የብዙዎች ተስፋ የሆነው የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎት

ሻምበል አሳዬ ጥላሁን ትውልድና እድገታቸው በጅማ ከተማ ነው፡፡ በሀገር መከላከያ ሠራዊት በውትድርና ሀገራቸውን ለሃያ ዓመት አገልግለዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በሰሜኑ ክፍል በነበረው ጦርነት ሁለት እግራቸው ላይ ጉዳት ደርሶባቸው ነበር፡፡ በሕይወታቸው ይገጥመኛል ብለው ያላሰቡት ነገር ስለገጠማቸው ሕይወት ፊቷን ያዞረችባቸው መስሎ ተሰማቸው፡፡

በአንድ በኩል ሕይወታቸው መትረፉም የፈጠረባቸው የማይደብቁት የደስታ ስሜት ነበራቸው፡፡ አካል ጉዳተኝነትን ያልተለማመዱት ሻምበል አሳዬ ብዙ ምስቅልቅሎች ገጥሟቸዋል፡፡ በደረሰባቸው የሥነ ልቦና ጉዳት ከቤት ለመውጣት ፍላጎታቸው ትንሽ ነበር፡፡ ሰዎችን ለማግኘትም ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ በገጠማቸው ችግር የአንዳንድ ሰዎችን አስተሳሰብ በሚገባ የመታዘብ ዕድል አጋጥሟቸዋል፡፡

ዛሬ ላይ ሻምበል አሳዬ በመንግሥት በኩል ባገኙት የአካል ድጋፍ አገልግሎት ተስፋቸው ለምልሟል፡፡ ራሳቸውንም ‹‹እኔ ዕድለኛ ነኝ፡፡›› በማለት ይገልጻሉ፡፡ ትናንት እርሳቸውን ሲታገሏቸው የነበሩ ክፉ ሃሳቦች ሁሉ እንደ ጉም በነው ጠፍተዋል፡፡ በተስፋ ተሞልተው ነገን ሠርተው መኖር እንደሚችሉም በሚገባ አምነዋል፡፡ እርሳቸው ያገኙት ድጋፍ ለሌሎች በስፋት እንዲዳረስ ይፈልጋሉ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎት›› ተቋም ለሌሎች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ እንዲያገኙ እስከታችኛው የመንግሥት መዋቅር እና በመላው ሀገሪቱ ተስፋፍቶ ማየትን ይሻሉ፡፡

ሻምበል አሳዬ ካነሱት ጉዳይ ጋር በተያያዘ ብዙ ነገሮችን ታዝበዋል፡፡ አካል ጉዳት ከገጠማቸው በኋላ ወደ ተለያዩ ተቋማት ለተለያዩ ጉዳዮች ሲያመሩ ተቋሞቹ ምቹ እንዳልሆኑ አይተዋል፡፡ የሕዝብ ትራንስፖርት ለመጠቀም መንገዶች ምቹ እንዳልሆኑና ለአካል ጉዳተኞች አመቺ ሆነው መሠራት እንዳለባቸው ያመለክታሉ፡፡ ጤናማ ሰው በሁሉም ሰው ዘንድ ተፈላጊ ቢሆንም በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚደርሰው ጫና ከበድ ይላል የሚሉት ሻምበል አሳዬ፤ ከዚህ እንፃር ለሁሉም አካል ጉዳተኞች አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ይጠቁማሉ፡፡

ትናንት በውትድርና ሀገራቸውን ያገለገሉት ሻምበል አሳዬ ኑሯቸውን የሚገፉት መንግሥት በሚከፍላቸው የጡረታ ክፍያ ነው፡፡ ካላቸው ሻምበልነት ማዕረግ አኳያ ‹‹አንቱ›› ተብለው ተገለፁ እንጂ በመካከለኛ ዕድሜ ያሉ ናቸውና ሥራ የመሥራት አቅሙም ሆነ ፍላጎታቸው ከፍተኛ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ መንግሥትም ለእርሳቸውና እንደርሳቸው ጉዳት ለገጠማቸው ዜጎች ሥራ የሚሠሩበት ሁኔታ እንዲያመቻችላቸው ይጠይቃሉ፡፡

የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ታሪኩ ታደሰ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት እንደ ሻምበል አሳዬ ያሉትን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ድጋፍ ለሚሹ ሁሉ አገልግሎት ለመስጠት የተለያዩ የሰው ሠራሽ አካላት እና አጋዥ ቴክኖሎጂዎችን ማምረት፣ መጠገን እና ማቅረብ ብሎም ሌሎች የተሐድሶ አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ለመስጠት ዓላማ አንግቦ እየሠራ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር በሰው ሠራሽ እና በአካል ድጋፍ አገልግሎት የአጭርና የረጅም ጊዜ ሥልጠና መስጠት እና ጥናትና ምርምር በማድረግ በቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ አገልግሎት መስጠት ከዓላማዎቹ መካከል ይጠቀሳል፡፡

ተቋሙ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል የአካል ተሐድሶ ሕክምና፤ የፕሮስቴቲክ እና ኦርቶቲክ ተሐድሶ ሕክምና አገልግሎት፣ የፊዚዮ ቴራፒ፣ ኦኮፔሽናል ቴራፒ ተሐድሶ ሕክምና አገልግሎት፣ የፊዚዮ ቴራፒ መለማመጃ ምርቶች እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ በአጋዥ ቴክኖሎጂ ምርትና መገጣጠም ደግሞ በቴርሞ ፕላስቲክ ሥራ ክፍል የሚሰጡ አገልግሎቶች፤ የአርቴፊሻል ግብዓት (ኮምፖነንት) ምርት፣ የክራንች እጄታ ምርት፤ የዊልቸር ግብዓት ምርት (ባላንስ ቦርድ፣ ዊል ባር፣ ላደር፣ ፊንገር እና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ከአዕምሮ ተሐድሶ ሕክምና አገልግሎት ጋር በተያያዘም ገፈርሳ አካባቢ በሚገኘው የአዕምሮ ማገገሚያ ሕክምና አገልግሎት በተመላላሽ እና በአስተኝቶ ሕክምና፣ የአርት ቴራፒ አገልግሎት፣ የሻማ (የጥልፍ) ሥራ አገልግሎት፣ የማኅበራዊ፣ የሥነ ልቦና ድጋፍና ክትትል አገልግሎት፣ የሱስ ሕክምና አገልግሎት በተመላላሽ እና በአስተኝቶ ሕክምና ይሰጣል፡፡ ለጊዜው ሦስት መቶ አልጋ ያለው ሲሆን፤ ታካሚዎች ወይም በሱስ የተጠቁ ዜጎችን ሦስት እና ከዛ ወራት በላይ ሆኗቸው አገግመው እንዲመለሱ እየሠራ ይገኛል፡፡

ዋና ሥራ አስፈፃሚው እንደሚያብራሩት ተቋሙ አሁን ላይ በሁለት ቦታዎች ላይ ተገድቦ ይሥራ እንጂ ለወደፊት ግን በመመሪያው መሠረት ሁሉንም የማገገሚያ አገልግሎት ለመስጠት እቅድ አለው፡፡ የሰው ልጅ የተለያየ ድጋፍ ይሻል፡፡ በተፈጥሮ ምክንያት ምንም ዓይነት ድጋፍ ባይሻ እንኳን በዕድሜ መግፋት ብቻ የአካል ድጋፍ ፈላጊ ሆኖ ይታያል፡፡ በዚህ መነሻነት ተቋሙ የተለያዩ የአካል ድጋፍ መሣሪያዎችን እንዲሁም ማሽኖችን እና ጥሬ እቃዎችን ከውጭ በማስመጣት እየሠራ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሀገር ውስጥ ያሉትን ግብዓቶችን በመጠቀምም አገልግሎቱን ይሰጣል፡፡ ይሁን እንጂ ከውጭ የሚመጡ ግብዓቶች በሀገር ውስጥ ካልተተኩ ኪሳራ ሊያጋጥም ይችላል፡፡

ምንም እንኳን በኢትዮጵያ የአካል ድጋፍ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ አልነበረም ባይባልም በግለሰቦችም ይሁን በአንዳንድ ድርጅቶች አማካኝነት በተለያየ መንገድ አገልግሎቱ ይሠጥ ነበር፡፡ ነገር ግን ቀጣይነት አልነበረውም፡፡ የኢትዮጵያ የአካል ድጋፍ አገልግሎትም እንደ አዲስ በመቋቋም የአካል ድጋፍ አገልግሎት ከዚህ ቀደም ትኩረት ያልተሰጠው መሆኑን በመገንዘብ ዛሬ አበረታች የሚባሉ ጅምሮች አሉ፡፡ ተቋሙም ከኢትዮጵያ አልፎ ምሥራቅ አፍሪካን የማገልገል ሃሳብ አለው፡፡ ሆኖም ያደጉት ሀገራት የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ ብዙ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ ድጋፎችን ከውጭ ሀገራት ከመጠበቅ ይልቅ በሀገር ውስጥ ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት መሥራት ይገባል፡፡

በኢትዮጵያ አካል ድጋፍ የሚሹ ሰዎች ቁጥር ሃያ ሚሊዮን እንደሆነ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያትታል፡፡ ይህ ቁጥር ከሁለት ዓመት በፊት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ከተከሰተው ጦርነት በፊት የነበረ እንደመሆኑ በሰው ሠራሽ አደጋዎች፣በግጭቶች፣ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች እና ከዕድሜ መግፋት ጋር በተያያዘ ቁጥሩ ከዚህም ሊልቅ ይችላል፡፡ በአሁን ወቅት ተቋሙ በቀን ከ40 በላይ ድጋፍ የሚሹ አካል ጉዳተኞችን በመቀበል ላይ ቢገኝም ሥራው ጊዜ፣ ትኩረት፣ ግብዓት እና የበጀት አቅም የሚፈልግ ነው፡፡ ካለው ድጋፍ ፈላጊ ቁጥር አንጻር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶበት ሊሠራ ይገባል፡፡

የተቋሙ ዓላማ ከኢትዮጵያ አልፎ ጎረቤት አገራትን ጭምር ማገልገል እንደመሆኑ መጠን በቀጣይ ቅርንጫፎችን በተለያዩ ክልሎች ላይ በማስፋፋት፣ በትምህርት እና በምርምር ከመሥራት ባሻገር ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል ፡፡

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2016 ዓ.ም

Recommended For You