ሞሪንጋ ለመቀንጨር ችግር ሁነኛ መፍትሔ እንደሆነ ተገለጸ

አዲስ አበባ፡– ሞሪንጋ ወይም ሺፈራው ለሕጻናት የመቀንጨር ችግር ሁነኛ መፍትሔ እንደሆነ ተነገረ፡፡
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የምግብ ሳይንስና ሥነ ምግብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አልጋነሽ ቶላ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ሞሪንጋ የመቀንጨር ችግርን መከላከል የሚያስችል የንጥረ ነገር ይዘት ያለው ቅጠል ነው፡፡

በሀገራችን እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ 38 ከመቶ ያህል ሕጻናት የመቀንጨር ችግር እንደሚገጥማቸው ያነሱት ዶ/ሯ፣ ሞሪንጋ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ሁነኛ መፍትሔ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡
በአይረን፣ ዚንክ፣ ፕሮቲን፣ ፖታሺየም፣ ካልሺየምና ሌሎችም ንጥረ ነገሮች የበለጸገው ሞሪንጋ የንጥረ ነገር ይዘቱ የሥነ ምግብ ችግርን ለመቅረፍ የሚያስችል ነውም ብለዋል፡፡

አልጋነሽ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በዓለም አቀፍ የእርሻና ምግብ ድርጅት ድጋፍና በኢንስቲትዩቱ አስተባባሪነት ሞሪንጋን ለተለያዩ ምግቦች ለማዋል የሚጠቅም ፕሮጀከት ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡
በደቡባዊ የሀገራችን ክፍል ሞሪንጋ ሐለኮ በሚል መጠሪያ እንደሚታወቅ የጠቀሱት አልጋነሽ (ዶ/ር) ፣ ቅጠሉን በተለያዩ ምግቦች ውስጥ በመጨመር የመጠቀም ልምድ መኖሩንም ተናግረዋል፡፡

በከተሞች አካባቢ ግን ከሻይ ቅጠል ውጪ ለምግብነት ከመጠቀም አኳያ ልምድ አለመኖሩንም አንስተዋል፡፡
በፕሮጀክቱ የተመራው ምርምር ይህን ሁኔታ በመቀየር በከተሞች አካባቢ ያለው ማኅበረሰብ ሞሪንጋን ከተለመዱ ምግቦች ጋር እንዲጠቀመው የሚያስችል ነው፡፡
በምርምሩ ሞሪንጋን በስንዴ ዳቦ፣ በቡላ ገንፎ፣ ኩኪስና አይስክሬም ውስጥ ጨምሮ መጠቀም እንደሚቻልም ተመላክቷል፡፡
ትምህርት ቤቶች ላይም በምገባ ፕሮግራምም ላይ ለምግብነት ከሚውሉ የተማሪ ምገባ ፕሮግራም ውስጥ ቢገባ በልጆች እድገት ላይ በጎ ተጽዕኖ ይኖረዋል የሚል አስተያየትም ሰጥተዋል፡፡

ሞሪንጋ ከሰው ልጆች ባሻገር፣ ለእንስሳት መኖም መዋል እንደሚችል የተናገሩት አልጋነሽ (ዶ/ር)፣ በተለይም የወተት ላሞች ሞሪንጋን ቢመገቡ የወተትን የንጥረ ነገር ይዘት ለመጨመር ያግዛል ነው ያሉት፡፡
እርሳቸው እንደገለጹት፣ ኢንስቲትዩቱ ሞሪንጋን የማስተዋወቁና የማስፋፋቱን ሥራ አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
የገበያ ትስስርን በመፍጠር ረገድም ተቋሙ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ጥረቶችን እያደረገ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡
በኢንስቲትዩቱ የምግብና ሥነ ምግብ ምርምር ክፍል ከፍተኛ ተመራማሪና የሞሪንጋ ፕሮጀክት አስተባባሪ ሰሎሞን አባተ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ሞሪንጋ እንደ ስኳር ደም ግፊትና መሰል ድምፅ አልባ በሽታዎች ለመከላከል እንደሚረዳ ይናገራሉ፡፡
ቀደም ሲል ሞሪንጋን በከተሞች ላይ ለማስተዋወቅ ሰፊ ሥራ መሠራቱንና ጥሩ ግንዛቤ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
ነገር ግን፣ ቅጠሉን ከሌሎች ባዕድ ነገሮችና ቅጠላ ቅጠሎች ጋር ቀላቅሎ የመሸጥ ሁኔታ ሲበራከት የኅብረተሰቡም ፍላጎትና ገበያው ሊቀዛቀዝ ችሏል ብለዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ፣ ከዓለም አቀፉ የእርሻና የሥነ ምግብ ድርጅት ጋር በመተባበር ሞሪንጋ የሚያበቅሉ ሴቶችን በማደራጀት ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን የገቢ ማግኛ መንገድ እንዲሆናቸው በማሰብ የማሠልጠንና የማስተዋወቅ ሠራ እየሠራ ይገኛል፡፡

ከዚህ በፊት ከተለመደው በሻይ መልክ ከሚጠጣው በተጨማሪ የለመድናቸው ምግቦች ላይ የንጥረ ነገር ይዘቱን እንደያዘ ለምግብነት እንዲውል ጥረት እያደረግ ነው ያሉት ሶሎሞን (ዶ/ር)፤ ፕሮጀክቱ በእስካሁኑ ሂደት ብዙ ርቀት መጓዙን አመልክተዋል፡፡

በከተማ አካባቢ ያለውን የሞሪንጋ አጠቃቀም ለማሳደግ ተጨማሪ የምርምር፣ የማስተዋወቅና የማስፋት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው ሰሎሞን (ዶ/ር) ያስታወቁት፡፡
በብዛት በቆላማ አካባቢዎች ላይ የሚበቅለው ሞሪንጋ በዓለም ላይ “ተዓምረኛው ቅጠል” በሚል በስፋት የሚታወቅና በተለያየ መልኩ ጥቅም ላይ የዋለ የዛፍ አይነት ነው፡፡

ዮርዳኖስ ፍቅሩ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You