አዲስ አበባ፡ -የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ከአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ጋር በመተባበር ከሁለት መቶ አርባ በላይ ለሆኑ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠሩን አስታወቀ፡፡
የማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን ገብሩ ትናንት በግሎባል ሆቴል በተደረገው ውይይት ላይ እንዳሉት የሥራ እድሉ ከአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት ጋር በመተባበር በተፈጠረው የሥራ ዕድል የሚቀጠሩት በቋሚነት ሲሆን የማስተባበር፣ የመቆጣጠር እና ትኬት መቁረጥ መሰል ስራዎች ላይ ይሰማራሉ፡፡ የባቡር ትራንስፖርት ብዙ ወጣቶችን ማሰራት የሚችል ትልቅ ፕሮጀክት በመሆኑ ስራው ቀጣይነት እንዳለው የተናገሩት አቶ ሰለሞን ሌሎች ወጣቶችንም የእድሉ ተጠቃሚ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለፃ፤ ከቀላል ባቡር ትራንስፖርት በተጨማሪም በሌሎች የሥራ እድሎች ላይ ለማሰማራት ከአየር መንገድ፣ ከአዲስ አበባ ወንዝና ዳርቻ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከሚገኙ መንግሥ ትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን እየሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ እንዲህ አይነት ስራዎች ብሔርና ሀይማኖትን ሳይለዩ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር አባል በመሆናቸው ብቻ የሚመቻቹ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የህዝብ ግንኙነት ዋና አማካሪ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ፤በበኩላቸው ወጣቱ የአዲስ ጉልበትና የእውቀት ባለቤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ስለሆነም በሚቀጥሉት የክረምት ወራት ዘረኝነትን በመፀየፍ በከተማችን ሰላምና ፅዳት ላይ የተጠናከረ ሥራ መስራት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
የአዲስ አባባ ወጣቶች ማህበር ከዘጠና ሺ በላይ አባሎች ያሉትና ትልቅ ማህበር በመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ ማህበሩን ለመደገፍ ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ወጣት ለሀገራቸው ብዙ ስራዎችን መስራታቸውን ያነሱት አቶ ተስፋዬ “በምትሰማሩበት ሥራ ሁሉ ኢትዮጵያዊነታችንን የሚያጠናክሩ ተግባራትን ማከናወን ይኖርባችኋል” ብለዋል፡፡ አሁን ያለውን መልካም ያልሆነ ሁኔታን ለመቀልበስ ወጣቱ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበትም አሳስበዋል
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የትኬት ቁጥጥር ሱፐርቫይዘር የሆነው ወጣት በላይ ይሁን እንደሚለው፤ በአሁኑ ወቅት ኤጀንሲዎች ህገወጥ በሆነ መንገድ የወጣቱን ጉልበት እየመዘበሩ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን የባቡር ኮርፖሬሽኑ ለአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር የሰጠው ትልቅ እድል ነው፡፡
የስራውን እድል ያገኙ ወጣቶችም ይህን መልካ አጋጣሚ ሊጠቀሙበት ይገባል ሲል አሳቧል፡፡ ወጣት በላይ በባቡር ኮርፖሬሽኑ ተቀጥሮ ባደረገው አስተዋፅኦና ለሥራ ባለው ታታሪነት በዝግጅቱ ላይ የዋንጫና የምስክር ወረቀት ተሸላሚ መሆን ችሏል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2011
ሞገስ ፀጋዬ