አዲስ አበባ፡- ከምግብ ጋር ባዕድ ነገር በሚቀላቅሉ አካላት ላይ አስተማሪ የሆነ ቅጣት እንደሚወሰድባቸው በአዋጅ ቢቀመጥም በአስፈጻሚው አካል ተግባራዊ እየተደረገ እንዳልሆነ የህግ ምሁራን አስታወቁ።
በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የህግ አማካሪና ጠበቃ አቶ ዝናቡ ይርጋ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ከምግብ ጋር ባዕድ ነገር በሚቀላቅሉ አካላት ላይ አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድ በአዋጅ ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
ሆኖም ግን ህዝቡ አዋጁን እንዲያውቀውና እንዲተገበር አላደረገም። ይህ በመሆኑም ወንጀል የሚፈጽሙ አካላት ቁጥር ተበራክቷል፤ በአቋራጭ ለመበልጸግ የሚጥሩ ወንጀለኞችንም ለህግ ማቅረብ እንዳይቻል አድርጓል።
በምግብና መድኃኒት አስተዳደር አዋጁ ቁጥር 11/2011 ላይ ቁጥጥር የሚደረግበትን ምርት መከለስ፣ ደረጃውን የማያሟላ ማድረግና በሰው ጤና ላይ ጉዳት ማድረስ፣ ባዕድ ነገር መቀላቀል፣ ከሰባት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራትና በብር 500 ሺ ብር ያስቀጣል፤ ይሁን እንጂ በዚህ ደረጃ እርምጃ እየተወሰደ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
“ተቋሙ ኃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም“ ያሉት አቶ ዝናቡ ከውጪ የሚመጡትም ሆኑ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የምግብ ምርቶች የሚመረመሩት በቴክኖሎጂ ተደግፎ ሳይሆን በአይን ብቻ በማየት ነው ብለዋል። ይህ ደግሞ የአገርን ስም እስከማጉደፍ እየደረሰ መምጣቱን ጠቅሰው በቅርቡ በአሜሪካ ከጀሶ ጋር የተደባለቀ እንጀራ ተልኮ ተገኘ የሚለው መረጃ አንዱ ማረጋገጫ መሆኑን ተናግረዋል።
በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት ዳኛ አቶ ጌታሁን ገብረመስቀል በበኩላቸው፤ ምግብ ነክ ምርቶችን ለሚያመርቱ አካላት የሚሰጠው ፈቃድ ስርዓቱን የጠበቀ ባለመሆኑ ፈቃድ ሳይኖራቸው በየስርቻው ምግብን ለሽያጭ የሚያቀርቡ አካላት እንዲበራከቱና ተጠያቂነት እንዳይኖራቸው አድርጓል ብለዋል።
“የአዋጁ ተፈፃሚ አለመሆን ምግብ ላይ ባዕድ ነገርን መጨመር ልምድ ሆኖ እንዲቀጥል አስተዋጽኦ አድርጓል” የሚሉት አቶ ጌታሁን፤ ችግሩ እንዳይፈጠር ማድረግ ላይ የአስፈጻሚው አካል ክፍተቱ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። በጉዳዩ ዙሪያ የሚሰሩ ተቋማትም ከመገፋፋት ይልቅ አዋጁን ማስፈጸምና አስተማሪ የሆነ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ላይ ችግር እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 እንደሚያመለክተው፤ በምግብ ላይ ባዕድ ነገር መጨመር እንደስፋቱና እንዳደረሰው ጉዳት አይነት ቅጣት ተጥሎበታል። ከዚያ ያለፈ ችግር ካደረሰም በወንጀል ህጉም እንዲታይ እድል ሰጥቷል፡፡ ሆኖም የማስፈጸም ችግር ስላለ አደጋው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል ሲሉ አቶ ጌታሁን ይናገራሉ፡፡
በምግብና መድኃኒት አስተዳደር አዋጁ ቁጥር 11/2011 ላይ ቁጥጥር የሚደረግበትን ምርት መከለስ፣ ደረጃውን የማያሟላ ማድረግና በሰው ጤና ላይ ጉዳት ማድረስ፣ ባዕድ ነገር መቀላቀል፣ መመረዝ ከሰባት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራትና በብር 500 ሺ ብር ያስቀጣል፡፡ በሰው ላይ ሞት ካስከተለ ደግሞ በ20 ዓመት ጽኑ እስራትና በብር ከ30ሺ እስከ 400ሺ ብር ቅጣት ተቀምጧል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው