮሌጅ፣ ቀረብ ባሉ ዓመታት ደግሞ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በውሃ እንዲሁም ሌሎችም በየዘርፋቸው በትኩረት የሚያስተምሩ ነበር። በመሃከሉ ዩኒቨርሲቲዎችን ለማስፋፋት ተብሎ በታሰበበት ጊዜ ትንሽ ስህተት የተፈጠረ ይመስለኛል።
ችግሩ ሁሉም የተቋቋሙ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩት ተመሳሳይ ትምህርት (Harmonization Principle) መሆኑ ነው። የሚማሩትም ስርዓተ ትምህርት አንድ አይነት ነው። አዳዲሶቹ ዩኒቨርሲቲዎች ብዙውን ነገር የቀዱት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው። ስለዚህ ስርዓተ ትምህርቱ ሁሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ድግግሞሽና ቅጂ ነው። ትኩረት አድርገው በግብርናው በጤናው በውሃውና በሌላውም ይሰሩ የነበሩ ዩኒቨርሲቲዎች አሁን እንደ አዳዲሶቹ ሁሉ ተመሳሳይ ትምህርት ማስተማር ውስጥ ገቡ።
ይህ ሃርሞናይዜሽን (Harmonization) የሚባለው ፖሊሲ ነው የትኩረት አቅጣጫን ያጠፋው። የማስተማሪያ ጽሑፎች ሁሉ የተቀዱት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው። በአሁኑ ወቅት ግብርና የሚባለው ነገር ተመናምኖ በእያንዳንዱ ኮሌጅ እንደ አንድ አነስተኛ ዲፓርትመንት እየተሰጠ ነው። የሚደረገው የትምህርት ትኩረት በጣም የተመናመነ ነው። በግብርና ዘርፍ የሚያስተምረው የሰው ኃይል ሁሉ ተበታተነ። በአንጻሩ በጤና አካባቢ ያለው ደግሞ ደህና የሚባል ነው።
ወደነበረበት መምጣት የሚቻለው የተጀመረውን ተመሳሳይነት ያለው የትምህርት አሰጣጥን ሙሉ በሙሉ እርግፍ አድርጎ በመተው ነው። አለማያን ወደነበረበት የግብርና መመለስና ሌሎቹም ለምሳሌ በግብርናው ዘርፍ ልምድ ያላቸው እንደ ሐዋሳ፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲዎችን እንዲሁ ማድረግ ነው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም የደብረዘይቱ ኮሌጅ በራሱ የግብርና ነው። የእንስሳት ሕክምና ኮሌጁ ከዓለማያ ጋር ጎን ለጎን ይሰራ የነበረ ነው።
ተመሳሳይነት ያለውን ትምህርት ማስተማር ካልቀረ ሁሉም አንድ አይነት ስለሚሆን የሚጠቅም ዜጋ ለማፍራት አስቸጋሪ ይሆናል። ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ መዋል የማይችል፤ ነገር ግን የምሩቃንን ቁጥር ብቻ ዳጎስ የማድረግ አካሔድ ይሆናል። ስለዚህ አንድ አይነት ሰው መፍጠር አስፈላጊ አይደለም። ለምሳሌ የሰመራ እና የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲዎች በመስኖ ዘርፍና በአርብቶ አደር ዙሪያ ስለሚካሔዱ እንቅስቃሴዎች ላይ ቢያስተምሩ መልካም ነው። ሌላውን አይማር ማለት አይደለም እነዚህ ላይ ቢያተኩር ለማለት ነው። የአካባቢውን ትኩረት ያማከለ ስልጠና መስጠት ለአገርም ለአካባቢም የተሻለ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል እያደረገች ያለውን ጥረት እንዴት ያዩታል?
ፕሮፌሰር ዘሪሁን (ዶ/ር)፡- ጥረቱ የሚደነቅ ነው። በኢትዮጵያ ላይ ስላለው የምግብ እጥረት በሰፊው የተነገረው በ1966 ዓ.ም ንጉሱ በወደቁበት ዘመን ነው። ከዛ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የምግብ እጥረት አለ የሚባል ዜና አልነበረም። በእርግጥ ሊኖር ይችላል፤ አይነገርም አንጂ።
እኔ በዩኒቨርሲቲ የአንደኛ ዓመት ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ ጂኦግራፊ ስንማር የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 25 ሚሊዮን ብቻ ነበር። በአሁኑ ወቅት ከ120 ሚሊዮን የዘለለ ነውና ቁጥሩ በጣም እያሻቀበ መጥቷል። ከሕዝብ ቁጥር ማደግ ጎን ለጎን የምግብ ፍላጎትን የሚያሟላ ነገር መፈጠር አለበት። በ25 ሚሊዮንም ጊዜ ሆነ አሁን ረሃብ አለ።
የምግብ ፍላጎታችንን ማሟላት አለብን በሚል በመንግስት ደረጃ በፖሊሲ ተይዞ መነሳቱ እንዲያውም ቀደም ሲል መሆን የነበረበት ሲሆን፣ አሁን መሆኑም ቢሆን አትራፊ ነው።
በምግብ ራሳችንን መቻል እንችላለን። ምክንያቱም ብዙ ሊታረሱና ሊለሙ የሚችሉ ቦታዎች አሉን። ይህን ስናደርግ ደግሞ ያለውን ስነ ምህዳር ጠብቀን መሆን አለበት። የራሳችንን የምግብ ፍላጎት ካማሟላት አልፈን ለውጪ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል አቅም አለን። ስለዚህ ይህ እንቅስቀቃሴ መጀመሩ በጣም የሚያበረታታ ነው፡።
እዚህ ላይ ግን ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን ልማታችን በአንድ የሰብል አይነት ብቻ እንዳይሆን ነው። በአሁኑ ወቅት በስፋት እየተሰራበት ያለው ስንዴ ላይ ነው። ጤፍ፣ ገብስ፣ አተር እና ሌሎችም ላይ መስራት አለብን። የአንዱን ማሳ ለስንዴ ስናደርግ ያኛው የሰብል አይነት ሊወደድ ይችላል። ጤፍና አተሩ ለኢትዮጵያውያኑ ምግብ የሚያስፈልጉ ናቸው። ስለዚህ ለስንዴ የሚሰጠውን ያህል ትኩረት ለአተሩም ለባቄላውም ሆነ ለጤፉና ለሌሎችም ቢሰጥ አስተማማኝ ይሆናል።
ስንዴ የዓለም የምግብ ትኩረት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የምግብ ሉዓላዊነት የሚባል ነገር ደግሞ አለ። ሉዓላዊ ሕዝብ እንደመሆናቸው የምግብ ሉዓላዊነታችንንም በማስጠበቁ ረገድ ልንሰራ ይገባል። ይህ የምግብ ሉዓላዊነት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ በእንጀራ፣ በሽሮ፣ በጎመን፣ በቅመማቅመም የሚገለጽ ነው፤ ወደደቡብ ሲመጣ ደግሞ እንሰትና ስራስር የምግብ ሉዓላዊነት የሚገለጽበት ነው።
ለምሳሌ አንድ ሶስተኛ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ቢያንስ በቀን አንዴ የእንሰት ውጤት ይመገባል። ስለዚህ እንሰት ሊዘነጋ አይገባም። እንሰትን አላስተዋወቅንም፤ ገና ከኢትዮጵያ አልወጣም። ስለሆነም አሁን ራስን በምግብ ለመቻል የሚደረገው ጥረት ጥሩ ነው፤ ሚዛናዊነትን መጠበቅ ደግሞ አስፈላጊ ነው።
አዲስ ዘመን፡- መንግስት እንደ አገር ኢንቨስት ያደረገባቸው ልምድ ያላቸው የዘርፉ ተመራማሪዎች በአገር ደረጃ ችግር ሲመጣ እንኳን ከልምዳቸው ተነስተው አያማክሩም። ይህ ከምን የመነጨ ይመስልዎታል?
ፕሮፌሰር ዘሪሁን (ዶ/ር)፡– እንደ እኔ አተያይ ከሆነ ይህ ጉዳይ ከሁለት ምክንያት የመነጨ ነው። አንደኛው የመንግስት ባለስልጣናት የመቀያየርና አገር ውስጥ ያለውን እምቅ እውቀት መኖሩንም ያለመገንዘብ ሊሆን ይችላል። ሌላው ደግሞ ምሁሩ ራሱ ተሰባስቦ “አለን፤ እናማክር” ሊል ይገባል። አለመቀራረቡ የመጣው ከአንድ አቅጣጫ ብቻ ሳይሆን ከሁለቱም ወገን የጎደለ ይመስለኛል። መንግስትም ረጋ ብሎ አስቦ “በሰው ኃይል መቀያየር ምክንያት ያለኝን አቅም ዘንግቼው ይሆን?” ብሎ ሊያጤን ይገባል።
ምናልባትም “መንግስት አርቆኛል፤ ብዙም አላቀረበኝም” የሚለውን ቁዘማ ትቶ ደፍሮ መቅረብ የሚያስፈልገግ ይመስለኛል። ያንን ደግሞ የሚያሰባስብ ኃይል ቢኖር ጥሩ ነው። በዚህ መልኩ ከሁለት ወገን ለመቀራረብ ጥረት ማድረግ ነው እንጂ ዝም ብሎ በጉዳዩ ብቻ እየተቆጩ መኖር ለሕዝብም ለመንግስትም ሆነ ለወደፊቱ ትውልድ አይጠቅምም። በተለይ ትውልዱ ከአንጋፋ ምሁራን መጠቀም የሚችልበት ሁኔታ አሁን ነው። ምክንያቱም አንድ ሰው ዘላለማዊ አይደለም። ስለዚህ ውስን የሆነው ምሁር ልምዱን ሊያካፍል ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከምትታወቅባቸው ምርቶች ዋነኛው ጤፍ ነው፤ አሁን አሁን ምርቱ ባህር ተሻግሮ በመሄዱ ‹‹ምርቱ የእኛ ነው›› የሚሉ ሀገራት ተፈጥረዋል። ከዚህ አኳያ ምን ይላሉ?
ፕሮፌሰር ዘሪሁን (ዶ/ር)፡- የዓለም ሕግጋት አሉ። ጥቅም ማግኘት ለሚችሉ አካላት ጉዳዩ ክፍት መሆን አለበት። የራስን ብዝሃ ሕይወት ደብቆ አልሰጥም ማለት ግን አይቻልም። ያለውን ሕግ ጥሶ ደግሞ መኖር አይቻልም። እናም ከሌላው አገር እንወስዳለን። እነርሱም ከእኛ ይወስዳሉ።
በአገራችን የምንመገባቸው ብዙዎቹ ምግቦች ከሌላ አገር ያገኘናቸው ናቸው። ለምሳሌ ፓፓያ፣ ብርቱካን፣ ሙዝ፣ ድንች፣ ስኳር ድንች፣ ሽንኩርት፣ ቃሪያ የእኛ አይደሉም። ከሰጠናቸው ይልቅ የወሰድናቸው ይበልጣሉ። አሁንም የምናገኛቸው ሊኖሩ ይችላሉ።
በእርግጥ ስንዴም ሆነ ገብስ ከሌላ ቦታ የመጣ ይሁን እንጂ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ የዳበረ ነው። እንዲያውም በአንድ ወቅት ከኢትዮጵያ የተወሰደ ገብስ የዓለምን ቢራ ከመጥፋት የታደገ ነው ይባላል። እንደሚታወቀው ገብስ በዋግ ይመታል። የአውሮፓንና የአሜሪካንን የቢራ ፋብሪካ ከመጥፋት ያደነው የዋግን በሽታ መከላከል የሚችል ገብስ ከኢትዮጵያ ተወስዶ ነው።
እሱ ሕጉ ከመውጣቱ በፊት ስለተወሰደ አሁን ልንጠይቅበት አንችልም። ሌሎች ብዙ ትኩረት ያልተሰጠባቸው የቅመማቅመም ዝርያዎችና እጽዋት አሉ። ነገር ግን እንሰትን ጨምሮ እነርሱን ማስተዋወቅ ይኖርብናል። ይህን ስናደርግ ከጥቅሙ ተካፋይ የምንሆንበትን ሁኔታ በማመቻቸት ነው።
ስለዚህ “ጤፍ የእኛ ነውና አንሰጥም፣ አናስነካም” ማለት አንችልም። ከጤፍ የሚገኘውን ጥቅም ግን መጋራት አለብን። ጤፍን የወሰደ አካልም ከእኛ ጋር የመጋራት ግዴታ አለበት። እንዲያውም ጤፍ አምራቾቹ ኢትዮጵያና ኤርትራ ናቸው ወደሚልም ተመጥቷል።
ይህ የመጋራት ጉዳይ ግን በእርግጥ አሁን የወጣ ሕግ ነው፤ ከዚህ በፊት ቃሪያ፣ ድንች፣ ሽኩርትና ሌላ ሌላውን ያገኘነው ከሕጉ በፊት በመሆኑ ነው። ይሁንና ከዚህ በኋላ ለሚሆነው እንጂ ወደኋላ ተመልሶ የሚጠይቀን የለም። እኛም ከዚህ በፊት ለወጣው ሳይሆን በቀጣይ ለሚወጣው እንዲሁ ተጠቃሚ የምንሆንበት አሰራር አለ።
ጤፍና ቡና እንዴት እንደተወሰሰዱ አይታወቅም፤ ከዚህ በኋላ ግን ሌሎች ለምሳሌ በቅመማቅመም እና በእንሰት ደረጃ ብዙ ብዝሃ ሕይወት ስላሉን ከእኛ የተወሰዱ ስለመሆናቸው ተረጋግጦ የዚያ ጥቅም ተካፋይ መሆን ያስችለናል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- የዓባይ ግድብ አካባቢ የምንጣሮ ስራ ጥናት ላይ ተሳትፈዋል፤ ጥናቱ ምን ይመስል ነበር ?
ፕሮፌሰር ዘሪሁን (ዶ/ር)፡- የዓባይ ግድብ በሚሰራ ጊዜ የደን ምንጣሮን በተመለከተ ሊደርስ የሚችለው ተጽዕኖ ምን ሊሆን ይችላል? በሚለው ጥናት ተካሄዷል። በወቅቱ የኢትዮጵያ ፓናል ኦፍ ኤክስፐርት የሚባል የግድቡ አማካሪም የጥናቱ አካል ነበር። በወቅቱ የደን ምንጣሮ ሊያድረስ የሚችለውን ተጽዕኖ አጥንቼ በስራ ላይ ውሏል።
ደኑ ባይመነጠር ሐይቁ ላይ ሊደርስ የሚችለው ተጽዕኖ ምን አይነት ነው? የሚለውን ነገር ስናጤን መመንጠሩና መነሳቱ ግዴታ መሆኑ ታውቆ ነው የተመነጠረው። መመንጠሩ ወሳኝ እና የግድ የሆነ ተግባር ነው።
በጉዳዩ ላይ ምርምርና ጥቆማ አድርጌያለሁ። ምን ያህል ደን እንደሚመነጠርም ጭምር። ከዚያ ከሚመነጠረው ደን ምን ያህል ክብደት ያለው የእጽዋት ስብስብ ነው የሚነሳው? ያ መነሳት ያለበት የእጽዋዕት ስብስብ እዛው ቢቀር ምን የሚያመጣው ጉዳትስ አለው? የሚለውንም ጭምር ለማየት እና ለማጥናት ሞክሬለሁ።
የደኑ መመንጠር ለሐይቁ ዘላቂነት ችግር እንዳይፈጥር ትልቅ ሚና ያለው ነው። ከእኛ አልፎ ደግሞ በሱዳን፣ በግብጽ በተለይም ደግሞ በዓባይ ውሃ ላይ ደኑ ባይመነጠር ኖሮ ትልቅ ጉዳት የሚያደርስ ይሆናል። ስለዚህ በእኛም በጎረቤቶቻችንን ላይም የሚያደርሰውን ጥፋት ደኑ በመመመንጠር መዳን አለበት። ደግሞም ግዴታም አለብን።
ደኑ ሳይመነጠር ውሃው ቢተኛ የሚያመጣው ከባድ ችግር አለ። ብስባሹ እዚያ ውሃ ውስጥ ያሉትን እንደዓሳ አይነት እንሰሳትን ሊገድል ይችላል። ብስባሹ ‘ሚቴይን’ የተባለ አደገኛ ጋዝ ስለሚፈጥር የአየር ንብረት ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ሚቴይን የካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ሃያ ጊዜ የአየር ንብረት ለውጥ የማምጣት ኃይል አለው። ከዚህ የተነሳ ውሃ ራሱ የባዮ ጋዝ ክምችት ሆነ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለ47 ዓመታት ያህል በማገልገል ላይ ይገኛሉና አሁን ያሉበት ሁኔታ እንዴት ይገለጻል?
ፕሮፌሰር ዘሪሁን (ዶ/ር)፡- በአሁኑ ወቅት እየሰራሁ ያለው በማስተማር እና በምርምር ስራ ላይ ነው። የማስተምረው የሁለተኛ እና የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ነው። ማስተማር ብቻም ሳይሆን የሚሰሯቸውን ምርምሮች መከታተልም ሌላው ስራዬ ነው፤ አማክራለሁም።
አሁን እያስተማርኩ ያለሁት ምንም እንኳ የእጽዋት ስነ ምህዳር ቢሆንም፤ በጣሊያኑ ትሬይሰቴ ዩኒቨርሲቲ በሰለጠንኩበት ሒሳብ ነክ የሆነ በእጽዋት ቀመር ላይ ነው። ትሬይስቴ ዩኒቨርሲቲ በሕይወቴ ላይ ያመጣው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። ወደጣሊያን እንዳቀና እና እንድሰለጥን ካደረገኝ ከፕሮፌሰር ኢንሪኮ ፌዎሊ ጋር በርካታ ጽሑፎችን በዓለማቀፍ ጆርናሎች ላይ ለማሳተም በቅቻለሁ።
እነዚያ ጽሑፎችም በብዙዎቹ ተማሪዎች ዘንድ የሚጠቀሱ ናቸው። ለ12 ዓመታት በተከታታይ ለሁለት ለሁለት ወር ወደ ትሬይስቴ ዩኒቨርሲቲ አቀና ነበር። እኔ በስዊድን ከቆየሁበት ትምህርት ጥልቀት ይልቅ በጣሊያኑ ዩኒቨርሲቲ ያደረግኳቸው ጥናትና ምርምሮች ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው ናቸው።
ከዚያ በኋላ ከፕሮፌሰር ኢኒሪኮ ጋር በመሆን ከአውሮፓ ሕብረት ለአራት ዓመት በብዙ ሺ ዩሮ የሚቆጠር እርዳታ ለምርምር ስራው ማምጣት ችለናል። ዋናው ስራችን በትግራይ፣ በወሎ ከአገራችን አልፎ ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ በታንዛኒያ፣ በኬንያ የተራቆተ ስነ ምሕዳር የሚያገግምበት መንገድ ለመመራመር የሚያግዝ ድጋፍ መሰብሰብ ያስቻለ ነው። ይህም ስራ የዘለቀው ለአራት ዓመት ነው። እኔ ብቻዬንም ሆነ ከሌሎች ጋር በመሆን ሳሳትማቸው የነበሩ የምርምር ጽሑፎች ሁሉም የሚያጠነጥኑት ስለ ስነ ምህዳር ማገገም ላይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልእክት ካለ?
ፕሮፌሰር ዘሪሁን (ዶ/ር)፡- ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት፤ አንድ ምሁር ከመመራመርና ከማጥናት ጎን ለጎን ቁጭት ሊኖረው ይገባል። እኔ በመጀመሪያ ከውጭ አገር ትምህርቴን ጨርሼ ስመጣ የነበረኝን ቁጭት ሙሉ በሙሉ የማሟላት አጋጣሚውን አላገኘሁም፡። ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው የተፈጠረበትንና የተማረበትን ዓላማ ለማሟላት በቁጭት ውስጥ መሆን አለበት።
እኔ ለምሳሌ ሕይወቴን ወደኋላ መለስ ብዬ የተቆጨሁትን በሙሉ አሟልቻለሁ ወይ ስል የዩኒቨርሲቲውን የመማር ማስተማር ሒደትና የሰው ኃይል ለመጨመር ያስብኩትን ቁጭት ከሞላ ጎደል ያሟላሁ ይመስለለኛል።
ከስነ ምህዳር ማገገም ጋር ያለኝን ቁጭት በተለያዩ አጋጣሚዎች ተሳክተዋል የሚል እምነት የለኝም። በእርግጥ አንድ ሰው ብቻውን በራሱ ምንም ነገር ማድረግ አይችልም። በማስተማሩ ዓለም የፈጠርኩት የሰው ኃይልም በዚህ ቁጭት ውስጥ ገብቶ የተቻለውን ማድረግ ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን፡- ፈቃደኛ ሆነው ከሕይወት ተሞክሮዎ ስላካፈሉን ከልብ አመሰግናለሁ።
ፕሮፌሰር ዘሪሁን (ዶ/ር)፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/2016 ዓ.ም