አዲስ አበባ:- ኢትዮጵያ በደጋማው የአገሪቱ ክፍል የአካባቢ እንክብካቤና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎችን በዘላቂነት ለማከናወን የሚያስችላትን የ500 ሚሊዮን ዶላር የእርዳታ ስምምነት ትናንት ከዓለም ባንክ ጋር ተፈራረመች።
የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር የእርዳታ ስምምነቱን በተፈራረሙበት ወቅት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በደጋማው የአገሪቱ ክፍል የአካባቢ እንክብካቤና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎችን በዘላቂነት ለማከናወን የሚያስችላትን የ500 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ከዓለም ባንክ እንደተበረከተላት ገልጸዋል።
ድጋፉ ሊደረግ የቻለው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለአካባቢ እንክብካቤና ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች በሰጡት ትኩረት ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገር ደረጃ አራት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የፈጠሩት መነሳሳት ተጠቃሽ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም፤ እርዳታው በጀት ተኮር የእርዳታ አይነት ሲሆን፤ በቀጥታ ከመንግሥት ቋት ወደ ክልሎችና ወረዳዎች ይተላለፋል። በመሆኑም በአገሪቱ ደጋማ ቦታዎች ላይ የአካባቢ እንክብካቤና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎችን በተቀናጀ የህብረተሰብ ተሳትፎ በዘላቂነት እንዲከናወን የሚያስችል ነው።እርዳታው የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ እንዲያገግሙና በደን እንዲሸፈኑ፣ የአፈር ለምነት እንዲጨምር፣ የአፈር መሸርሸር እንዲቀንስ፣ የአገሪቱ የደን ሽፋን እንዲያድግ እና የውሃ ሀብትን በመጠበቅ የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዲሻሻል ለማድረግ ያስችላል።
በተጨማሪም ለ100ሺ ወጣቶች የሥራ እድል የሚፈጥር እና በ280 ወረዳዎች የሚገኙ ስምንት ሚሊዮን አርሶ አደሮችን የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ትልቅ ፕሮጀክት መሆኑን አስረድተዋል።
በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ በተፈጥሮ ሃብትጥበቃና በአካባቢ እንክብካቤ ስራዎች ላይ ቋሚ የህዝብ አደረጃጀት የአሰራር ስርዓትን በመዘርጋት የአገሪቱን ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ ያሻሽላል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል ።
የአለም ባንክ የሀገራት ዳይሬክተር ካሮልያን ቱርክ በበኩላቸው በፊርማ ስርዓቱ ወቅት እንደተናገሩት፤ እርዳታው መንግስት የአየር ንብረት ብክለትን ለመከላከል በመጀመሪያው እና በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መሰረት በዘላቂነት የአካባቢ እንክብካቤና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎችን ለማከናዎን የሚውል መሆኑን ተናግረዋል። አምስት ሺ ማህበረሰብ ዘላቂነት ያለው የውሃ ጥበቃ ስራዎችን እንዲያከናውንና በ280 ወረዳዎች 2ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ በዘላቂነት የአካባቢ እንክብካቤ ስራዎች እንዲሰሩ የሚያግዝ መሆኑን አመልክተዋል።
ስምምነቱን የተፈራረሙት በኢትዮዽያ በኩል የገንዘብ ሚንስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ሲሆኑ በአለም ባንክ በኩል ደግሞ የአለም ባንክ የሀገራት ዳይሬክተር ካሮልያን ቱርክ ናቸው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2011
ሶሎሞን በየነ