አዲስ አበባ፡- የወሎ ህዝብ የሚታወቅበትን የአብሮነት ባህሉን በመጠቀም በህዝቦች መካከል እየተፈጠሩ ያሉ ልዩነቶችን ለመፍታት ሊሠራ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሳሰቡ።ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ከደሴ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ትናንት ተወያይተዋል።
በዚህ ውይይት ላይ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን እንዲሁም የከተማዋ ነዋሪዎች የተገኙ ሲሆን
ነዋሪዎቹም የሥራ አጥነት ችግር፣ የህግ የበላይነት አለመከበር፣ የመሰረተ ልማት እና የህጻናት የህገ ወጥ ዝውውርን በተመለከተ ጥያቄዎች አንስተዋል።
ከዚህ ባለፈም አካል ጉዳተኞችን በልማት ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር ያሉ ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት ሊሠራ እንደሚገባ እና ከወሎ ተርሸሪ ሆስፒታል ግንባታ መዘግየት ጋር በተያያዘ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ በጋራ በመሆን እና በመሰባሰብ ችግሮችን መፍታት ይገባል ብለዋል። የወሎ ህዝብ የሚታወቅበትን የአብሮነት ባህሉን በመጠቀም በህዝቦች መካከል እየተፈጠሩ ያሉ ልዩነቶችን ለመፍታት ሊሠራ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የወሎ ተርሸሪ ሆስፒታል ግንባታ መዘግየት ጋር ተያይዞ ላነሱት ጥያቄም በቀጣዩ በጀት ዓመትም በደሴ ከተማ ሪፈራል ሆስፒታል ለመገንባት በጀት መያዙን በምላሻቸው ጠቁመዋል።
ከዜጎች መፈናቀል ጋር በተያያዘም እስካሁን ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ዜጎች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ጠቅሰው፥ በቅርቡም ሁሉም ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ይደረጋል ብለዋል።
የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመፍታትም መንግሥት ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከአጠቃላይ በጀቱ ውስጥ ለክልሎች የመሰረተ ልማት ግንባታ ማስፈጸሚያ 140 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር መመደቡን ና የነዋሪዎቹ ጥያቄዎች በዚህ አግባብ እንደሚመለስም አውስተው የወሎ ህዝብ የሚታወቅበትን የአብሮነት ባህሉን በመጠቀም በህዝቦች መካከል እየተፈጠሩ ያሉ ልዩነቶችን ለመፍታት ሊሠራ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከህዝባዊ ውይይቱ በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አይጠየፍ አዳራሽ በሚገኝበት የንጉስ ሚካኤል ቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ ችግኝ ተክለዋል ሲል የዘገበው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ነው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2011