ኪነ ጥበብ ትናንትናም ሆነ ዛሬ ለጥበብ የሚሰጠውን አጥቶም ሆነ ነፍጎ አያውቅም። ሁሌም አዳዲስ ስጦታዎች እንደጎረፉ ናቸው። እናስ ኪነ ጥበብ ከሰሞኑ ምንስ አዲስ ነገር ይዞ ብቅ ብሎ ይሆን…ስጦታው ትልቅም ይሁን ትንሽ ያቺኑ ጭብጦ በቀኝ ይዘን፤ በደረቁ እንዳያንቀን በትንታም እንዳይኮረኩመን በግራ ደግሞ መማጊያ የሚሆኑንን ሀሳቦች እያነሳን ፉት እንላለን።
ከሰሞኑ ከኪነ ጥበብ መንደር ከተፍ ያለው አዲስ ጉዳይ በህሊና ታሽቶ፤ በህሊና የማንነትና የምንነት መዳፍ ሸንተረሩን እየሰራ የወጣ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ነው። ከህሊና የሚፈልቁ የማንነት ጅረቶችም፤ የዚህን ሸንተረር መስመሮችን እየተከተሉ እንደ አባይ ወንዝ ይፈሳሉ። በሌላ አቅጣጫም ከአንድ ስፍራ ሰክነው እንደ ጣና ሀይቅ ይንጣለላሉ። ይህን ተከታታይ ድራማም፤ ከዚህ ቀደም በ”አጼ ማንዴላ፤ ድንግሉ፤ ሚስቴን ዳርኳት፤ የፍቅር ጥግ፤ የፍቅር ሰው…” በእነዚህና በሌሎች ፊልሞች ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ለመድረስ የቻለው፤ የሳልቃን ፊልም ፕሮዳክሽን አሁን ደግሞ በይዘቱም ሆነ በአይነቱ የተለየ “ህሊና” የተሰኘ ተከታታይ ድራማ ይዤ ቀርቤያለሁ ሲል ከአጋሮቹ ጋር በይፋ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቶበታል።
ፕሮዳክሽኑ እንደ ፊልም ላቅ ያለ ደረጃን የያዘ ቢሆንም በተከታታይ ድራማ ይህ የመጀመሪያ ሥራው ነው። ይህን ድራማ ለዚህ ለማድረስ ሁለት ዓመታት ፈጅቶበታል። እውቅ የፊልምና ድራማ ባለሙያዎችን እንዲሁም 2 መቶ ያህል ተዋናይናን ይዞ ወደፊት የሚገሰግሰው “ሕሊና” ምንስ ያሳየን ይሆን..
“ህሊና” የዋና ገጸ ባህሪዋ ስም ቢሆንም ግን ደግሞ ለስያሜ ያህል ብቻ የተቀመጠ አይደለም። የታሪኩ የመነሻ ገመድ እየተጠቀለለ ክቧን የሕይወት ዓለም የሚሠራበት ጠጣር ህብለሰረሰር ነው። ሁላችንም እንደየመልካችን አሻራ ማንነታችን የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን፤ ይህን ማንነት የሚሠራው ደግሞ ህሊናችን ነው። የእሾህ ፍሬ የበተኑበት ህሊና ለከርሞ ስንዴ አብቅሎ አናገኘውም። ከፊት የሚታየው ማንነታችን የበቀለው ከውስጥ በተዘራው የህሊናችን ማሳ ላይ ነውና ድራማው ውስጥ የምንመለከታቸው እያንዳንዱ ትዕይንቶች በህሊና ገመድ የተጠፈሩና በተሻለ እይታ የምንረዳቸው ናቸው።
ይህቺ የድራማው ዋና ገጸ ባህሪ የራሷ ብቻም ሳትሆን የማህበረሰቡ ነጸብራቅ ሆና ትታያለች። ድራማው በሚያጠነጥኑበት መንገድ ላይ ህሊና ከወዲያና ከወዲህ ባለ የማንነት ባላ በሁለት ጫፍ ገመዱ ተወጥሮ፤ አንዴም ለመበጠስ ሲከር፤ አንዴም ሲላላ፤ ደግሞ መልሶ ሲወጠር እናያላን። በድራማው ውስጥ ያለችውን የህሊናን ማንነት በአይን አይተን በልብ ለመፍረድ የምንቸገርበትና የእርሷ ውጫዊ ማንነት በእኛ ውስጣዊ ህሊና ላይ የተመሠረተ ነው።
አንድ ጊዜም አብረን ስናለቅስላት ሌላ ጊዜም ልባችንን እርር! እያደረገች በቃላት ናዳ የምናወርድባት አይነት ልጅ ናት። በአስተዳደግና በድሮ ማንነቷ በዛሬና በአሁን እሷነቷ ውስጥ የሚፈጠሩት ግጭቶች እያየን የምናልፋቸው ሳይሆን እራሳችንን እያስተያየን የምንሄድባቸው ናቸው።
ጥሩ ህሊና ችግሮችን ሁሉ ወደ መፍትሄነት ይቀይራቸዋል፤ የደከረተ ህሊና ግን መልካም መፍትሄዎችንም ወደ ችግር ይለውጣቸዋል። በ”ህሊና” ውስጥ ህይወት ትነጋለች ደግሞ ትጨልማለች። አንደኛው ከፀሐይ ጋር አንዱም ከጨረቃ ሌላኛውም፤ ደመና ብርሃን፤ ጨለማ ሁሉም እየተፈራረቁ በህይወት መስኮት ሲገቡና ሲወጡ እንመለከታለን። ህሊና ውስጥ ህይወት እንዲህ ናት፤ እንደሚገባና እንደሚወጣው ሁሉ የእርሷም ማንነት ለአንዱ ጨለማ ለሌላኛው ብርሃን ናት።
የህይወት ዕጣ ፈንታዬ ነው ብላ የፍቅር ጉዞ የጀመረችበት መንገድ በቀጥታ ይዟት ወደ ጠላቷ ቤት ያደርሳታል። ከአንድ ቤት ከአንድ ቤተሰብ የህይወቷ ሁለት ማንነቶች ሲፋጠጡ ህሊና ማንን ትምሰል? የድራማው ጭብጥ በሌላኛው መስመሩ የሴት ልጅን ዘመናዊ ጥቃቶች ያሳየናል። ገንዘብ በፍቅር ላይ፤ ገንዘብ በህሊናና በማንነት ላይ እግሩን ሰቅሎ ቁልቁል በጫማው ሲረግጥ አይንና ልብ ተጨፍነው ይጨልማሉ። በተለይ ደግሞ አሁን አሁን በከተማችን አዲስ አበባ ላይ መልኩን ቀይሮ የመጣውን ዘመናዊ የጥቃት ልምድ እየሸለተ ውስጥ ውስጡን ያሳየናል።
ልብ ሲሰበር መንፈስም ይሰበራል፤ ህሊና ይደማል ይቆስላል ግን በምን ይሽራል? አንዳንዴም የገዛ ህሊና ይክዳል፤ አብዝተው የማንነት በረሃ ላይ ከተጓዙ ይደክመዋልና ከአንደኛው ክምር አሸዋ ላይ ገብቶ ይሰወራል። በዚህም በማንነት ከማህበረሰብ ሸሽቶ፤ በተወላገደ ጫማ የሚደረግን ጉዞ መዘዝና የመጨረሻውን መልኩን እናያለን። በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉትን ችግሮች ነቅሶ ከማሳየት አንጻርም ድራማው ብዙ የታሰበበት ይመስላል።
በሀገራችን ኪነ ጥበብ ውስጥ የተከታታይ ድራማ ያለው እድሜ እጅግ ትንሽና የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው። ለጥበብ ከተበረከቱ ስጦታዎች መሃከልም ትኩስነቱ ያልበረደና በአዲስነት ቃናው እንዳለ ነው ለማለት እንችላለን። ጥቂት ዓመታትን ወደኋላ መለስ ስንል በኢትዮጵ የጥበብ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያ የነበረው የ”ገመና” ድራማ ከማናችንም ማህደረ ትውስታ ውስጥ የተፋቀ አይመስለኝም። እሁዳችንን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣቢያ ከልባችን ጋር አጋምዶት፤ በፍቅር እየተመለከትነው፤ እየጣፈጠን አጣጥመነዋል።
ቀጥሎ ሁለተኛውን እርካብ “ሰው ለሰው” ድራማ ሰራው። አይናችን ፈጦ ልባችን እንደ ፊኛ እስኪወጠር ድረስ አብረን ከገጸባህሪያቱ ጋር እላይ ታች ብለንበታል። እያሉም ቀጥለው ዛሬ ላይ ብዙ ተባዝተዋል። መቼም በዛራና ቻንድራ እንኳን ቀልባችን ጠፍቶ ቀልብ ፍለጋ የወጣንበት አንድ ሰሞንም አለና እንዲህ በሀገራችን ድራማዎች ቢጠፋም መልካም እንጂ የሚቆጭ አይደለም። የግል የቴሌቪዥን ጣቢያዎችና ዓለም ዓቀፍ የሳተላይት ስርጭት ከዲኤስ ቲቪ ጋር ብቅ ማለታቸውን ተከትሎ ደግሞ የተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ፤ ገና ከውልደቱ የኪነ ጥበብ መንደር አብዮት ቀስቃሽ ሆኗል። እናም ዛሬ ላይ ጣቢያው በየአይነቱ፤ ድራማው በየፈርጁ ሆነና እንደየፍላጎታችን እየመረጥን እንኮመኩም ይሆናል እንጂ የተከታታይ ድራማ ፍቅራችን ላይ ንፋስ ገብቶበታል ለማለት አንችልም።
በዚህ ሁሉ የምናጤነው አንድ ነገር ቢኖር ተከታታይ ድራማዎች በማህበረሰቡ ውስጥ ያለው ተቀባይነትና ተወዳጅነት እጅግ ከፍ ያለ መሆኑን ነው። ለዚህ ደግሞ ልንጠቅሳቸው የምንችላቸው ምክንያቶች አሉ። የመጀመሪያው ነገር ከህጻናት እስከ አዛውንቱ፤ ከሊቅ እስከ ደቂቁ ስለሚታጨቁበት እያንዳንዱ ሰው እራሱን ከአንደኛው ስፍራ ላይ ያገኝበታል።
የሚተላለፉት ሰፊው ሕዝብ በሚከታተለው የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደመሆኑ በድራማው ከሚነሱ ጭብጦቹ እያንዳንዱን ተመልካች ያገናዘቡ ናቸው። ርዕሰ ጉዳዮቹም ከማህበረሰቡ የወጡ፤ የማህበረሰቡ መስታየቶች ናቸው። በእያንዳንዱ ክፍል የሚፈጠሩት አዳዲስ ሴራዎች አሰልቺ እንዳይሆን ያደርጉታል። እያደር እንደ ወይን ለሚጣፍጠፈው ጥፍጥናው ደግሞ ልብ ሰቃይ ልብ አንጠልጣይነቱ ይህን መሳዩን መልክ ሰጥቶታል።
ከላይኛው የሀሳብ ጥልፋችን አንዲቷን ሰበዝ መዘን ስንመለከት፤ አንድ ጥያቄ ውልብ ካለብን ይህን መሳይ ነው፤ መምጣቱንስ ብዙዎች ይመጣሉና “ህሊና” ምን የተለየ ነገር ይዞ መጣ? ጥያቄው ወሳኝና አግባብ ነው። ስለ ድራማው በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፤ ብዙ አዳዲስ ነገሮች እንዳሉበት የሳልቃን ፊልም ፕሮዳክሽን ገልጿል። ነገር ግን ቀደም ሲል በነበረው የድራማው ሂደት ከሲኒማቶግራፊ የቦታ መረጣና ቀረጻው አንስቶ ድራማውን በኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ መንደር ውስጥ ከፍ ባለ ደረጃ እንዲቀመጥ ለማስቻል መደረግ ያለበትን ሁሉ ከማድረግ አልተቆጠብንም። ተመልካቹም እንዳይጎረብጠው ብቻም ሳይሆን እየወደደው በተመስጦ አይኑን ሳይነቅል የሚያየው ድራማ አድርገው ስለማዘጋጀታቸውም ከጋዜጠኞች ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች አስታከው ገልጸውታል። ከሙያዊ ጉዳዮች አንጻር፤ “በትንሹ ሎኬሽን ላይ እንኳን ያለምንም መገደብ ተንፍሰን የሰራንበት ነው” በማለት ከዚህ ቀደም በሀገራችን ፊልሞችም ሆኑ ድራማዎች ላይ በተደጋጋሚ ይነሱ የነበሩ ትችቶች አሉና በዋናነት ይህን ሰንኮፍ ለመቅረፍ ከእስክሪፕት ጀምሮ ሁሉንም ነገሮች በጥንቃቄ ስለማዘጋጀታቸው ዳይሬክተሩ ይናገራል።
እስከዛሬ ከነበረው ልምድ አንጻር ከሙያዊ የጥራት ምልከታ አንጻር ፊልሞቻችን ከድራማው የተሻሉ ናቸው። በፊልሙ ላይ የብዙ ዓመታት ልምድና እውቀት ያለው ሳልቃን በዚህ መልክ ወደ ድራማው በመግባቱ ምናልባትም የተሻሉ ነገሮችን እንድናይ ያደርገናል። አዘጋጆቹ የ”ህሊና” ድራማን የሠራነው፤ ቀደም ሲል ለድራማዎች ይደረግ በነበረው አይነት ሳይሆን ለፊልሞች ይደረግ በነበረው መልኩ ነው ሲሉ አንድም ከዚሁ ነው። ምን የተለየ ነገር ይዞ መጣ? የሚለው ጥያቄ በተከታታይ ድራማ ውስጥ በአንድ ጀንበር የሚመለስ አይደለም። ምክንያቱም፤ እንደ ፊልምና ቲያትር አስቀድሞ መጀመሪያና መጨረሻው ተመጥኖ የሚደቆስ አይደለምና በጅምር ላይ ያልታሰቡና ያልታዩ ብዙ አዳዲስ ነገሮችን በመሀሉ ልንመለከት እንችላለን።
ታዲያ የ“ህሊና”ን ምናባዊ አፈር ፈጭተው፤ ጭቃውን አቡክተው፤ ከዚያም ነብስ ዘርተው መልክና ደምግባቱን ያበጁ እነማን ናቸው፤ ከምትለው ዳገት ላይም ጥቂት እንሸራተት። ጽንስ ሳይኖር ውልደት የለም፤ የመነሻ ሀሳቡ በራሱ በፕሮዲዩሰሩ ዮሴፍ ካሳ ሲሆን በድርሰት ደረጃ ተለውሶና ልሞ የተድቦለቦለው ደግሞ በዋና ደራሲው ዳንኤል ሰይድና በረዳቷ በአመለወርቅ መዘምር ነው። በረከት ወረደ/ማያ ብዙ ፊልሞችን ዳይሬክተር በማድረግ ምናልባቱም አሉ ከምንላቸው አንደኛው ነው።
የ”ህሊናን” ምናባዊ ትዕይንት በገጸ ባህሪያቱ ነብስ እየዘራ መልክና ደግም ግባታቸው ትክክለኛውን የማንነት ቅርጽ ይዞ እንዲሄድ ከፊት ሆኖ ይመራዋል። ሳልቃን ፊልም ፕሮዳክሽንም እንዲሁ የፊልሙ ዓለም ደጀን ነው። ከዚህ ዓለም ወጣ ብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ በድራማ የባቡር ሃዲድ ውስጥ ገብቷል። እነማንስ በመሪ ተዋናይነት ይሳተፉበታል? እንደ ኪነ ጥበብ ለዛ ቢስ ጥያቄ ቢሆንም፤ እንደ አንዳንዱ ተመልካች ግን ጥያቄው ወሳኝነት አለው። ምክንያቱም ጸሀፊውን አይተው መጽሀፉን፤ ፖስቸሩን ተመልክተው ፊልሙን…የሚሉት ያልወጣ ውስጣዊ ብሂል አለና ነው።
የሠሯቸው ፊልምና ድራማዎች ብዙ ቢሆኑም፤ በ”ሞጋቾች” ተከታታይ ድራማ ደምቆ የወጣው እንግዳሰው ሀብቴ/ቴዲ እና በ”ኪያዬ” ፊልም እንደ እንጉዳይ የበቀለው ቸርነት ፍቃዱ ጥምረታቸው የጓደኛማችነት አሊያም የወንድምነት ሳይሆን የአባትና የልጅ ሆኖ ተገኝቷል። አባት ግን ህሊናው ገፍትሮ ከስፍራው ላይ ሌላ ፈንጂዎችን ቀብሮበታል። ከራስ አልፎ ማህበረሰባዊ ማንነትን የሚያደባይ ፈንጂ ነው።
በተለያዩ ዘውጎች የሚምዘገዘገው ህሊና አንደኛው በፍቅር ህይወት ሰማይ ላይ ይበራል። ከዚህ ቀደም በሙዚቃው የምናውቀው ድምጸ መረዋው መሳይ ተፈራ በዋና ገጸ ባህሪዋ በህሊና ህይወት ውስጥ ተሸጉጧል። ከትወናው በተጨማሪም በማጀቢያው ሙዚቃው ውስጥ “የፍቅር ወጥመድ ነው መላ ሁሉ ገላሽ፤ ምክንያት አጣሁኝ በምን ሰበብ ልጥላሽ…” ሲል የሚንተከተከው የድምጹ ቅላጼ በ”ህሊና“ ነፋሻማ አየር ላይ ይረብባል። በሌላኛው ጎን ደግሞ የፍቅር ሊቁ ቸርነት ፍቃዱ የተላበሰው ገጸ ሰው እንባ የሚያዘራለት የፍቅር ወጥመድ ውስጥ ወድቆ ካልጠበቀው የህይወት ዘመን አጋጣሚና ከሌላ ማንነት ጋር ተፋጧል። ፍናን ህድሩ የ“ህሊና” የማንነት ቀሚስ ለብሳ የብዙ ታሪኮች የፀሐይ መውጫና የጀንበር መጥለቂያ ናት።
የጥበብ ሥራዎች ውስጥ ከታሪኩ ጋር መሳ ለመሳ ቆመው ከሚሄዱ ነገሮች አንደኛው መቼቱ ነው። እንግዲህ “ህሊና” ከአዲስ አበባ ተነስቶ “አንተ ባለጋሪ ቶሎ ቶሎ ንዳ…” ሲል ከናዝሬት አዳማ ላይ ደርሷል። መቼ? ለሚለው እራሱ ድራማው ይነግረናል። የት? ለሚለው ግን ከአዲስ አበባ ተነስቶ ናዝሬትን ከጫፍ እስከ ጫፍ ለማካለል ተነስቷል።
ሌላኛው ጉዳይ ድራማው፤ የመጀመሪያ ዙር ግብሩን አጠናቆ ተመልካቹ ዘንድ ለመድረስ እግሩ አጥሯል። በዚሁ ጉዞው ውስጥ እንደ አንድ ተከታታይ ድራማ ሳይሆን የተለየ የገንዘብና ሙያዊ ጉልበት ፈሶበታል የሚሉት አዘጋጆቹ፤ እንደ ጅምር 16 ያህል ክፍሎች የተሰናዱ መሆናቸውን በመጠቆም፤ ለዚህ ብቻ 10 ሚሊየን ብር ወጪ ተደርጎበታል ብለዋል። እውቁ ተዋናይ እንግዳ ሰው ሀብቴ “ከዚህ ቀደም ብዙ ድራማዎች ላይ ተሳትፈናል፤ ነገር ግን የነበረው ልምድ እንዲህ ለፊልሞች እንደሚደረገው አይነት አልነበረም። ”ህሊና” ከቅደም ዝግጅቱ ጀምሮ ልዩ ነው። ድራማው ለማስተላለፍ ከሚፈልገው መልእክት አንጻር ብቻ፤ ፕሮዲዩሰሩ አንዳችም ስለ ወጪና ትርፉ ሳይጨነቅ፤ ስለ ኪነ ጥበቡ መደረግ የነበረባቸውን ነገሮች ሁሉ ያለ ስስት አድርጓል” በማለት ምስጋናውንም ችሮታል።
“ህሊና” በስተመጨረሻ ማረፊያው ከሀገሬ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሆኗል። እንደሚታወቀው በርከት ያሉ ጣቢያዎች አሉና፤ ፕሮዲዩሰሮቹ እንዴትስ ፊታቸውን ወደዚያ ለማዞር መረጡ የሚለው ሀሳብ ከጋዜጠኞች በጥያቄ መልክ ቀርቦላቸውም ነበር። ምላሹም ይሄው ነው፤ “ሀገሬን ስንመርጥ፤ የሰጡን የገንዘብ አሊያም የጥቅማጥቅም ጉዳይ ከሌሎቹ የተሻለ ስለሆነ ላይሆን ይችላል። ለሙያውና ለጥበብ ባለሙያው ያላቸው ክብር፤ እስከዛሬ ድረስም መስዋዕትነት ልንለው በምንችለው መልኩ ለኢንዱስትሪው ለማበርከት የከፈሉትን ዋጋ በማየት ሀገሬን ትቶ ወደየትም ለመሄድ አላስቻለንም” የሚል ነበር።
“ህሊና” ሐሙስ ሚያዚያ 3፤ በዛሬው ዕለት በሀይሌ ግራንድ ሆቴል ውስጥ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ፤ ወደ ማህበረሰቡ ለመሄድ ካባውን ለብሶ ይመረቃል፤ ጥበብም ጸአዳውን ጋቢዋን ደርባ በክብር ትመርቃለች። የምርቃት ሥነ ሥርዓቱ በራሱ በሀገሬ ቲቪ በቀጥታ ስርጭትም እንደሚኖረው አስታውቀዋል። በኪነ ጥበብ ሠረገላ ታጅቦ በዕለተ ሰንበት፤ ዘወትር እሁድ እሁድ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በሀገሬ ቴሌቪዥን ይታያል።
አዘጋጆቹ ስለ ድራማውም ሆነ አጠቃላይ ይዘቱ ብዙ ብለውናል። እኛም ሰምተን ጥቂትም አይተን ይህችን ብለናል። እንግዲህ እኚህን ሁሉ በአንድ የእይታ ፌስታል አሊያም ዘንቢል ውስጥ አድርጎ በግራም ሆነ በቀኝ መያዙ የናንተው ነው። ሚዛኑም በማየት ነውና ፍርዱም ለተመልካች ይሁን።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2016 ዓ.ም