ደን ለሰው ልጆችም ሆነ ለእንስሳት ህልውና እጅግ ወሳኝ ነው። የአፈር መከላት እና በረሃማነትን ለመከላከል፣የብዝሃ ሕይወት ሀብት ለመጠብቅ ፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እና የቱሪዝም መስህብ በመሆንም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። በተለይ ዓለም አየር ንብረት ለውጥ እየፈተነ ያለበትን ሁኔታ ለማለፍ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው። የዓለም ሀገራት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት በሚያከናውኗቸው ተግባሮች ለደን ሀብት ልማት ትኩረት ሰጥተው በርካታ ሥራዎች ሲሰሩ ይስተዋላል።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የደን ሽፋን 30 በመቶ ሲሆን ፤የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ደግሞ 17 ነጥብ ሁለት በመቶ ያህል ነው። በኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርህ ግብር በኩል ለደን ልማት በተሰጠው ልዩ ትኩረት በመርሀ ግብሩ የመጀመሪያ ምዕራፍ 25 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል። በባለፈው ዓመት 2015 በጀት ዓመትም በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር 7 ነጥብ 2 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል። በተለይ የአምናውን ለየት የሚያደርገው ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር ችግኞችን በመስጠት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተምሳሌት የሚሆን ሥራዎችን እየሰራች መሆኑ ነው ።
የዓለም ሀገራት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያስችል ዘንድ ለደን ልማት ትኩረት ሰጥተው ይሰሩ ዘንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እ.ኤ.አ 2012 ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት የዓለም አቀፍ የደን ቀን በየዓመቱ ማርች 21 እንዲከበር ወስኗል። የዘንድሮ የዓለም የደን ቀን አከባበርም የደን ሀብቱን ማዘመን የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። በኢትዮጵያ በቅርቤ የተከበረው የደን ሀብት ልማትን ማዘመን በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በመምከር ነበር።
የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የደን ቀን መሪ ቃል ከኢኖቬሽን ጋር የተገናኘ መሆኑ የቴክኖሎጂው ከደን ልማት አንጻር ያለውን ፋይዳና በምን መልኩ መጠቀም ይቻላል የሚለውን ለመገንዘብ ያስችላል ያሉት የኢትዮጵያ ደን ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሞቱማ ቶሌራ (ዶክተር) ናቸው።
እሳቸው እንደሚሉት፤ የደን ሀብትን በዘመናዊ መንገድ በማስተዳደር አሁን ላለውም ሆነ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፈ ያስፈልጋል። ደን ውስጥ በርካታ የብዝሃ- ሕይወት ሀብቶች እና የገቢ ምንጫቸው በደን ላይ ያደረጉ ሕዝቦች አሉ። ደን ዓለም እየፈተነ ካለው የአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው። ይህም ሙቀት አማቂ ጋዞችን ከአየር ውስጥ በመምጠጥ እና ለሌሎች ዘርፎች ጭምር የተለያዩ የስነምህዳር ግልጋሎት በመስጠት ውጤታማና ምርታማ እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
መጪው ትውልድ የተሻለ ምድር እንዲረከብ የደን መስፋፋትና መጠበቅ ብዝሃ ሕይወትን መጠበቅ ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚ እንዲኖር እንደሚያደርግ ያመላክታሉ። ደን ካለው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ መካከል አፈር እንዳይሸረሸር ፣የግብርናው ዘርፍ እና ከተሞች ውሃ ያለማቋረጥ እንዲያገኙ የሚያደርግ ከራሱ ዘርፍ በዘለለ ብዙ አበርክቶ ያለው መሆኑን አብራርተው፣ የደን ሀብትን ማልማትና መጠበቅ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል ።
ደን ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለን መስተጋብር በመጨመር ለቀጣናው የኢኮኖሚ መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያም ደን ማልማት ላይ በርካታ ሥራዎችን እየሰራች መሆኗን ይገልጻሉ ።
እንደሳቸው ማብራሪያ፤ በኢትዮጵያ በርካታ የተራቆቱ አካባቢዎች ይታያሉ። የእነዚህን አካባቢዎች ምርታማነት ለማሳደግ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞች መተከል አለባቸው። እስካሁን በአረንጓዴ አሻራ በተሰራው ሥራ የተመዘገበው ውጤት ትልቅ ስኬት ያስገኘ ነው። እንደ አጠቃላይ አረንጓዴ አሻራ በደን ልማት የሚታይ ሲሆን፣ ያሉትን ደኖች መጠበቅ እና በደኑ ውስጥ ያሉትን ብዝሃ ሕይወት ሀብቶች እንዲጠበቁ ማድረግ የአረንጓዴ አሻራ አካል ነው።
የደን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች መስራታቸውን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ይጠቅሳሉ። ከተሰሩት ሥራዎች ውስጥ በአብዛኛው በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ችግኞች እንደሚጠቀሱ ተናግረው፣ እነዚህ ችግኞች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳላቸው ተናግረዋል፤ በተለይም ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ችግኞች በአርሶ አደሩ መሬት አካባቢ የሚተከሉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ለምግብነት፣ ለእንስሳት መኖ የሚውሉ መሆናቸውን አመልክተዋል። አረንጓዴ አሻራ የኀብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል፣ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ለመቋቋም እና ያሉትን ደኖችና የብዝሃ ሕይወት ሀብቶች ለመጠበቅ በማለም የሚሰራ ማዕቀፍ ነው ሲሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በዘርፉ ብዙ ሥራዎችን እየሠራች ትገኛለች። እነዚህም ለመጪው ትውልድ የተሻለ አገርና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ሊያመጡ የሚችሉ ከመሆናቸውም ባሻገር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለማስፈን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ያሉትንም ደኖች መጠበቅን ያካትታል። በአሁኑ ወቅት የተፈጥሮ ደን እንክብካቤ ሥራ በኀብረተሰቡ ተሳትፎ እየተሰራ ይገኛል።
‹‹የተተከሉ ችግኞች የጽድቀት መጠን መሻሻሎች የታዩበት ነው›› ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ በባለፉት ጊዜያት ከተካሄደው አረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ብዙ ትምህርት በመውሰድ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ዝርያዎችን ከአካባቢ ጋር የማመሳሰል እና ችግኞች ከሚተከሉበት አላማ ጋር በማስተሳሰር የሚሰሩ ሥራዎች መኖራቸውን እንዳሉና ይህም መሻሻሎችና ለውጦች እንዲታዩ አድርጎል ሲሉ አብራርተዋል።
ችግኞች እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ሰፊ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የችግኞች የጽድቀት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል ሲሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። ቀደም ሲል የተተከሉት ችግኞች የጽድቀት መጠን ምን ይመስላል? የነበሩት ስኬቶች ምንድ ናቸው? የተገኙ ተሞክሮዎችስ ምን ይመስላሉ የሚሉትን የተመለከተ ጥናት ነጻ በሆነ ተቋም ተሰርቶ አልቆ እየተገመገመ መሆኑንም ጠቁመዋል።
‹‹ደን ለሰው ልጆች እንዲጠቅም ስለሚፈለግ ወደፊት በኢንዱስትሪ እየተመረተ ለሰው ልጆች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ሊያስገኝ የሚችል ደን ሊኖረን ይችላል። ይህ እንዲሆን ደግሞ ብዙ መልካም አጋጣሚዎች ስላሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ልክ እንደ አርሶ አደርና አርብቶ አደር እንደምንለው ሁሉ ‹ደን አደርን› መፍጠር ይቻላል›› ብለው እንደሚያስቡም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። አሁን ላይ ደንን በማልማት የደን ሀብት መጠበቅና መንከባከብ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን እንዳለበት ያስገነዘባሉ።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ እያሱ ኤልያስ (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው ደን በሥርዓተ ምህዳር ውስጥ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት እንደ ምሰሶ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል መሆኑን ይገልጻሉ። የዝናብ ውሃን በመቆጣጠር፣ ውሃ ወደ መሬት እንዲሰርግ የአፈር ለምነት እንዲጠበቅ በማድረግ ከባባዊ የአየር ንብረት በመቆጣጠር ጭምር ከፍተኛ ሚና የሚጫወት የሥርዓተ ምህዳር ሀብት ነው ይላሉ።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ፤ ይህ ሀብት ባለፉት ዘመናት ሲጨፈጨፍና ሲራቆት ቆይቷል። በዓመት እስከ 100 ሺ ሄክታር የተፈጥሮ ደን ሲመነጠር፣ በሰደድ እሳት ሲወድም ኖሯል። በዚህም የተነሳ ሀገሪቱ ለድርቅ፣ ለአካባቢ መራቆት፣ ለበረሃማነት፣ ለምግብ ጥረት እና ለድህነት ስትጋለጥ ቆይታለች። የድርቅ አለ ማለት ደግሞ የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዳይኖር ያደርጋል። ዝናብ በሚከሰትበት ወቅት ደግሞ የዝናቡ ውሃ ሰርጎ ወደ ከርሰ ምድር ስለማይገባ ጎርፍ ሆኖ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል። የአፈር መሸርሸር ይመጣል፤ የታችኛውን ተፋሰስ አካል ደግሞ ጎርፍ የሚያጠቃበት ሁኔታ ይከሰታል።
እንደ ሀገር ይህን ለመቀልበስና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት አቅጣጫ ተቀምጦ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው ያመላክታሉ። በዚህም የአረንጓዴ አሻራ ባለፉት አምስት ዓመታት በዓለም ትልቁ የአካባቢ ጥበቃ እና የደን ልማት ሥራ ተደርጎ ሊወሰድ በሚችል ደረጃ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ሃሳብ አመንጪነት በሕዝብ ተሳትፎ በርካታ ችግኞች የተተከሉበት ነው ብለዋል።
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ በዚህ መርሀ ግብር 32 ነጥብ 5 ቢሊዮን የተለያዩ ችግኞችን የተተኩሉ ሲሆን፤ 35 በመቶ ያህሉ የወደመውን የደን ሀብት የሚተኩ እና 60 በመቶ ያህሉ ለእንስሳት መኖ ፣ለፍራፍሬ እና ለተለያዩ የምርት አይነቶች የሚውሉ ችግኞች ናቸው።
‹‹በዚህም የደን መጨፍጨፍ ምጣኔን በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ ተችሏል›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ባለፉት ሃያ ዓመታት በአንድ መቶ ሺ ሄክታር መሬት ላይ ባለ የደን ሀብት ላይ ይደርስ የነበረውን ምንጣሮ አሁን ወደ 32 ሺ ሄክታር እንዲወርድ በማድረግ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ተችሏል። በሌላ በኩል ለአርሶ አደሩ ማገዶ 58 ሚሊዮን ሜትሪክ ኪዮብ ደን እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ አርሶ አደሩ የሚጠቀመው ማገዶ ሲያጣ የሰብሎችን ተረፈ ምርቶች ለማገዶነትና ለእንስሳት መኖነት እንደሚጠቀም ያመላክታሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ይህ ሲሆን ደግሞ የአፈር ለምነት በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳል። ይህን ለመከላከል በደን ልማት ላይ በትኩረት መስራት ስለሚጠይቅ አረንጓዴ አሻራ የደን ልማት የግብርና ቁልፍ መሳሪያ ተደርጎ ይወሰዳል። ‹‹ይህም ጎርፍን በመከላከል የአፈር ለምነት በማስጠበቅ፣ አማራጭ ማገዶ በማቅረብ የመሬቱን ጤንነትና ለምነት በማስጠበቅ፤ ምርትና ምርታማነት በመጨመር፤ ምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ራሳችንን እንድንችል የሚያስችል ቁልፍ ተግባር ነው›› ይላሉ።
በአካባቢ ጥበቃ የሚተከለውን ደን ብቻ ሳይሆን በአርሶ አደሩ የግል ማሳ ላይ ዛፎች እንዲተከሉ በማድረግ ዛፎች የውሃ ሚዛንንና የአፈር ለምነትን እንዲያስጠበቁ የሚደረግ መሆኑን አመላክተዋል። ከዚህ አንጻር የጥምር ደን እርሻ ጭምር በማስፋፋት የሀገሪቱን የደን ሽፋን 17 ነጥብ 2 በመቶ እንዲደርስና ዓመታዊ የደን ጭፍጨፋ ምጣኔ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ተደርጓል ሲሉም አስረድተዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የሚለሙት የፍራፍሬ ተክሎች( አቦካዶ፣ ማንጎ…የመሳሳሉት) የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አልፈው ለውጭ ገበያ እየቀረቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ መርሀ ግብሩ የአቦካዶ ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ሀገሪቱ ከአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃ ላኪ ሀገር እንድትሆን ማስቻሉን ተናግረዋል። በ2015 ጀምሮ በሌማት ቱሩፋት በጥምር ደን ላይ በተተከሉት ዛፎች እና በመኖ ተክሎች አካባቢ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው የወተት፣ የማር እና የስጋ ምርት እንዲያመርቱ መደረጉን ገልጸዋል። ኅብረተሰቡ የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ እና በሥርዓተ ምግቡ ላይ የተስተካከለ ሥርዓት እንዲኖር የሚያደርጉ ሰፊ ሥራዎች መሰራታቸውን አመላክተዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ፤ በባለፈው ዓመት 6ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ፤ 7ነጥብ 2 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል። ከአንድ ወር በፊት የቴክኒክ ቡድን በየክልሉ ተልኮ ባቀረበው ጥናት መሠረት ብሔራዊ አብይ ኮሚቴው ያረጋገጠው የችግኞቹ የጸድቀት መጠን 90 በመቶ ተመዝግቦል። የ2016 በጀት ዓመት እንደ አምና 6ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ሰፊ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል የመሬት ልየታ ተከናውኗል፤ እስካሁን 4ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች (በየጊዜው ችግኞች እየተዘጋጁ ስለሆነ ቁጥራቸው ከዚህም ሊጨምር ይችላል) ተዘጋጅተዋል ።
ከመጋቢት መጨረሻ እና ሚያዚያ መጀመሪያ አካባቢ ጀምሮ በበልግ አብቃይ አካባቢዎች ላይ ችግኝ ተከላ ይጀመራል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በልግ አብቃይና ዝናብ በሚያገኙ አካባቢዎች ዝግጅቱ መጠናቀቁን አስታውቀዋል፤ ዋናው የተከላ ሥራ በሰኔ ወር መጨረሻ በሀገራዊ የተከላ ፕሮግራም ይጀምራል ብለዋል። አሁን ላይ ችግኞቹ የሚተከሉባቸው ቦታዎች ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ጂኦግራፊካል መገኛቸውን በትክክል ለማወቅ የሚያስችል ሥራ ለመስራት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ አመላክተዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም