አዳማ፡- የፌዴራል ስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በተመረጡ ዘርፎች ላይ ጥናት ቢያስጠናም የጥናቱን ውጤት ተቀብሎ የሚተገብር ተቋም እንደሌለ አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ትናንት በአዳማ ከተማ ከረዩ ሆቴል ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች እና አባላት በሰጠው ስልጠና ላይ እንዳስታወቀው የሙስና እንቅስቃሴና ስጋት በሚታይባቸው ዘርፎች ላይ የተካሄደውን የጥናት ውጤት የተገበረ አካል የለም።
በኮሚሽኑ የስነ ምግባር አውታሮች ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ ሀረጎት አብርሃ እንዳሉት ኮሚሽኑ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት በተለያዩ ጊዜያት የሙስና ስጋት እና እንቅስቃሴ በሚታይባቸው እንደ መሬት፣ ገቢዎች እና መሰል ሴክተር መስሪያ ቤቶች እንዲጠኑ ተደርጎ ምክረ ሀሳብ ቢቀመጥም ጥናቱን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ችግሮችን ለማሻሻል የሚጠቀም ተጠኚ መስሪያ ቤትም ሆነ የበላይ አካል የለም።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ እና አባላት የተዘጋጀው ስልጠናም ኮሚሽኑ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክን ጨምሮ ከሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች እና አካላት ጋር ጥምረት በመፍጠር የተጠኑ ጥናቶችን እንዲተገበር ለማድረግ ነው፡፡
እንደ አቶ ሀረጎት ገለጻ የስልጠናው መድረክ ለኮሚሽኑ ግብዓት ሲሆን ይህም የአዲስ አበባን ምክር ቤት በሙስና ትግሉ ላይ ያላቸውን ሚና ከፍ ለማድረግ ይረዳል፡፡ በተጨማሪም በመንግሥት መስሪያ ቤቶች የሚገኙ የሥነ ምግባር መኮንኖች እንደጠላት እየተቆጠሩ ቢሮ እንኳን የሌላቸው ባለሙያዎች አሉ ፤እነዚህንም ባለሙያዎች ወደ ስራቸው እንዲገቡና እንቅፋት እንዳይገጥማቸው የምክር ቤቱ አባላት ይረዱናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።
ጠንካራ አገር ለመገንባትም ሙስናን መከላከል ወሳኝ በመሆኑ ሰፊ ሥራ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም የተናገሩት ዳይሬክተሩ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ጠንካራ አቋም ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆነ ገልጸዋል። በአገሪቱ ስር የሰደደውን የሙስና ችግር ለማስወገድ የተሻለ የፀረ-ሙስና ትግል ለማድረግ ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረም አብራርተዋል።
የፌዴራል ስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አትክልቲ ግደይ በበኩላቸው ጊዜ እና ገንዘብ የፈሰሰባቸውን ጥናቶች የመደርደሪያ ማሞቂያ እንዲሆኑ ሳይሆን የጥናቱ ውጤት ታይቶ የሚታረመው እንዲታረም፤ የሚገሰጸው እንዲገሰጽ እንጂ ጥቅም አልባ ሆነው እንዲቀመጡ አይደለም ብለዋል፡፡
እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ ጥናቶቹን በአግባቡ መርምሮ የሚያያቸው የለም እንጂ እንደ አገር ብዙ ብክነቶችን ልንከላከልባቸው እንችል ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን አልረፈደም የተጠኑትን ጥናቶች በመተግበር የአዲስ አበባ መስተዳድር ምክር ቤት አባላት እና ቋሚ ኮሚቴዎች ጋር በመተባበር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2011
አብርሃም ተወልደ