የመመሪያ ክፍተት የፈጠረው የጎተራ የጋራ መኖሪያ ቤት ውዝግብ

የዛሬው የፍረዱኝ ዓምድ ዝግጅታችን በመዲናችን አዲስ አበባ የተፈጠረን አንድ ውዝግብ ያሰቃኘናል:: ውዝግቡ የተፈጠው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 በተለምዶ የጎተራ ኮንዶሚንየም እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው:: አለመግባባቱም በጎተራ የጋራ መኖሪያ ቤት የቦርድ አመራሮች እና ነዋሪዎች መካከል የተፈጠረ ነው::

“የጎተራ የጋራ መኖሪያ ቤት የቦርድ አመራሮች የማኅበረሰቡን ጥቅም ለማስጠበቅ የተመረጡ ቢሆንም የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠር እና በመደርደር አላስፈላጊ ክፍያዎችን እንድንፈጽም ያስገድዱናል:: ማኅበሩ የነዋሪውን ደህንነት ማስከበር አልቻለም፤ ጭፈራ ቤቶች ያሉበት በመሆኑ ስራ ውሎ የሚገባ ነዋሪ እረፍት እያጣ ነው። በግቢው ውስጥ ያሉ ኮሚናሎች ለነዋሪው አገልግሎት ከመስጠት ይልቅ ማኅበሩ በማከራየት የገቢ ምንጭ አድርጓቸዋል። ይህም ለከፍተኛ ችግር እየዳረገን ነው:: ይህንን ያልተገባ የቦርድ አመራሮች እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ሕዝብ አይቶ ይፍረደን” ሲሉ የጎተራ የኮንዶምንየም ነዋሪዎች ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ክፍል አቤት ብለዋል::

የኢትዮጰያ ሕዝብ ግራ ቀኙን አይቶ መፍረድ ይችል ዘንድ የመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ክፍል ከሰነዶች እና ከሰዎች በምርመራ ያገኛቸውን የምርመራ ውጤቶች እነሆ ብሏል:: መልካም ንባብ!

ከቅሬታ አቅራቢዎች አንደበት

በጎተራ የጋራ መኖሪያ ቤት በርካታ ሰዎች ይኖራሉ:: እነዚህ ሰዎች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመቅረፍ የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ አድርገው የቦርድ አመራሮችን መርጠዋል:: የቦርድ አመራሮችም የግል ስራ ስላላቸው ነዋሪዎች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ተከታትለው ለመፍታት በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ሰራተኞችን ቀጥረዋል::

የቦርድ አመራሮቹ ነዋሪዎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት በሚል በተለያዩ ጊዜያት ነዋሪዎችን አላስፈላጊ ክፍያዎች እንዲከፍሉ ያስገድዳሉ:: ለሚያስክፍሏቸው ክፍያዎች ደረሰኝ አይቆርጡም:: ለማሕበረሰቡ ይሰራሉ የተባሉ ስራዎችም ሲሰሩ አይታዩም::

በተጨማሪም የቦርድ አመራሩ የማሕበሩን ኮሚናሎች አከራይቶ የሚያገኘውን ገንዘብ የት እንደሚገባ ሕብረተሰቡ አያውቅም:: በአጠቃላይ የቦርድ አመራሮች በርካታ ችግሮችን በማሕበረሰቡ እየፈጸሙ መሆናቸውን እና ጊዜ ወስዶ ምርምራ ቢደረግ በቦርዱ ላይ በርካታ ችግሮች ሊገኙ እንደሚችሉ ያስረዳሉ::

የጎተራ ኮንዶምኒየም የቦርድ አመራሮች ምላሽ

ተፈጠረ ስለተባለው ችግር ዝግጅት ክፍሉ “የጎተራ ኮንዶሚንየም ማሕበር” የቦርድ አመራሮች በጋራ አነጋግሮ የሚከተለውን ምላሽ አግኝቷል:: መልስ የሰጡን አመራሮች አቶ አዲሱ የኔው ምክትል ሰብሳቢ፣ አቶ በቀለ እውነቱ ገንዘብ ያዥ እና አቶ እዮብ አሰፋ የቦርድ አባል ናቸው::

እንደ ቦርድ አመራሩ ገለጻ፤ “የጎተራ ኮንዶሚንየም ማሕበር” ግንቦት አንድ 2002 ዓ.ም የተቋቋመ ነው፤ 78 ሕንጻና 2ሺህ 168 መኖሪያ ቤቶች፤ 245 የንግድ ቤቶች አሉት:: በዚህም ከ11 ሺ በላይ ሕዝብ ይኖርበታል:: ማሕበሩ በጠቅላላ ጉባኤ ሰባት የስራ አስፈጻሚ ቦርድ መርጦ የሚተዳደርና ሶስት ቁጥጥር ኮሚቴ ያለው ነው:: የራሱ የሆነ ጽህፈት ቤት ሲኖረው፤ 26 ቋሚ እና 53 ጊዚያዊ ሰራተኞችንም ቀጥሮ ያሰራል::

የማህበሩ ስራ አመራር ቦርድ በየሶስት ዓመቱ የሚመረጡ ናቸው። አሁን በስራ ላይ ያለው አመራር ከተመረጠ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል:: በስራ ዘመናቸው የማሕበረሰቡን የውሃ እጥረት፤ የጸጥታ እና ሌሎች ችግሮችን ለመቅረፍ ያስችላቸው ዘንድ 42 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅደው እየተንቀሳቀሱ ነው::

በማህበሩ መተዳደሪ ደንብ ላይ በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት የተሰጣቸው ከማሕበረሰቡ ደህንነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ናቸው የሚሉት አመራሮች፤ ይህን ዕውን ለማድረግ ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ‹‹ስማርት ፓርኪንግ›› ስራ ላይ አውለዋል::

ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ከመጀመሩ በፊት በግቢው ውስጥ በርካታ ወንጀሎች ይፈጸሙበት ነበር ያሉት የቦርድ አመራሮቹ፤ ተሽከርካሪዎችን መስረቅ እና በግቢው የቤት ባለቤት ያልሆኑ ግለሰሰቦች መኪና አቁመው ጥለው መጥፋት፤ ዘረፋና ሌሎች መሰል ወንጀሎች ይፈጸሙ እንደነበር፤ አሁን ላይ “በስማርት ፓርኪንጉ” ችግሮችን በተወሰነ መልኩ መቅረፍ መቻላቸውን ጠቁመዋል::

ማሕበሩ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በማሕበራት ማደራጃ የታየ የራሱ የሆነ መተዳደሪ ደንብ ያለው፤ የስራ አመራር ቦርዱም ማሕበረሰቡን የሚያስተዳድረው ደንቡን መሰረተ አድርጎ ነው:: ቦርዱ ማሕበረሰቡ የሚጋጥሙ ችግሮች በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት ለማስከበር ጥረት ቢያደርግም አልፎ አልፎ ማኅበረሰቡ የቦርዱን አሰራር አይረዳም ባይ ናቸው::

እንደ ቦርድ አመራሩ ከሆነ፤ የጎተራ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከተገነቡ 16 ዓመት በላይ ሆኗቸዋል:: የሕንጻ እድሳት፤ የኮሚናል ግንባታ፤ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ስራ እና መሰል ችግሮች የነዋሪዎቹ ጥያቄዎች ናቸው:: ጥያቄዎቹን ለመመለስ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የሚጠይቅ መሆኑንና ይህን ሀብት ለማሰባሰብ የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ዘዴዎች ሲጠቀሙ ቆይተዋል፤ ከእነዚህ መካከል ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ አንዱ ነው ::

ማኅበረሰቡ ልጆቹ የሚዝናኑበት ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ጥያቄ ነበረው የሚሉት አመራሮቹ፤ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጭ በማድረግ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ተገንብቶ ተጠናቋል::

በ3 ዓመት ውስጥ 42 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ የተለያዩ ስልቶችን መጠቀም አስፈላጊ ነው:: በዚህም የቤት ዕድሳቱ፣ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ እና መሰል ስራዎችን ለመስራት ሰፊ ዝግጅት እያደረጉ ይገኛል:: የግቢውን አጥር ለማጠር ከወረዳ 04 ፈቃድ ለማግኘት በሂደት ላይ ነው፤ ፈቃድ እንደተገኘ ግንባታው ይካሄዳል::

የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሲገነቡ 13 ኮሚናሎች ይገነባሉ ተብሎ ነበር:: ለ13ቱም ኮሚናሎች እያንዳንዱ የቤት ባለቤት ክፍያ ፈጽሞባቸዋል:: ክፍያ ቢፈጽምባቸውም 13 ኮሚናሎች ግን ተሰርተው ለማኅበረሰቡ የተሰጡት ሰባቱ ብቻ ናቸው:: በመሆኑም እነዚህን ሰባት ኮሚናሎች ምን እናድርግ? እንዴትስ እንጠቀም? የሚል ሀሳብ ለጠቅላላ ጉባኤ ቀርቦ፤ ኮሚናሎችን ለሁሉም ኅብረተሰብ በፍትሀዊነት ማዳረስ እንደማይቻል፤ አንዱን ኮሚናል ለአዳራሽ ሌላኛውን ደግሞ ለጽህፈት ቤት እንዲሆኑ እና ቀሪዎቹ ደግሞ እንዲከራዩ ተወስኗል::

ይህ እንደዘላቂ መፍትሔ የተያዘ ሳይሆን ሌሎች ቀሪ ኮሚናሎች እስከሚገነቡ በጊዜያዊነት የተወሰዱ መፍሔዎች ናቸው:: ስራ አመራር ቦርዱ በተለያዩ ጊዜያት ለአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ገንዘብ የተከፈለባቸውን ቀሪ ኮሚናሎች እንዲገነቡ ጥያቄ ማቅረቡን፤ እስካሁን ድረስ መልስ የሚሰጥ አካል አለማግኘታቸውን ይናገራሉ::

የጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ ተቀባይነት የሚኖረው በሀገሪቱ ካሉ ሕጎች እና ከቤቶች ልማትና አስተዳደር መመሪያዎች ጋር ካልተጣረሰ ብቻ ነው:: የቤቶች ልማትና አስተዳደር ደግሞ ኮሚናሎችን የገነባው ለጋራ መጠቀሚያ ነው:: ከዚህ አንጻር ጠቅላላ ጉባኤው ምንን መነሻ በማድረግ ኮሚናሎች ሊያከራይ ቻለ? የሚል ጥያቄ ከዝግጅት ክፍሉ ጥያቄ የተነሳላቸው አመራሮች፤ መዋቅር ላይ እንደሚታየው ጠቅላላ ጉባኤው የውሳኔ ሰጭ አካል ነው:: ቦርዱ ያከራየው በቤቶች አስተዳደር መመሪያ መሰረት ሳይሆን በጠቅላላ ጉባኤው መመሪያ መሰረት ነው:: ጠቅላላ ጉባኤው መተዳደሪያ ደንብ አለው:: በዚህ ከተወሰነ ማከራየት ይቻላል:: በመተዳደሪያ ደንቡ ጠቅላላ ጉባኤ የበላይ አካልና የውሳኔ ሰጭ አካል ነው ይላል:: ጠቅላላ ጉባኤው ያከራየው የራሱን ንብረት ነው:: ስለዚህ ጠቅላላ ጉባኤው ከወሰነና እንዲተገበር ካዘዘ ቦርዱ ተጠሪነቱ ለጠቅላላ ጉባኤው ስለሆነ በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት አከራይቶ ለተለያዩ ገቢዎች ማዋል ይችላል::

ጠቅላላ ጉባኤው ከሀገሪቱ ሕጎች እና መመሪያዎች በታች ነው:: ስለሆነም በቤቶች ልማትና አስተዳደር መመሪያ መሰረት የጋራ ኮሚናሎችን ማከራየት ክልክል ነው:: ከዚህ አንጻር እናንተ ከምን ተነስታችሁ ልታከራዩ ቻላችሁ? መመሪያ አለ ወይ ? አሳዩን ? ተብለው የተጠየቁት አመራሮች፤ መመሪያ ይኑርም አይኑርም ጠቅላላ ጉባኤ ካጸደቀ የጠቅላላ ጉባኤውን ውሳኔ እንደሚያስፈጽሙ ተናግረዋል::

“ቤቱን በተረከብንበት ወቅት ኮሚናሎች ያልተሟሉ ስለነበር ኮሚናሎችን አንረከብም ብለን አራት ዓመታት ዝግ ነበሩ:: ሕዝቡ አምስት በመቶ ለኢንጂነሮች የከፈለውን ብር መልሱና ማህበሩ በራሱ ይገንባ? የሚል ጥያቄም ለቤቶች ልማትና አስተዳደር ቀርቦ ነበር:: ነገር ግን ምላሽ አልተገኘም::

ኮሚናሎችን ማከራየት አይቻልም የሚል መመሪያ ካለም ይህ መመሪያ ለጎተራ ሊሰራ አይችልም ብሎ ቦርዱ ያምናል:: ምክንያቱም ነዋሪው ገንዘብ የከፈለበትን ኮሚናል አሟልቶ ያላቀረበ አካል እንዴት መመሪያን መሰረት አድርጎ ሌሎች አካላትን ሊጠይቅ ይችላል? ይጠይቃሉ::

የአዲስ አበባ ቤቶች ቢሮ ቤት ማስተላለፍና ቤቶች ልማት ቢሮ ተብሎ ለሁለት መከፈሉን፤ በዚህም የሚጠይቁት አካል አጥተው መሃል መንገድ ላይ መቆማቸውን አመላክተዋል:: በመሃል ጠቅላላ ጉባኤው ተሰብሰብቦ ቤት ተገንብቶ ለጥቅም ሳይውል እየፈረሰ ነው:: ለሌቦች እና ወንጀለኞች መደበቂያ እየሆነ ነው:: የጠየቅነው ጥያቄ መልስ ካጣ ቢያንስ ቤቶቹ መፍረስ የለባቸውም፤ የወንጀለኛ መደበቂያም መሆን የለባቸውም ተብሎ እንዲከራዩ መደረጉን ያስረዳሉ::

ኮሚናሎቹ ከመከራየታቸው በፊት ሽንትና ሰገራ የሚታይባቸው ፈራርሰው የሚታዩ ነበሩ:: የሚመለከተውን አካል አናግረን ተገቢ መልስ ቦርዱ ሲያጣ ለችግሩ እንደመፍትሔ የተወሰደው ማከራየት ነው:: ስለዚህ ኮሚናሎች ተከራይተው ለሌሎች ኮሚናሎች እንዲገነቡ ገንዘብ አቅም ይፍጠር በሚል እሳቤ የተከናወነ ነው:: የማኅበረሰቡን የማዕድ ቤት ጥያቄ ለመመለስ ዘመናዊ የሆነ ተንቀሳቃሽ የሆኑ ጭስ አልባ ማዕድ ቤት ለመገንባት በዕቅድ ተይዞ እተሰራ ነው::

አመራር ቦርዱ ከተመረጠ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል:: ከታቀዱት 19 ፕሮጀክቶች ምን ያሉ ተፈጸሙ? ከማኅበረሰቡ በተለያዩ ሰበቦች ገንዘብ መሰበሰባችሁ ይነገራል:: ይህ ለምን ሆነ? ተብሎ የተጠየቀው የአመራር ቦርድ ማኅበረሰቡ ከ20 ብር ወራዊ መዋጮ ውጭ አንድም ብር በማኅበሩ አልጠየቀም፤ አይጠየቅም:: ከዚህ ውጭ ከፍያለው የሚል የቤት ባለቤት ካለ ማስረጃ ይዞ መምጣት እንደሚችል ጠቁመዋል::

መንግስት ገንብቶ በሰጠው የጋራ መኖሪያ ቤት ላይ ኬላ ጥሎ ለፓርኪንግ ማስከፈል መመሪያውና አሰራሩ አይፈቅድም:: ይህን ለምን አደረጋችሁ? ተብሎ የተጠየቁት የስራ አመራር ቦርድ አባላቱ፣ የጎተራ ኮንዶሚንየም ነዋሪዎች ማኅበር በማኅበራት ማደራጃ የተደራጀ አንድ ትልቅ ማኅበር ነው:: ግቢው ውስጥ አንድ ሺ 200 በላይ መኪና ያድራል:: ግቢው በ52 የጥበቃ ሰራተኞች የሚጠበቅ ነው:: ይህን የወር ደሞዝ ወጭ ግለሰቦች አዋጥተው የሚከፍሉት አይደለም:: የግቢ ውበትና ጽዳትም ይከናወናል:: እነዚህ ስራዎች የሚሰሩት ገቢን በማሳደግ እንጂ ከማኅበረሰቡ 20 ብር በመሰብሰብ አይደለም:: አስፈላጊ የሆነውን ገቢ ለማሰባሰብ የተለያዩ አመራጮችን እየተጠቀመ መሆኑን ተናግረዋል::

ገንዘብ የምናስከፍለው ለፓርኪንግ አይደለም የሚሉት የቦርድ አመራሮች፤ የተሽከርካሪ ባለቤቶች የሚከፍሉት ክፍያ ተሽከርካሪያቸውን ለሚጠብቅ ሰራተኛ (ለጥበቃ) መሆኑን ያስረዳሉ:: አንድ የጎተራ የጋራ ቤት ነዋሪ ግለሰብ ተሽከርካሪ ካለው ተሽከርካሪውን ለጠበቁ ሰራተኞች ደምወዝ 35 ብር ይከፍላል::

በእርግጥ ኪዚህ ክፍያ የሚገኝ ትርፍ የለም ማለት አይደለም:: የሚተርፈውን ገንዘብ ለኅብረተሰቡ

መሟላት ያላባቸው ነገሮች ማሟያ ይደረጋሉ:: ለምሳሌ ኅብረተሰቡ ምንም አይነት ገንዘብ ሳያወጣ ቤቱን ለማደስ ቦርዱ ቃል ገብቷል:: ይህን የገባውን ቃል ለመፈጸም ከፓርኪንግ የሚገኘውን ገንዘብ እንደሚጠቀምበት ገልጸዋል::

ምንም እንኳን ከፓርኪንግ የሚሰበሰበው ገንዘብ ለጥበቃ ማጠናከሪያ ይውላል ቢባል የጋራ መኖሪያ ቤቱ አባላት ግን ያለው ጥበቃ ደካማ በመሆኑ ብዙ ጊዜ ንብረታቸው እንደሚዘረፍባቸው ያነሳሉ:: እዚህ ላይ የእናንተ ምላሽ ምንድን ነው? ተብለው የተጠየቁት የቦርድ አመራሮች እንደሀገርም ሆነ እንደ ክፍለ ከተማ እዚህ ግቢ የሚንቀሳቀሰው ማኅበረሰብ በጣም ብዙ ነው::

ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ በርካታ የውጭ ሀገራት ዜጎች ጭምር የሚኖሩበት ግቢ ነው:: የግቢው አብዛኛው ነዋሪ ደግሞ ተከራይ ነው:: በዚህም የተለያዩ የጸጥታ ችግሮች በየቀኑ ያጋጥሙናል:: ከዚህ አኳያ አሁን ላይ የቦርድ አመራሮች አንገብጋቢው የቤት ስራ በግቢው የሚስተዋለውን ጸጥታ ችግር እንዴት ማስወገድ አለብን የሚለው መሆኑን ያስረዳሉ:: ወደ ግቢ የገባ አንድ ተሽከርካሪ ግቢ ውስጥ አቁሞ እያለ ስፖኪዎ እንኳን ቢሰረቅ የተሰረቀውን ንብረት ማኅበሩ የመሸፈን ግዴታ እንዳለበት ይናገራሉ::

ማኅበሩ ከቀጠራቸው ጥበቃዎች በተጨማሪ ለግቢው ሰላም ሲባል የኮሚኒቲ ፖሊሲንግ አገልግሎት እንዲቋቋም ተደርጓል የሚሉት የቦርድ አመራሮች፤ ይህም የሆነው የግቢውን ጸጥታ የተሻለ ለማድረግ በማሰብ መሆኑን አመላክተዋል:: ማኅበሩ የቀጠራቸው ጥበቃዎች የሚያደርጉት ጥበቃ የላላ ነው የሚሉት የቦርድ አመራሮች፤ ይህ ምን አልባትም ማኅበሩ ከሚከፍለው ክፍያ ማነስ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል። በመሆኑም አሁን ላይ ከጥበቃ ጋር የተገናኙ አሰራሮችን ለማዘመን እየሰሩ እንደሚገኙ ይናገራሉ::

በግቢው በርካታ የጸጥታ ችግሮች አሉ:: የሉም እያልን አይደለም:: ምክንያቱም በቀን ውስጥ ወደ ግቢው ውስጥ የተለያየ ማኅብረሰብ ይገባል:: በአንድ ቀን ገብቶ የሚለቅ ሰው አለ:: በአንድ ቀን ገብቶ የሚለቅን ሰው ደግሞ ምን እና ማን እንደሆነ ለማወቅ ይከብዳል::

እንደ አመራሩ ገለጻ፤ ከጸጥታው ችግር በተጨማሪ በግቢው ውስጥ የድምጽ ብክለት አለ:: ይህ ችግር በወረዳ እና በበላይ አመራሮች የሚፈታ ነው:: ምክንያቱም ማኅበሩ ተው ከማለት ባለፈ እርምጃ መውሰድ አይችልም:: ከንግድ ቤቶች ጋር በተያያዘ ቁጥጥር የሚያደርገው የንግድ ፍቃድ የሰጠው አካል ነው:: ስለዚህ ኅብረተሰቡ ያነሳው የጸጥታ ችግር ትክክል ነው:: የቦርድ አመራሩም ችግር ነው::

በግቢው ሶስት አይነት የፓርኪንግ አገልግሎት ክፍያ መኖሩን የሚናገሩት አመራሮቹ፤ በአንድ ቀን 1ሺህ 200 በላይ የተከራይ እና የነዋሪ ተሽከርካሪዎች በግቢው ውስጥ እንደሚያድሩ ያስረዳሉ:: በዚህም ለተከራይ በቀን 10 ብር፤ ይከፍላል ለቤት ባለቤቶች ደግሞ በወር 35 ብር እንዲከፍሉ ይደረጋል:: ነዋሪዎች ከበፊት ጀምሮ በወር የሚከፍሉት 35 ብር ነው:: እስካሁን ምንም አይነት ጭማሪ ሳይደረግ ባለበት እንደቀጠለ ነው::

ሶስተኛው የፓርኪንግ ክፍያ የሚጠየቀው በግቢው ነዋሪ ያልሆኑ እና ወጣ ገባ የሚሉ ተሽከርካሪዎች ናቸው:: እነዚህ ሰዎች በ30 ደቂቃ አምስት ብር እንዲከፍሉ ይደረጋል:: ይህም የተጋነነ ገንዘብ ይከፍላሉ የተባለው ፈጽሞ ውሸት መሆኑን ያስረዳሉ::

ብዙ ጊዜ ወጣ ገባ የሚሉት ተሽከርካሪዎች ግቢ ውስጥ ገብተው ጫት ይቅማሉ:: ስርቆትም ይፈጽማሉ:: እነዚህ ሰዎች የወንጀል ድርጊታቸውን የሚፈጽሙት መኪና ውስጥ ቁጭ ብለው ነው:: ስለዚህ እነዚህን መሰል ሰዎች 10 ብር ብቻ አስከፍሎ ቀኑን ሙሉ ግቢ እንዲውሉ መፍቀድ ተገቢ አይደለም:: ስለዚህ ፓርኪንጉ ከገቢ ባለፈ ለግቢው ጸጥታ ከፍተኛ አበርክቶ እያደረገ ነው::

የአመራር አባላቱ እንደሚሉት፤ የቦርዱ አመራረ ከተመረጠ ሁለት ዓመት ባይሞላውም በማኅበረሰቡ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በርካታ ስራዎችን እከናወነ ይገኛል:: ለአብነት ያህል ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት የስፖርት ማዝወተሪያ ሜዳ እየተገነባ ነው:: ለማኅበረሰቡ ድህንነት ሲባል ማኅበሩ ባለው ወሰን ላይ አጥር ለመገንባት እየተንቀሳቀስን ነው:: ፓርሴሎች ላይ ‹‹ኮብል ስቶን›› ለማስለጠፍ ከፍተኛ ስራዎች ተሰርተዋል::

በዚህም አሁን ላይ ከአንድ ፓርሴል ውጭ በሁሉም ፓርሴሎች “የኮብል ስቶን” ንጣፍ ስራ ተከናውኗል:: ዘመናዊ የፓርኪንግ ስራ አስጀምረናል:: በዚህም ለማኅበሩ ገቢ ከማስገኘቱም ባለፈ የግቢውን ሰላም በከፍተኛ ደረጃ ማስጠበቅ ተችሏል:: ከዚህ በተጨማሪም ኮሚናሎች ውስጥ ከረንቡላ ከማጫወት ማህበረሰቡን የሚጠቅም ስራ ለመስራት በማሰብ የኅጻናት ማቆያ እንዲከፈት ተደርጓል:: ከዚህ ባሻገር በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የወረዳ 4 አስተዳደር በዘመናዊ መልኩ የሚገነባ የኅጻነት ማቆያ የግንባታ ፈቃድ ወስዷል::

በግቢው ውስጥ በርካታ አዋኪ ተግባራት ይፈጸማሉ:: በአረንጓዴ ስፍራዎች ጫት ይቃማል፤ ሲጋራ ይጨሳል:: በተጨማሪም ለንግድ ቤት ከተከራዩ ቤቶች ድምጽን የሚበክሉ ነገሮች ይስተዋላሉ:: እዚህ ላይ ምን ትላላችሁ? የተባሉት የማህበሩ የቦርድ ኃላፊዎች፤ ንግድ ፈቃድ ቦርዱ ስለማይሰጥ እነሱን መቆጣጠር አይችልም:: ቦርዱ በጣም እየተቸገረበት ያለው በዚህ ነው::

በማኅበሩ የመተዳደሪያ ደንብ ከድምጽ ጋር በተገናኘ ከምሽት አራት ሰዓት በኋላ ማንም ሰው ታኮ (ሂል) ጫማ ማድረግ አይችልም:: በተጨማሪም ማንም ሰው በምሽት ሙዚቃ መክፍት አይችልም:: ከፍቶ ማዳመጥ ቢፈልግ በኤርፎን ብቻ እና ብቻ ነው:: ይህን መመሪያ መጀመሪያ አካባቢ እያስከበርን ነበር:: ይሁን እንጂ ከወረዳ ድምጽ የራሱ መለኪያ አለው የሚባል ነገር መጣ:: ከዚህ በኋላም በርካታ ችግሮች ማህበሩን አጋጥመውታል::

ይህንንም ለበርካታ ጊዜያት ለወረዳ እና ለከተማ አስተዳደሩ አሳወቅን:: ነገር ግን ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ቁጠባ እየቆጠበ ቤት ያላገኘ ማኅበረሰብ ባለባት ከተማ እናንተ ደግሞ ስለድምጽ ብክለት ቅሬታ ታቀርባላችሁ:: ‹‹እናቱ የሞተችበት እና ወንዝ የሄደችበት እኩል ያለቅሳል›› የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ይናገራሉ:: አሁንም ጥያቄውን በተደጋጋሚ ቢያቀርቡም ምላሽ የሚሰጣቸው አካል ማግኘት አለመቻላቸውን ያስረዳሉ::

በማኅበሩ የሚገኙ የንግድ ቤቶች ድምጽ ሲበክሉ ይስተዋላል:: ይሁን እንጂ ቦርዱ ለእነሱ የንግድ ፈቃድ ስለማይሰጥ እነሱን ማስቆም አይችልም:: ይህን ማድረግ የነበረበት የንግድ ፈቃድ የሚሰጠው አካል ነው :: በዚህ ጉዳይ ኅብረተሰቡ እና ቦርዱ ለከፍተኛ ቅራኔዎች መዳረጋቸውን ይገልጻሉ::

እንደ አመራሩ ገለጻ፤ ንግድ ቤቶች ለግሮሰሪ ሲጫረቱ በምን መልኩ እንደሆነ እስካሁን እውቅና የላቸውም:: በግቢው “ናይት ክለቦች” ነበሩ :: ማንጊያ ቤቶች እስካሁንም አሉ:: ከእነዚህ ጋር ተያይዞ ሁልጊዜም ለወረዳ እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ሪፖርት ያቀርባሉ:: ሰሚ ግን አልተገኘም::

የንግድ ቤቶች በጨረታ ነው የተሸጡት:: ገዥዎች ደግሞ ቤታቸውን አከራይተዋል:: 245 ንግድ ቤቶች የግል ናቸው:: የጎተራ ኮንዶሚንየም አይደሉም:: ንግድ ፈቃድ ሲወጡ ማኅበሩ አያውቅም:: ስራ ላይ ሲሰማሩ ብቻ ነው የሚታዩት::

ጥበቃ የምንቀጥረው ከፌደራል ፖሊስ ፈቃድ ከተሰጣቸው ኤጀንሲዎች ነው:: ነገር ግን ኤጄንሲዎች በተጨማሪ እያቀረቡልን ያለው ኃይል በቂ የፖሊስ ወይም የውትድርና ስልጠና ያላቸው አይደሉም:: ይህ ደግሞ በጥበቃ ቁጥጥራቸው ላይ ክፍተት መፍጠሩን ይናገራሉ ::

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የወረዳ 04 ዋና ስራ አስፈጻሚ ምላሽ?

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የወረዳ 04 ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ናሆም መንግስቱ እንደገለጹት፤ በጎተራ ኮንዶምንየም ውስጥ በርካታ ሕገ ወጥ ድርጊቶች የሚፈጸምባቸው ብዙ ተቋማት ነበሩ:: በዚህም በ19 ተቋማት ላይ እርምጃ ተወስዷል:: በተለይ ከድምጽ ብክለት ጋር ተያይዞ የነበረውን ችግር መቀነስ ችለዋል::

በጋራ መኖሪያ ቤቶች ጭፈራ ቤቶች አሉ:: ነገር ግን ለጭፈራ ቤት የንግድ ፈቃድ አይሰጥም:: ፈቃድ የሚወስዱት ባርና ሬስቶራንት በሚል ነው:: ይህን በመጠቀም ወደ ጭፈራ ቤት የሚለውጡ ይኖራሉ:: 251 የሚባል ቤትና ብሎክ 28፤ 27፤ 26 ያሉ ቤቶች ፈቃድ ሲወስዱ ባርና ሬስቶራንት ብለው ነበር:: ነገር ግን ከተሰጣቸው ፈቃድ ውጭ ሲሰሩ ተገኝተው እርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑን አመላከተዋል::

ምግብ ቤት፤ ባርና ሬስቶራንት ተብሎ ፈቃድ የሚሰጥበት አግባብ አሰራር እና መመሪያ መኖሩን የጠቆሙት አቶ ናሆም ፤ ጭፈራ ቤት የሚል ፈቃድ አለመኖሩን ያስረዳሉ::

ከተማ አስተዳደሩ በቤቲንግ ቤቶች ላይ እርምጃ ከመውሰዱ ጋር በጎተራ ኮንዶምንየም እርምጃ የተወሰደባቸው አሉ:: ዘመናዊ “ፓርኪንግ” የተጀምረው ጫት ለመቃም እና ወንጀል ለመስራት ወደ ግቢው የሚገቡትን አካላት ለመቀነስ ታስቦነው የሚሉት አቶ ናሆም፤ “ፓርኪንጉ” የታለመለትን ዓላማ ማሳካቱን ገልጸዋል::

እንደ አቶ ናሆም ገለጻ፤ ማኅበሩ ሕጋዊ እውቅና ያለው በመሆኑና የራሱ መተዳደሪ ደንብ ያለው በመሆኑ ሕገ ወጥ ድርጊት ሲፈጽሙ በሚገኙ የንግድ ቤቶች ላይ እርምጃ የመውሰድ ስልጣን አለው:: የንግድ ቤቶች ምንም እንኳን መንግስት በሽያጭ ለግለሰቦች ያስተላለፋቸው ቢሆኑም በግቢው መተዳደሪያ ደንብ የመግዛት የግዴታ አለባቸው::

ስለዚህ በማህበሩ መተዳደሪ ደንብ አይገዙም የሚለው ተጠያቂነት ሲመጣ የመሸሻ መንገድ እንጂ በሁሉም ዘርፍ ያለውን ሁኔታ የማስተዳደርና የመቆጣጠር ኃላፊነት አለባቸው:: የወረዳ አስተዳደሩም የግቢውን ሕግ ባልጣሰ መልኩ የሚሰራ ሲሆን የሚያከናውናቸው ስራዎች ግን መንግስታዊ ስራዎችን ብቻ ነው ::

ግቢው ማንም ሰው ገብቶ ወንጀል ፈጽሞ የሚወጣበት ግቢ ነበር:: አሁን ላይ በአንጻራዊነት መኖሪያ ግቢ እየሆነ የመጣ ነው:: ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ሰላማዊ የመኖሪያ መንደር እየሆነ መጥቷል የሚል ግምገማ እንደሌላቸው ጠቁመዋል::

የጋራ መኖሪያ ቤቱን ወደ መኖሪያነት ለመቀየር እንቅፋት የሆነው የተለያዩ አካላት ፍላጎት ያለው በመሆኑ ነው:: ቦርዱ በግቢው ውስጥ እንዳይጠፉ የማይፈልጓቸውን ነገሮች በግልጽ አስቀምጧል:: ለምሳሌ የጸጥታ ችግር ምንጭ በሆኑ አካላት ላይ እርምጃ ይወሰድ ሲባል መረጃ አይሰጥም::

እያንዳንዱ የቤት ባለቤት የቤት ካርታ ይዞታ ስላለው አጠቃላይ ምድረ ግቢው ይዞታ አለው ማለት ግን አይደለም:: በመሆኑም ማህበሩ የሚጠይቀውን የአጥር ግንባታ ፈቃድ መስጠት አልተቻለም:: የማህበሩ ወሰን በታወቀ ጊዜ የቦርዱ ጥያቄ ምላሽ እንደሚያገኝ ጠቁመዋል::

የወረዳው ቤቶች አስተዳደር ምላሽ

በወረዳው ቤቶች አስተዳደር ቡድን መሪ የሆነው አቶ አበበ ትርፌ እንደገለጹት፤ በጋራ መኖሪያ ቤት ለሚገኙ የንግድ ቤቶች ጋር በተያያዘ የከተማ አስተዳደሩ ምንም መመሪያ ባለመኖሩ በጎተራ የጋራ መኖሪያ ቤት የንግድ ቤቶች የፈጠሯቸውን ችግሮች መቅረፍ አልተቻለም::

ይህ ብቻ አይደለም ከጋራ መኖሪያ ቤቶች እድሳት ጋር እንዲሁ መመሪያዎች ባለመኖራቸው ሰዎች ቤታቸውን እያፈረሱ እንደፈለጉ ቢሰሩ ማስቆም አይቻለም:: ነገር ግን በተለምዶ መመሪያ አይፈቅድላችሁም እያሉ እደሚያስቆሙ ይናገራሉ::

የጎተራ የጋራ ቤት ነዋሪዎች 13 ኮሚናሎች እንዲገነቡላቸው ለቤቶች አስተዳደር ገንዘብ ከፍለው ነበር:: ነገር ግን እስካሁን የተሰሩላቸው ሰባቱ ብቻ ናቸው:: ይህን ታውቃለችሁ? ተብለው የተጠየቁት አቶ አበበ “አዎ እናውቃለን” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል::

ለነዋሪዎች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ በተሰራ ጊዜ ቀሪዎቹ ይገነባሉ የተባሉ ኮሚናሎች እንደሚያሰሩ ገልጸዋል:: በተጨማሪም የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ከተሰራ ማህበሩ ለሚያነሳው የአጥር ግንባታ ምላሽ እንደሚሰጠው ተናግረዋል:: “እስከዚያው ግን ባለው ይጠቀሙ” ብለዋል::

ወረዳ 04 የሰላም እና ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ

በጎተራ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት ምን እየሰራችሁ ነው? ብለን የጠየቅናቸው የወረዳው የሰላም እና ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አትንኩት ውድነህ እንደገለጹት፤ በጎተራ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ በሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮች ጽህፈት ቤታቸው በተደጋጋሚ እርምጃዎችን መውሰዱን ይናገራሉ:: ከጭፈራ ቤቶች በተጨማሪ ጸጥታን የሚያውኩ የቤቲንግ ቤቶች፣ ሺሻ የሚያጨሱ እና የሚያስጨሱ፣ የፑል ማጨዋቻዎች እና መሰል ነገሮች ላይ እርምጃ መውሰዳቸውን ገልጸዋል::

እንደ አቶ አትንኩት ገለጻ፤ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጭምር መጥተው የተዘጉ የጭፈራ ቤቶች አሉ:: ከማኅበረሰቡ ባህል እና እሴት ውጭ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ይሰተዋላሉ:: በእነሱም ላይ እርምጃዎችን ወስደናል::

በጎተራ ኮንዶሚኒየም ባለቤቶችን ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው:: አብዛኛው ተከራይ ነው:: የጋራ መኖሪያ ስፍራው በርካታ ውስብስብ ችግርች ያሉበት ነው የሚሉት አቶ አትንኩት፤ እርምጃ በሚወሰድበት ወቅት እርሳቸው ታፍነው እንደነበር አመልክተዋል::

ሞገስ ተስፋና ሙሉቀን ታደገ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You