መሰባሰብ ወደ አንድ ለመምጣት መነሻ ነው። የተለያየ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች ቢሆኑ እንኳ መሰባሰባቸው ብቻውን ወደ አንድነት ሊያመጣቸው የሚችል ቀዳሚው ውሳኔ ነው፤ ልክ አንድ ታማሚ ህክምና ማዕከል መሄዱ ግማሽ በመቶ ጤናውን ይመልስለታል እንደሚባለው። እኛ ኢትዮጵያውያንም በራሳችን ከገነባነው ማንነት መካከል አንዱ ይህ መሰባሰብ ነው። በየአንዳንዱ እርምጃችንና እንቅስቃሴአችንም የሌሎች ሰዎች አስተያየት የሚያሳስበንም ተሰባስቦ ከመኖራችን የተነሳ ነው።
እንዲህ ሰብሰብ ከምንልበት አውድ አንዱ ደግሞ ገበታ ነው። «ምንድን ነው እንጀራ እየቆነጠሩ በየግል ሰሃን መያዝ። ሲበሉማ በአንድ ላይ ነው’ንጂ» የሚሉ በእድሜ ጠና ያሉ ሰዎች ሳይገጥሙን አይቀሩም። አዎን! አብሮ መብላት ከመደጋገፍና መረዳዳት አንጻር ብቻ ሳይሆን ከየግል ሩጫው ሲመለስ፣ ከዋለበት ሲገባ እህሉን በአንድ ትሪ በአንድ ገበታ መብላት የአገሬው ባህል ነው።
በክብ መሶብ፣ በክብ እንጀራ፣ በክብ ጠረጴዛ ላይ ክብብ ብሎ፤ እንደ ክብ ቅርጽ ጥቅልል ያለ ጉርሻን «አፈር ስሆን ይህቺን ብቻ!» እየተባባሉ መጎራረስም የአገር ወግ ነው። ይህ ስርዓት ሁሉም አገር ይገኛል ወይ? ሁሉም ጋር አይገኝም። የዓለም ውበቷም ይህ ልዩነቷ አይደለ? እንግዲህ ውብ ስለሆነ ልዩነት ካነሳን ብሔር ብሔረሰቦችን፤ ብሔር ብሔረሰቦችን ከጠቀስን ባህላቸውን፤ ባህላቸውን ካስታወስን ከዛ መካከል አንዱ የሆነውን የምግብ ዓይነትና አመጋገብን ማንሳታችን አይቀሬ ነው።
ገበታ
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993ዓ.ም ባሳተመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ላይ፤ ገበታ ለሚለው ቃል ተቀራራቢነት ያላቸው ስድስት ትርጓሜዎች ተቀምጠዋል። ከዛ መካከል አንዱ «ከመቃ ወይም ከቀርከሃ ባለእግር ሆኖ የሚሠራና እንደ መሶብ ያለ እቃ» የሚል ሲሆን ቀጥሎ ያለው «ማዕድ፣ ምግብ የቀረበበት እቃ» በሚል ተገልጿል። እንግዲህማ ገበታ ተዘረጋ ማለት ምግብ ቀረበ ማለት ነው።
ኢትዮጵያውያን ገበታን ያከብራሉ፤ እናከብራለን። ከቃሉም «ገበታ ክቡር ነው!» ይባላል። ትልቅ ሰው የመጣ እንደሆነ እንኳ ከገበታ ላይ መነሳት ነውር ነው። «ከእኔ በላይ ማን አለ?!» የሚል አንቱ የተባሉ ሰው ቢሆን እንኳ፤ መግባቱን አይተው ሰዎች ከተቀመጡበት ቢነሱለት፤ «ኧረ ከገበታ መነሳት ነውር ነው» ይላል እንጂ የራሱን ክብር ከገበታ አያስበልጥም።
ይህን የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች በምርምር ብዙ ገለጻዎችን ሊያደርጉበት ይችላሉ። ነገሩ በዘመናት ከተገነባ ሥነ-ልቦና አልያም ከማኅበራዊ እሳቤ የመነጨ እንጂ እንደው በአንድ ጀንበር የተከሰተ ባለመሆኑ ጥናት መጠየቁ አይቀርም። ከዛ መለስ ብለን ስናይ ግን፤ ኢትዮጵያዊ በቃሉ «ገበታ ክቡር ነው» የሚለውና በተግባርም ከገበታ ላይ ያለበቂ ምክንያት ሊነሳ የማይፈቅደው መሰባሰቡን ስለሚያከብር ነው።
ልብ በሉ! ሌላው ቀርቶ በገበታ ላይ በጋራ ከቀረቡ ሰዎች መካከል አንዱ ሰው ቀድሞ የጠገበ ቢሆን እንኳ፤ ሌላው ሳይጨርስ ጥሎ አይነሳም፤ አብሮት ሲበላ የቆየው ሳያበቃ እጁን መታጠቢያ ውሃ አይጠይቅም። «ገበታው ከፍ ይበል እንጂ!» ወይም «ቆይ ሌሎቹ ይጨርሱና አብረን እንታጠባለን!» ይላል፤ ይባላል። ይህ ገበታ መተሳሰብንና መከባበርን እንደሚያጋራን የምናይበት ነው።
ይህ መተሳሰብና መከባበር ከግለኝነት የጸዳ ነው። እዛም ውስጥ የምናየው ሌላ አንድ እውነት አለ፤ በአንድ ትሪ እየተበላም ቢሆን ማንም ከራሱ ፊት አልፎ ከአጠገቡ ካለው ተመጋቢ ፊት ሄዶ እንጀራን አይቆርስም። ከርሱ ፊት አልቆ ቢሆን እንኳ አሳላፊው ይጨምራል አልያም ከጎኑ ያለው ከራሱ ቆርሶ ያካፍለዋል። ይህም እንደሚሆን ስለሚያምን ይጠብቃል፤ እጁንም ወደሌላው አያሳልፍም።
በአንድ ገበታ እየበሉ፤ እየተደሰቱና እየተጨዋወቱ ግን ተማምኖና ተከባበሮ በስርዓቱ መኖርን ከአንድ ገበታ ላይ ብቻ እናያለን። ይህ ከአውሮፓውያን ስልጣኔ የተቀዳ፤ ከባህር ማዶ በውሰት ያመጣነው ሀብት አይደለም፤ የእኛ ነው። ሊቃውንትና አስተዋይ ቀደምት እናቶችና አባቶቻችን፤ በእነዚህ ስርዓቶች ውስጥ አውቀንም ይሁን ሳናውቅ ወይም አስተውለንም ይሁን ሳናስተውል የምንላመዳቸውን በጎ ስርዓቶች አውርሰውናል። ከራሳችን አስቀድመን ለሌላ ማጉረስን፤ ከእኔ ይልቅ እኛ የሚለውን ማስቀደምን፣ በአንድ ገበታ እየበሉም ቢሆን ከራስ ፊት እንጂ ከሌሎች ፊት ሄዶ አለመቁረስን ነግረውናል።
ይህ ሁሉ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየን ኢትዮጵያ ውያን ለመሰባሰብና ለአንድነት ያላቸውን/ያለንን እሳቤ ነው። የጠቀስነው የገበታ ስርዓት ታድያ በአሁኑ አማርኛ በአንድ ክልል ወይም በአንድ ውስን አካባቢ ብቻ የሚገኝ አይደለም፤ ይልቁንም ከዓለም በተለየ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ባሉበት ሁሉ የተለመደ ነው። ታድያ ምግቡን ብቻ አይምሰላችሁ፤ መጠጡንም በጋራ፤ በአንድ አፎሌ /ብርጭቆ/ መጠጣት በአገራችን እስከ ጥግ ድረስ ይታያል።
በየዓይነት
በከተሞች በተለይም በጾም ወቅት የተለመደ የምግብ ዓይነት ነው፤ በየዓይነት። እሱን አሁን አናነሳም። ግን በየዓይነት እኛ ነን፤ በየዓይነት ኢትዮጵያ ናት። መቼስ አሁን ባለንበት ጊዜ፤ «ሥራ ከመፍታት ልጄን ላፋታት» የሚለው ጥቂት ስላልሆነ፤ «እኛ በአንድነት ስንታይ በየዓይነት ከሆንን፤ እኔ የትኛው ወጥ ነኝ ማለት ነው?» ብሎ ይጠይቅ ይሆናል። ምሳሌ እስከፍጻሜው አያደርስምና ይቆየን ብለን ካላለፍነው በቀር።
ገበታ አቀራረብ ከላይ እንዳነሳነው ሆኖ፤ የሚቀርበው ምግብ ደግሞ በአራቱም አቅጣጫ የተለያየ ባለዓይነት ነው። ሁሉም ኢትዮጵያ ያሰባሰበቻቸው፤ እነርሱም ኢትዮጵያን ያቆሟት ብሔሮችና ብሔረሰቦች የየራሳቸው የምግብ ዓይነቶች አሏቸው። ከአልጫ ወጥ እስከሚጥሚጣ፣ ከሱፍ ፍትፍት እስከ ዳጣ፣ ከቆጮ እስከ ቆጭቆጫ፣ ከጨጨብሳ እስከ ክትፎ…በርካታ የሚባሉ የምግብ ዓይነቶች አሉ።
እነዚህን የምግብ ዓይነቶች በእርግጥ ሁሉም ሰው ያውቃቸዋል ማለት አይደለም። ይህ ጥብቅ የሆነ የባህል ትስስር ሥራን የሚጠይቅ ነው። እኛም እንደ አገር እዛ ደረጃ ላይ ለመድረስና፤ ከጭፈራው ባለፈ በምግቡና በአመጋገቡ እርስ በእርስ ለመተዋወቅ፣ አኗኗሩንና አዋዋሉን ለመነጋገር፣ እርቁንና ሽምግልናው እንዴት ነው ብሎ ለመጠያየቅ የሚቀሩን ብዙ ሥራዎች መኖራቸው ግልጽ ነው።
ነገራችንን ወዲህ ስንመልሰው ከተለያዩና ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የተውጣጡ ብሔሮችና ብሔረሰቦች መሰባሰቢያ ቀን የሆነችው ህዳር 29 ላይ ያደርሰናል። በዚህ እለት ትኩረትም ቅድሚያም የሚያገኙ ጉዳዮች ከሶስት አይዘሉም። አንደኛው የፖለቲካ እይታ ነው፤ ይህም እዚህ የምንዘረዝረው አይሆንም። ሌላው አለባበስ ሲሆን ሶስተኛው የአጨፋፈር ባህል ነው። ከነዚህ ነጥቦች አለፍ ተብሎ የሚታይበት ጊዜ እንደሚመጣ በማሰብ እንቀጥል።
ዘንድሮ 13ኛውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን አዲስ አበባ ደግሳለች። እናቶች በማኅበር ከአንዳቸው ቤት ሌላቸው ጋር እየተቀባበሉ እንደሚያከብሩት ጽዋ፤ ይህም ኢትዮጵያውያን እየተቀባበሉ የሚያስቡትና የሚሰባሰቡበት ሆኗል፤ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን። ታድያ አዲስ አበባ፤ የበርካታ ባህልና ብሔር ብሔረሰቦች መናገሻ ማዕከል ከመሆኗ አንጻር «እንደምን ናት?» ብለን እንጠይቅ
አዲስ አበባ
አዲስ አበባ የሁሉም ናት፤ የሁላችንም መሰባሰቢያ። ልክ ተመጋቢ ሰብሰብ ብሎ፤ ለሰውነቱ አቅም ይሆነው ዘንድ እጁን ልኮ እንጀራን እንደሚ ቆርስበት፤ ብዙና የተለያየ ዓይነት ጣዕም ያለው የምግብ ዓይነት እንደቀረበበት ገበታ፤ አዲስ አበባ ባለብዙ ቀለምና መልክ፤ ሁሉን በአንድ የምታስተናግድ ከተማ ናት።
እንደው ነጥለን እንጥቀስ ከተባለ፤ አዲስ አበባ ማለት ጨጨብሳ ለቁርስ፣ ቁርጥ ለምሳ፣ ክትፎ ለራት የሚስተናገድባት ወይም ማለዳ ፈጢራ፣ እኩለ ቀን ጥህሎ፣ ምሽት ዶሮ ወጥ የሚቀርብባት፤ አልያም ጠዋት አምባሻ፤ ቀን ተጋቢኖ ማታ በየዓይነት የሚበላባት ከተማ ናት። የሁሉንም ይዛለችና፤ እንደየመልኩ እንደፈላጊው ታስተናግዳለች። ታድያ ነገራችን ከምግብ ጋር ነውና፤ የእነዚህን ሁሉ ብሔረሰቦች ባህል ያስተናገደችበት መንገድ ይኖራት እንደሆነ እንጠይቃለን።
በነገራችን ላይ ማኅበረሰቡ እርስ በእርሱ በዚህ ላይ ምንም ጉድለት የለበትም። ለምሳሌ ብዙውን እድሜያቸውን ትግራይ አካባቢ ያሳለፉ ቤተሰቦች ቤት በዓልን ምክንያት አድርጎ ጥህሎ ሊዘጋጅ ይችላል። ይህን ጥህሎ ያዘጋጀ ቤተሰብ ብቻውን አይበላም፤ ጎረቤት ይጠራል። ከተማው አዲስ አበባ በመሆኑ ጎረቤቱ ልክ እንደእርሱ የትግራይ ተወላጅ ብቻ የመሆን እድሉ ያንሳል።
እንደውም «ዘመዶችሽ የት ናቸው?» «ቤተሰቦችህ ከዚህ ይርቃሉ?» በሚል መጠያየቅና አጋጣሚ ተነጋገሮ፤ «እንዴ የ… ልጅ ነሽ/ህ እንዴ?» መባባል ካልመጣ በቀር፤ ከአጠገቡ የሚኖረው ሰው ጎረቤቱ እንደሆነና ለችግሩ ቀድሞ ደራሽ፣ ደስታና ሀዘኑን ተጋሪ፣ አብሮት እድር የሚከፍል፣ ቀዳዳውን ለመድፈን እቁብ የገባለት መሆኑን እንጂ ምን ይሁን ምን አይጠያየቅም።
እና ታድያ፤ ጥህሎ የተሠራበት ቤት ኦሮሞ ወይም አማራ አልያም ጉራጌ፣ ካልሆነም ከሌላ አካባቢ የተወለደ ሰው ተጋብዞ ይሄዳል። ያደንቃል ይደናነቃል። ልክ እንደዛው ሁሉ፤ ክትፎዋ የመስቀል በዓልን የሚያስናፍቅ፣ ዶሮ ወጧ ከሩቅ የሚጣራ፣ ጠጇ ከቤቷ የማያስወጣ፣ ጭኮዋ የማይጠገብ፣ ዳጣዋ እየፈጀ የሚጣፍጥ፣ «ሠርተሽ ጥሪን እንጂ!» ብሎ ጎረቤት የሚጠያየቅበት የምግብ አሠራርና የተለያየ ባህል በየአካባቢያችን አለ።
አዲስ አበባ ታድያ ነዋሪዋ እንዲህ በፍቅር የተሳሰረባት ትሁን እንጂ፤ የደረሰ ሁሉ የኢትዮጵያን የባህል ምግቦች ቢፈልግ የሚያገኘው ከምግብ ቤቶች ነው። ይህም በእጅ ያለን አቅም ወደ ንግድ ለውጦ ለብዙዎች የማቅረብ ጉዳይ ነው። ታድያ በዚህ መሰረት በአዲስ አበባ የባህል ምግቦች ተከሽነው የሚገኙባቸው ቦታዎች አሉ። ወደቀደመ ነገራችን እንመለስ፤ እንዲህ ብለን ነበር፡- ታድያ አዲስ አበባ የእነዚህን ሁሉ ብሔረሰቦች የባህል ምግቦች እንደምን አስተናግዳለች?
የባህል ምግቦችና ቤቶቻቸው – በሸገር
ክዳናቸው ሳር የሆነ ጎጆዎች ያሉበት፣ በሸንበቆ፣ ቀርከሃ እና እንጨት የደመቀ፤ ዙሪያውን በኮባ ዛፍ የተከበበ፤ ለዓይን እጅግ ማራኪ በመሆነ መልኩ የተቀመጠ የባህል ምግብ ቤት፤ ቶቶት የባህል ምግብ አዳራሽ። የባህል አዳራሹ በ2001ዓ.ም ከአስር ዓመት በፊት ነው የተቋቋመው። ታድያ እግሩ ቶቶትን የረገጠ ሰው ቅድሚያ የጉራጌን የባህል ምግቦችና ስርዓት ያገኛል፤ ያያል። አልፎም አገሩንም ይመለከታል።
በቶቶት ባህላዊ ምግቦችና እንቅስቃሴዎች ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡኝ ወደ ስፍራው አቅንቼ ነበር። ወይዘሮ ሃና ሽፈራው፤ በቶቶት የባህል አዳራሽ ሥራ አስኪያጅ ስለቶቶት አገልግሎት አንዳንድ ነጥቦችን አጋርተውናል። በዛም የቶቶት ደንበኞች ረክተውና ደስተኛ ሆነው እንደሚመለሱ፤ እንኳን ገብተውና ተስተናግደው ገና ከውጪ የሚያዩት እንደሚማርካ ቸውም ነው የሚናገሩት።
በቶቶት የባህል አዳራሽ ውስጥ የሚገኙ ቁሳቁሶች በሙሉ ባህላዊ ወይም አገርኛ ናቸው። ወንበሩ፣ ጠረጴዛው፣ ዙሪያ ግድግዳው፣ ኮርኒስ፣ የተሰቀሉት የቤት ማድመቂያ ጌጦች፣ ወለሉ፣ የቤቱ መዓዛ፤ የሲኒ አደራደሩ፣ ጀበናው፣ በተለይ የጉራጌ ተወላጅ የተወለደበትና ያደገበት የትውልድ አካባቢውን የሚያስታውሰው ዓይነት ነው።
ወይዘሮ ሃና እንደነገሩን ደግሞ የሚቀርበውም ምግብ በዋናነት የጉራጌ የባህል ምግብ ነው። ይህ ማለት በቦታው ሊገኝ የሚችለውና የሚዘወተረው የምግብ ዓይነት ክትፎ ነው ማለት ነው። ምግቡን የሚያቀርቡ ትም በባህል አልባሳት የደመቁ አስተናጋጆች ናቸው።
ወይዘሮ ሊድያ ዳኜ በቶቶት የሰው ኃይል አስተዳደር ላይ በመሪነት ይሠራሉ። በጊቢው አንድ መቶ ሰላሳ የሚጠጉ ሠራተኞች እንደሚገኙ ነግረውናል። ታድያ በተለይ በምግብ ዝግጅቱ ይልቁንም በክትፎ ላይ ባለሙያዎቹና ክሽን አድርገው መሥራት የሚያውቁበት የጉራጌ ሴቶች ተሰይመዋል። በዛም ለክትፎ ማባያ የሚሆኑ የተለያዩ ዓይነት ምግቦች ያዘጋጃሉ፤ አንዱ ደግሞ አይብ ነው።
ሶስት ዓይነት አይብ አለ አሉን፤ አንደኛው ነጭ አይብ ነው። ሁለተኛው ደግሞ «ዘማሙጀት» የሚባል ነው። ይህ የተከተፈ ጎመን ከአይብ ጋር ሲቀላቀል የሚፈጠር ነው። ሌላውና ሶስተኛው ደግሞ አቆት የሚባለው የአይብ ዓይነት ነው። ይህኛው የደረቀና በደቃቁ የተወቀጠ ጎመን ከአይብ ጋር ተቀላልቅሎ ሲገኝ የሚሰጠው ስያሜ ነው።
ልክ እንደዛው ሁሉ ቆጮም ዓይነት አለው። ይህም ጥሬ፣ የበሰለ እና ቀይ ይባላል። ሁሉንም የሚያዘጋጁት የጉራጌ ልጆች በመሆናቸው እንደባህሉ፤ እንደባህላችን ነው ገበታንው የሚጣፍጡት። ከዚህ ባሻገር የጾም ቡፌ፣ ዶሮ ወጥ፣ የተለያየ ዓይነት ጥብስ፣ የበግ ወጥና የመሳሰለው ሁሉም የባህል ምግብ በቶቶት ይገኛል።
በመጠጥ የተለመደው ጠጅና ብርዝ አልፎም አገር በቀል የሆነ አረቄ (ካቲካላ) አለ ብለዋል። ወይዘሮ ሊድያ እንደነገሩን እንደውም በቅርቡ ከጎጆዎቹ መካከል አንዱ እንደ አረቄ ቤት ባህላዊ መጠጦች የሚስተናገድበት ይሆናል ተብሏል።
ከቶቶት እንሻገር፤ 13 ኪሎ ሜትር አካባቢ ርቀት ላይ ወደሚገኘው ዲማ የባህል ምግብ አዳራሽ። ዲማ የባህል ምግብ አዳራሽ በ2003ዓ.ም ጥር ላይ ተመሥርቷል። ሰፋ ያለ ቦታን የያዘው አዳራሽ ከእንጨት በተሠሩ ቁሳቁሶች የተሞላ ነው። ከመካከል ላይ የሚገኘው ትልቅ መሶብ በርካቶችን አሰባስቦ እንደ አንድ ገበታ በአንድ ማስተናገድ የሚችል ነው።
በባህል ልብስ የደመቀች አስተናጋጅ ፈንድሻ፣ ጀበና፣ ሲኒዎችና እጣን ማጤሻ ይዛ ቀረበችና ከቡናው ቀዳችልን። የዲማ ባህል አዳራሽ ምክትል ሥራ አስኪያጅና አስተባባሪ አቶ ሰለሞን መስፍን ደግሞ ተከታዩን አጫወቱን። በዲማ የባህል ምግብ አዳራሽ የአገር ባህል ምግቦችና መጠጦች ተዘጋጀተው ይቀርባሉ። ከነዛም በቀዳሚነት የሚጠቀሱት ክትፎን ጨምሮ ጎመን ክትፎና አይቤ፣ ዶሮ ወጥ በአልጫ እና በቀይ፣ ጎመን በስጋ፤ ዝልዝል አልጫና ዝልዝል ቀይ ወጥ ናቸው።
ለደንበኞቻቸውም ምግቡን በአንድ ትሪ በመሶብ ያቀርባሉ። በዚህ አዳራሽ ታድያ በጾም ወቅት ሙሉ በሙሉ የባህል ምግቦች የሚዘጋጁ ሲሆን፤ ጎመን ክትፎና ተጋቢኖን ጨምሮ በየዓይነቱ የሚባለው የተለመደው ምግብም በልዩ ሁኔታም ጭምር ይቀርባል።
ከእነዚህ ወጥተን ደግሞ በተለያዩ የጾም ቡፌ ላይ የሚካተቱ ምግቦችን እንዘርዝር። ስልጆ – /ከባቄላ ዱቄት፣ ስናፍጭ፣ ነጭ አዝሙድ እና ዝንጅብ፣ ነጭ ሽንኩርት በድፍኑ የሚገባ/ ፤ እልበት – /ምስር ክክ፣ ስንዴ፣ አብሽ እና አተር ተቀላቅለው ተፈጭተው የሚዘጋጅ/፤ አዚፋ – /ሎሚ፣ ስናፍጭ እና ሽንኩርት ተጨምሮ ከድፍን ምስር የሚዘጋጅ/፤ ሽንብራ አሳ – ከሽንብራ ዱቄት /ዱቄቱ ተቦክቶና በተለያየ ቅርጻ ቅርጽ ተቆራርጦ በተቁላላ ሽንኩርት ውስጥ የሚቀላቀል/ ፤ ቡጥጫ – /ከባቄላ ዱቄት ይሠራል፤ ሽንኩርት፣ ዘይት እና ቃሪያ ተዋህዶ የሚዘጋጅ፤ በአጭር ደቂቃ ተሠርቶ በፍጥነት የሚደርስ / ነው።
የዱባ ቋንጣ – /ዱባ በቀጫጭን ተከትፎና ደርቆ ከተቁላላ ሽንኩርት ጋር የሚቀላቀል/፤ የምጣድ ሽሮ፣ ተልባ እና ሱፍ ፍትፍት እና መሰል ባህላዊ ምግቦችም አሉ። ይህ ሁሉ በአንድ ገበታ የሚቀርብ፤ በባህላችን የሚዘወተርና እንደባህላችን የሚዘጋጅ የእኛው የምግብ ዓይነት ነው። አዲስ አበባ ታድያ ያላትን ሁሉ በአግባቡ ተጠቅማለች ለማለት ያስቸግራል። ከባህል ምግቦችም ጥቂቶቹን በትልቅ እውቅና፤ ብዙዎቹን ደግሞ እንደ እናት ጓዳ በውስጥ ለውስጥ መንገዷ ነው የምታቀ ርበው።
ብዙውን ጊዜ የባህል አዳራሾችም ተከፍተው አገልግሎት ሲሰጡ የሚያቀርቡት የምግብ ዓይነት በቀዳሚነት ክትፎ ነው። በዚህም ይህ የምግብ ዓይነት ተፈላጊነቱና እውቅናውም ከፍ ያለ መሆኑን ማስተዋል እንችላለን። ልክ እንደዛው ሁሉ ታድያ ያልታወቁና በሚገባ ያልተዋወቁ የምግብ ዓይነቶች አሉ። ምክንያቱ በእርግጥ ያለመታወቅም አይደለም፤ በየእለቱ ለመመገብ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት የማይሆኑና ለበዓል አልያም በተለየ አጋጣሚ ብቻ ሊቀርቡ የሚችሉ የምግብ ዓይነቶች አሉ። ከዛ ባሻገር ደግሞ ሰዎች በቀላሉ ቤታቸው ሊሠሯቸው የሚችሉ በመሆናቸው ጎልተው የማይነገሩ ባህላዊ የምግብ ዓይነቶችም ይገኛሉ።
ልክ እንደ ክትፎው ሁሉ እነዚህ በርካታ የሆኑ የምግብ ዓይነቶችም በገበያው ስርዓት ውስጥ ገብተው እንዲተዋወቁና፤ ለመሰባሰብ ምክንያት የሚሆነውን ገበታም እንደሚያደምቁ አንጠራጠርም። ለዚህ የባህል ዘርፍ ላይ የሚንቀሳቀስ መንግሥታዊ ተቋም፣ በምግብ ቤት ላይ ገንዘቡን ማፍሰስ የሚፈልግ ባለሀብትና ምግቦቹን ማዘጋጀት የሚችሉ ባለሙያዎች ሊያስቡበት የሚገባ ነው።
ባለኮከቦቹ
በአገራችን ከባህል ምግብ ቤቶች በላይ እጅግ በርካታ ባለኮከብ ሆቴሎች ይገኛሉ። እነዚህ ሆቴሎች በሚሰጡት የተለያየና በርካታ አገልግሎት ምክንያት በተለይ ከባህር ማዶ የሚመጡ እንግዶች ያርፉባቸዋል፤ ይመገቡባቸዋል። ታድያ የሚያቀር ቧቸው ምግቦች በአብዛኛው የባህር ማዶዎቹን ነው፤ ከግዙፍ ህንጻቸውም ላይ ለባህል ቤቶች ክፍል ለመስጠት የፈቀዱት ጥቂቶች ናቸው።
ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴን ስንቀላቀል ወይም ሉላዊነትን ስንከትል፤ ለአውሮፓውያኑ እንግዶቻችንም ቢሆን የሚመቸውን ማቅረብ የእንግዳ ተቀባይነታችን ማሳያ ነውና አይጠላም። ይሁንና እነዚህ ባለኮከቦች አሩስቶና ላዛኛውን አሳምረው ሲሠሩ ሽሮና ምስር ወጣቸው ግን በዛ ልክ ግሩም ሆኖ የሚሠራ አይደለም። ሌላ ዓይነት አሠራር ኖሮ፤ ወይም ኢትዮጵያን በእነዚህ ባለኮከብ ሆቴሎች ማስተዋወቅ ክልክል ሆኖ ከሆነ አናውቅም፤ ግን እነርሱም ይህን ልብ ቢሉ የተመቻቸው እድል በእጃቸው እንዳለ ያስታውቃል።
እዚህ ላይ እናብቃ። አዎን! ኢትዮጵያዊ ገበታ ክቡር ነው ይላል፤ ሆዱን የሚወድ ሆኖ አይደለም። ገበታ አንድም ያሰባስበዋልና ነው። መሰባሰቡ ለበጎ ምክንያት እስከሆነም ድረስ ገበታውን ቢያከብር ማንም አይከስሰውም። እንዲህ ስልጣኔ መጣሁ መጣሁ ሲል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የመለያየት ወሬ ሲወራ፤ ግለኝነት ባልታወቀ መስኮት ገብቶ ሲነፍስ፤ በገበታው ዙሪያ ሰብሰብ ማለት ያስፈልጋል። በአንድ ገበታ- በባህላችን- እንደባህላችን መመገብ ብቻ ሳይሆን መመካከርም የእኛው ወግ ነው። ሰላም!