ከወራት በፊት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስራውን በጀመረበት ወቅት የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ “መንግስት በ2016 ዓ.ም አሰባሳቢ ትርክት ፈጠራና ስራ ላይ ትኩረት ይደረጋል” ነበር ያሉት። ይህ በእንዲህ እንዳለ እንግዲህ ኢትዮጵያውያን የወል ትርክት አለን ወይ? እንዴትስ ነው በትርክታችን ውስጥ አገራችንን የምናያት የሚለውን በዚህ የትንታኔ ጽሁፋችን የምናይ ይሆናል።
አሰባሳቢ ትርክት እንግዲህ ሁላችንም በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ እንዳለን ሁሉ በአገራችን ጥላ ስር መሰባሰብ እንደሆነ እንረዳለን። ነገር ግን ይህ እሳቤ ብዙዎች በሚረዱት መንገድ ማለትም ሁሉን ጨፍልቆ አንድ የማድረግ ጉዳይ አለመሆኑን ማወቅ መረዳት ይገባል። አሰባሳቢ ወይም ሀገራዊ ትርክት ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ማንነቶቻችን ውበቶቻችን መሆናቸውን በመረዳት እነሱን በአግባቡና በስርዓቱ ተግባራዊ እያደረገን በአብሮነታችን መቀጠል የሚያስችለን ነው።
በኢትዮጵያዊነት ውስጥ በተሰባሰብን መጠን ታሪካችንም እሱን ለማስተላለፍ የምንጠቀምበት ትርክታችንም አንድ እየሆነ መምጣቱም የማይቀር ነው። ከዚህ የተነሳም ኢትዮጵያውያን ከፋፋይ ትርክቶችን በመተው በሕብረ-ብሄራዊ አንድነት ላይ የተመሰረተ የወል ትርክት በመገንባት ሰላምን ማጽናትና የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ያስፈልገናል የሚባለውም ለዚህ ነው።
የወል ትርክት የአንድን አገር ሕዝብ አብሮነት በማጠናከርና የጋራ አገራዊ ዓላማ ለመሰነቅ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለውና የታሪክ ሁነቶችን ጭምር የሚያስተሳስር መሆኑን ብዙ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።
የወል ትርክት አብሮነትና አንድነትን የማጠናከር ፋይዳው የላቀ ሲሆን በንኡስ ትርክት ላይ አተኩሮ መስራትና ጽንፍ የረገጠ ትርክት መያዝ ደግሞ የመለያየትና የመከፋፈል ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ይታመናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ በተለያዩ መድረኮች ባስተላለፉት መልእክት ኢትዮጵያዊያንን በጋራ ሊያስተሳስር የሚችልና አንድነትን የሚያጸና የጋራ የሆነ ታላቅ ትርክት ያስፈልጋል ማለታቸው ይታወሳል።
የወል ትርክትን በመገንባት ሕብረ ብሔራዊ አንድነት፣ የጋራ ተጠቃሚነትና የሀገር ግንባታ መሰረቶችን ማኖር እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ከፋፋይ አጀንዳዎች ሰላም እንዳይጸና፣ ልዩነትና ተቃርኖ እንዲበረታ የሚያደርጉ በመሆናቸው ሕዝብን የሚጎዱ ናቸው። በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክር የወል እውነትን መሰረት አድርገን መስራት ይገባናል ።
ሐሰተኛ ትርክት በኢትዮጵያውያን መካከል ጥርጣሬና ግጭትን በመፍጠር ሀገር የሚያዳክም ሲሆን ብዝሃነትን ያከበረ የወል ትርክትን መገንባት ደግሞ አገርን አጠናክሮ ወደቀጣይ ምዕራፍ የሚያሻግር ድልድይ ነው።
ይህ በመሆኑም እንደ አገር የተቋቋመው የሰላም ሚኒስቴር የተለያዩ የታሪክ አረዳዶችንና አገላለጾችን ለማቀራረብ ከታሪክ ምሁራን ጋር በትብብር እየሰራ ነው። በዚህም በሕብረተሰቡ ውስጥም ሀሳቡ እንዲሸራሸርና ወደ አንድ ማዕቀፍ መምጣት እንዲቻል ብዙ ጥረቶቸን ሲያደርግ እንመለከታለን።
ፍጹም ጠቅላይነትም፤ ፍጹም ነጣጣይነትም ለኢትዮጵያ የማይበጁ በመሆናቸው ሕብረ-ብሔራዊነትን ያከበረ አሰባሳቢ መንገድን መምረጥና መከተል አስፈላጊ መሆኑንም ልብ ማለት ይገባል።
ከታሪካችን፣ ከሕልሞቻችን፣ ከአገራዊ ጥቅሞቻችንና ከእሴቶቻችን የሚመዘዝ የጋራ ማንነት ያለን በመሆኑ ይህንን ማጠናከር ላይ መስራት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ከመሆኑም በላይ በተለይም ፓርቲ አደራጅተው ሕዝቡን የሚያነቃንቁ ፖለቲከኞችም ይህን ልብ ሊሉ ይገባል።
በመሆኑም ኢትዮጵያውያን የወል እውነት ላይ የተመሰረተ አገራዊ ትርክት በመገንባት የጋራ ሰላምንና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መስራት የውዴታ ግዴታችን ነው። የወል እውነት ለሀገር በጋራ በመቆም መስራትን፣ ሉዓላዊነትን፣ ሰላምና አንድነትን የሚያጸና በመሆኑ ለዚህ መልካም ዓላማ በጋራ መስራትም ተገቢና አስፈላጊ ነው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር የሆኑት አቶ ሽመልስ ሀይሉ እንደሚሉት በመጀመሪያ አገረ መንግስት ስንል በጠንካራ ምሰሶ ላይ የቆመ የጋራ ስነልቦናና ማንነትን መፍጠር የቻለ ማለት ሲሆን፤ እነዚህን የጋራ ስነልቦናና ፍላጎቶችን ለመመለስ የሚችሉ ተቋማትን ያቆመ ማለት ነው።
እንደ አቶ ሽመልስ ገለጻ የጋራ ማንነት ስንል እንደ አገርና ሕዝብ የሚያስተሳስረን አንድ የሚያደርገን አስተሳሰብ የጋራ ፍላጎትን የያዘ ከመሆኑም በላይ የጋራ ትላንት ዛሬና ነገን የያዘም ሊሆን ይገባል። በዚህ ውስጥም እንደ አገር ሁላችንም በጋራ የምናስታውሰው የጋራ ትውስታ ሲኖረን ነው። ይህ ትውስታችን ደግሞ አያት ቅድመያቶቻችን በጋራ ያኖሩትን፤ ያደረጉትን ፖለቲካዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውጣውረዶችን የምንጋራበት የጋራ ትውስታ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ የዛሬው ትውልድ በጋራ የሚሰራው እያደረገ ያለው ነገር የጋራ ዛሬ በመሆኑ እነዚህን ሁለቱን ያስተሳሰረ የጋራ ራዕይ ማኖር ማለት ነው፤ የሚሉት አቶ ሽመልስ የትላንቱና የዛሬው በደንብ ተሰናስለው ከሌሉ የጋራ አገረ መንግስት ችግር ውስጥ ይገባል፤ እነዚህ ነገሮች ግን በአግባቡና በስርዓቱ ተሰናስለው መቀጠል ከቻሉ የጋራ የሆነ አገረ መንግስትና ትርክት የመገንባት ስራችን ውጤታማ ይሆናል በማለት ያስረዳሉ።
እነዚህን ለአገረ መንግስት ግንባታ ላቅ ያለ ሚና ያላቸው ነገሮች በአግባቡ ለመገንባት ደግሞ በተለይም በእኛ አገር በጣም ያፈነገጡ ሁለት ሃሳቦች ላይ መስራት ይጠበቅብናል፤ አንደኛው እስከ ዛሬ በመጣንባቸው የአገረ መንግስት ግንባታ ሂደታችን ውስጥ አብረን እንዳልኖርን፤ እንዳልተጋባን፤ እንዳልተዋለድን በፖለቲካ በኦኮኖሚ እንዲሁም በማህበራዊ ዘርፎች ላይ አብረን ብዙ ውጣ ውረዶችን እንዳላሳለፍን በማስመሰልና ዝም ብለን ተበታትነን ነው የኖርነው የሚል የተንሻፈፈ አተያይና ትርክት አለ፤ ይህንን በጣም መግራት ይገባል፤ የትላንት የጋራ ትዝታዎችና ታሪኮች እንዳሉን የሚያሳዩ ብዙ የአብሮነት መገለጫዎች ስላሉን እነሱን አምኖ መቀበል ያስፈልጋል።
ለምሳሌ በኢኮኖሚው ዘርፍ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ከሰሜን እስከ ደቡብ ብቻ በአራቱም ማዕዘን የግንኙነት መስመሮች ነበሩን እነዚህ መስመሮች ደግሞ የሚያሳዩት ኢትዮጵያውያን በጋራ እየነገዱ ማህበራዊ ኑሯቸውን በዛ ውስጥ እየኖሩ በፖለቲካና ወታደራዊ ዘርፍም በተመሳሳይ ጥላትን ድል ለማድረግ ሆ ብለው ሲዘምቱ እንደነበር የሚያሳዩ የጋራ የሆኑ ነገሮች አሉን። እነዚህን የጋራ ስነልቦናዎቻችንን በተዛቡ ትርክቶች ማንሻፈፉ የሚጠቅም ባለመሆኑ እነዚህን ማቃናት ላይ ሁላችንም ተረባርበን መስራት ይገባናል ይላሉ።
ሁለተኛው ደግሞ ኢትዮጵያ ሲባል እንዲሁ መለኮታዊ አድርጎ ማሰብና በኢትዮጵያውያን መካከል የሀይማኖትም፤ የብሔርም ምንም ልዩነት የለም ብሎ ያፈነገጠ ሀሳብም አለ። ነገር ግን ነባራዊው ሁኔታ ይህንን እንደማያሳይ ሁላችንም የምናውቀው ሃቅ ነው የሚሉት አቶ ሽመልስ ኢትዮጵያውያን በጣም ብዙ ልዩነት ያላቸው በሀይማኖት፤ በብሔር፤ በስራ፤ በፖለቲካዊ አመለካከት ቢኖራቸውም እነዚህን ልዩነቶቻቸውን አቻችለውና አዋደው አንድ ሆነው የኖሩ በርካታ የጋራ ትዝታዎችና ትርክቶች ያሏቸው ሕዝቦች መሆናቸውም ሊታወቅ የሚገባው እንደሆነም ነው ያስገነዘቡት።
በመሆኑም አሁን ላይ እነዚህን ሁለቱን አስተሳሰቦች ማስታረቅና ወደመካከል ማምጣትና ትክክለኛውን መንገድ ማሳየት መቻል አለብን። ይህንን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው የምንገፈልገውን የጋራ ማንነት መገንባት የምንችለው ይላሉ አቶ ሽመልስ።
የሚገርመው ነገር ይላሉ አቶ ሽመልስ ዛሬም ድረስ በውስጣችን ልዩነቶች አሉ እየተባባልን ጦር እየተማዘዝን እንኳን አንድ የሚያደርጉንን ብዙ የጋራ ማንነቶች እየኖርናቸው ነው። በመሆኑም አገራችን ላይ እንደ ማህበረሰብ የማንስማማባቸው ማህበራዊ ችግሮች በየጊዜው ያጋጥሙናል እንጂ እንደ ሕዝብ የተጣላንባቸው ቂምና ቁርሾ የያዝንባቸው ነገሮች የሉም። ይህ ሲባል ደግሞ የማይመቻቸው ፖለቲከኞችም ብዙ ናቸው። ነገር ግን የአገራችንን ታሪክ መለስ ብለን ማጥናት ከቻልን እስከ ዛሬ ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ብሔር በሌላ ብሔር ላይ ጦርነት ከፍቶ ቁርሾ ውስጥ የገቡበት ነገር አይገኝም።
በጠቅላላው የጋራ ማንነታች እንዲገነባ የቆዩት የእኛነት ትርክቶቻችን ሳይበረዙ ሳይከለሱ ለትውልድ እንዲያልፉ ጠንካራ ስራን መስራት ይጠይቃል የሚሉት አቶ ሽመልስ ሕብረተሰቡ እስከ አሁን የመጣበት የአብሮነት ገመዱ እንዳይላላ ማስተማር እንዲሁም ልዩነትን የሚያራቡት የፖለቲካ ልሂቃን ወደ አንድ ጎራ ሰብሰብ እንዲሉ ማድረግ ያስፈልጋል። ከዛ ሁሉ በላይ ደግሞ የፖለቲካ ገበያው መሪ ተዋናይ የሆኑት የመገናኛ ብዙሃን ከኤዲቶሪያል ፖሊሲያቸው ጀምሮ አንድነትን ወደ መስበኩ መዞርና ትኩረት ማድረግ ይገባቸዋል። የጋራ ትዝታዎች እንዳሉን ማውጣትና በዛ ውስጥ የነበሩ ህጸጾችንም እያሳዩ እውነታውን መቀበል ያስፈልጋል።
ትላንት ስህተት ብቻ ወይንም ደግም መልካም ነገሮች ብቻ የተከናወኑበት አይደለም ብለን ማሳየትና ዛሬም በደረስንበት ደረጃ ከእኛ ምን ይጠበቃል በማለት የትላንቱ ስህተት እንዳይደገም የትላንቱ ጥሩ ነገር ደግሞ ተሻሽሎ እንዲቀጥል የሚያደርጉ ስራዎች ላይ ማተኮር ያስፈልጋል ይላሉ አቶ ሽመልስ።
የጋራ ማንነት በመገንባት በኩል ውጤታማ ነንም አይደለንምም ማለት ይቻላል የሚሉት ደግሞ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ዶክተር እምሩ ገመቹ ናቸው።
እንደ ዶክተር እምሩ ገለጻ መሰረታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮቻችን ብዙ ናቸው፤ አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እይታ የለንም ለዚህ ማሳያው ደግሞ በባንዲራ እንኳን የምናደርገው ፍጅት ነው። በመሆኑም እነዚህን ነገሮች ወደመካከል አምጥቶ ውጤት ለማየት ዜጎች በተለያየ መልኩ መነጋገርና መግባባት ላይ መድረስ ይጠበቅባቸዋል።
በሌላ በኩልም ምሁራኖች ትልልቅ የሚባሉት የአገር መሪዎች ችግሩን ተቀብለው ለመፍትሔው የተጠናከረ ስራን መስራት አለባቸው፤ የሚገርመው ነገር አንዳንድ አገሮች አሁን እኛ የገባንበትን አይነት የጋራ ማንነትን የማጣት ችግር ውስጥ ገብተው ነበር፤ ነገር ግን በተጠናከረ ስራ ችግሩን ለማቃለል ችለዋል፤ እኛም እነሱ እንዴት ይህንን ጊዜ አለፉት የሚለውን በሚገባ ማየትና ማጥናት ልምድን ቀምሮ እንደ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ተግባር ላይ ማዋል እንደሚያስፈልግም ነው የሚናገሩት።
አገራዊ የሆኑ የጋራ ማንነቶቻችን ላይ ትኩረት አድርገን መስራት አለብን የሚሉት ዶክተር እምሩ በዚሁ መካከል ደግሞ ለምንድን ነው? የጋራ ማንነትን የማጉላት ስራችን ጥላ ያጠላበት የሚለውንም በጥሞና ማየትና መገንዘብ ይገባል። ከዛ ውጪ ግን ይህንን ሃሳብ ብቻ ተቀባይ የሚል ግን ማምጣት እንደሚከብድ መረዳት ያስፈልጋል ይላሉ።
እዚህ ላይ ከፖለቲከኞች ውጪ ምሁራን በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ ጊዜን ወስደው ቢነጋገሩ ለውጥ የሚመጣ ይመስለኛል የሚሉት ዶክተር እምሩ በመሆኑም ሌሎች አገሮችም በዚህ ሂደት ውስጥ ያለፉ በመሆኑና አሁንም እያለፉ ያሉ ስላሉ ከእነዚህ የምንማረውን ይዘን እስከ አሁን እኛም የሞካከርናቸውን ነገሮች አቀናጅተን በመነሳት እንዴት ወደፊት እንሂድ የሚለውን ማስቀመጥ ይገባል ብለዋል።
ሕዝብ አብሮ የሚኖር ነው። የጋራ ማንንቱም የእሱ ነው። በመሆኑ ተወካዮቹ በሰከነ መንፈስ ቁጭ ብለው ፖለቲካዊ እሳቤ ትተውት እንደ ሕዝብ ሆነው ቢነጋገሩ ምናልባት የምንፈልገውን የጋራ ማንነት ግንባታ ለማምጣት እንችላለን በማለት አስረድተዋል።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1/2016 ዓ.ም