የቆዳ ውጤት የእጅ ቦርሳዎች

 

ሀገራችን በቆዳ ሀብቷ በእጅጉ ትታወቃለች፡፡ ሀገሪቱ ለውጭ ገበያ ከምታቀርባቸው ምርቶች ውስጥ እነዚሁ የቆዳ ውጤት ምርቶች ይጠቀሳሉ፡፡ የቆዳ ውጤቶቹ በሌሎች ሀገሮች ዜጎች ዘንድ በእጅጉ ተወዳጅ እና ተፈላጊ ናቸው ፡፡

ከእነዚህ የቆዳ ውጤቶች ውስጥ ለተለያየ አገልግሎት የሚውለው ቦርሳ አንዱ ነው፡፡ በአብዛኛው ሴቶች በእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ቦርሳን የሚጠቀሙ ሲሆን፤ ወንዶችም አነስ ባሉ እና በተለምዶ ዋሌት የሚባለውን የኪስ ቦርሳ ይጠቀማሉ ፤ ከዛ በዘለለም የቆዳ ውጤቱ በተለያየ ዲዛይን እና መጠን በገበያ ላይ ይቀርባል፡፡

ወጣት ዮሐንስ በቀለ የቆዳ ውጤቶችን ተጠቅሞ ከእደ ጥበብ ጋር የተገናኙ ቦርሳዎችን እየሰራ ለሀገር ውስጥ እንዲሁም ለውጭ ገበያ ያቀርባል፡፡ ዮሐንስ ሙያውን በቴክኒክና ሙያ ከሚሰጠው የሌዘር ኢንስቲትዩት በመማር ያገኘ ሲሆን፣ ከዚያ በመቀጠልም ሌሎች ስልጠናዎችን በመውሰድ ይበልጥ ወደ ሙያው መዝለቅ ችሏል ፡፡ በአሁኑ ወቅትም በስሩ 11 ሰራተኞችን ቀጥሮ እየሰራ ሲሆን፣ በስራው ላይም ስድስት ዓመትን አስቆጥሯል ፡፡

‹‹ እኔ ተምሬ በወጣሁበት ሰዓት የቆዳ ውጤት ቦርሳዎችን የሚጠቀሙ ሰዎች እንደአሁኑ ብዙ አልነበሩም፤ በማምረት ደረጃም የነበረው የሥራ እድል ጠባብ ነበር፡፡ አሁን ብዙ አምራቾች እና ኢንተርፕራይዞች ተፈጥረዋል፡፡›› የሚለው ዮሐንስ፣ አሁን ሰዎች በየጊዜው የሚወጡ ፋሽኖችን እንደየምርጫቸው በመከተል የቆዳ ውጤቱን ይጠቀማሉ፤ ለቆዳ ውጤቱ ያለው ፍላጎትም እየጨመረ መጥቷል ሲል ያብራራል፡፡ ዮሐንስ ሥራ ፈጣሪም ዲዛይነርም መሆኑን ጠቅሶ፤ የራሱ ዲዛይን እና ፈጠራ የሆኑ ከቆዳ የተሰሩ ቦርሳዎችን ለገበያ እንደሚያቀርብ ይገልጻል፤ የራሳቸውን ዲዛይን ይዘው ለሚመጡ ተቋማትም ሆነ በግል ለሚመጡ ደንበኞች እንደየምርጫቸው ይሰራል ፡፡

ከዚህ በፊት በነበረው ሁኔታ ሰዎች የቆዳ ውጤት ቦርሳዎችን የሚመርጡት ከጥንካሬ እና ለረጅም ጊዜ ከማገልገል አኳያ ነበር የሚለው ዮሐንስ፣ ገበያ ላይ የሚቀርበውን ይህን ፍላጎት ታሳቢ ባደረገ መልኩ መሆኑን ገልጿል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያ ሁኔታ መቀየሩን ገልጿል፡፡ አሁን ለእለት ተዕለት ከሚያዙ ቦርሳዎች እጅግ ውድ እስከሚባሉት የጉዞ ቦርሳዎች ድረስ በገበያው ላይ ይገኛሉ ብሏል፡፡

እሱ እንዳብራራው፤ ከቆዳ ውጤቶች ለሚሰሩ ቦርሳዎች ዋናው ግብዓት ራሱ ቆዳው ነው ፡፡ ይህን የቆዳ ግብዓት በሀገራችን ካሉ የተለያዩ የቆዳ አምራች ፋብሪካዎች ለሀገር ውስጥ አምራቾች በሚደረገው አቅርቦት መሰረት በፋብሪካ ሂደት ያለፈን ቆዳ በሚፈልገው መጠን እና አይነት ይገዛል፡፡ የሚጠቀማቸው የቆዳ አይነቶች በአብዛኛው የበሬ ቆዳዎች ናቸው፤ በፋብሪካ ሂደት ሲያልፍ ደግሞ በአዞ ቆዳ ላይ ያለ የተለየ ቅርጽ እንዲኖረው ተደርጎ የሚዘጋጅ፣ ቀለም ያልተነከረ ቆዳን ይጠቀማል ፡፡

በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ እንደ ችግር የሚነሳው የተለያዩ የግብዓት እጥረቶች ናቸው፤ እንደ ዮሐንስ ገለጻ፤ አሁን ይህ ችግር እየተቀረፈ ነው፤ በየጊዜው የሚኖረው የዋጋ መለዋወጥ እና አንዳንድ በደንበኞች ትእዛዝ የሚመጡ ለየት ያሉ ዲዛይኖች ያላቸው ቦርሳዎችን ለመስራት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለማግኘት ከመቸገር በስተቀር አሁን ያለው አቅርቦት ጥሩ ነው ፡፡

ከዚህ ቀደም የቆዳ ውጤት ቦርሳ ተጠቃሚዎች የነበራቸው የቀለም ምርጫ ጥቁር እና ቡኒ የቀለም አይነት እንደነበር የሚያስታውሰው ዮሐንስ፤ አሁን ግን በተለያየ የቀለም አማራጭ ሰዎች የቆዳ ውጤት ቦርሳዎችን ምርጫቸው እያደረጉ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡ በአብዛኛው ከወንዶች ይልቅ ሴቶች የቆዳ ውጤት ቦርሳን ምርጫቸው ያደርጋሉ ሲል ይገልጻል፡፡

ዮሐንስ የሚፈልገውን የቆዳ አይነት ከፋብሪካው በሚፈልገው መጠን ከተረከበ በኋላ ዲዛይነሩ ባዘጋጀው ንድፍ መሰረት ቆዳው ይቆረጣል ፤ ከተቆረጠ በኋላም በዲዛይኑ መሰረት ተሰፍቶ የማጠናቀቂያ ሥራ ከተሰራለት በኋላ በሚፈለው መንገድ ታሽጎ ለገበያ ይቀርባል ፡፡ ይህ ሥራ ከንድፉ ጀምሮ እስከ መጨረሻ ውጤቱ ድረስ የእጅ ውጤት ሲሆን፤ እንደ ግብዓት የሚጠቀሙት ቆዳ የፍየል እና የበግ ከሆነ የመሳሳት ባህሪ ስላለው በእጅ ፣ የበሬ ቆዳ ከሆነ ደግሞ ማሽኖችን በመጠቀም ይቆረጣል፡፡ ቆዳው ተቆርጦ በሚሰራበት ጊዜ የሚተርፈውን ቆዳም የተለያዩ ዲዛይኖችን በማውጣት ቦርሳዎችን ያዘጋጃል፡፡

እነዚህ የቆዳ ውጤት ቦርሳዎች በገበያው ላይ ከፍተኛ ዋጋ ተተምኖላቸው የሚሸጡ ቢሆንም፣ ዮሐንስ ግን ለውጭ ገበያ ከሚያቀርው በተጨማሪ፣ ዝቅተኛ ገቢ ላለው ማህበረሰብ ጭምር ምርቶቹን ያቀርባል፡፡

ዮሐንስ የተለያዩ ደንበኞች አሉት፤ በተለያዩ ኤግዚቢሽኖች እና ባዛሮች ላይ ይሳተፋል፡፡ ከሀገር ውስጥ ባለፈ የሌሎች ሀገር ዜጎች የሚሳተፉባቸው ዓለምአቀፍ ባዛሮች ላይም ይሳተፋል፤ በእዚህ መድረክም የራሱ ዲዛይኖች የሆኑ ቦርሳዎችንና ሌሎች የቆዳ ውጤቶችን ይዞ ይቀርባል፡፡ በዚህም ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ ደንበኞችን ያፈራበታል ፡፡

‹‹ የቆዳ ውጤት ቦርሳዎችን ብቻ የሚጠቀሙ ደንበኞች አሉኝ፡፡ በየስድስት ወሩ እየመጡ የተለያዩ ዲዛይኖችን የሚጠቀሙ ደንበኞችም አሉኝ ›› የሚለው ዮሐንስ፣ የቆዳ ውጤት ለሆኑ ቦርሳዎች ልዩ ፍቅር ያላቸው ደንበኞች እንዳሉትም አንስቷል ፡፡

የቆዳ ውጤት ቦርሳዎች ለረጅም ጊዜ የሚያገለግሉ ቢሆኑም፣ ፋሽናቸውም በየወቅቱ ይለዋወጣል ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ለመያዝ ምቹ የሆኑ ትንንሽ ቦርሳዎች ይፈለጋሉ፡፡ እሱ እና የሥራ ባልበደረቦቹ የገና በዓል እና የአውሮፓውያኑ አዲስ አመት በሚሆንበት ጊዜ ሥራ እንደሚበዛባቸው ይገለጻል ፡፡ በገና በዓል ሰዎች ስጦታ የመስጠት ልምድ እንዳላቸው ጠቅሶ፣ ለእዚህ ደግሞ ከቆዳ የተሰራ ቦርሳ ለስጦታ ምርጫቸው ያደርጋሉ ብሏል ፡፡

የተጠቀመውን ቆዳ ባህሪ ለደንበኞቹ በመንገር፣ አንድ የቆዳ ቦርሳን ምርጫው ያደረገ ሰው ቦርሳውን ውሀ ላይ እንዳያስቀምጥ ምክር እንደሚሰጥ ይገልጻል፡፡

ቦርሳዎቹ ከቆዳ የሚሰሩ እና የእጅ ውጤቶች እንደመሆናቸው የሚኖራቸው ዋጋም ከሌላው ይለያል ሲል የገለጸው ዩሀንስ ፣ ዋጋቸው እንደ ዲዛይኑ ፣ እንደሚፈጀው የቆዳ ውጤት እና እንደሚጠቀማቸው አንዳንድ ግብዓቶች ፣ ሰርቶ ለማጠናቀቅ እንደሚወስደው ጊዜ እንደሚወሰንም ተናግሯል፡፡ ፡፡ ቀለል ያሉ ቦርሳዎች ከአንድ ሺህ 500 ብር ጀምሮ ፣የሴት ቦርሳዎች እስከ አራት ሺህ ብር ድረስ ለገበያ እንደሚቀርቡም ጠቁሟል፡፡ ወንዶች በብዛት ለሚጠቀሟቸው ተንቀሳቃሽ ኮምፒውተሮች ( ላፕቶፕ ) የሚያገለግሉ ቦርሳዎች እስከ ስምንት ሺህ ብር ድረስ ፣ ለጉዞ የሚሆኑ ቦርሳዎች ደግሞ እስከ 15 ሺህ ብር ድረስ በገበያው ላይ ይገኛሉ ብሏል ፡፡

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You