አዲስ ዘመን ድሮ

የዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ወደ 1966 ዓ.ም ላይ ማረፊያው አድርጋል። ከየአቅጣጫው አመጾች ተስፋፍተው በነበሩበት በዚያ ጊዜ የሠራተኛው እንቅስቃሴ፤ ሁለቱ ኢትዮጵያውያኑ አውሮፕላን ጠላፊ ባልና ሚስት በኢንቴቤ፤ ከአራቱ ሚስቶቹ ሦስቱን በአንድ ጊዜ ስለፈቱት የአፍሪካ መሪ እንዲሁም ሆዳሞች ተብለው ከሥራቸው ስለተባረሩት ሁለት ሠራተኞች የወጡ ዘገባዎች ያስታውሰናል።

የሠራተኛ እንቅስቃሴ

ቁጥራቸው ከ90 ሺህ በላይ የሆነው የኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማኅበር አባሎች፤ በኢትዮጵያ ሲደረግ የመጀመሪያ የሆነው የ4 ቀን ጠቅላላ የሥራ ማቆም አድማ ካደረጉ በኋላ፤ በዚህ ሳምንት በሙሉ ሥራቸውን ጀምረዋል። የኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማኅበር አባሎች የ4 ቀን ሥራ ማቆም አድማ ያደረጉት የኑሮ ውድነት ወደ 60 በመቶ ከፍ በማለቱ ተመጣጣኝ የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግላቸውና አንዳንድ የመሻሻል ለውጥ እንዲደረግ ለመጠየቅ ነበር። ሠራተኞች ሥራ ባቆሙበት አራት ቀን ውስጥ በነሱ ተወካዮችና በመንግሥት፤ እንዲሁም ከምክር ቤት በተውጣጣ ቡድን መካከል የተደረገ ንግግር ሠራተኞች በጠየቋቸው 17 ጉዳዮች፤ በየደረጃ በሥራ እንዲውሉ የሚመለከት ስምምነት ተደርጓል።

የሲቪል አቪዬሽን መሥሪያ ቤት ሠራተኞች የአበል ጭማሪን፤ የሕይወት ዋስትናን፤ የማኅበር ማቋቋምና የቋሚ ሠራተኛነትን መብት ጥያቄ አመልክተው የሥራ ማቆም አድማ በማድረጋቸው፤ በኢትዮጵያ አየር ላይ የነበሩ የውጪ አገር ኤሮፕላኖች እንዳይገቡ አድርጓል።

መምህራን ቀደም ሲል የጀመሩት የሥራ ማቆም አድማ እንደቀጠለ ነው።

(አዲስ ዘመን መጋቢት 6 ቀን

1966 ዓ.ም)

አውሮፕላን የጠለፈው ኢትዮጵያዊ ታወቀ

ባለፈው ረቡዕ ንብረትነቱ የምሥራቅ አፍሪካ አየር መንገድ የሆነ ፎክነር ፍሬንድሺፕ ፕ.ኤፍ.57 የተባለ ኤሮፕላን ከኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ወደ ማሊንዲ 30 መንገደኞችንና አራት የኤሮፕላን ሠራተኞችን ይዞ በሚበርበት ወቅት በኢትዮጵያውያን ባልና ሚስት ተጠልፎ ዑጋንዳ ውስጥ ኢንቴቤ ኤሮፕላን ማረፊያ ነዳጅ ለመሙላት እንዳረፈ በጉዳዩ ጄኔራል ኢዲ አሚን ጣልቃ ገብተው ኢትዮጵያዊው ጠላፊ ከነባለቤቱ እጁን መስጠቱ መገለጡ ይታወሳል።

ይህንኑ የሚመለከተውን ጉዳይ ኢስት አፍሪካን ስታንዳርድ የተባለው ጋዜጣ በዝርዝር አውጥቶታል። በጋዜጣው እንደተመለከተው፤ አቶ ከሠተ የተባለ ኢትዮጵያዊና ባለቤቱ ኤሮፕላኑን የጠለፉት፤ ከናይሮቢ ወደ ማሊንድ በበረራ ፕሮግራሙ መሠረት ተነሥቶ የ15 ደቂቃ በረራ እንዳደረገ ነው። ኢትዮጵያውያኑ ባልና ሚስት የኤሮፕላኑን ሠራተኞች በሽጉጥ ካስፈራሩ በኋላ የኤሮፕላን ነጂ አቅጣጫውን ለውጦ ወደ ሊቢያ እንዲበር አለዚያ ግን እንደሚገደል ጠላፊዎቹ ነግረው የኤሮፕላኑን ነጂ ካፒቴን ፔንፎልድ ጉዞውን ወደ ሊቢያ ከመቀጠሉ በፊት ነዳጅ ለመጨመር ዑጋንዳ ውስጥ ኢንቴቤ ኤሮፕላን ማረፊያ አረፈ። የምሥራቅ አፍሪካ አየር መንገድ ባለሥልጣኖች የዑጋንዳ ባለሥልጣኖች ርምጃ ለመውሰድ ጣልቃ እንዳይገቡ ቢጠይቁም፤ የዑጋንዳው ፕሬዚዳንት አሚን በአስቸኳይ ወደ ሥፍራው ሔደው ጠላፊውን በማነጋገር ከነባለቤቱ እጃቸውን እንዲሠጡ ለማግባባት መቻላቸውን ጋዜጣው አመልክቷል።

ኢትዮጵያዊው መምህርና ባለቤቱ ኤሮፕላኑ ለጊዜው ወደ ሊቢያ እንዲበር አስገደዱት እንጂ ለመሔድ ያሰቡት ወደ ሞስኮ እንደነበር በጋዜጣው ተጠቅሷል። ጄኔራል አሚን ጠላፊዎቹን አግባብተው እጃቸውን እንዲሰጡ ካደረጉ በኋላ ከተሳፋሪዎቹና ከኤሮፕላኑ ሠራተኞች ጋር ምሳ ተጋብዘዋል።

ከአዲስ አበባ መጣሁ የሚለው ከሠተ ያልተስተካከለ እንግሊዘኛ መናገር የሚችል ሲሆን ስሟ ያልተጠቀሰው ባለቤቱ ግን፤ የምትናገረው አማርኛ ብቻ መሆኑን ጋዜጣው ገልጧል። መምህር ነኝ የሚለው ከሠተ ኤሮፕላን የጠለፈው ሀገሩ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ስለምትገኝ ከዚሁ ለመራቅ በማሰብ መሆኑን ገልጧል።

(አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 1966ዓ.ም)

ፕሬዚዳንት አሚን ከአራት ሚስቶቻቸው ሦስቱን ፈቱ

ካምፓላ፤ የዑጋንዳው ፕሬዚዳንት አሚን ከአራቱ ሚስቶቻቸው መካከል ሦስቱን እንደፈቱና የፈቱበትን (ሰማንያ ያወረዱበትን) ምክንያት ለዑጋንዳ ሚኒስትሮች ምክር ቤት አባሎች ያብራሩ መሆናቸው ተገለጠ። ጀኔራል አሚን የፈቷቸው ኬይ፤ ኖራና፤ ማማ ማሪያም የተባሉትን ሲሆን የቀሩት ባለቤታቸው መዲና አሚን የተባሉት ናቸው።

በዜናው እንደተገለጠው አሁን ከተፈቱት የጀኔራል አሚን ባለቤቶች መካከል ኬይ የተባሉት በቅርቡ ባልታወቀ ምክንያት ተገድለው አስክሬናቸው በዓባይ ጅረት ላይ ሲንሳፈፍ የተገኘው የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሌተና ኮሎኔል ማይክል አንዶጋ የቅርብ ዘመድ ሲሆኑ፤ ማማ ማሪያም ደግሞ ባለፈው ዓመት የተሰደዱት የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ዋኑሜ ኪቤዲ ዘመድ መሆናቸው ታውቋል።

እነዚህን ሁለት ሚስቶቻቸውን የፈቱት ከራሳቸው ፍልስፍና ጋር የማይሔድ የንግድ ጥቅም የመሠረቱ በመሆናቸው እንደሆነ ጀኔራል አሚን ገልጠዋል። ሦስተኛ ባለቤታቸውን የፈቱት ግን ከራሳቸው ጋር ዝምድና ስላላቸው ብቻ መሆኑን ገልጠዋል።

(አዲስ ዘመን የካቲት 17 ቀን

1966ዓ.ም)

ሆዳሞች ተብለው ከሥራ ተባረሩ

ጃካርታ ፤ በኢንዶኔቪያ ውስጥ በሰሜናዊ ሴሊበስ ደሴት በአንድ የወይን ጠማቂ ፋብሪካ የሚሠሩ ሁለት ሰዎች ከሚፈቀድላቸው በላይ ሩዝ በመመገብ ችግር ስለፈጠሩ ከሥራ መባረራቸውን ሲናር ሃራፖን የተባለው የጃካርታ ጋዜጣ አመልክቷል።

በወይን ጠማቂው ፋብሪካ ውስጥ አሥር ዓመት የሠሩት ሁለት ሰዎች ሆዳሞች ተብለው እንዲባረሩ ምክንያት የሆነው በያንዳንዱ የምግብ ሰዓት እያንዳንዳቸው ሦስት ሦስት ሣህን ሩዝ መብላታቸው ነው።

ሁለቱም ሠራተኞች ከሥራ የመባረራቸውን ሁኔታ ለክፍሉ የሠራተኛ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በአቤቱታ መልክ አቅርበው ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ጋዜጣው ጨምሮ ገልጧል።

(አዲስ ዘመን የካቲት 17 ቀን 1966 ዓ.ም)

 

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You